Monday, January 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ስንቱን እንልመደው?

ሰላም! ሰላም! ፍቅር፣ ጤና፣ በረከት ከእናንተ ዘንድ አይጥፋና እንዴት ከርማችኋል? ኧረ እንደ እኔ ዓይነቱን ሰላምተኛ ተው ጠበቅ እያደረጋችሁ ያዙ ተው! ምቀኛ፣ ቀማኛ፣ ሐሜተኛ፣ ሐኬተኛ ምኑ ቅጡ በበዛበት በዚህ ዘመን እንደ እኔ እንደ አንበርብር ምንተስኖት ዓይነት ሰው እንዴት ቸል ይባላል? ምንድነው እንዲህ ራስን ማዋደድ እንዳላችሁኝ ጠረጠርኩ። ጎበዝ በዚህች መከረኛ አገራችን የመጣ የሄደው በሕዝብ ስም ራሱን ሲያዋድድ አልኖረምና ነው የእኔ የሚገርማችሁ? ወደን ነው እንዴ ከዚህ ቀደም የነበሩትን የተቀየምነው? አንድ የልማት ዜና አንድ ወር እየተረኩልን ለሌላ ሥራ ከማነሳሳት ይልቅ እያኩራሩን ስላሰነፉን ጭምር እኮ ነበር። አሁንማ እነሱም በሌሎች ተተክተው፣ የተተኩትም ቀን ወጥቶላቸው ከመንደር ወሬ እስከ ቤተ መንግሥት ያንበለብሉታል፡፡ አቤት! ስንቱ በራሱ ዓለም ትልቅ ነኝ ሲል ወደቀ መሰላችሁ? እኔማ ስንቱን እታዘበዋለሁ ይብላኝ እንጂ ማስተዋል ለተሳነው። ‹‹እኔምለው ማስተዋልና ማመዛዘን የሚባሉትን የጠቢብ ሰው መለያዎች ከፈረንጅ አገር ማስመጣት ይቻል ይሆን እንዴ?›› በማለት ምሁሩን የባሻዬ ልጅ ጠየቅኩት። ‹‹አንተ ደግሞ ሰው ያው ሰው አይደል እንዴ? ፈረንጅ እንደ ቁሳቁስ ያልካቸውን ነገሮች ማምረት ቢችል ኖሮ ስንቱን አስቀያሚ ታሪክ ባልተጻፈ ነበር…›› አለኝ። እኔማ ፈረንጅ የማይፈበርከው የለም ከሚል የሞኝ አስተሳሰብ መላ ያገኘሁ መስሎኝ ነበር። ‹‹የቸገረው እርጉዝ ያገባል›› ነዋ ተረቱ። ኧረ ዘንድሮ ነገር ያረገዘው በዝቷል!    

እግረ መንገዳችንን ስለእርጉዝ እናቶች አንስተን ትንሽ ብናወራስ? ያው እንዳልኳችሁ ትንሽ በዛ ብለውብኛል። እናም አንድ ወዳጄን ‹‹ምንድነው እሱ?›› ብዬ ብጠይቀው፣ ‹‹ያለፈው ዙር ተጋቢዎች ናቸው። አንዳቸውም አልጠሩህም ነበር?›› ብሎ በሽሙጥ መለሰልኝ። ያለፈው ተጋቢዎች ማለቱ የተገለጠልኝ ቆይቶ ነው። አቤት! የአንዳንዱ ሰው ሽሙጥ እኮ፡፡ እናም ከእርግዝና ጋር ተያይዞ አንድ ማለዳ ከባሻዬ ልጅ ጋር ታክሲ እየጠበቅን ስለሕዝብ ቁጥር መጨመር የተጨዋወትነው ትዝ አለኝ። የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹አካሄዳችን እንደዚህ አገም ጠቀምና ኑሮ ሰጥቶ እየነሳን እንዲህ የምንቀጥል ከሆነ ጉዳዩ ሊታሰብበት ይገባል…›› ሲል ሐሳቡን አካፍሎኛል። ወዲያው ከእሱ ጋር ተለያይተን ታክሲ ይዤ ወደ ሥራዬ ስሄድ አጠገቤ የደረሰች እርጉዝ መጥታ ተቀመጠች። ‹‹ስንት ወርሽ ነው?›› ብላት፣ ‹‹አይታወቅም አሁንም ሊመጣ ይችላል…›› ብላ እየሳቀች አስፈራራችኝ። የታክሲው ሰው በሙሉ ሲያዋልድ ታሰበኝ፡፡ ኧረ ለዘብ ብሎ የሚያስፈራራን በዛ ጎበዝ፡፡ በመቀጠልም፣ ‹‹ለመሆኑ መውለድንና የሕዝብ ቁጥር መጨመርን እንዴት ታያቸዋለሽ?›› አልኳት ቀስ ብዬ። ‹‹ልጅማ መወለድ አለበት። የሚወለደው ልጅ እኮ ምላስ ብቻ ሳይሆን እግርና እጅም አለው። እንዴት አድርገን ጠንካራ፣ ታታሪና ብርቱ ሠራተኛ እንደምናደርገው ነው ማሰብ ያለብን። ቻይናን አታይም? ከ1.5 ቢሊዮን በላይ ናቸው እኮ…›› ብላኝ እርፍ። ወይ ጉድ! አልኩላችኋ፡፡ ለነገሩ ልጆቻችንን እንዴት በሥርዓት ማሳደግ እንዳለብን የድሮዎቹ የነገሩንን ሳስታውስ፣ ይህች ሴት ልበ ብርሃን ናት በማለት ደመደምኩ፡፡ ልክ ነዋ! 

እናንተዬ! እንዲያው ልፉ ቢለን ቅድም ተስቶኝ ስለማይሰሙን ፖለቲከኞች አጓጉል ነገር ተነጋግረናል ለካ? ለነገሩ አለመደማመጥ ፋሽን ስለሆነ ብዙ አንገረምም። ጊዜ የሰጠው ሁሉ በዘመኑ ነገሮችን እየቆራረጠ አለመደማመጡን ማብዛቱን ታስታውሳላችሁ አይደል? ‹‹አይ የለም ይኼ አያዋጣንም ያንን እንሞክረው…›› እውነት የሚል ጠፍቶ ይመስላችኋል ብዙ ነገራችን በአንድ ቦይ ብቻ የሚፈሰው? አይደለም! ክፉኛ አልደማመጥ ብለናል ወገኖቼ፡፡ አዛውንቱ ባሻዬ፣ ‹‹ይኼ ኢንተርኔት ሰውን አላከባብረው አለ። ያም ከአንዱ ይኼም ከአንዱ የአገር መረጃ ሲጎለጉሉ ቆይተው አካኪ ዘራፍ ይሉብናል። ፌስቡክ የምትሉት ደግሞ ለአገር ለምድሩ የጥላቻ ንግግር ማባዘቻ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሰው ግን ወፈፍ እያደረገው ነው እንዴ?›› ቢሉኝ ትዝብታቸው ገርሞኝ ተደመምኩ፡፡ ‹‹በበኩሌ ከቴክኖሎጂው ሠፈር አልያም ከቡቲኩ መንደር፣ ብቻ ከየትኛው ገዝተን እንዳጠለቅነው አልገባኝ ብሏል…›› ስላት፣ ‹‹ምኑን?›› አለችኝ ውዴ ማንጠግቦሽ ድንግርግር እያለች። ‹‹እንዴ መደማመጥ አለመቻልን ነዋ! ስለምን እያወራን ነው ታዲያ?›› አልኩዋት ልቤን ስታደርቀው። አንዳንዶቻችን ግን ኑሮ ምን ቢወደድ የተሻሻሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና ፋሽን ልብሶችን መግዛት ያቃተን  አንመስልም፡፡ ‹‹ፉርቱና›› አለች ዘፋኙዋ፡፡ ‹‹እንዴት ላዳምጥህ አንበርብር? ወትሮ ለወር ሲበቃን የነበረው የሸመታ ገንዘብ ዛሬ የሳምንቱን አልችልልኝ አለ። ያለሁ መስሎህ ነው? ሐሳብ ጨረሰኝ እኮ…›› ብትለኝ ውድ ባለቤቴ ወከክ አልኩላችሁ። የኑሮ ውድነት ያሳቀቃት ጉብል መንገድ ላይ የተጎለተ ጎረምሳ ቢለክፋት ኖሮ አልቆለት ነበር። ‹‹ምን ዋጋ አለው! ትናንት የሚቆጡትና የሚገስፁት ጎረምሳ እያንቀላፋ ዛሬ ኑሮ ፈንድቶብን አረፈው! አይ ጊዜ!›› አለች በታከተ ድምፅ፡፡ ይታክታል!

ጨዋታን ጨዋታ ያነሳዋል አይደል? እስኪ ስለፌስቡክ ደግሞ ትንሽ እንጨዋወት። በድለላ የማገለግላቸው አንዳንድ ደንበኞቼ፣ ‹‹በዚህ ኑሮ ቤት ለመሥራት የቁጠባ ‘አካውንት’ ከመክፈት የፌስቡክ ‘አካውንት’ መክፈት ይቀላል…›› ይሉላችኋል። ‹‹እንዴት?›› ስላቸው፣ ‹‹አብዛኛው ሰው ውሎና አዳሩ እዚያ ሆኗልና…›› ነው መልሳቸው። በበኩሌ ፌስቡክን ሳስብ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ጎልቶ ይታሰበኛል። ‘የፕሬስ ነፃነት ተገድቧል’ የሚሉ ወገኖችን ‘ሄዳችሁ ፌስቡክ ላይ ፈልጉት’ ተብሏል ብለው ስም ሲያጠፉ የሰማሁትም ጉድ አለላችሁ። ብቻ ጆሮ ስትሰጡ እኮ ብዙ ስለሚወራ ብዙ መስማታችሁ ግድ ነው። በነገራችን ላይ በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግና መሰል ተግባሮች ወደፊት በፌስቡክ ላይ ብቻ መወሰናቸው አይቀርም ሲባል አልሰማችሁም? አቤት የወሬውና የወሬኛው ብዛት። ከዓመታት በፊት ውጭ አገር የነበረ አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አዲስ አበባ ውስጥ ወረቀት መበተኑን ቢያወራ ተሳቀበት አሉ፡፡ ‹‹በፌስቡክ ዘመን ወረቀት መበተን ያስለቅሳል…›› ተባለ አሉ፡፡ ያ ፓርቲ ለለውጡ ምሥጋና ይድረሰውና ያረጁ አመራሮቹን ይዞ አዲስ አበባ ከገባ ወዲህ፣ ውሎና አዳሩ የት እንደሆነ አይታወቅም ብላችሁ እንዳትገረሙ፡፡ እንግዲህ ተኝተው በቅዠት ውስጥ ያሉትን ትተን ወደ ራሳችን ወግ እንግባ፡፡ አንድ ማኅበራዊ ድረ ገጽ በአገርኛ ሥልት መዘርጋት ቢያቅተንም ማኅበራዊ ወሬኞች መሆን ግን አላቃተንም። ‹‹እኔስ የምፈራው መብላት መጠጣታችንንም ‘ኮምፒውተራይዝድ’ አድርገነዋል እንዳይሉን ነው…›› አለኝ አብሮኝ ጨዋታውን ሲኮመኩም የቆየው ወዳጄ። እናቅለው ስንል የምናከብደውን ሳስብ የዓለም ነገር አንገሸገሸኝ። ‹‹አወይ ዴሞክራሲ! እንዲህ ሄደሽ ሄደሽ መጨረሻሽ ምን ይሆን?›› ይላል ምሁሩ የባሻዬ ልጅ እንዲህ አንዳንድ ኩመካዎችን ሲሰማ። ቀልድም ጠነዛ መሰል!

ሰሞኑን የኮምፒዩተር ሶፍትዌር የሚያዘጋጅ ወጣት ሰፋ ያለ ቤት ተከራይቶ መሥራት ፈለገና ቤት እንድፈልግለት ነገረኝ። እኔም ተንከራትቼ ኮንዶሚኒየም ሕንፃ ምድር ላይ ያለ ቤት አገኘሁለት። ተስማማውና ተዋውሎ ሲያበቃ፣ ‹‹ለመሆኑ ምን ይሆን የምታዘጋጀው?›› ብዬ ጠየቅኩት። በረጅሙ ተንፍሶ፣ ‹‹ብዙ ነገር፣ ግን ዋናው ኮምፒዩተርን ከእግር ጥፍሩ እስከ ራስ ቅሉ ድረስ በአማርኛ ቋንቋ እንድንጠቀምበት ለማድረግ ነው…›› አለኝ። ‹‹ይኼ ነው እውነተኛው ትራንስፎርሜሽን!›› አልኩ ጮክ ብዬ። ስሜታዊ ጭምር ሆኜ መናገሬን ለዘብ ብሎ አስተውሎ፣ ‹‹አየህ እንደኛ ያለ ሕዝብ ልጣለው ቢል እንኳ ብዙ የማይለቀው የማንነቱ መገለጫ አለ። ማስተዋል ቢሰጠን የሚያምርብንንና የማያምርብንን፣ የሚያኮራንንና የሚያዋርደንን ነገር በጊዜ ብንለይ ጥሩ ነበር። ከወዲሁ ሥራ የሚፈልጉ ነገሮች ቢኖሩም ከማንነት በፊት የሚቀድሙ አይደሉም…›› ሲለኝ ከመጪው ትውልድ አዲስ ነገር የመጠበቅ ጉጉቴ ጨመረ። ቀጠለናም፣ ‹‹ስንቱን ዘለልነው መሰለህ? ትንሽ ተጉዘን ስናርፍ፣ ትንሽ ሠርተን ሲደክመን፣ ትንሽ ይዘን ስንጣላ ስንቱን ዕድሜና አቅም አባከንነው? ስንቱን ቀዳዳ ሳንደፍን ዘለልነው መሰለህ?›› ሲለኝ በአንዴ ዕድሜ ያስተማረው አዛውንት መስሎ ታየኝ። ኧረ የአንዳንዱስ ወጣት ልብ ከደረጀ ቆይቷል እናንተዬ!

ታዲያ አገራችን አሁን በተያያዘችው የዕድገት ጎዳና (ስለዕድገት አልገባን ያለው ሁሉ እንዳለ ሆኖ) ዋናው ግንበኛ ወጣቱ ትውልድ መሆኑ ነው (ግንበኛን በቀጥታም በዘወርዋራም መፍታትና መረዳት ተፈቅዷል)፡፡ ሐሳብ የጠፋበትና ቁሳዊነት የገዘፈበት ዘመን ከቶ ከዚህ በፊት መቼ ይሆን? ምን ላጫውታችሁ መሰላችሁ? ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹አንበርብር!›› አለኝ የሆነ ቀን ከሥራ መልስ ስንገናኝ። ‹‹እህ ምን ተገኘ?›› ስለው፣ ‹‹ጉድ ሊፈላ ነው። የዲቪ ሎተሪ ማግለልና መድሎን ልትጀምር ነው እረፈው…›› አለኝ። ግራ ገብቶኝ ምን እንደሰማ ስጠይቀው በዲቪ ሎተሪ ምትክ በዓለም ላይ ላሉ ምርጥ ተማሪዎች ነፃ የትምህርት ዕድል ሊመቻች መታሰቡን አጫወተኝ። ‹‹በሥራ ማጣትና በትምህርት ተስፋ የቆረጠው ሁሉ ጥሎን መሄዱ ነው አትለኝም?›› ስለው፣ ‹‹ኧረ ከዚያም በላይ ነው አንበርብር። እውነት እንደተባለው የሚሆን ከሆነ አሜሪካ ድኅረ ዘመናዊነት አዲሱን ቅኝ አገዛዝ ተግባራዊ አድርጋ ጉድ ማስባሏ አይቀርም…›› አለኝ በመደነቅ ተሞልቶ። ትንሽ ከአቅም በላይ ስለተጫወተ አልገባኝ ብሎኝ፣ ‹‹ምን ማለትህ ነው?›› ስል ጠየቅኩት። ‹‹ምን ነካህ አስተምራ ስታበቃ ምን ሞኝ ናት ሂዱ እናት አገራችሁን አገልግሉ ብላ የምትለቀው? እንዴ! ጨዋታው እከክልኝ ልከክልህ ነው…›› ሲለኝ ተገለጠልኝ። የባሰ አታምጣ የሚባለው እኮ ይኼኔ ነው እናንተ! ምናለበት የአገር ጠንቅ የሆኑ የፖለቲካ ወፈፌዎችን አሜሪካ በነፃ ዝውውር ወስዳ በገላገለችን፡፡ እንዲያውም ሩሲያም ከምዕራባውያን ጋር ለጀመረችው ፍትጊያ ፖለቲከኞቹ ከቻሉ በምላሳቸው፣ ጉልበተኞቹ ደግሞ በጡንቻቸው ተሰማርተው ዶላርና ዩሮ ቢያስገኙልን እኮ ይጠቅሙን ነበር፡፡ ግና ምን ያደርጋል እነሱ ግን ለእማማ ኢትዮጵያ ቢኖሩ ዕዳ ሆነው አስቸገሩ፡፡ ኤጭ!

ነገሩ በጣም ስለከነከነኝ ግራ የገባ ስሜት ወዲያው ፈጠረብኝ። ‹‹በአንድ በኩል ዜጋችን እንዲህ ያለ ዕድል ማግኘት መቻሉን (ገና ለወደፊትም ቢሆን) ሳስበው ደስ ብሎኛል። ነገር ግን አሁን አንተ የምትለኝ ነገር ሥጋት ለቀቀብኝ…›› አልኩት ለምሁሩ የባሻዬ ልጅ የልቤን ሳልደብቅ። ‹‹አንበርብር የእኛ የዘመናት ችግር አንድን ነገር ከሥር ከመሠረቱ መርምረን ውጤቱንና ኪሳራውን በትክክል መረዳት መቸገራችን ነው። ለምሳሌ በተለይ ታዳጊው ትውልድ ጥራቱ በወደቀ የትምህርት መርሐ ግብር ውስጥ እያለፈ ነው። አብዛኛው ተማሪ እንደምታውቀው ሳይማር ነው የሚመረቀው። ኮሌጆቹም የዲግሪ ወፍጮ ሆነዋል ሲባል ቀልድ አይምሰልህ፡፡ ገለባ ማምረቻ በላቸው፡፡ በዚህ መሀል ምርጦቹን የሚሰበስቡ ኃይሎች ቢመጡ አይድነቅህ…›› ብሎ ለገዛ ራሴ ፍርድና ምልከታ ተወኝ። ከዚህ በፊት አሜሪካውያን የልጆቻቸው ለሒሳብና ለፊዚክስ ትምህርቶች ጠላት መሆን እንዳስደነገጣቸው የባሻዬ ልጅ ራሱ ያጫወተኝ ትዝ አለኝ። ወይ አሜሪካ ከትንሽ እስከ ትልቁ፣ ከማይማን እስከ ምሁራን አግዛ የማትጠረቃ አገር እያልኩ ብቻዬን መገረም ጀመርኩ። ምናለበት አገር በጥባጮችን በካቴና አስረን ሰጥተናት ዕፎይ ባልን? ሳይሻል አይቀርም!

መቼም ቀን መንጎዱን፣ ዕድሜ መጨመሩን፣ ሕይወት መቀጠሏን የምናውቀው እንዲህ ስንገናኝና የሰማነውንና ያየነውን አዲስ ነገር ስንጨዋወት ነው። ‘ከፀሐይ በታች አዲስ የሚባል የለም’ የሚባል ቢሆንም፣ በምድር ስንኖር ግን አሮጌም እኮ አዲስ አለው። ቆይቶ ቆይቶ ተመልሶ ሲመጣ አዲስ መባሉ ይቀርና ነው ታዲያ እጅግ የሚያስደንቅ ነገር እንዲህ ሲገጥማችሁ ወይ ሲያገኛችሁ ይህችንማ ማወራረጃ ይዘን ነው መኮምኮም ያለብን ትባባሉና ወደ ግሮሰሪ ታመራላችሁ። ስለሚጠጣውና ስለሚበላው ነገር ማስታወቂያ በበዛበት ጊዜ እንደ እኔና እንደ ባሻዬ ልጅ አመል ያለበት የሚሮጠው ግሮሰሪ ነው። ሊስተናገድ እንጂ ሊያስተናግድ የቆመ የማይመስለውን አስተናጋጅ፣ በልምምጥና በመከራ የምንፈልገውን ነግረነው ጨዋታችንን ቀጠልን። ‹‹እኔምለው? ለመሆኑ ግንባታቸው የዘገየው የቁጠባ ቤቶች እንደሆኑ እንኳን አሁን ለምፅዓትም የሚደርሱ አይመስልምና ምን ልታደርግ አስብሃል?›› አልኩት ቤት የማግኘት ጉጉቱን ስለማውቅ። ‹‹አይ አንበርብር፣ የእኔ ቢጤዎችን አሰባስቤ በሕግም ቢሆን መጠየቄ አይቀርም። ከዚያ በፊት ግን ብርቱ ውይይት ያስፈልገናል…›› አለኝ እየተጎነጨ። ‹‹ምን ይሆን ውይይቱ?›› ስለው፣ ‹‹እንዲያው አሳቢ መንግሥት አጥተን ነው እንጂ ይህንን ያህል ዓመታት በቤት ዕጣ ጥበቃ ዕድሜያችንን አንፈጀውም ነበር…›› ብሎኝ የያዘውን ጅው አድርጎ ተጋተው። እኔም ነገሩን ሳስብ ውስጤ በገነ። መጠጥና ብሽቀት ባይጣጣሙም እኔም የመጣልኝን ማንቆርቆር ጀመርኩ፡፡ ዘንድሮ በሁሉም ነገር በግነን አንዘልቀውም፡፡ ማንም መጣ ወይም ሄደ ለራሱና ለቢጤው እንጂ ለሰፊው ሕዝብ ደንታ እንደሌለው ከተረዳን ቆየን፡፡ በጣም ቆየን!

ግሮሰሪው ውስጥ የታደሙትን ማየት ጀመርኩ፡፡ ከጥግ እስከ ጥግ የአገሬ ልጆች ነገን የረሱ እስኪመስሉ የቀረበላቸውን ያንቆረቁራሉ፡፡ የዛሬው አጠጣጥ ለየት ስላለብኝ ወደ ባሻዬ ልጅ ዞር ስል የቀረበለትን በአንድ ትንፋሽ ጨልጦ ድጋሚ መጠባበቅ ጀምሯል፡፡ ‹‹ምነው ዛሬ ፈጠን አልክ?›› አልኩት፡፡ ሳቅ እያለ እያየኝ፣ ‹‹ማጅራት መቺ በበዛበት ዘመን ቶሎ ላፍ ላፍ አድርጎ በጊዜ ወደ ቤት መግባት አይሻልም?›› አለኝ፡፡ ውስጠ ወይራ ዘይቤ በበዛበት በዚህ ዘመን አነጋገሩ የበለጠ ጠጠር አለብኝ፡፡ ‹‹የምን ማጅራት መቺ?›› በማለት ጥያቄ አቀረብኩለት፡፡ ‹‹አንበርብር ነገር ይግባህ እንጂ? በዚህ በሠለጠነ ዘመን እንደ ወረደ ወሬ ቀርቷል…›› ሲለኝ ባይገባኝም እንደ ገባው ለመሆን ሞከርኩ፡፡ ስንቶቻችን እንሆን እያስመሰልን የምንኖረው? ‹‹ማስመሰልና አስመሳይነት በሚያዋጣበት በዚህ ዘመን አጉል ድርቅና ወይም ግትርነት ዋጋ የላቸውም፤›› ያለኝ ራሱ የባሻዬ ልጅ ነው፡፡ እኔም ዛሬ ከድርቅና ወደ አስመሳይነት ሽግግር በማድረግ ያልገባኝን እንደገባኝ ተቀብዬ ወደ ቤቴ አዘገምኩ፡፡ በሴረኞች ዘመን ስንቱን እንልመደው? መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት