‹‹ባለቤቱ የናቀውን አሞሌ ባለዕዳው አይቀበለውም››
በያሬድ ነጋሽ
የዚህ ርዕሰ አንቀጽ ዝግጅት እንደመነሻ ስደት፣ የስደት ምክንያቶችንና ስደተኛ የሚሉ አንኳር ጉዳዩችን ከኢትዮጵያውያን ግንዛቤ አንፃር ለመመልከት እንዲያስችለን በሦስት ዘመናት ውስጥ ከፍለን በመመልከት፣ በመቀጠል ለአገራችን ስደተኞች የስደተኛ ተቀባይ አገሮች ምላሽና በመጨረሻም ከመደበኛ የስደት ምክንያት ውጪ እንደ መንስዔ መጠቀስ የሚችል በወጣቱ ውስጥ ያለው ሽሽግ ፍላጎት ምን ይመስላል የሚለውን ይመለከታል።
‹‹ስደት ሰብዓዊ መብት ነው›› የሚሉ ወገኖች እየተመለከትን ባለበት በአሁኑ ወቅት ስለስደተኛ ከማውራታችን በፊት ስለስደትና ስለምክንያቶቹ ማንሳት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ ስደት (ማይግሬሽን) ሰዎችም ይሁን እንስሳት በቋሚነት ይሁን በጊዜያዊነት በአገር ውስጥም ይሁን ከአገር ውጭ በተለያየ ምክንያት ነባር ሥፍራቸውን በመልቀቅ ወደ አዲስ ቦታ የሚያደርጉትን ጉዞ ወካይ ቃል በመሆን ያገለግላል፡፡
የሰው ልጅ ስደት ላይ እናተኩራለን። ሰዎች ለምን ይሰደዳሉ? ብለን ስንጠይቅ እንደ ምክንያት ሆነው የምናገኛቸው ኢኮኖሚያዊ (ሥራ ለማግኘት)፣ ማኅበራዊ (ከቤተሰብ ወይም ከጓደኞች ጋር በመሆን ለተሻለ የሕይወት ጥራት ወደ አንድ ቦታ መሄድ)፣ የፖለቲካ (ፖለቲካዊ ንፍገት ወይም ጦርነትን ለማምለጥ)፣ የተፈጥሮ ሥጋቶች (እንደ ጎርፍ ያሉ የተፈጥሮ አደጋዎች) የሚሉ ጠቅለል ያሉ ምክንያቶችን ይጠቀሳሉ።
ሰዎች ከነባር መቀመጫ አገራቸው እንዲሰደዱ ከውስጥ ሆነው የሚገፉ ምክንያቶች በሚል የአገልግሎት አሰጣጥ እጥረት፣ የደኅንነት ሥጋቶች፣ ከፍተኛ ወንጀል መበራከት፣ የሰብል በተለያየ ምክንያት መውደም፣ ድርቅ፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ፣ ድህነትና ጦርነት ሲጠቀሱ፤ ከመኖሪያ ሥፍራቸው ውጪ ሆነው ሰዎች ከአገራቸው እንዲሰደዱ የሚያስገድዱ አማላይ ምክንያቶች በሚል ደግሞ ከፍተኛ የሥራ ዕድል፣ የውጭ አገሮች ሀብትና ብልፅግና የተሻሉ አገልግሎቶች፣ ተስማሚ የአየር ንብረት፣ አስተማማኝ ደኅንነት፣ ከወንጀል የፀዳ ቀጣና፣ የፖለቲካ መረጋጋትና ለም መሬት በሚል ይጠቀሳሉ።
እነዚህ ለስደት ምክንያት የሆኑ ነገሮች በዘመን ሒደት ውስጥ እየተለዋወጡ፣ በመጠን እየጨመሩ መምጣታቸውና ዛሬ የነበሩ ምክንያቶች እየቀሩ በሌላ እየተተኩ መሄዳቸው፣ መልካቸው እንደ አገር የሥነ ሕዝብና የኢኮኖሚ ደረጃ መወሰናቸው፣ በተለያየ ምክንያት የተሰደደውን ሕዝብ የሌሎች አገሮች የመቀበል ፍላጎት ስደተኛው ከመጣበት አካባቢ የሥነ ሕዝብና ኢኮኖሚ ደረጃ አንፃርና እንደ የግለሰቦቹ የትምህርት፣ የዕውቅናና የሀብት መጠን ልክ፣ እንደ አገር ወዳጅነት፣ የደም መዋረስና በቅኝ ግዛት ቀጣና መተሳሰር ልክ ተቀባይነት ሊያገኙ ወይም ሊያጡ መቻሉ ሌላው ገጽታቸው ነው።
ሌላው የስደት ምክንያት ዓይነቶች፣ የስደተኛውን መጠንና የስደተኛውን ዓይነት ለማስቀመጥ መነሻ፣ መከፋፈያና መተንተኛ የሚሆን ድንበር (ሪፈረንስ) አስፈላጊ የሆነ ሲሆን፣ እነዚህን ድንበሮች ተመርኩዘው ለምሳሌ በአፍሪካ፣ በደቡብ አሜሪካ፣ በእስያና ከዓረብያን አካባቢ በቅድመ ቅኝ ግዛት ወቅት፣ በቅኝ ግዛት ወቅትና ድኅረ ቅኝ ግዛት ወቅት፣ በአውሮፓ ከኢንዱስትሪ አብዮት ወይም ከአብርሆት (ኢንላይንትመንት) በፊትና በኋላ፣ በዓለም ደረጃ ከዓለም ጦርነት በፊትና በኋላ በማለት መሥፈሪያ የሚሆን ድንበር በማበጀት የስደት መጠኑንና ዓይነቱን፣ ስደተኛው ተመልሶ ወደ አገሩ መመለስ መቻሉንና አለመቻሉን ሌላም ተያያዥ ጉዳዮችን ለማንሳት ሲሞክሩ ይስተዋላል።
እኛም ከአገራችን ወደ ውጭ ስለሚሰደዱ ዜጎች ከማውራታችን በፊት የስደቱ ይዘትና ምክንያትን በዘመናት መነጽር ከፋፍለን ማየት እንድንችል በመጀመርያ በኢትዮጵያ የዜጎች ስደት ከንጉሣዊው ሥርዓት ማብቂያ (1967 ዓ.ም.) በፊት፣ ከደርግ መምጫ (1967 ዓ.ም.) እስከ ውድቀቱ (1983 ዓ.ም.) ባለው ወቅትና ከኢሕአዴግ መምጫ (1983 ዓ.ም.) አሁን እስካለንበት ድረስ በሚል ልንመለከተው ወደናል። በመቀጠል የውጭዎቹ በተለይም የዓረብ አገሮች ለኢትዮጵያውያን ስደተኞች ያላቸውን አቀባበልና በአገራችን ስላለ ሽሽግ የወጣቱ የስደት መንስዔ በሚል አንድ ጉዳይ እንመለከታለን።
ከኢትዮጵያውያን የምልከታ ተፅዕኖ የሚመነጭ የወጣቱ ሽሽግ የስደት ፍላጎት ‹‹ባለቤቱ የናቀውን አሞሌ ባለዕዳው አይቀበለውም››
በመጀመርያ በኢትዮጵያ የዜጎች ስደት ይዘትና ምክንያቱን ከዘውድ ሥርዓቱ ማብቂያ በፊት የነበረውን ወቅት ስናይ ይህንን ወቅት አስመልክቶ አብዛኞቻችንን በሚያስማማ መልኩ ደራሲና ሐያሲ ዓለማየሁ ገላጋይ ዘመኑን አስመልክቶ የአፄ ቴዎድሮስንና የቤተሰባቸውን ታሪክ በማንሳት የደረሰበት መደምደሚያ ላይ መድረስ እንዲያስችለን ታሪኩን በአጭሩ እንቀነጭበዋለን።
ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ፣ ‹‹እጅ ቢሰጡ ለግርማዊነትዎና ለመላው ቤተሰቦችዎ የክብር አያያዝ እናደርጋለን፤›› የሚለውን የጠቅላይ አዛዥ ሮበርት ናፔር ደብዳቤ ካዩ በኋላ ‹‹ያልገባኝ ነገር ይህ የክብር አያያዝ የሚለው ነገር ምንድነው? እንደ እስረኛ ተይዤ ነው የክብር አያያዝ የሚለው? ወይስ አገሪቱን ከሽፍታ ሊያፀዱልኝ ነው? አውቀዋለሁ በእስረኝነት እንዴት እንደሚይዘኝ ማለቱን። እጄን ለጠላት ሰጥቼ የማንም መጫወቻና መዘባበቻ አልሆንም ብለው ብቻቸውን ሲተክዙ ከቆዩ በኋላ ወዲያው ተነስተው መሬቱን በግንባራቸው እያስነኩ ሦስት ጊዜ ከሰገዱ በኋላ፣ ሦስት ጊዜ አማተቡና የታጠቁትን ባለሁለት አፈሙዝ ሽጉጥ እንደቆሙ መዘው ራሳቸው ላይ ደቀኑ። ነገሩን ይመለከቱ የነበሩ ሰዎች ሮጠው ወገባቸውን ሲይዟቸው በትንቅንቁ መሀል ጥይቱ ባርቆ ጆሮዋቸውን በትንሹ አቆሰላቸው። በሁለተኛው ወደ ግንባራቸው አዙረው ለመተኮስ ሲሞክሩ ሽጉጡ ውስጥ ጥይት ባልነበረበት በኩል በመሆኑ ከሞት ዳኑ። … በመቅደላው ጦርነት እንግሊዞች እሳቸውን በሕይወት ለመማረክ ስለፈለጉ አነጣጥረው ወደ እሳቸው አይተኩሱም ነበር። …እሳቸው ወደ መቅደላ ከፍታ ቦታ ከወጡ በኋላ ወደ ወልደ ጋብር ዞረው ‘በእንግሊዞች እጅ ከመያዝ ራሴን እገድላለሁ’ ብለው ሽጉጣቸውን አፋቸው ውስጥ ከትተው ተኮሱ። ጥይቷ በላንቃቸው በኩል አልፋ በማጅራታቸው ወጣች። …ተኩሰው ከተረፉበትም ይሁን ከሞቱበት ዋነኛ ምክንያቶቻቸው ውስጥ ተማርከው ከአገር መውጣትና መንገላታት አለመፈለጋቸው እንደ አንድ ምክንያት ይጠቀሳል፤›› ይላል ታደለ ብጡል ክብረት አፄ ቴዎድሮስና ልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ በሚል መጽሐፉ።
‹‹እቴጌ ጥሩ ወርቅ ውቤ ልጃቸው ዓለማየሁን ተከትለው ከእንግሊዝ ጦር ጋር ጉዟቸውን ቀጠሉ። መቅደላን ከለቀቁ ጀምሮ ጤና አልነበሩም። ህንጣሎ አጠገብ ሐይቅ ሃላጥ ከሚባል ሥፍራ ሲደርሱ መከረኛዋ ጥሩ ወርቅ ሞቱ። ጨለቆት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከታላቁ ከራስ ወልደ ሥላሴ አጠገብ ተቀበሩ፤›› ጳውሎስ ኞኞ አፄ ቴዎድሮስ በሚል መጽሐፉ ‹‹እቴጌ ጥሩ ወርቅ አባት ሁነው ብለው ቃል ባስገቡኝ መሠረት የጠየቁኝን ለዓለማየሁ እፈጽማለሁ ብዬ ማልኩላቸው፤›› የሚለው ካፒቴን ስፒዲ በቃሉ መሠረት ጥበቃውን እንዳያደርግለት ተከልክሎ ነበር። ንግሥት ቪክቶሪያ ስለዓለማየሁ አኗኗርና አሟሟት ከጻፉት ማስታወሻ ውስጥ ‹‹የልዑል ዓለማየሁ አሟሟት በእርግጥም አሳዛኝ ነው። ምክንያቱም እስከዚህ ዕደሜው ድረስ በሰው አገር ኑሮ በብቸኝነት ዘመኑን ስላሳለፈና ወገኑ የሆነ ዘመድ ወይም ጓደኛ ሳይኖረው፣ የአገሩን ሽታ እንደናፈቀ መሞቱና ጀግና ጥሩ ወጣት እንደነበረ ትዝ ሲለንም ሆነ ስናስታውሰው ያጋጠመውን ሰንካላ ዕድል እንደ እርሱ ለመቋቋም የሚችል ያለ አይመስለንም። ሕይወቱ በሙሉ ደስተኛ አልነበረም። ማንኛውም ዓይነት ችግርና ሥቃይ ያጋጥመው ነበር። በሁሉም ነገር ከፍተኛ ሐዘን እንደተሰማው አለፈና በከርሰ መቃብር ዋለ፤›› ይላሉ፡፡ ይህንን ታሪክ የተንተራሰው ደራሲ ዓለማየሁ ገላጋይ በዚህ ዘመን የነበረ የስደት አስተሳሰብና ግንዛቤ እንደሚያመለክተው ስደት የማይታሰብ ሲሆን ኢትዮጵያውያን ገና ከሩቁ ሲያስቡት እንደ ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ሞትን የሚመርጡበት፣ ተገደው መንገድ ቢጀምሩ እንኳን እንደ አፄ ቴዎድሮስ ባለቤትና የዓለማየው እናት ጥሩወርቅ ከአገር ሳይወጡ ሕይወት የሚያልፍበት፣ ድንገት ባህር ተሻግረው ቢሰደዱት እንኳን እንደ ልጅ ዓለማየው በሐዘን የሚቆራመዱበትና ሕይወት አጭር ሆና የምታልፍበት ነበር፤›› ይለዋል።
ሁላችንንም የሚያስማማ ሐሳብ ሲሆን የክብርን ጥያቄ አገር ውስጥ በመሆን ማስመስከሩ ፋሽን እንደነበር እንረዳለን። ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ከውጭ አገሮች የሚመጣላቸውን የግብዣ ጥሪዎች እንኳን ለአክስት ልጃቸው ራስ መኰንን አሳልፈው ሲሰጡ አስተውለናል። አፄ ኃይለ ሥላሴ እንኳን የአምስቱ ዓመት የፋሽስት ወረራ ወቅት እንግሊዝ የቆዩበት ምክንያት አጨቃጫቂ ቢሆንም፣ በወቅቱ ንጉሥ ተማርኮ ኃፍረቱ ለአገር እንዳይተርፍ የተዘየደ መላ እንደነበር በርካቶች ይስማማሉ። በወቅቱ ስደት ላይ የነበረው ዜጋም ቢሆን በ1950ዎቹ ከመላ አፍሪካ የተውጣጡ ተማሪዎች ባገኙት የትምህርት ዕድል አማካይነት በእንግሊዝ ካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በእንግሊዝ መንግሥት የሚሰጣቸውን የመኖሪያ ፈቃድ ላለመቀበል አሻፈረኝ በማለት ወደ አገራቸው የሚመለሱ ተማሪዎች ኢትዮጵያውያን ብቸኞቹ ነበሩና ዜጋውም የነገሥታቱን ምልከታ የሚጋራ እንደነበር ማመሳከሪያ ይሆነናል።
በሁለተኝነት ከደርግ መምጫ (1967 ዓ.ም.) እስከ ውድቀቱ (1983 ዓ.ም.) የነበረውን የኢትዮጵያውያን የስደት ምክንያትና ግንዛቤን የምንመለከት ይሆናል። ወቅቱ በኃይል ይሁንም በመግባባት (ይህንን ለታሪክ ጸሐፊዎች ትተን) የዘውድ ሥርዓቱና የንጉሥ አፄ ኃይለ ሥላሴ የንግሥና ዘመን አብቅቶ ወታደራዊው መንግሥት ደርግ በትረ ሥልጣኑን የጨበጠበት ጊዜ ሲሆን፣ ይህ ጅማሮ በመላው ኢትዮጵያውያን በተለይም በወጣቱ ዘንድ ትልቅ ተስፋን እንዲሰንቁ በር የከፈተ፣ በሠለጠነው ዓለም ላይ የሚታየው መልካም ነገር ሁሉ በአገራቸው የሚያዩበት ጊዜ ሩቅ አለመሆኑን በመገመት ምሁራኑ፣ ተማሪው፣ ነጋዴው፣ መላው ማኅበረሰብ ለአገሩ የበኩሉን ለማበርከት መሰናዳት የጀመረበትና ውጭ አገር ትምህርት ላይ የነበሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን በገፍ ወደ አገር የተመለሱበት ወቅት ነበር (የፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ‹‹ጤዛ›› የተሰኘ ፊልም ይመለከቷል)፡፡ ወቅቱን በጉልህ ለመረዳት ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ የፈነጠቀውን ተስፋ ዓይነት ይመስል ነበር ብንል ሁነኛ ምሳሌ ይሆንልናል::
ጅምሩ እንዲህ እንዳለ ወታደራዊው መንግሥት የኢትዮጵያ ሠራተኛ ፓርቲን (ኢሠፓ) በማቋቋም በሕዝቡ የጋለ ስሜት ላይ ቀዝቃዛ ውኃ በመቸለስና በመቃረን መጓዝ ቀጠለ፡፡ ከዚህ ፓርቲ መስመር ውጪ ነው ብሎ ያመነበትን የዳቦ ስም እየሰጠ በእስርና በሞት ሲቀጣ፣ ተስፈኛ ወጣቱም የራሱን ጎራ በመያዝ ምላሹን መስጠት ጀመረ፡፡ ደም መፋሰሱ በረከተ፡፡ በማያባራ የወንድማማቾች ጦርነት ውስጥ በርካታ የኢትዮጵያ ወጣት ውድ ሕይወቱን ይማግድ ያዘ፡፡ በአንድ በኩል ከኢሠፓ መስመር ውጪ ነህ በሚል በሌላ መልኩ ደግሞ በማያልቅ ጦርነት ውስጥ በየሥፍራው ሬሳው እየተጣለ ያለው ወጣት ሕይወቱን ለማትረፍ እግሩ ያደረሰው ድረስ ለመድረስ የአገሪቱን ድንበር እየጣሰ ይሰደድ ጀመር፡፡
በዚህ መነሻነት በወቅቱ የነበረው የሰው ልጅ ስደት ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያን ሳይጠግቧት ልክ የእናቱን ጡት ግራዋ ወይም መራራ ቀብተው ዓይን ዓይኑን እያየ እንዳስጣሉት ጨቅላ ሕፃን የመነጠቅ ያክል አድርገን መውሰድ እንችላለን፡፡ ስንጠቀልለውም በዚህ ወቅት የፖለቲካው አለመረጋጋት ዋነኛ የስደት መንስዔ እንደነበር መገመት እንችላለን፡፡
በሦስተኛ ደረጃ የምንመለከተው የደርግ ሥርዓት አብቅቶ የሽግግር መንግሥት ሥልጣን ከያዘበት ዕለት (1983 ዓ.ም.) ጀምሮ አሁን እስካለንበት ወቅት ድረስ ያለውን የኢትዮጵያውያን የስደት ምልከታና መንስዔ ይሆናል፡፡
የወቅቱ ጅማሮ በድጋሚ አገሪቱ በወታደራዊ መንግሥት ቁጥጥር ሥር የዋለችበትና መንግሥቱም በአንፃራዊ መልኩ ሰላም ለማስፈን ሰፊ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ አጠናክሮ ይሠራበት የነበረበት ወቅት ስለነበር ድጋሚ በወታደራዊ መንግሥት ሥር መሆናቸው ያላስደሰታቸው ወገኖች ቢኖሩም በአብዛኛው የአገሪቱ ሕዝብ ዘንድ አዲስ ተስፋን ለማጫር ቻለ፡፡ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ለማድረግ መዳረሻ ይሆን ዘንድ በሚል አገሪቷ በጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ሥር እንድትቆይ ተደረገ፡፡
በወቅቱ በኃይል አገሪቱን የተቆጣጠረው ወታደራዊው መንግሥት ዴሞክራሲያዊ ይሁን የዴሞክራሲ ሜካፕ አብዝቶ የተቀባ በውል ባይታወቅም (ይህንንም ለፖለቲካ ተንታኞች በመተው) ፓርላማውን፣ ሕዝቡን ይወክላሉ የተባሉ የፖለቲካ ፖርቲዎች ተወያይተው ተግባብተውበታል ያለውን ሕገ መንግሥት በማሰናዳትና ነፃና ፍትሐዊ ነው ያለውን ምርጫ በማዘጋጀት የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) የተባለ ፖለቲካ ፓርቲ እንዳሸነፈ አስታወቀ፡፡
በምርጫ ያሸነፈው የኢሕአዴግ መንግሥት ኢትዮጵያን ባስተዳደረበት ዓመታት አገራችን ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ውጪ በአንፃራዊ መልኩ ከውጭ ኃይላት ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ያዳበረችበትና የኢኮኖሚ መነቃቃት ያሳየችበት ወቅት ተደርጎ መወሰድ ቢችልም በሌላ መልኩ ግን ከበርካታ ውስጣዊ ችግሮች ማምለጥ ያልተቻለም ነበር፡፡ (ከርዕሰ ጉዳያችን ጋር ተያያዥ በሆነ ውስጣዊ ችግር ላይ እናተኩራለን) የሕዝብ ቁጥር በፍጥነትና በመጠን ተበራክቶ የታየበትና ይህንን የሚመክት አስተዳደራዊም ይሁን የኢኮኖሚ ዕድገት ማየት ያልተቻለበት መሆኑ የወቅቱ ዋነኛው የአገሪቱ ውስጣዊ ችግር ተደርጎ መወሰድ ይችላል፡፡
ለማብራራት ያክል
የአገሪቱ ቁጥሩ በገፍ እየበዛ ለመጣው አምራች ኃይል ወደ ሥራ የሚያሰማራውና ራሱን የሚችልበት የኢኮኖሚ አቅም ያላዳበረችበት፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ያልሰፈነበት፣ ሙስና የተንሰራፋበትና የመልካም አስተዳደር ዕጦት የሞላበት ገጽታን ተላብሳ የታየችበት ወቅት ነበር ብንል ያለማጋነን ወቅቱን ያስረዳልናል፡፡
የዚህ ዓይነቱ ሁኔታ ሦስት ዓይነት ማኅበረሰብ በአገሪቱ ውስጥ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡ አንደኛው ክፍል የገዥው ፖለቲካ ፓርቲ አቀንቃኝ በመሆንና በልማታዊ ስም በአገሪቱ ከተንሰራፋው የሙስና ገመድ ጋር ራሱን በማሰር የሚጠየቀውን በመስጠት የሚጠይቀውን እየተደረገለት በአንድ ጀንበር ሚሊዮኖችን የሚያፍሰው የማኅበረሰብ ክፍል ነው፡፡
ሁለተኛው ሕጋዊ የንግድ ሰንሰለቱን በመከተል ቀን ከለሊት እየለፋ ኑሮን ለማሸነፍ የሚጥር፣ ሆኖም ግን የቤተሰቡን የዕለት ጉርስ እንኳን ለመሸፈን አዳጋች የሆነበት የማኅበረሰብ ክፍል ነው፡፡
በሦስተኛነት የምናገኘው ተስፋ በቆረጠ መንፈስ ከሁሉ ነገር እጁን ሰብስቦ ‹‹ባገኝም በልቼ ባጣም ተደስቼ›› የምትለዋን ዘፈን እየዘፈነ በአንድ የመንደሩ መሰብሰቢያ ሥፍራ ላይ ውሎ ቤት ያፈራውን ለመቀማመስ ወደ እናቱ ቤት የሚመለስ በርካታ ወጣትን ያቀፈ የማኅበረሰብ ክፍልን ነው፡፡
ሕዝቡ ማብቂያው መቼ ይሆን? በሚል የሚጠይቀውን የኢሕአዴግን አገዛዝ ሥልታዊ በሆነ መንገድ ከሥልጣን አውርዶ የተካውና አካሄዱ ተስፋ ሰጪ የነበረው የአገራችን የአሁኑ መንግሥትም መፍትሔ ላይ መድረስ ሳይችል ቀርቶ (ከቀድሞ የባሱ ነገሮች እንዳሉ ሆነው) የጥቂቶች ብቻ እስክትመስል ድረስ ከአቋራጭ ከባሪው በስተቀር ከአገሩ ትሩፋት መቋደስ ያልቻለው ሁለተኛውንና ሦስተኛ በሚል የገለጽነው የማኅበረሰብ ክፍል የኢኮኖሚው አቅሙን ያደረጅልኛል ካለው ሐሳብ ውስጥ ስደትን ተቀዳሚ በማድረግ በኢኮኖሚ ደረጃ ከአገሬ ይሻላሉ ወዳላቸው አገሮች በሕጋዊም ይሁን በሕገወጥ መልኩ እየተሰደደ ያለንበት ወቅት ድረስ ደርሰናል፡፡ ከዚህ በመነሳት ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣበት ወቅት አንስቶ አሁን እስካለንበት ድረስ ያለውን የኢትዮጵያውያን የሰው ልጅ ስደት ምልከታ እንደሚያስረዳን የዜጋው ዋና ዋና የኢኮኖሚ ጥያቄዎች መጨመርና ጥያቄዎቹን የሚመልስበት አማራጭ በበቂ ሁኔታ አለማግኘቱ በዋነኝነት መንስዔ ተደርጎ መወሰድ ይችላል።
በመጀመርያው ክፍል ወቅት ስደት የማይታሰብበትን፣ በሁለተኛው ወቅት በፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት ኢትዮጵያውያን በመገደድ የሚሰደዱበትንና በሦስተኛ ወቅት የኢኮኖሚ አለመረጋጋት ለስደት መንስኤ የሆነበትን ዘመን በአጭሩ ለመመልከት ችለናል፡፡
መነሻችንን ለማጠቃለል ያህል ወደፊትም ቢሆን እንደ ልደትና ሞት ሁሉ ምክንያቱ ይለያይ እንጂ የዓለም ሕዝብ እኩል በተጋራው ሰማይ ሥር በየትኛውም ሥፍራ ተዘዋውሮ መኖርና ካሰቡት ግብ መድረስ ተፈጥሯዊ በመሆኑ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚያደርገው ስደት የማይቀር ጉዳይ ነው፡፡ መሠረታዊው ነገር የስደቱ መነሻ የፖለቲካውና አሁን እንደምናየው የኢኮኖሚ አለመረጋጋቱ አይሁን እንጂ የተቀናጀና የተሟላ መረጃ አቅርቦት ያለበትና ሕጋዊ አሠራርን የተከተለ ከሆነ ከአገር ውጪ ያሉ ዜጎች እንደሀብት የሚቆጠሩና ዳያስፖራውን ከወላጅ እናቱ በላይ ባካበተው ሀብት ወደ አገር ቤት በመመለስ የሥራ ዕድል ይፈጥራል የሚል ተስፋ የእናት አገሩም ህልም ነው፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊም እናት አገሩን አስጥሎ ያስወጣውን ዓላማ አሳክቶ በድል አገሩ ይመለስ ዘንድ ምኞቴ ነው።
ሌላውና የዚህ አንቀጽ አትኩሮት የሆነው ጉዳይ ከአገራችን የሚሰደዱ ዜጎች በስደት አገራቸው ያላቸው አቀባበልን በተመለከተ ሲሆን፣ በተለይም ወደ ዓረብ አገር የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን የሚገጥማቸው ምቹ ያልሆነ አቀባበል ዓረብ አገሮቹ ከታዳጊ አገሮች ለሚመጡ ዜጎች ካላቸው ዝቅተኛ አመለካከት የመነጨ ነው ‹‹ብንል እንኳን ለምን ኢትዮጵያውያን ላይ በረታ? ብለን እንድንጠይቅ የሚያስገድድ ነው።
በአንድ ወቅት በሰሜን አሜሪካ በሚኖር መስከረም በተባለ ኮሚዲያንና አርቲስት ትዕግሥት አማካይነት የተዘጋጀ የኮሜዲ ቪዲዮ ሲዲ ከሌሎች ሰዎች ጋር በመሆን በማየት ላይ ሳለን ኮሜዲያኑና ትዕግሥት ልጆቻቸውን ዓረብ አገርና አሜሪካ የላኩ ሁለት የኢትዮጵያ እናቶችን ገጸ ባህሪ ለብሰው ያጫውታሉ፡፡ ልጇ አሜሪካ ያለላት እናት በረንዳ ላይ ሆና በላኘቶፕ ቻት እያደረገችና ልጇን ዓረብ አገር የላከችው እናት ላይ እያፌዘች የሚታይ ሲሆን፣ ልጇን ዓረብ አገር የላከችው እናት ደግሞ ልጇን አሜሪካ በላከችው እናት ላይ ቀናተኛና ነገር ነገር የሸተታት አድርጎ የሚተውኑበት ነበር፡፡ በወቅቱ ትዕይንቱን ይመለከቱ ለነበሩ ብዙኃን አዝናኝ የነበረ ቢሆንም፣ የመላ ኢትዮጵያውያንን የተሳሳተ አመለካከት የተሸከመና የሚያመለክት ሆኖ ይታየኝ ነበር።
ይኼውም፣ ‹‹የሰው ልጅ የሚፈራው ጨለማን ሳይሆን በውስጡ ያለውን ነገር ነው›› ይባላል፡፡ ይህም ኮሜዲያን በሁለቱም ኢትዮጵያውያን እናቶች ምልልስ ውስጥ እንዳጀለው ‘ማኅበረሰባችን ዓረብ አገር ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ያነሰና በተቀረው ዓለም ለሚገኙት ኢትዮጵያውያን ደግሞ የላቀ ግምት ሰጪ’ እንደሆነ ልብ ይለዋል፡፡ በተጨማሪም ከዓረብ አገር ለሚመጡ ዜጎች ‹‹ከዳያስፖራ ይልቅ ላሜቦራ በሚል የቀለደም ኮሜዲያን ተመልክተናል። ይህ የተሳሳተ አመለካከት በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ባህል ተደርጎ የተያዘ ሲሆን፣ ወደ ዓረብ አገር የሚጓዘው ስደተኝ ታፍሮበት ከወገኑ የሚለይ፣ ሲመለስም የሚንጓጠጥ ሆኖ እናገኘዋለን። በእኔ እምነት ‹‹ባለቤቱ የናቀውን አሞሌ ባለ ዕዳው አይቀበለውም›› እንዲሉ፣ እስካሁን ድረስ በመካከለኛው ምሥራቅ ኢትዮጵያውያን ላይ ለደረሰው ግፍና እንግልት በርካታ ጉዳዮች እንደ መንስዔ መነሳት ቢችሉም፣ ይህ የተዛባ አመለካከት በራሱ ያደረገው አስተዋጽኦ ይህ ነው የማይባል ነው፡፡ ክብር ከራስ ይጀምራልና፡፡ በዚህ ላይ ልንገነዘበው የሚገባው ነገር በየትኛውም አገር እንዳሉ የአገራችን ልጆች ሁሉ በዓረብ አገሮቹም በጉልበት ሥራ ላይ፣ አዕምሮ በሚጠይቅ የኃላፊነት ቦታዎችና በዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰርነት ደረጃ ለበረሃው ግልጋሎት እየሰጡ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እንዳሉ ላወሳ እወዳለሁ።
በመጨረሻም ከታዳጊ አገሮች ውስጥ ለስደት መንስዔ ተደርገው ከሚዘረዘሩት ምክንያቶች መካከል ያልተካተተ፣ ነገር ግን በወጣቱ ልብ ውስጥ ሽሽግ ፍላጎት እንዳለ ይሰማኛል። ይኼውም አገር የመጎብኘት ፍላጎት፣ ‹‹እዚያ እያለሁ›› ኄን አይ ወዝ የሚል የወሬ ጅማሮ፣ በየባህር ዳርቻው የመገኘት፣ በየግዙፍ ከተሞችና ሕንፃዎች ሥር ሆኖ ፎቶዎችን ማጋራትና የመሳሰሉት። ባደጉት አገሮች በአብዛኛው ይኼን ፍላጎት ወጣቱ የሚወጣበት ሥልት ያበጁ ሲሆን፣ የታዳጊ አገሮች ወጣቶች ይህንን ዕድል ለማግኘት በተለያየ ምክንያት አልታደሉም። ይኼ የአገራችን የወጣቱ ሽሽግ ፍላጎት የሚመነጨው ደግሞ በውጭ አገር ያሉ የአገራችን ሰዎች ተጠጋግተን አንዳችን የአንደኛችን ኑሮ በጥሞና በምንከታተልበት እንደኛ ዓይነት ማኅበረሰብ ውስጥ የሚፈጥረውን ተፅዕኖ ከግምት ሳያስገቡ በውጭ አገሮች ከየሥፍራው ሆነው በማኅበራዊ ሚዲያው የሚያጋሩት ፎቶና አገር ቤት ሲመለሱ የውጭ ቆይታቸው እውነታ በካደ መልኩ የሚያሳዩት ወጣ ያለና አባካኝነት የተሞላበት ድርጊት አገር ውስጥ ያለውን ወጣት ከእውነታው ይልቅ አርቴፊሻል በሆነው መንገድ ልቡ እንዲሸፍትና እንዲንጠለጠል ትልቁን ሚና ይጫወታል።
እንደዚያ ባይሆን አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ውጭ በወጣ በወሩ ውጭ የመኖር አምሮቱ የሚወጣለትና በቅጽበት አገሩን የሚናፍቅ ሆኖ ባልተገኘ ነበር። ‹‹ይቀናብኛል፣ ካጠገቡ በሄድኩ ያለውን ጓደኛው›› ባልናፈቀው ነበር። ኢትዮጵያውያን በመጀመርያ በመዝናናት መልክ የውጭ አገሮቹን የመመልከት ዕድል ቢያገኙ በሳምንታት አምሮቱ የሚወጣላቸውና አገር ቤት ካሉበት ድህነት ጋር አብሮ ወይም በሥራ ለውጠው ለመኖር የሚያስችላቸው ውሳኔ ላይ እንደሚደርሱ አልጠራጠርም።
እንደ መፍትሔ በውጭ የሚገኙ ዜጎቻችን ከላይ ባነሳሁት ችግራቸው ላይ አግባብነት ያለው አፋጣኝ መፍትሔ ቢያበጁ። በተጨማሪም (አይደለም በአኅጉር ደረጃ በአገራቸው ከተሞች እንኳን ተገኝተው መጎብኘት የኑሮ ሁኔታ የማይፈቅድላቸው ሰዎች እንዳሉ ብንረዳም) ተፈጥሯዊውንና ትክክለኛውን የስደት ምክንያት ከሰው ሠራሹ ግንዛቤ አንጥሮ ማየት የሚያስችለው መፍትሔ፣ አውሮፓውያኑ ለዜጎቻቸው ያዘጋጁትን ከአገር አገር የመዘዋወር ነፃ ዕድልና የየብስ ትራንስፖርት አገልግሎት ዓይነት በአፍሪካ አገሮች መካከልም ነፃ የቪዛ ዕደላና የቅናሽ የግብዣ ፓኬጅ በማሰናዳት በተቻለ አቅም ወጣቶቹ ከአፍሪካ ውጪ ካሉ ከተሞች ጋር ተቀራራቢ በሆኑ እንደ በደቡብ አፍሪካ ከተሞች፣ እንደ ኬንያና ታንዛኒያ የባህር ዳርቾች ተገኝቶ አገር የማየት አምሮቱን የሚያወጣበትን መላ ቢያመቻቹ፣ አንደኛ ወጣቱ ከእነ ችግሩ አገሩ መኖር ይመርጣል፡፡ ካልሆነ ሁለተኛ ችግሩን አሸንፎ በአገሩ ለመክበር ይነሳሳል፡፡ ካለፈም ሦስተኛ በትክክለኛው ተፈጥሯዊ የስደት ምክንያት ይሰደዳል ብዬ አምናለሁ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡