Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትየግለሰቦች እጅ የሚዘውረው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ

የግለሰቦች እጅ የሚዘውረው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ

ቀን:

ከኢትዮጵያውያን ታላላቅ አትሌቶች ስኬት ጀርባ ስሙ በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ ጌጤ ዋሚ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ አየለ አብሸሮ፣ ስለሽ ስህን፣ አልማዝ አያና፣ ለተሰንበት ግደይ፣ የዓለምዘርፍ የኋላውና ለሌሎችም በርካታ ኢትዮጵያውያን ታላላቅ አትሌቶች ጋር በመሥራት አራት አሥርታትን አስቆጥሯል፣ እስካሁንም እየሠራ ይገኛል፡፡ ግሎባል ስፖርት ይህን ያህል ዓመት በአገሪቱ ሲኖር በጎረቤት አገሮች ኬንያና ኡጋንዳ እንዳለው፣ በኢትዮጵያ ግን ከአትሌቶች መኖሪያ ካምፕ ጀምሮ ማዘውተሪያ ግንባታ ላይ ሲሳተፍ አይስተዋልም፡፡ በአሁኑ ወቅት ግሎባል ስፖርት የሚያስተዳድራቸውን ጨምሮ በርካታ አትሌቶች ልምምድ የሚያደርጉት ከተሽከርካሪ ጋር እየተጋፉ መሆኑን ተከትሎ ለአደጋ የሚጋለጡበት አጋጣሚ እየበዛ ነው፡፡ ከግሎባል ስፖርት ጋር በመሥራት ከሚታወቁ ቀደምት አትሌቶች መካከል አሠልጣኝ ተሰማ አብሽሮ አንዱ ነው፡፡ የቀድሞ አትሌት በጉዳትና መሰል ችግሮች በኦሊምፒክና ዓለም ዋንጫ አገሩን ወክሎ የመወዳደር እድል ባያገኝም፣ በዓለም አቀፍ ታላላቅ የጎዳና ውድድሮች ግን ከስኬታማዎቹ መካከል ይጠቀሳል፡፡ አትሌቱ ከ20 ዓመት የሩጫ ሕይወቱ በኋላ ፊቱን ወደ አሠልጣኝነት በመዞር፣ የግሎባል ስፖርት ተወካይ ሆኖ የድርጅቱን አትሌቶች እያሠለጠነ ይገኛል፡፡ ወደ አሠልጣኝነት ሙሉ በሙሉ ከመግባት በፊት በግሎባል ስፖርት መሥራችና ባለቤት ጆንስ ሔርመንስ ድጋፍ የተለያዩ የአሠልጣኝነት ሥልጠና መውሰዱን ጭምር ይናገራል፡፡ አሠልጣኙ ከአትሌት እስከ አሠልጣኝነት ሕይወቱ እንዲሁም በአትሌቲክሱ ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ በሙያው ውስጥ የሚያጋጥሙና እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በዝርዝር ይናገራል፡፡ ከደረጀ ጠገናው ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- የአትሌቲክሱ ቤተሰብ ከሚባሉት መካከል ትጠቀሳለህ፡፡ ይህን አባባል እንዴት ትገልጸዋለህ?

አሠልጣኝ ተሰማ፡- ተሰማ አብሽሮና አየለ አብሽሮ ወንድማማቾች መሆናችን ይታወቃል፡፡ ቤተሰቦቻችንም ልክ እንደ እኛ ተወዳዳሪዎች አይሁኑ እንጅ የአትሌቲክሱ ቤተሰብ ናቸው፣ በአጠቃላይ አትሌቲክስ ሕይወታችንን የምንመራበት ሙያ ነው፡፡

- Advertisement -

ሪፖርተር፡- ተወዳዳሪ እያለህ አሠልጣኝ የመሆን ፍላጎቱ ነበረህ? ከሆነ ለምርጫህ ተምሳሌት የምታደርገው አሠልጣኝ ማን ነው?

አሠልጣኝ ተሰማ፡- እውነቱን ለመናገር በአትሌቲክሱ ታላላቆቼ ቀደምት ኢትዮጵያውያን የተጎናፀፉትን ስኬት ማሳካት ካልሆነ አሠልጣኝ የመሆን ህልም አልነበረኝ፡፡ በትራክ (መም) እና አገር አቋራጭ ውድድሮች ላይ ጠንካራ ከሚባሉ አትሌቶች ተርታ ባለሁበት ወቅት ባጋጠመኝ ተደጋጋሚ ጉዳት፣ የሩጫ ሕይወቴ ባልጠበቅኩት መንገድ እንዲሄድ ምክንያት ሆኖኛል፡፡ በዚህም የተነሳ ለኦሊምፒክና ለዓለም ዋንጫ የነበረኝ ህልም ባይሳካም፣ ምንም እንኳ ጉዳት ቢኖርብኝም ፊቴን ወደ ጎዳና ውድድሮች በማዞር ትልልቅ ስኬቶችን አሳክቻለሁ፡፡ ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደሞከርኩት ጉዳቱ በጎዳና ውድድሮችም ሊያስቀጥለኝ ባለመቻሉ ነው ወደ አሠልጣኝነት ሙያ ለመግባት የተገደድኩት፡፡ ማን ነው ተምሳሌትህ ለሚለው ሁሉም እንደሚያውቀው ዶክተር ወልደ መስቀል ኮስትሬ የመጀመርያው ናቸው፡፡ ሲቀጥል ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ፣ የክለቤ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሠልጣኝ የነበሩት ካሱ ዓለማየሁ፣ ኮማንደር ሁሴን ሽቦና ማራቶን ላይ ጌታነህ ተሰማ ይጠቀሳሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ግሎባል ስፖርት በኢትዮጵያ በተለይ አትሌቲክሱ ላይ ከሚሠሩ የውጭ ድርጅቶች (ማናጀሮች) ቀደምት ከሚባሉት ይጠቀሳል፡፡ ይሁንና ድርጅቱ የዕድሜውን ያህል ኢትዮጵያ ውስጥ አትሌቶችን ሊጠቅም የሚችል መሠረተ ልማት ላይ ተሳትፎ የለውም፡፡ በጎረቤት አገሮች እንደ ኬንያና ኡጋንዳ በመሳሰሉት ግን የሥልጠና ማዘውተሪያዎችን ጨምሮ የአትሌቶች መኖሪያ ካምፕ እንዳሉት ይነገራል፡፡ በሌሎች አገሮች የሚያደርገውን በኢትዮጵያ ለመተግበር ችግሩ ምንድነው?

አሠልጣኘ ተሰማ፡- ግሎባል ስፖርት እንደተባለው ታላላቅ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በማስተዳደር ትልቅ ሥራ ሠርቷል፣ እየሠራም ይገኛል፡፡ እንደ አገር በተለይም ከመኖሪያ ካምፕና ማዘውተሪያ ጋር ለምን አይሳተፍም የሚለው ትክክለኛና ተገቢ ጥያቄ ነው፡፡ ምክንያቱም ድርጅቱ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ዓለም ላይ ትላልቅ ስምና ዝና ያላቸው እንደ ኤሊዩድ ችፕቾጌ፣ ሲፋን ሐሰንና ጆሽዋን የመሳሰሉ አትሌቶችን በማስተዳደር የሚታወቅ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ግሎባል ስፖርት አንድ አትሌት እስከ 20 ዓመትና ከዚያም በላይ መሮጥ እንዳለበት ስለሚያምን፣ በተለይ አንድ አትሌት የጎዳና ውድድሮችን እንዳይደጋግም አምስተርዳም ውስጥ በሚገኘው ሆስፒታሉ፣ በራሱ የሕክምና ባለሙያዎች ክትትል በማድረግ ጭምር ጥንቃቄ ያደርጋል፡፡ ትጥቅና መሰል ጥቅማ ጥቅሞችን በተመለከተም ከተለያዩ ድርጅቶ ጋር ከናይኪ በተጨማሪ ኤንኤን ከመሳሰሉት ጋር ስለሚሠራ ምንም ችግር የለበትም፡፡ እንደተባለው ድርጅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ አትሌቶች የሚያዘወትሩባቸው እንደ ካምፕና መሠረተ ልማት የመሳሰሉት የለውም፡፡ በኬንያ ግን ትልቅ ካምፕ አለው፡፡ እንደነ ችፕቾጌን የመሳሰሉ ትልልቅ አትሌቶች ሳይቀር የሚኖሩበት ነው፡፡ ብዙዎቹ የኬንያ አትሌቶች እሑድ ካልሆነ ቤተሰቦቻቸውን ለመጠየቅ እንኳ ከካምፕ አይወጡም፡፡ በዚያ ልክ ዑጋንዳ ውስጥም አለው፡፡ ታዲያ በኢትዮጵያ ለምን ብለን እንጠይቃለን፣ እነሱም ካምፑን ለመገንባት ምንም ችግር የለባቸውም፡፡ ችግሩ ግን የአትሌቶቻችን ብቻ ሳይሆን የማኅበረሰባችን የአኗኗር ዘይቤ እነሱ ለሚያስቡት ዕቅድ አያመችም፡፡ ከእኔ ጭምር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ካምፕ ለመኖር ፍላጎታችን እምብዛም ነው፡፡ ይሁንና እንደ ኬንያና ዑጋንዳ በአገራችን መሠራት እንዳለበት አምናለሁ፣ ሊሠራም ይገባል፣ እኛም እያሰብንበት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ያሰባችሁት ምንድነው?

አሠልጣኝ ተሰማ፡- ካምፕ በአብዛኛው የሚያስፈልገው ለኤሊት (ትልልቅ) አትሌቶች ነው፡፡ የአገራችን ኤሊቶች ደግሞ መኖር የሚፈልጉት ካምፕ ሳይሆን ከተማ ውስጥ ነው፡፡ በመሆኑም የእኛ የወደፊት እቅድ ታዳጊ ወጣቶች የምናገኝበትን ቦታ በመምረጥ ቦታው ላይ ካምፕ በመገንባት ለመሥራት ነው፡፡ አቅም ያላቸው ታዳጊዎች የሚፈሩባቸው አካባቢዎችም ተለይተዋል፡፡ በእርግጠኝነት በዚህ አንድና ሁለት ዓመት ውስጥ ተግባራዊ እናደርገዋለን የሚል እምነት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- አካባቢዎቹን መግለጽ ይቻላል?

አሠልጣኝ ተሰማ፡- በአማራ፣ በደቡብና በኦሮሚያ አካባቢዎች አትሌቶች በብዛት የሚወጡባቸው ቦታዎች ታስቧል፡፡

ሪፖርተር፡- የልጅነት ህልምህ ባይሆንም በአሁኑ ወቅት አሠልጣኝ ሆነህ እየሠራህ ትገኛለህ፡፡ ከሥልጠና ጋር በተያያዘ ጣልቃ ገብነትና መሰል ችግሮች እንዳሉ ይነገራል፡፡ ምን ያህል እውነት ነው?

አሠልጣኝ ተሰማ፡- በእኛ ጊዜ አሠልጣኞቻችን እናከብራለን፣ እንፈራለን፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ድሮ የነበረው ሙሉ በሙሉ ማለት በሚያስችል መልኩ መከባበሩም ሆነ መፈራቱ ቀርቷል፣ እንዲያውም የለም፡፡ እነ ወልደመስቀል (ዶ/ር) በነበሩበት ጊዜ አንድ አትሌት አድርግ የተባለውን ካልሆነ፣ የሙያው ሥነ ምግባርም ስለሆነ ምንም ነገር ማድረግ አይችልም፡፡ የውጤታማነታችን ምስጢርም ይህ ይመስለኛል፣ ዲሲፕሊን ወሳኝ ነው፡፡ አሁን ላይ ግን በብዙ ነገርች ጣልቃ የሚገቡ አካላት አሉ፡፡ ለምሳሌ የእህቶቻችን የትዳር አጋሮች ትልቅ ፈተና እየሆኑ ነው፡፡ በድፍረት የአሠልጣኝን ኃላፊነት ለመውሰድ ይፈልጋሉ፡፡ የሆኑበት አጋጣሚም ብዙ ነው፡፡ አሠልጣኙ አትሌቷን ለረዥም ጊዜ ምን መሥራትና ምን ማድረግ እንዳለባት ለማሰብ ሙሉ መብት የለምውም፡፡ ባሎች ጣልቃ በመግባት፣ አትሌቷ ባላሰበችው መንገድ ሳይሆን ጉዳት ሊያስከትልባት በሚችል ግን ጊዜያዊ ጥቅምን ብቻ  በሚያስገኙ ተደጋጋሚ ውድድሮች ላይ እንድትሳተፍ የሚያደርጉ አሉ፡፡ ባለው ነገር የባሎች ጣልቃ ገብነት የብዙ አሠልጣኞች ችግር መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ ምናልባትም ችግሩ መፍትሔ የማያገኝ ከሆነ የስፖርቱ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ አደጋ መሆኑ የማይቀር ነው፡፡ ፖለቲካው ላይ የምናየው መጎሻሸም በስፖርቱም እየታየ ነው፡፡ ከዚህና ከዚያ ነው የመጣው የሚል አላስፈላጊ መቆራቆሶች ይታያሉ፡፡ በተለይ የሴት አትሌቶች የትዳር አጋሮች ጉዳይ ቢታሰብበት የሚል እምነት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ችግሮቹን ሙያዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት ጥረት የምታደርጉበት አግባብ የለምን? በተለይ ስፖርቱን  በባለቤትነት የሚስተዳደረው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በዚህ ጉዳይ ምን ይላል?

አሠልጣኝ ተሰማ፡- በየደረጃው ውይይቶችን እናደርጋለን፡፡ ያማ ባይሆን ባለው ሁኔታ ስፖርቱ ጭራሽ ባልነበረ ነበር፡፡ ምክንያቱም ዞሮ ዞሮ ጥቅሙ ለራሳቸው ለአትሌቶቹ ስለሆነ ነገሮችን በማቻቻል ነው እየሠራን ያለው፡፡ እንደ እኔ ይህ የሙያ ጉዳይ ስለሆነ ለባለሙያው ቢተው ነው የምመክረው፡፡ ፌዴሬሽኑ ለተባለው እነዚህ አካላት በራሱ በፌዴሬሽኑ የውስጥ ጉዳይ ሳይቀር ጣልቃ በመግባት ውሳኔ እስከማስቀየር የሚደርሱ ናቸው፡፡ ወደ ዝርዝሩ መግባት ባያስፈልግም ማሳያዎችን ግን መመልከት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ የምትሮጠው ልጅቷ ሆና እያለ ባልየው ከፌዴሬሽኑ ጋር ለስብሰባ ቁጭ የሚልበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡ በቅርቡ በተከናወነው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ላይ ለዚያ ሁሉ ችግር አንደኛው ምክንያቱም ይህ ነበር፡፡ በአጠቃላይ እንደ አሠልጣኝ በማዘውተሪያ ሥፍራ፣ ራሱ ፌዴሬሽኑ በጣልቃ ገቦች ተፅዕኖ ውስጥ በመውደቁ የተነሳ ለስፖርቱ ትልቅ ችግር የሚሆኑበት አጋጣሚ ይበዛል፡፡

ሪፖርተር፡- በነበረኝ የአሠልጣኝነት ሕይወት ስኬታማ ሆኛለሁ የምትልበት ደረጃ ላይ ደርሻለሁ ብለህ ታስባለህ?

አሠልጣኝ ተሰማ፡- በፍፁም ጀማሪ እንጅ ስኬታማ ልባል የምችልበት ደረጃ ላይ ገና ብዙ ይቀረኛል፡፡ በእርግጥ በእኔ ሥር እንደነ ደጊቱ አዝመራው፣ የዓለምዘርፍ የኋላው፣ አሚናታ አህመድ፣ አይቸው በንቲ፣ ኤደን ኃይሉ፣ አዳነች አንበሴና ሌሎችም በአሁኑ ወቅት በማራቶን ጥሩ ደረጃ ላይ የደረሱ አትሌቶችን አሠለጥናለሁ፣ ውጤታማም ናቸው፡፡ የዓለምዘርፍ የኋላው በቅርቡ ያሳካችው ስመኘው የነበረውን የዓለም ፈጣን ሰዓት ነው፡፡ ግን ደግሞ እንደ አሠልጣኝ የዓለም ክብረ ወሰንን ነው የማልመው፡፡ ሌላው የዓለምዘርፍ በዓለም ሻምፒዮና ላይ ወርቅ ስጠብቅ ያመጣችው ነሐስ ነው፣ አይደገምም፡፡ ባለኝ አቅም ሁሉ በዓለም አደባባይ አገሬን ወክዬ ባንዲራዋን ከፍ አድርጌያለሁ፡፡ አሁን ደግሞ እንደ አሠልጣኝ ከፊት ለፊታችን ኦሊምፒክና የዓለም ዋንጫ ስለሚጠብቀን፣ አትሌቶቼ በዓለም አደባባይ የኢትዮጵያን ባንዲራ ከፍ ለማድረግ እንዲዘጋጁ ነው የምሠራው፡፡

ሪፖርተር፡- በማዘውተሪያ ችግር ልምምድ የምትሠሩት በአስፋልት እንደሆነ ይታያል፡፡ የአንተን አትሌቶች ጨምሮ በርካታ አትሌቶች በተሽከርካሪ አደጋ ሕይወታቸውን አጥተዋል፣ ለከፋ የአካል ጉዳት የተዳረጉም በዚያው ልክ ናቸው መፍትሔ የምትለው ይኖራል?

አሠልጣኝ ተሰማ፡- እውነት ነው ከተሽከርካሪ ጋር እየተጋፋን ነው ልምምድ የምናሠራው፡፡ በፈጣሪ ቸርነት እንጂ ከዚህ ቀደም የአምስተርዳም ማራቶን ሳምንት ሲቀረው ሰንዳፋ አካባቢ ልምምድ እየሠራን አራት ልጆች ላይ የመኪና አደጋ ደርሶብናል፡፡ ሰበታም አካባቢም በተመሳሳይ ችግሩ ገጥሞናል፡፡ በዚያ ላይ ለትራክ (መም) ውድድር የምንዘጋጅበት ቦታ የለም፡፡ ለወትሮ አንድ ለእናቱ የነበረው የአዲስ አበባ ስታዲየም ትራክ እድሳት ተብሎ አገልግሎት እየሰጠ አይደለም፡፡ ትራክ ወጣቶች አካዴሚ ግቢ ውስጥ ቢኖርም፣ ፈቃድ የሚሰጥ አካል የለም፡፡ አሁን ላይ እየተጠቀምን ያለው በአንድ አትሌት 200 ብር እየከፈልን በቀነኒሳ ትራክ ነው፡፡ በማዘውተሪያ ቦታ ጉዳይ መንግሥትም ሆነ ፌዴሬሽኑ ሌላውም የሚመለከተው አካል ዝም ብለው የተኙበት ነው የሚመስለው፡፡ የሚገርመው በአሁኑ ወቅት ሙሉ ማራቶንና ግማሽ ማራቶን ወርደው ወርደው የፍጥነት ልምምድ የሚጠይቁ የውድድር ዓይነት ሆነዋል፡፡ ፍጥነት ደግሞ በትራክ ላይ ካልሆነ በጎዳና አይሠራም፡፡ ጎረቤታችን ኬንያ ትራክ ብቻ ከስድስትና ከሰባት በላይ አላት፡፡ እንድንፎካከር የሚፈለገው ደግሞ ከእነዚህ አገሮች ጋር ነው፣ እንዴት ይሆናል? ምንም በሌለበት ኦሊምፒክና ዓለም ዋንጫ ላይ ውጤት ሲጠፋ ተነስቶ መጮህ ብቻውን ትርጉም ያለው አይመስለኝም፡፡ በግሌ ወዴት እየሄድን ነው የሚለው ጥያቄ ሊሆንብን ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- ችግሩ መሬት ወይስ ምንድነው ትላለህ?

አሠልጣኝ ተሰማ፡- መሬትማ ቢሆን ኖሮ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ለቁጥር የሚታክት መሬት ታጥሮ ባልተመለከትን ነበር፡፡ መሠረታዊ ችግሩ የሚመስለኝ ትኩረት የሚሰጥ አካል መጥፋት ነው፡፡ ቀናነቱ ቢኖር ናይኪን ጨምሮ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ትጥቅ አምራች ድርጅቶች ምርታቸውን ለማስተዋወቅ ሲሉ ማዘውተሪያ ለመገንባት ወደ ኋላ እንደማይሉ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ግን እንዴት? አሁንም ከፊት ለፊታችን ትልቁ የዓለም አትሌቲከክስ ሻምፒዮና ስለሚጠብቀን፣ ቢያንስ በዕድሳት ምክንያት የተዘጋው የአዲስ አበባ ስታዲየም ትራክ አገልግሎት የሚሰጥበት ሁኔታ ቢመቻች ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ካልሆነ ግን ይህ ጠዋትና ማታ ከልጅ እስከ አዋቂ የምንዘምርለት አትሌቲክስ ቀይ መብራት ላይ መውደቁ የማይቀር ነው፡፡              

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...