Monday, September 26, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

  የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

  ቀን:

  ይህንን ገጠመኜን የጻፍኩት በአገራችን በኢትዮጵያ እየተስተዋለ ያለው አደገኛ ሁኔታ ስላሳሰበኝ፣ በእኔ በአንድ ግለሰብ ላይ ከደረሰው ፈተና በመነሳት ምናልባት ዙሪያ ገባውን ለማየት ቢረዳ በሚል ዕሳቤ ነው፡፡ ወገኖቼ ለችግሮቻችን የመፍትሔ ጠጠር መወርወር የምንችለው ባለን አቅም ስለሆነ ተከተሉኝ፡፡ ‹‹ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው›› የሚለውን ቢሂል እንደ ዋዛ ከሚመለከቱት መካከል አንዱ ነበርኩ ብል ማጋነን አይሆንም፡፡ በአንድ ወቅት የወሬ ሞገድ ያደረሰው መናወፅ ምስቅልቅሌን ካወጣው በኋላ፣ እንደ ገብስ ያልተፈተገ ወሬ በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ የሚፈጥረው አደጋ ለሰዎች ማስተማሪያ ይሆን ዘንድ እንዲህ አቀረብኩት፡፡ ወሬ በቤተሰብ፣ በመኖሪያ አካባቢ፣ በመሥሪያ ቤትና በተለያዩ ቦታዎች በተካኑበት ሰዎች ተከሽኖ ሲቀርብ እውነት ይመስላል፡፡ ነገር ግን እንደ ወንፊት ሳያጣሩ እንዳለ የሚቀበሉትና የሚያስተጋቡት ሲያገኝ ደግሞ፣ እንደ ሰደድ እሳት በአገር ላይ ከፍተኛ አደጋ ይፈጥራል፡፡

  ከዓመታት በፊት ነው አለቃዬ ‹‹በግል ላነጋግርህ እፈልጋለሁ›› ይሉኝና ምሳ ጋብዘውኝ አንድ ሬስቶራንት እንገናኛለን፡፡ የምንፈልገውን ምሳ እየበላን የባጥ የቆጡን ስናወራ ቆይተን ቡናችንን ፉት ማለት ስንጀምር፣ ወደ ዋናው የተፈለግኩበት ርዕሰ ጉዳይ አመራን፡፡ አለቃዬ ዙሪያ ዙሪያውን ሲሉ ቆይተው፣ ‹‹አንተና እከሊት ግንኙነታችሁ በምን ላይ ነው የተመሠረተው?›› በማለት ያልጠበኩትን ጥያቄ አቀረቡልኝ፡፡ ‹‹እከሊት›› በማለት የምገልጻት የሥራ ባልደረባዬ ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት ስትሆን፣ እኔ ምንም እንኳን ላጤ ብሆንም በቅርቡ በትዳር የምቆራኛት ጓደኛ አለችኝ፡፡ የአለቃዬ ጥያቄ ግን በጣም አስደነገጠኝ፡፡

  ‹‹እኔና እሷ የሥራ ባልደረባ ከመሆናችን በተጨማሪ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ሐሳብ ለሐሳብ ስለምንለዋወጥ እንግባባለን፡፡ የምናነባቸውን መጻሕፍትም እንዋዋሳለን፡፡ ከዚህ ውጪ ምንም ዓይነት ግንኙነት የለንም፡፡ ነገር ግን በሁለታችን መቀራረብ ወይም ግንኙነት ማን ምን አግብቶት ነው ይኼ ዓይነቱ ጥያቄ የቀረበልኝ?›› ብዬ ቱግ አልኩ፡፡ ሰውነቴ ተንቀጠቀጠ፡፡ እኛ ግን በሌሎች ግላዊ ጉዳይ ውስጥ ገብተን ለምን መፈትፈት እንደምንወድ እያሰብኩ በጣም ተናደድኩ፡፡

  አለቃዬ ትክ ብለው ሲያዩኝ ቆይተው፣ ‹‹አየህ ወዳጄ! አንተ ወንደ ላጤ ነህ ገና ያላገባህ፡፡ እሷ ባለትዳርና የልጆች እናት፡፡ የሁለታችሁ መቀራረብ በጣም ሲበዛ ሊፈጥረው የሚችለውን አደጋ አይታሰብህም? አንድ ወንድና አንዲት ሴት በጣም በተቀራረቡ ቁጥር ሰይጣን በመሀል ገብቶ የሚፈጥረው ችግር አይታይህም?›› እያሉ የማወጣጣት ይሁን የማራራቅ ዓይነት ወሬያቸውን ሲደረድሩ አናደዱኝ፡፡ እኔና ይህች ንፁህ ሴት አብረን በሥራ ዓለም የቆየንባቸውን ሰላማዊ ጊዜያት እያሰብኩ ስለእሷ ማሰላሰል ስጀምር፣ ንዴቴን መቆጣጠር የማልችልበት ደረጃ ላይ ደረስኩ፡፡

  ‹‹እርስዎ በዕድሜም ሆነ በዕውቀት፣ በሥራ ልምድም ሆነ በበርካታ አገሮች ባደረጉዋቸው ጉዞዎች ለእኔም ሆነ ለሌሎች የሚተርፍ አርዓያነት ይኖርዎታል ብዬ አስብ ነበር፡፡ ነገር ግን ምንም መያዣ መጨበጫ በሌለው ወሬ ወይም አሉባልታ ላይ ተመሥርተው፣ እንዴት የእኔንም ሆነ የዚችህን የተከበረች ሴት መልካም ስም የሚያጎድፍ ንግግር ያደርጋሉ? ወንድ ከወንድ፣ ወይም ሴት ከሴት ጋር ጓደኛ የሚሆኑትን ያህል እኮ ወንድና ሴትም የልብ ጓደኛሞች ይሆናሉ፡፡ ባይገርምዎት ለእኔ እየነገሩኝ ያለውን አሉባልታ ይህች የተከበረች ሴት ብትሰማ ችግር ይፈጠራል…›› ብያቸው ራሴን በሐዘን ወዝውዤ ዝም አልኩ፡፡ በመካከላችን ረዥም ፀጥታ ሆነ፡፡

  አለቃዬ እንደ ምንም ብለው ጉሮሮአቸውን ካፀዳዱ በኋላ፣ ‹‹ወዳጄ ምን መሰለህ? የሁለታችሁ በጣም የጠነከረ ግንኙነት ያሳሰባቸው በጣም ጨዋ የምላቸው ሁለት የሥራ ባልደረቦች እስኪ ምከራቸው ስላሉኝ ነው እንጂ፣ እኔማ በሰዎች ግላዊ ጉዳይ ውስጥ መግባት ፈልጌ አይደለም፡፡ እንደነገርከኝ ግንኙነታችሁ ከእንከን የፀዳ ከሆነ ጥሩ ነው፡፡ ሆኖም እነዚህ ጥሩ ሰዎች እንደነገሩኝ የሁለታችሁ ግንኙነት የተዛባ ከሆነ አደጋ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ለምሳሌ ባለቤቷ ቀንቶ እዚህ ያለህበት ቦታ ድረስ መጥቶ ቢገድልህስ? አንተም አሟሟትህ አሳፋሪ ይሆናል፡፡ የድርጅታችንም መልካም ስም ይጠፋል፡፡ አየህ ወዳጄ! ለአንተም ሆነ ለድርጅቱ ደኅንነት በማሰብ ነው ይህንን አሳሳቢ ጉዳይ ያነሳሁብህ…›› እያሉ ሲቀባዥሩ ውስጤ ታመመ፡፡

  ‹‹እርስዎ የምትሏቸው ጨዋ መካሪዎች እነ ማን ናቸው?›› በማለት ጥያቄ ሳቀርብ ሊነግሩኝ ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ ‹‹በደንብ መወያየት ካለብን ይንገሩኝና መፍትሔውን እንፈልግ…›› በማለት ማሳሰቢያ ባቀርብም፣ የወሬ ፈብራኪዎቹን ማንነት መናገር አልፈለጉም፡፡ ብላቸው ብሠራቸው ለጥያቄዬ መልስ ጠፋ፡፡ ‹‹አዩ ጌታዬ! እኔ ከእርስዎ በዕድሜም ሆነ በተለያዩ ጉዳዮች ባንስም፣ በመልካም ሰብዕናዬና በጨዋነቴ እበልጥዎታለሁ፡፡ የወሬ ምንጩን ብቻ ሳይሆን፣ ተጨባጭ ሁኔታውን ሳልመረምርና ሳላረጋግጥ አደባባይ አልወጣም፡፡ በስማ በለው የሰው ስም እያነሳሁ ጭቃ አልቀባም፡፡ በአሉባልታ ፈረስ እየጋለብኩ የሰው ስም አላጠፋም፡፡ እርስዎ ግን ይህንን የማድረግ ድፍረት ስለሌለዎት ንቄዎታለሁ…›› ብያቸው የተቀመጡበት ጥያቸው ሄድኩ፡፡ ቢሮ መግባት ስላስጠላኝ በቀጥታ ወደ ቤቴ ነው የሄድኩት፡፡ ያቺን ጥሩ የሥራ ባልደረባዬን ጨምሮ አንዳንድ ጓደኞቼ ስልክ ቢደውሉም፣ ለጊዜው ራሴን ስላመመኝ ቤት መሄዴን ከመግለጽ ውጪ ለማንም ምንም ነገር አልተነፈስኩም፡፡

  ሌሊቱን ሙሉ እንቅልፍ አጥቼ አድሬ በጠዋት ቢሮ የደረስኩት የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤዬን ጽፌ ነበር፡፡ አየሩ በወሬ የተበከለበት ቦታ ብዙ መቆየት ጥሩ ስላልነበር ሥራ መልቀቄ ትክክል ነበር፡፡ ደመወዙ በጣም ጥሩ ቢሆንም ሌላ ቦታም አገኘዋለሁ፡፡ ለአዕምሮ ሰላም ሲባል ክፉዎች ያሉበትን ሥፍራ ለቆ ወደ ሌላ ቦታ መሄድ ለእኔ የተሻለ ምርጫ ነበር፡፡ የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤዬ የደረሳቸው አለቃዬ እየበረሩ መጥተው፣ ‹‹ና እንነጋገር እፈልገሃለሁ…›› ሲሉኝ፣ ‹‹መፈላለግ ድሮ ቀረ…›› ብዬ ሸኘሁዋቸው፡፡ በአለቃዬ የፀፀት ንግግር ያፈተለከው ሚስጥር መሥሪያ ቤታችን ውስጥ የዚያኑ ዕለት ሲሰማ የአማላጅ ብዛት ቢሮዬን አጥለቀለቀው፡፡ ‹‹የወሬው ምንጭ መታወቅ አለበት…›› የሚለው ግትር አቋሜ በመበርታቱ አለቃዬ እጅ ሰጥተው ሰዎቹ ተጋለጡ፡፡ አንዷ የእሳቸው ጸሐፊ፣ ሌላዋ ደግሞ የአንድ ክፍል ኃላፊ ናት፡፡ ምክንያታቸው ሲጠየቅ የሚናገሩት ጠፋ፡፡ በዕድሜ የገፉት የፋይናንስ ክፍል ኃላፊ፣ ‹‹ሁለቱንም አውቃቸዋለሁ፡፡ ውስጣቸው ያለው ምቀኝነት እንኳን ሰው ብረት ያቀልጣል…›› ሲሉ ሁለቱም በኃፍረት አንገታቸውን ደፉ፡፡ ወሬኛና አሉባልተኛ እንደ አሸን በፈላበት አገር ውስጥ መጠየቅና መመርመር ማንን ገደለ? አንዴ በብሔር ሌላ ጊዜ በሃይማኖት እየተመካኘ ንፁኃን እየተጎዱ ነው፡፡ አገር ልትፈራርስ ነው፡፡ እባካችሁ የመፍትሔ ያለህ እንበል፡፡

  (ሚኪያስ በፈቃዱ፣ ከሳር ቤት)

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በኢትዮጵያ ላይ የቀጠለው የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት

  ምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዲፕሎማሲም...

  የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የድጎማ በጀት ለፖለቲካ ሥራ ማስፈጸሚያ እንደሚውል የሚያሳይ ሪፖርት ቀረበ

  ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ የበጀት ድጎማ ከመደበኛው ሥራ ይልቅ ከዋናው...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የአመራሮች ምርጫና ቀጣይ ዕቅዶቹ

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሲጠበቅ የነበረውን...