Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊለከተሞች ዕድገት ወሳኝ የሆነው ሕጋዊው ካዳስተር

ለከተሞች ዕድገት ወሳኝ የሆነው ሕጋዊው ካዳስተር

ቀን:

የከተሞች መሬትን በመመዝገብና ትክክለኛውን ልኬት ለባለቤቱ በሠርተፊኬት ማረጋገጥ ለከተሞች ዕድገት ወሳኝ እንደሆነ ታምኖበት ወደ ሥራ ይገባል ከተባለ ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆንም፣ በፖለቲካ ቁርጠኝነት ማጣት፣ በሕዝብ ግንዛቤ አለመኖር፣ ለሥራው የሚያስፈልጉ ዘመናዊ መሣሪያዎችና ብቁ ባለሙያ አለመኖር ለሥራው የሚያስፈልገው ገንዘብ በበቂ አለመገኘትና በሌሎችም ምክንያቶች ሥራው ለአምስት ዓመታት ተጎቶ ቆይቷል፡፡

አሁን ላይ እንደ አዲስ የተጀመረ ቢሆንም፣ በሚፈለገውና በሚታሰበው ልክ እየተከናወነ  ባይሆንም፣ በመላ ኢትዮጵያ ባሉ ከ170 በላይ ከተሞች ሥራው ተጀምሯል፡፡

በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ሥር የሆነውና ይህንን ሥራ ቀድሞ በበላይነት ይመራ የነበረው የፌዴራል መሬትና መሬት ነክ ምዝገባና ፈቃድ ሰጪ ኤጀንሲ ዘንድሮ ሕጋዊ ካዳስተር በከተሞቻቸው በመተግበር የላቀ አፈጻጸም አምጥተዋል ያላቸውን ሐዋሳ፣ አዳማና ዲላ ከተሞችን የተለያዩ ሚዲያዎችን በመጋበዝ የመስክ ጉብኝት አካሄዶ ነበር፡፡

- Advertisement -

ሕጋዊ ካዳስተር ለከተሞች ዕድገት ወሳኝ ብቻ ሳይሆን፣ ዋናው ቁልፍ መሆኑን በጉብኝቱ ወቅት ከኤጀንሲው የተገኙ ባለሙያዎች ያብራሩ ሲሆን፣ የሕጋዊ ካዳስተር ማረጋገጫ ማግኘት ከተሞች ያላቸውን ቁራሽ መሬት በሕጋዊ ካዳስተር ከመመዝገብ ባለፈ ለነዋሪዎቻቸው የተቀላጠፈ ማዘጋጃዊ አገልግሎት ለመስጠት፣ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር፣ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ከተሞቹም ከፍተኛና ቋሚ የሆነ ገቢ ሊያገኙ የሚችሉበትንና እንደ ዘመናዊ ከተማ ሊያስቆጥራቸው የሚችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከአዲስ አበባ 224 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውና 10ኛ ክልል ሆኖ የተመዘገበው የሲዳማ ክልል ዋና መቀመጫ የሆነችው ሐዋሳ ከተማ፣ የመጀመርያዋ ተጎብኚ ነበረች፡፡

ፀጋዬ ኬኢ (ረዳት ፕሮፌሰር) የከተማዋ ከንቲባ ናቸው፡፡ ‹‹የካዳስተር ሥራ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የከንቲባዎች ሥራ ነው፣ ከንቲባውም የሚያስተዳድረውን ከተማ በፍጥነት ዕድገት እንዲያመጣ ከፈለገ ቅድሚያ ሕጋዊ ካዳስተር በቆራጥነት ማስተግበር አለበት፤›› ይላሉ፡፡ እንደ ፀጋዬ (ረዳት ፕሮፌሰር)፣ እሳቸውን ጨምሮ በክልሉ ባሉ አምስት ከተሞች የሚገኙ ከንቲባዎች ግልጽና ቁርጥ ያለ አቋም በመያዝ ወደ ሥራው ገብተዋል፡፡ 22 ሺሕ ቁራሽ መሬቶችን ለመመዝገብ አቅደውም 20 ሺሕ መሬቶችን የመዘገቡ ሲሆን፣ ከዚህም ከ28 ሚሊዮን ብር በላይ አግኝተዋል፡፡ ሥራው ዘመናዊ መሣሪያዎችን የሚጠይቅ በመሆኑም ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመያዝ ግዢዎችን በማከናወን ላይ እንደሆኑም አክለዋል፡፡

በከተማዋ ሕጋዊ የካዳስተር ምዝገባ ተግባራዊ መሆን የጀመረው በአራዳ ክፍለ ከተማ መናኸሪያ አካባቢ በሚገኘው የምዝገባና የይዞታ ማረጋገጫ ጽሕፈት ቤት ሲሆን፣ በክፍለ ከተማው ባሉ 756 ቁራሽ መሬቶች ተመዝግበዋል፡፡ የሲዳማ ክልል የከተማ መሬት ይዞታና ምዝገባ መረጃ ክፍል ኃላፊ አቶ ዘርፉ ዘውዴ፣

በቢሮው የተመዘገቡ ቁራሽ መሬቶች በሶፍት ኮፒና በሃርድ ኮፒ ሆነው በተዘጋጀው የተቀመጡ በመሆኑ ተገልጋዮች ጉዳዮቻቸውን በደቂቃ እንዲጨርሱ ማስቻሉን ገልጸዋል፡፡

ዲላ ከተማ በአሁኑ ሰዓት በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል የጌዴኦ ዞን ዋና ከተማ ስትሆን፣ ከዛሬ 110 ዓመታት በፊት እንደተቆረቆረች ይነገራል፡፡ ከሲዳማና ከኦሮሚያ ክልሎች የምትዋሰን በመሆንዋ የንግድ ልውውጥ የሚከናወንበት ከተማ ነች፡፡ ከተማዋ ንግድ ዓመቺ በመሆኗ ለብዙ ዓመታት የንግድ መናኸሪያ ሆና ብትቆይም ዕድገቷ ግን ኋላቀር መሆኑን በቅርብ የተመሠረቱ ከተሞች ምስክሮች ናቸው፡፡

አቶ ተስፋፂዮን ዳካ የዲላ ከተማ ከንቲባ ናቸው፡፡ ከተማዋን ለማሳደግ የተሠሩ ሥራዎች እስካሁን ዝቅተኛ በመሆናቸውና በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ወደኋላ ልትቀር እንደቻለች ይናገራሉ፡፡ አሁን ላይ ባላት አቅም የዘመናዊ ከተማን መልክ ለመያዝና ከሌሎች እኩል ለማስጠራት በሚያስችል ደረጃ ሥራዎች የተጀመሩ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ የዕድገቱ መሠረት ለሆነው ሕጋዊ ካዳስተር ቅድሚያ ተሰጥቶ በከተማዋ እየተተገበረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የተመዘገቡ ቁራሽ መሬቶችም ከእሳትና ከአቧራ እንዲጠበቁ በዘመናዊ ፋይል  የተቀመጡ ሲሆን፣ በዳታ ማስቀመጫ ሠርቨርም ተቀናብሮ እንደሚገኝና በሰከንዶች ውስጥ ሙሉ መረጃን ማግኘት እንደሚቻል አክለዋል፡፡

የዲላ ከተማ ማዘጋጃ ቤት አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አረጋ በዴቻ እስካሁን በከተማ በሁለት ቀበሌዎች በስድስት ሰፈሮች የሚገኙ መሬቶችን መመዝገባቸውን፣ ጠቅሰዋል፡፡ በከተማው በአሁኑ ሰዓት አምስት ያህል ቀበሌዎች  ሲኖሩ፣ ኅብረተሰቡ ለሚፈልገው ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት በተገቢው ምላሽ ለመስጠት የሕጋዊ ካዳስተር ተግባራዊ መሆን አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑም ገልጸዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል የምትገኘው አዳማ ከተማ ሞቅ ደመቅ ያለችና ከአዲስ አበባ ካላት ቅርበት አንፃር የስብሰባና የመዝናኛ ማዕከል ነች፡፡

አቶ ሳሙኤል ሊዮን፣ የአዳማ ከተማ የመሬት አስተዳደር ምክትል ቢሮ ኃላፊና የከተማዋ የሕጋዊ ካዳስተር ምዝገባ ቡድን መሪ ናቸው፡፡ በአንድ ወቅት ሕገወጥ የመሬት ወረራ የመልካም አስተዳደር ችግር እስከመሆን ደርሶ እንደነበር ይገልጻሉ፡፡

በአሁኑ ሰዓት ሽራፊ መሬት በሕገወጥ መንገድ ተይዞ ቢገኝ፣ የቀበሌውን አስተዳደር በቀጥታ በሕግ የመጠየቅ አሠራር መጀመሩ፣ ችግሩን ከመቀነስም በላይ ከቁጥጥር ውጪ የሆነ የመሬት ወረራ እንደማይታይ ተናግረዋል፡፡ የካዳስተሩን ሥራ በተመለከተ ከ28 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች በተለያዩ መድረኮችና ሚዲያዎች በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው በመደረጉና ሥራውም ተቀባይነት በማግኘቱ በአምስቱም ክፍለ ከተሞች እየተገበረ እንደሚገኝ አክለዋል፡፡

በሥራው ወቅት የሰነድ አልባ ይዞታዎችና የልኬት መዛነፍ፣ በእጃቸው ያለው ሰነድና የካዳስተር ፎቶው አለመገናኘት ያጋጠሙ ችግሮች መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡  የተጣረሱ መረጃዎችን ለማስተካከል ጊዜ የሚፈልግ መሆኑን፣ በአግባቡ በሕጋዊ ካዳስተር ተመዝግቦ የሚገኝ ማንኛውም አገልግሎት ፈላጊ መረጃው በቋት ውስጥ ካለ አገልግሎቱን በደቂቃ ማግኘት እንደሚችል ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ሕጋዊ ካዳስተር ማለት እያንዳንዱን የከተማ ቁራሽ መሬት በተለያዩ ጊዜያት በሚነሱ የአየር ላይ ካርታዎች እንዲሁም በባለይዞታው እጅ ያለውን ሰነድ በማመሳከር የትክክለኛው ልኬት ሠርተፍኬት በመስጠት ይዞታውን ማረጋገጥ ነው፡፡

ከተሞችም ይህን መሠረት አድርገው የተመሠረቱ በመሆናቸው በከተሞችና በገጠሩ አሉ የሚባሉ ልዩነቶች በፎቶ ወይም የተወሰነ ኪሎ  ሜትር ባላቸው አስፋልት ብቻ ነው፡፡ ከተሞች ከተመሠረቱ በኋላ ዕድገትቸው በሚዘወረው ፖለቲካ ምክንያት የሚሞቱና የሚቀዘቅዙ በመሆኑ አዲስ አበባን ጨምሮ ያሉ ከተሞች ዘመናዊ ናቸው ለማለት አያስደፍርም፡፡

የሕጋዊ ካዳስተር ሥራም ዛሬም ትግበራው ጉራማይሌ ነው፡፡ ለዕይታ የተመረጡ ከተሞችን ጨምሮ ሥራው ቢኖርም፣ ለዚህ የሚመጥን ዝግጁነት አለመኖር ሒደቱን እያጓተተው ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...