Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ነገ ከዛሬ ካልተሸለ ምኑን ተኖረ?

ሰላም! ሰላም! ሰላም በያላችሁበት ይሁን፡፡ በዚህ ክፉና ደግ እንደ ዘይትና ውኃ በተቀላቀሉበት ዘመን ሰላምን አስቀድመን ለጋራ ደኅንታችን ካላሰብን፣ እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ሥጋት ይገባኛል፡፡ ይህንን ሥጋቴን የምትጋራው ውዷ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ (በእርግጥም አትጠገብም) ዓይኖቿን ወደ ሰማዩ ልካ ወደ ፈጣሪዋ ታንጋጥጣለች፡፡ አንደኛው የድለላ የሥራ ባልደረባዬ፣ ‹‹ነገረኞች በሚያንጓጥጡበት በዚህ ጊዜ ወደ ላይ ማንጋጠጥ ሳይሻል አይቀርም…›› እያለ ሥጋቴን ማባባስ ሲጀምር የማይታክተውን እግሬን ተንቀሳቀስ አልኩት፡፡ ቆመን ማዳመጥ ከጀመርን እኮ ከተራው ሰው እስከ አገር የሚመሩት ጓዳ ጐድጓዳ ድረስ ምን የማይወራ አለ? ሰላም ለሁላችሁ ይሁን ሲባል ክፉ ነገር ከእናንተ ይራቅ መሆኑን የሚነግሩኝ ባሻዬ ናቸው፡፡ ‹‹አንበርብር! ውስጥህ ሰላም ከሌለው ቀልብ አይኖርህም፡፡ ከራስህ ጋር እየተጣላህ ሌላውን ትነጅሳለህ፡፡ ብዙዎቻችን ሰላም ሲርቀን ደም ይሸተናል፡፡ ካገኘነው ጋር ሁሉ ካልተጋደልን እንላለን፡፡ ሰው በውስጡ ሰላም ይኖረው ዘንድ ከፈጣሪው ጋር መታረቅ አለበት፡፡ ያጠፋውን ሁሉ ተናዞ እንደ አዲስ ሰው መወለድ አለበት፡፡ በክፋት አዕምሮአቸው የናወዘ ምን እየሠሩ እንደሆኑ እያየህ ለሰላም መቆም ካልቻልክ የዘራኸውን ታጭዳለህ…›› እያሉ ሲመክሩኝ የክፋት አባዜ የሚወልደው ግብዝነት አረመኔነቱ የት ድረስ እንደሚጓዝ ሳስብ ውስጤ ታወከ፡፡ ወይ ነዶ!

ያዘኑትን ማፅናናት፣ የተቸገሩትን መርዳት፣ ግራ የተጋቡትን መምከር የመሳሰሉ የደግነት መገለጫዎች የሆኑ እሴቶች ባሉበት ዓለም ውስጥ እኔ ያልሆንኩትን ለምን አትሆንም ብለው ዕልቂት የሚያውጁ፣ ግዞት የሚሰዱና የሚያፈናቅሉትን ሳስብ ለእነሱ ጭምር እንዳዝን መንፈሴ ሲወተውተኝ ነው የከረመው፡፡ የባሻዬ ልጅ በምሁር አዕምሮው ሞርዶኛል መሰል ሰው መሆን ምን ማለት ነው እያልኩ እንደ ፈላስፋው ዘርዓ ያዕቆብ ማሰብ ይዳዳኛል፡፡ ሐሳቤን በፈለግኩት መንገድ ለመግለጽ ስሞክር አፍ አፌን እያሉ የሚያስፈራሩኝ አሉ፡፡ ጓደኞቼ ‘እንደተገኘ አወራለሁ ብለህ ቂሊንጦ እንዳታመላልሰን’ ሲሉኝ፣ ንግግሬ ያልተመቸው ዘመናይ ደግሞ፣ ‘ምን ለማለት ፈልገህ ነው?’ ብሎ ያጉረጠርጥብኛል፡፡ በፈሪዎችና በኃይለኞች መካከል ትንሽ ሥፍራ ማጣት ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ ሳስብ የሰላም ዋጋ ክብደት ጐልቶ ይሰማኛል፡፡ ኦ ሰላም ትናፍቂያለሽ!

ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ከዓመታት በፊት ያዘኑትን ቤተሰቦች ለማፅናናት ሄዶ ሲመለስ የነገረኝ አይረሳኝም፡፡ እሱ እንደ ነገረኝ አንድ አፅናኝ የሃይማኖት ሰው ለሐዘንተኞቹም ሆኑ ለአፅናኞች አደረጉት ያለው ንግግር ልቤን ነካው፡፡ ልበ ብርሃን የሆኑ ሰዎች በጠፉበት በዚህ ዘመን አንድ ሰው ሲገኝ ተመስገን ቢባል አይበዛም፡፡ ‹‹አንበርብር ልቤ ነበር የተነካው፤›› አለኝ፡፡ ‹‹እኚህ ሰው ‘ሰው ብቻ ማለት ምንድን ማለት ነው? ብዬ ሳስብ የሚበላ፣ የሚጠጣ፣ በሚለብሰው ልብስ፣ በሚነዳው መኪና የኑሮን ስኬት የሚለካ ማለት ነው፡፡ እስከ ሞት የሚኖር ማለት ነው፣ እንደ እንስሳ፡፡ ታላቁ ሊቅ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ ይላል፡፡ ሰው እግዚአብሔር ሲለየው ፀባዩ እንደ አራዊት፣ አመጋገቡ እንደ እንስሳ ሆኖ መልኩ ብቻ የእግዚአብሔር ሆኖ ይቀራል፡፡ በጣም ቀለል ባለ አገላለጽ ሲም ካርዱ የወጣ ሞባይል ማለት ነው፡፡ ጥሪ የማይቀበል፡፡ ለጉትቻ ማንጠልጠያ ብቻ የተሠራም ጆሮ አለ’ ሲሉ ልቤ ከመጠን በላይ ተነካ…›› ሲለኝ እኔ ራሴ ፈዝዤ ነበር ያደመጥኩት፡፡

የባሻዬ ልጅ እንደነገረኝ ሰውየው ከተማ ፈርሶ እየተገነባ ነው እየተባለ ሲወራ እንደሚሰሙ (ዓይነ ሥውር በመሆናቸው)፣ ነገር ግን ፈርሶ መሠራት ያለበት የሰው አስተሳሰብ ነው ማለታቸውን አከለልኝ፡፡ ‹‹የሰው አስተሳሰብ ፈርሶ ካልተሠራ የተሠራው ከተማ ይፈርሳል፡፡ ጃፓንና ቻይና አገራቸውን ያለሙት መጀመሪያ አስተሳሰባቸውን አልምተው ነው፡፡ አስተሳሰቡ ያልለማ ሕዝብ ያለማውን ያወድማል…’ ብለው ሲያክሉበት እንዲህ ዓይነት መካሪ አያሳጣን ብዬ በሆዴ ምስጋናዬን አዥጐደጐድኩት፤›› ብሎ ሲነግረኝ ሳይታወቀኝ ባርኔጣዬን አንስቼ እጅ ነሳሁ፡፡ ቃለ ሕይወት ያሰማልን ማለት አሁን አይደለም? ‹‹ሰባኪው በዝርዝር ለህሊና ጠቃሚ በሆኑ ምክሮች የሰዎችን ነፍስ ሲያረሰርሱ፣ ዓይኖቻቸው ከንዋይ ላይ አልነቀል ያሉ ደግሞ ምዕመኑን በቀደዱት ቦይ እንደፈለጉት ይነዱታል…›› እያለ የባሻዬ ልጅ ተብሰከሰከ፡፡ ፖለቲከኞች፣ የሃይማኖት ሊቅ ተብዬዎች፣ ምሁራን ነን እያሉ የሚኮፈሱት፣ በየአደባባዩ እዩን እዩን የሚሉት፣ ወዘተ ለአገር ጠቃሚ የሆኑ ነገሮችን ከማበርከት ይልቅ በየተሰማሩባቸው መስኮች ገንዘብ ላይ መረባረባቸው፣ ለዝና መሯሯጣቸው፣ በሐሰት እየመሰከሩ ወገንን የሚያበጣብጡ ገንነው መታየታቸው ያበሳጨዋል፡፡ እንዲህ ሲሆን ደግሞ ያሳዝነኛል፡፡ ውስጡ ብግን ብሎ ደም ሥሮቹ ሲገታተሩ የክፉዎች ተግባር የፈጠረው ሰላም መንሳት ድቅን እያለብኝ አፅናናዋለሁ፡፡ እስቲ ፅናቱን ይስጠን!

‹‹እስኪ እንጨዋወት ጨዋታ ምን ከፋ፣ የሆድን በሆድ እያልን ጊዜ ከምንገፋ…›› ያለው ዘፋኝ ይናፍቀኛል። ዘፋኙ ይሆን ጀምሮ የተወው የጨዋታ ርዕስ? በእውነቱ ማንኛቸው እንደሚወሰውሱኝ እርግጠኛ አይደለሁም። ለመሆኑ እርግጠኛ ሆነን እናውቃለን? ብንሆንስ በምን? እንዳትሉኝና የጨዋታው ርዕስ መፍታታት እንዳይጀምር። እንዲያ ነው እንጂ! ነገር ካነሳን አይቀር ታዲያ ቀብረን እንለፍ። አይመስላችሁም? የቆመን እንጂ የሞተን መቅበር እርግፍ አድርገን በተውንበት፣ ጨዋነታችንና ወጋችን አጥንቱ ሰጎ በወጣበት በዚህ ዘመን፣ ለወደቀ ሞራል ምስክር ከመሆን ያድነን ነው የሚባል። ሌላ ምን ይባላል? እናም ወደ ሌላ ነገር ስታጠፍ፣ እርግጠኛ መሆን የቻልንባቸውን ወይም መሆን የምንችልባቸውን ነገሮች ቆጠራ መጀመሬ ነበር። አይዟችሁ ምንም እንኳ ድምፅ የመስጠት ዘመን ቢሆን እዚህ ላይ ‹ፒክኒክ› መውጣት ይቻላል። በዚያው እንዳትቀሩ እንጂ። አላምናችሁም እኮ እናንተን!

በዚህች ሲለን በምናፍርባት ሲለን በምንኮራባት፣ ‹ሁለት ሞት ሙቱ› ሲለን ደግሞ ‹አያሳየን› ብለን በምንመርቃት ምስኪኗ አገራችን እርግጠኛ መሆን ብሎ ነገር መዝገበ ቃላታችን እንዳይጓደል ያለ ቃል እንጂ፣ በበኩሌ አቻ ምሳሌ ያለው አይመስለኝም። የታየው እንግዲህ ማሳየት ነው። በልዩነት ማመን ከእኔና ከእናንተ ካልጀመረ ከላይ ይመጣል ብሎ መጠበቅ አላዋጣም። ለነገሩ በዚህም እርግጠኛ አይደለንም። አንድ ቀን ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ሳይቀር፣ በነፈሰው ነፍሶ በነደደበት ስለሚያነደን ኑሯችን ስንጫወት፣ ‹‹እኔ አንዳንዴ ሳስበው እንኳን ስለዕርምጃችን፣ በልተን ስለማደራችን፣ ስለኢኮኖሚ ዕድገታችን ቀርቶ ስለድህነታችንም እርግጠኞች ነን ብዬ አላስብም። ዓይናችን ስለማየቱ፣ ጆሯችን ስለመስማቱ፣ በማሰባችን ከእንስሳት የምንለይ የዓላማ ፍጡራን መሆናችንን ማመን ብሎ ነገርማ እርሳው…›› አለኝ። ከሁሉ ደሃ ስለመሆናችንም እርግጠኞች አይደለንም አባባሉ አስደንግጦኝ ትንሽ ቆይቶ፣ ‹ድህነታችን በጥናት ይረጋገጥ› እንዳይለኝ ፈርቼ ዞር አልኩ። ዞር ስል ለስንት አሥርት ዓመታት በኖርኩበት ሠፈር የሚገኝ ፎቶ ቤት አንዱ ቢጠይቀኝ፣ ‹‹ወደ ቀኝ ታጥፈህ መሰለኝ…›› ብዬ መመለስ። በዚህ ዓይነት አልኩ ወዲያው፣ በዚህ ዓይነት ‹የረገጥከው አፈር የማን ነው?› ቢለኝ ‹የእኛ መሰለኝ› ልለው ይሆን? ሆሆ!

እንዲህ የኖርኩትን ሁሉ በዜሮ የሚያጣፋ ግራ መጋባት ሲጠናወተኝ ታዲያ መድኃኒቴን አውቀዋለሁ። እሱም በሥራ መወጠር ነው። መድኃኒት በመግዛትና መድኃኒት በማሠራት ያዳከምነው ወኔ ሥራ ላይ ውሎ ቢሆን… አቤት ዛሬ እኛን ነበር ማየት። ለነገሩ አድርገነው ቢሆን ዛሬ የያዝነውን ይዘን እንዳለነው፣ ቢሆን የምንለው ዕድሜ ይመርበት ይክፋት እርግጠኛ መሆን አንችልም። ነገርኳችሁ እኮ። መራገጥ እንጂ ማረጋገጥ የእኛ አይደለም ስላችሁ? እኔን ካላመናችሁ አዛውንቱ ባሻዬ አንድ የሚሉት አባባል አለ። ‹‹ላለፈው ዕድሜ ከመቆጨት ለሚመጣው አስብ…›› ይላሉ። ይህች የባሻዬ አባባል ‹ከዚህ በፊት የሰማናት ስለመሰለን የራሳቸው ይሁን አይሁን እርግጠኛ መሆን አንችልም› ካላችሁ ደግሞ እንደ ፈቀዳችሁ። የመጠርጠር መብታችሁ በሕገ መንግሥቱም ሆነ በጎዳናው ተምኔት የተፈቀደ ነው። ግን አደራ ባሻዬን በኩረጃ ስማቸውን ስታጠፉ እንዳልሰማና እንዳንጣላ። የምሬን ነው! ፍራሽ ማደስ በእሳቸው አልተጀመረም። አያችሁ ሰው መጠየቅ ያለበት ባለው አቅም ዕውቀት ልክ መሆን አለበት። አልተሳሳትኩም መቼም። ‹‹ጥሬ ልፈጭ ብለሽ ዱቄት አታፍሺ…›› ሲባል የሰማሁበት ግዜ ለምን እንደሆነ እንጃ ሩቅ ይመስለኛል። እናንተ ጊዜው ነው ወይስ ትውስታችን ነው እየፈጠነ ያስቸገረን ግን? በ40 ሳንጨማደድ እንደ ባለ 80 ምርኩዝ አስፈለገን እኮ!

‹‹እንደ እኔማ ቢሆን እንዳስተሳሰቤ…›› ግጣም በማጣት እንጂ ስንኝ በመጨረስ ስለማንታማ፣ እንድትጨርሱት ትቼላችሁ ማልጄ ወጥቼ የሚሸጥ ‘ሲኖትራክ’ አደራድሬ ያስማማኋቸውን ደንበኞቼን ጉዳይ ከሰዓት በኋላ ለመቋጨት ሳስብ የገጠመኝን ላጫውታችሁን። አጉል ወጪ ቆጣቢ ልሁን ስል ቤት ገባሁና ማንጠግቦሽ ክሽን አድርጋ የሠራችውን ወጥ በሠርገኛ ጤፍ እንጀራ ሰልቅጬ፣ ሁለት ስኒ ቡናዬን ልፌ ለመመለስ ነበር አገባቤ። በነገራችን ላይ ለወትሮው የሥራው ባህሪ ሆነና ምሳ ሰዓት ሲደርስ የተገኘው ምግብ ቤት ገብቼ ነበር የምመገበው። አሁን አሁን ግን ሁለት ስህተት እንደ ድር ደጋግሜ ሳደራ መኖሬ ገባኝ። አንደኛው ‘የተገኘ’ የሚባል (እኔ እንደማስበው ዓይነት ምስኪንና ለትርፍ ያልቆመ ምግብ ቤት ማለቴ ነው) እንደሌለ፣ የምሳ ወጪዬ የሳምንት አስቤዛዬን ሲያስከነዳው ሳይ የተረዳሁት ነው። ሁለት እስከ ዛሬ በየካፌና በየሬስቶራንቱ ለምግብና ለመጠጥ ያወጣሁትን ቆጥቤው ቢሆን ኖሮ፣ የደርሶ መልስ የአውሮፕላን ትኬቴን ሸፍኖልኝ አሜሪካ ደርሼ እመለስ ነበር። ማን ነው ‹መምጣቱንስ ተመልሰህ አትመጣም› ሲለኝ የሰማሁት? እንጃ!

ጨዋታ እያነሱ ጨዋታ መጣልን እንግዲህ አንዴ ለምደነዋል። ቁም ነገሩንስ ቢሆን? ያዝ ለቀቅ መታወቂያችን ላይ አለመጻፉን እንደ ዕድል እንቆጥረዋለን መሰለኝ። “በደግ በደጉ እየተገናኝ ያዙኝ ልቀቁኝ ስንል ድል በሜዳውና በደጋፊ ጩኸት የሚቀናው ብሔራዊ ቡድናችን ሳይቀር ስንት ዘመን ያለተመልካች እንደተጫወተ አስበን እናውቃለን?” እያለ የሚነዘንዘኝ አንድ ወዳጅ ነበረኝ። ይኼ ወዳጄ ሁሉም ነገር ሲጠለዝ አብዝቶ የሚወድ ነበር። ኳስም ሆነ ነገር ካልተጠለዘ ደስ አይለውም። ብሎ ብሎ ታዲያ ሁሉም ነገር እያደር በአንድ ፓርቲ መዳፍ ሥር ውሎ ሲያድር፣ ኳሱም ተስፋ ባስቆረጠበት ሰዓት እሱን ራሱን ‘ዲቪ’ አሜሪካ ድረስ ጠልዞ አሸሸው። እሱን እያስታወስኩ አዕምሮው በአግባቡ ለመሥራት እያመነታ ለመታወክ ዳር ዳር እያለ ካሰጋኝ፣ የረጅም ዘመን ደንበኛዬ ጋር ወረዳና ክፍለ ከተማ ዘው ዘው ስል ሰነበትኩ። ኳተንኩ ማለት ይቀላል!

ይኼኛው ጓዴ ነጋዴ ነው። ቀልጣፋ ነው። ነበር ልበል መሰል አሁን እንኳ። ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ ትልቅ ሆቴል አለው። ሰሞኑን፣ ‹‹ከየትም ብለህ ጥሩ መኖሪያ ቤት ውለድ…›› አለኝ። እንደ አጋጣሚ ሲኤምሲ አካከቢ አንድ ዳያስፖራ “ጆሮውን በልልኝ” ያለኝ ቤት ነበርና አገናኝቼው ገዝቶታል። ቤት ሲገዛ በሥራው ደስተኛ፣ በገቢው የተማመነ መስሎኝ ነበር መጀመሪያ። ኋላ ሳየው ግን እጅግ ተስፋ መቁረጥ ይታይበታል። እንዳልኳችሁ የአዕምሮ ጤናው እየተቃወሰ ነው። የቤቱን ካርታና ይዞታ በስሙ እያዛወረ ሳለ ምን እንደሆነ ብጠይቀው ‹‹ዕዳ!›› አለኝ። ‹‹የምን ዕዳ?›› ስለው፣ ‹‹ግብር አናቴ ላይ ወጣ…›› አለኝ። ‹‹መቼ ዕለት ከፍዬ ጨረስኩ ተመስገን ስትል አልነበር?››› እያልኩ ሰቅዤ ስይዘው፣ ‹‹የአምናና የካቻምናን ኦዲት አድርገው ከአቅሜ በላይ እንደሚጭኑብኝ መቼ ጠረጠርኩ?›› ብሎ ብቻውን ማውራት ጀመረ። በከንቱ እኮ ነው ለሀብታም ልደት አላስፈላጊ የርችት ወጪ የምናወጣው ጎበዝ!

በአጭሩ ወዳጄና የዘመናት ደንበኛዬ ዕዳ እያለበት ቤት የገዛው ንግድ ቤቱ እስከ መታሸግ ቢደርስ ደንታ አልሰጠው ብሎ፣ የዕረፍት ኑሮ ተጠምቶ መሆኑን ወዲያው ደረስኩበት። የአዕምሮው መታወክ ያሳሰባቸው ቤተሰቦቹ ነጋ ጠባ ወትውተው ይዘውት ሄደው ፀበል ማስጠመቅ ሥራቸው ሆኗል። ውሎ አድሮ ባሻዬም ያውቁት ነበርና የሆነውን ሳጫውታቸው፣ ‹‹ግብር መክፈል የውዴታ ግዴታ ስለሆነ አታነካካኝ…›› ብለው ዝም አሉ። ‹‹ምነው ፈሩ?›› ስላቸው ዘራፍ ብለው አቅራሩ። ሳበርዳቸው ደግሞ፣ ‹‹ይኼ ዓለም የድካም ዓለም ነው። ብዙ ስታስብ ብዙ ታጣለህ። ብዙ ስታስገባ ብዙ ትከፍላለህ። ትርፍህ ሰላምህ ነው። በመጠን ኑር…›› ብለው ዝም አሉ። ‹‹ግን እንዴት ነው በመጠን ተኑሮ፣ በጎመን በጤና ብሂል በፈጣን ግስጋሴ ላይ ካለው ኢኮኖሚያችን ጋር መስማማት የሚቻለው?››› ብላቸው፣ ‹‹እሱን ዕድገትህን አላውቅልህም። ነገር ግን በገቢህ ልክ መኖር ስትችል ሰላም ታገኛለህ፡፡ እሱን መምረጥ ያንተ ፋንታ ነው…›› አሉኝ። ‹‹‹እንቀጥለዋለን…›› ብዬ ትቻቸው ሄድኩ። እውነት መስሏችሁ አደራ ቀጥልልን እንዳትሉኝ። እንዲህ ያለ ወሬ ከመቀጠል መጀመሪያ በየሠፈራችሁ እየተቋረጠ ያስቸገራችሁን ኤሌክትሪክ ማስቀጠል ይቅደም። አይሻልም?

እንሰነባበት? ሳይሻል አይቀርም። ምክንያቱም ብዙ ልብ የሚያጠፋ ነገር ወሮናል። ‹‹አሁን እስኪ ልብ ደም እንጂ ወተት ይረጫል በፈጣሪ? ምነው ታዲያ እያደር ወተት ወተቱን ትተን ደም ደሙን አልን?›› ብዬ ባሻዬን ነገራችንን ባነሳላቸው፣ ‹‹የቃየል ሥራ ነዋ…›› ብለው ዝም። እሳቸው ዝም ሲሉኝ ወደ ግሮሰሪዬ ሄድኩ። ‹‹መንግሥታት ለሕዝባቸው የቀን የቀኑን እንጂ የሌት የሌቱን አስበውለት አያውቁም…›› አለኝ ተከትሎኝ የደረሰው ምሁሩ የባሻዬ ልጅ። ‹‹ምን ማለት ነው?›› ስለው፣ ‹‹በቃ! እንደምታየው ነው። ሕዝብ ምርታማና ታታሪ ሠራተኛ የሚሆነው ሰላም ሲኖረው ነው። ከሰላምም ደግሞ ትልቁ ሰላም ሰላማዊ የአልጋ እንቅልፉ ነው …›› ሲል ሳለ አንዱ ጣልቃ ገብቶ፣ ‹‹ይኼው እኔ አልጋ መስሎኝ አልጋ ቀየርኩ። ፍራሽ መስሎኝ ፍራሽ አሳደስኩ። ትራስ ነው ብዬ በአዲስ ሞከርኩት። እህሳ? ፍጥጥ እንዳልኩ መንጋት። ‘አሁን ነገ ጉዳዬን በቶሎ ይጨርሱልኝ ይሆን? ከአቅሜ በላይ ግብር ቢጣልብኝስ? አቤት ብል ሰሚ አገኝ ይሆን? ያላግባብ ተጥሎብኛል ይቀነስልኝ ከምለው ገንዘብ በላይ ጉቦ እጠየቅ ይሆን?’ ነው በቃ እንቅልፍ የሚነሳኝ። በጥርጣሬና በፍርኃት ዝሎ ልቤ ያለ አንዳች አጋዥ ኃይል መምታቱ ብቻ ይገርመኛል…›› ብሎ በሞቅታ መጠጥ ካልጋበዝኩ አለ።

የባሻዬ ልጅ ወደ እኔ ዞሮ፣ ‹‹ጨርሶልሃል፣ ሥጋትና ተስፋ በልባችን ታዛ መሳ ለመሳ ነግሠው ወደፊት መጓዝ ብሎ ነገር የለም። ከጠራ የመንግሥት አቋምና ፖሊሲ በፊት፣ የረጋና የተማመነ የሕዝብ ልብ ሊኖር ያስፈልጋል…›› ብሎ ጋባዣችንን ወደ ማመሥገን ዞረ። ‘ልብ ለልብ’ የሚባል አጀንዳ ፓርላማ ቀርቦ ውይይት ሲደረግ ማየት ናፈቀኝ። ግን ፓርላማ ከመግባታችን በፊት እዚህ ጎዳናው ላይ እንደ ሰው፣ እንደ ወገን፣ እንደ ፍጡር…  ልብ ለልብ መገናኘት የለብንም መጀመሪያ? አሁንስ ልቤን አመመኝ መሰል፡፡ አንዳንዴ እኮ ወፈፍ ሲያደርገኝ ዛሬ ከትናንት ለምን አይሻልም ብዬ አስባለሁ፡፡ አንዳንዶች እንደቆሙበትና እንደሚያምኑበት አቋም ዛሬና ነገን በስሜታቸው ልክ ይመዝኑታል፡፡ እኔ ግን ለራሴ ብቻ ሳይሆን ለሁላችንም በማለት እንዲህ አስባለሁ፡፡ ‘ትናንትና ከዛሬ ጋር ባይወዳደርም፣ ነገ ግን ከዛሬ መብለጥ አለበት’፡፡ ነገ ከዛሬ ካልተሻለ እኛ ምንድነን? ነገ ከዛሬ ካልተሻለ ምኑን ተኖረ? መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት