Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹መሪነት ሁሉንም ነገር ማወቅ ወይም ሁሉም ቦታ መገኘት አይደለም›› አረጋ ይርዳው (ዶ/ር)፣ የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት

በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኃላፊነታቸው ወደ 12 ሺሕ ሠራተኞችን የያዙ ከ27 ያላነሱ ድርጅቶችን አንድ ላይ አስተዳድረዋል፡፡ ከአቪዬሽን ዘርፍ አንድ ብሎ የጀመረው የሙያ ሕይወታቸው አሁን እስከ ሚገኙበት የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትነት ድረስ ረዥም ታሪክ ያለው ነው፡፡ በትምህርት በኩል ከአንድም ሁለት ፒኤችዲ ዲግሪዎችን ጨምሮ ብዙ ሥልጠናዎችንና ትምህርቶችን እስከ ውጭ አገሮች ድረስ ገብይተዋል፡፡ በብዙ መለኪያዎች በዕውቀታቸው ብቻ ሳይሆን በሳለፉት የሥራ ሕይወትም፣ በአመራርነት ሁለገብ ዕውቀትና ልምድ ካላቸው ሰዎች ተርታ የሚሠለፉ ናቸው፡፡ የዛሬው ቆይታ ዓምዳችን እንግዳ የሆኑት አረጋ ይርዳው (ዶ/ር) ላለፉት 14 ዓመታት ስለቆዩበት የትምህርት ዘርፍ፣ በተለይም ስለግል ከፍተኛ ትምህርት ሰፊ ውይይት ከሪፖርተር ጋር አድርገዋል፡፡ ለረዥም ዓመታት በሥራ አመራር ዘርፍ ያሳለፉ እንደ መሆናቸው ስለአመራርነት ልምድና ዕውቀታቸውን አካፍለዋል፡፡ ወደ ፖለቲካው እንደማያዘነብሉ በግልጽ ቢናገሩም፣ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ እንደሚታዘብ እንደ አንድ አንጋፋ ምሁር ‹‹መጨካከናችን በዝቷል›› ያሉበትን የግል ምልከታቸውን አጋርተዋል፡፡ አንጋፋው ምሁር የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አረጋ ይርዳው (ዶ/ር) ከዮናስ አማረ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- እንደ አገር በትምህርት ዘርፍ የገጠመው ፈተና እንዴት የሚገለጽ ነው?

አረጋ (ዶ/ር)፡- በትምህርት ዘርፍ ያጋጠመን ችግር በሌሎች መስኮች እንዳጋጠመን ዓይነት ችግር ነው፡፡ በመንግሥት ደረጃ ስታየው ትምህርት ከሥራዎቹ አንዱ ነው፡፡ ትምህርት ልዩ ትኩረት ያስፈልገዋል የሚባለው የትውልድ ቀረፃ ጉዳይ በመሆኑ ነው፡፡ ውጤቱ በ20 እና በ30 ዓመታት የሚለካ ስለሆነ፣ ችግሩን ነገ ጠዋት እናስተካክላለን ልንለው ስለማንችልና የዛሬ ብልሽቱ ለብዙ ጊዜ የሚዘልቅ በመሆኑ ነው ትምህርት ይተኮርበት የሚባለው፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ሌሎች መስኮችን የሚፈትኑ ችግሮች በሙሉ ትምህርትንም ይፈትናሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ ሆኖም የትምህርት ዘርፍ ችግር ከተባለ ቀድሞ የማነሳው የዘርፉ አለመረጋጋትን ነው፡፡ የፖሊሲ መረጋጋት የለውም፡፡ ተከታታይና ፈጣን ለውጦች ይስተናገዱበታል፡፡ እንደ ትምህርት ያሉ አንዳንድ ዘርፎች ግን ይህን አይፈልጉም፣ መረጋጋት ያስፈልጋቸዋል፡፡ የ20 እና የ30 ወይም የ50 ዓመታት አገልጋይ ፖሊሲ ተቀርፆ ያንን ውጤቱን በየጊዜው መገምገም ይሻላል እንጂ፣ ሰዎች በተቀያየሩና ሐሳብ በተለዋወጠ ቁጥር ትምህርት ፖሊሲን መቀያየሩ አደጋ አለው፡፡ ድሮ እኛ ስንማር ስምንተኛ ክፍል ነበር ብሔራዊ ፈተና የሚሰጠው፡፡ ቀጥሎ ወደ ስድስተኛ ወረደ፣ ወደ አሥረኛ ተሄደ፣ አሥራ ሁለተኛ ገባን፡፡ ከዚያ እንደገና ወደ በፊቱ ይመለስ ተባለ፡፡ በዓለም ላይ ምርጥ ተሞክሮ በብዛት አለ፡፡ አንድ ጊዜ ተሞክሮ ውጤት ያመጣውን ዓይነት ትምህርት እያሻሻሉና እያዳበሩ መሄድ አስፈላጊ ነው፡፡ የፖሊሲዎች መለዋወጥ፣ የሰዎች መለዋወጥና ዘርፉ የተረጋጋ አለመሆኑ ችግር ፈጥሮበታል ብዬ አምናለሁ፡፡ ቋሚ የሆነና ለረዥም ጊዜ የሚያገለግል ፖሊሲ አለመኖሩ አንዱ ችግር ነው፡፡ ከዚህ ውጪም የእኛ አገር ትምህርት የፖለቲካ ተፅዕኖ የበዛበት ነው፡፡ ሁሉም ሰው የሚያተኩርበትና ገለልተኛ ሆኖ መቀረፅ ያልቻለ ሥርዓት ነው ያለን፡፡ በእኔ እምነት ትምህርት ከፓርቲም ሆነ ከመንግሥት አተያይ ትንሽ ለየት ያለ መሆን አለበት፡፡ ትምህርት መቀረፅ ያለበት ለአገር በሚበጅ መንገድ ነው እንጂ፣ የፖለቲካ ፍላጎት ወይም ተፅዕኖ ሊያርፍበት አይገባም፡፡ የፈለገው ፓርቲ ቢኖር ትምህርት መቀረፅ ያለበት ለአገር በሚበጅ መንገድ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ግብርና መር ኢኮኖሚ ያላት አገር ናት፡፡ ለዚህች አገር የሚበጃትን ትምህርት ፈልጎ መቅረፅ እንጂ፣ ከሌላ ቦታ ቀድቶ ብቻ ማምጣትም አያዋጣም፡፡

‹ቲቬት› የሚባል ነገር አለ፡፡ የትምህርት አሰጣጣችን ከቲቬት በተጨማሪም፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና ሳይንስ ተኮር ይሁንም ይባላል፡፡ ነገር ግን የአገር ኢኮኖሚን ለማዳበር የትኛው ነው በአንገብጋቢነት የሚያስፈልገን የሚለው መመርመር አለበት፡፡ ቴክኖሎጂ ወይም አይቲ አያስፈልጉም እያልኩ ሳይሆን፣ ግብርና ዋናው የኢኮኖሚያችን ምሰሶ ሆኖ የግብርና ዘርፍ ትምህርት በጣም ሊያስፈልገን ይችላል የሚል ግምት አለ፡፡ በመጪዎቹ አሥር ዓመታት በጣም የሚያስፈልገን ሥልጠና የቱ ነው ብሎ መወሰን አስፈላጊ ነው፡፡ ጊዜው ሲደርስ ደግሞ እንደ ወቅቱ በመከለስ የሚጠይቀንን ማሻሻያ ማድረግ አስፈላጊ ሒደት ይሆናል፡፡ ትልቁን የግብርና መስካችንን የማይለውጥ አሠራርን ኮፒ እያደረጉ ማምጣትም አዋጭ አይደለም፡፡ በአጭሩ ጠቅለል አድርገን ስናስቀምጠው የትምህርት ዘርፉን የሚፈትኑት ችግሮች የፖሊሲ መለዋወጥ፣ ለረዥም ጊዜ የሚያገለግል ቋሚ ፖሊሲ አለመኖርና የፖለቲካ ተፅዕኖ ናቸው፡፡ ሰላምና መረጋጋት ደግሞ የጋራ ጉዳይና ለሁሉም ዘርፍ የሚያስፈልግ ነገር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ጥራትና ተደራሽነትን ማስታረቅ የሚቻለው እንዴት ነው?

አረጋ (ዶ/ር)፡- የጥራት (ኳሊቲ) አረዳዳችንና ፍልስፍናችን ሊገመገም ይገባዋል፡፡ ጥራትን በተመለከተ አንድ የተወሰነ ነገር ስላደረግህ ነገ ጠዋት ጥሩ ውጤት ይመጣል ማለት አይደለም፡፡ ጥራት በትምህርት ብቻ ሳይሆን በሁሉም ነገራችን ውስጥ አስፈላጊ ነው፡፡ በንግድ መስክ የጥራት ጉዳይ አስፈላጊ ነው፡፡ በንግድ ሚኒስቴር፣ በፖለቲካና በውጭ ጉዳይም ሆነ በሁሉም መስክ የጥራት ጥያቄ አለ፡፡ ጥራት መታሰብ ያለበት አንድን ነገር ለመሥራት ወጥ የሆነ ደረጃና መለኪያ መሥፈርት አዘጋጅተህ በዚያ ስታንዳንርድ መሠረት ሲሠራ የሚገኝ ውጤት ነው፡፡ ይህንን ውጤት ለማምጣት የብዙ ነገሮች ድምር ያስፈልጋል፡፡ ሁልጊዜ የሚያስጨንቀው ጥራት ሲባል በትምህርት ላይ ነው የምናጠነጥነው፡፡ ትምህርት ግን በባዶ ወይም ብቻውን መሄድ አይችልም፡፡ ተማሪዎቹም ሆኑ መምህራኑ የዚህ ማኅበረሰብ አካል ናቸው፡፡ በሌሎች ዘርፎች ጥራት ከሌለ በትምህርት ዘርፍም ያው ዓይነት ውጤት ነው የሚጋባው፡፡ ሌላው መስክ ተበላሽቶ ትምህርት ዘርፉ ብቻውን የተለየ ጥራት ይኖረዋል ማለት አይቻልም፡፡ ለምሳሌ በአዲስ አበባ ያለውን የአነዳድ ጥራት እንመልከት፡፡ ሥርዓት በማያከብር ሾፌር በሚሽከረከር አውቶብስና ሚኒባስ ወደ ትምህርት ቤት የሚመላለስ ተማሪ ይኼው ችግር እየተቀረፀበት ነው የሚያድገው፡፡ ሥርዓት ያለው ሾፌርን አነዳድ ሲያዩም ሾፌር በሚሆኑበት ጊዜ ያንኑ ነው የሚያንፀባርቁት፡፡ ጥራት የሚለው ሐሳብ ለትምህርት ብቻ ሳይሆን፣ በአጠቃላይ ለሁሉም መስክ የሚሠራ መሆኑን ማሰብ አለብን፡፡

ወደ ጥያቄው ስመጣ ጥራትና ብዛት አንድ ላይ አይሄዱም ነው የምለው፡፡ ብዛት ስትጨምር ሁል ጊዜ ጥራትን እያወረድክ ነው የምትሄደው፡፡ ጥራትን መስዋዕት እያደረግክ ነው ተደራሽነትን የምትጨምረው፡፡ ጥራትን ሳልቀንስ ብዛትና ተደራሽነትን እጨምራለሁ ካልክ ግን ተሳስተሃል፣ አብረው ስለማይሄዱ ነገሩ የውሸት ነው፡፡ ጥራት ያለውን ነገር ማቅረብ አለብኝ ስትል ግን ቁጥሩን ትቀንሳለህ፡፡ እንደ እኛ 114 ሚሊዮን ሕዝብ ያለውና በየዘርፉ ሰፊ ፍላጎት ያለው አገር ያለውን ውስን አቅርቦት ለሁሉም ለማቃመስ መፈተን ሁሌም የተለመደ ነው፡፡ ለማዳረስ ሲባል ብዛት የማይቀር ይሆናል፡፡ ነገር ግን በማዳረስ ሥራ ውስጥ ጥራት ይጠበቅ ካልን እጅግ ከፍተኛ አቅም ይጠይቀናል፡፡ የምትሠራቸው ትምህርት ቤቶች፣ አካባቢው፣ ተማሪውና አስተማሪው ሁሉ በተመቻቸ ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ ይህን ጊዜ የሚሰጠው ትምህርትም የጠራ ይሆናል፡፡ ጥራትም ሥርጭትም በተመሳሳይ ጊዜ በአንድ ዓይነት ሁኔታ ይጠበቃል ብሎ ማስገደድ ግን ድካም ብቻ ነው፡፡ ተደራሽነትና ቁጥር ሲጨምር ጥራት እንደሚቀንስ ዕውቅና በመስጠት በሒደት ችግሩን እየቀረፉ ለመሄድ መሥራት እንጂ፣ አዋጅ ወይም ክትትልና ኦዲት ለማድረግ መሞከር ግን ጊዜ መግደል ነው የሚሆነው፡፡ በሒደት እየተሻሻለ ምንፈልገው የጥራት ደረጃ ላይ እንደርሳለን በማለት እንጂ፣ የሚሠሩትን ሰዎች ‹ጥራት የሌለው› እያሉ በመተቸት ጥራት አይጠበቅም፡፡

ንግድ ሚኒስቴር ውስጥ ለምሳሌ ጥራት ያለው አገልግሎት ለማቅረብ በየቦታው ጥራት ማስጠበቂያ አሠራሮችን መተግበር ያስፈልጋል፡፡ ንግድ እንዲስፋፋ በማሰብ የንግድ ቢሮዎችን በየቦታው ተደራሽ ማድረግ ይኖርብሃል፡፡ በተመሳሳይ ደግሞ ንግድ ቢሮዎቹ አገልግሎት ጥራቱን የጠበቀ መሆን ይኖርበታል፡፡ የተንዛዛ አሠራር፣ ሙስናም ሆነ ቢሮክራሲ የሌለው አገልግሎት ለማቅረብ ዕቅድ ተይዞ በየደረጃው በተከታታይ ካልተሠራ በስተቀር፣ የሚፈለገው ጥራት በዘርፉ ይመጣል ማለት ዘበት ነው የሚሆነው፡፡ ጥራትን ለማሻሻል ችግሮችን እያወቁም ቢሆን ማበረታቻና ድጋፍ መስጠት አለብህ፡፡ ነጋዴን ስግብግብ እያልክ አይሆንም፡፡ የግል ትምህርት ተቋማትን ‹‹ገንዘብ ለመሰብሰብ የተቋቋሙ›› እና ‹‹ለትርፍ ያጋደሉ ነጋዴዎች›› እያልክ ጥራት አይመጣም፡፡ ጥራት የሚጠበቀው በወቀሳና በትችት አይደለም፡፡ ጉድለት ካለ እሱ ላይ ብቻ አተኩሮ መናገርና ለማሻሻል መደገፍ ነው የሚያዋጣው፡፡ ነጋዴ የሆነ ሁሉ ሌባ ነው ማለት አይደለም፣ ንግድ ሥራ ነው፡፡ እንኳን ንግድ ድለላም ብለን የሥራ መደብ እናወጣለን፡፡ በግሌ መሆን ያለበት የምለው ስንጀምር ከጥሩው ነገር ተነስተን በጎውን በማሳየት ጉድለቱ ይህ ነው ብለን እንዲሻሻል ማድረግ ነው፡፡ ሁልጊዜ ሌባ ሲባል ግን የሚሠሩ ሰዎችም ተስፋ እንዲቆርጡ የሚገፋፋ ነው፡፡

ሚዲያዎችም ብትሆኑ ጥራት ወደቀ ስትሉ ትንሽ ጥንቃቄ ማድረግ አለባችሁ፡፡ እውነት እንነጋገር ከተባለ በዚህ አገር የወደቀው የትምህርት ጥራት ብቻ አይደለም፡፡ በሁሉም ዘርፍ በሁሉም ተቋማት የጥራት ችግር የሚታይ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሯቸውን የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እያንዳንዳቸውን ብንመለከታቸው የጥራት መጓደል ይኖራል፡፡ በአንድ ዘርፍም ቢሆን ጥራት ያለውና የሌለው ነገር ተቀይጦ እናገኛለን፡፡ በግብርናው ዘርፍ ጥራት እንዳለው ሁሉ ጥራት የጎደለው ነገርም ይኖራል፡፡ ጥራት ዝም ብሎ የሚመጣ ነገር አይደለም፡፡ ጥራት ይኑር ስንልም ጥንቃቄ በማድረግ መመርመር ያስፈልጋል፡፡ በጥናት እንደተረጋገጠው ሥራ ሲሰፋ ሁልጊዜ ጥራት የሚቀንስ በመሆኑ፣ በእኛ በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ የምንከተለው በውስን ካምፓሶች ብቻ የማስተማርን አማራጭ ነው፡፡ በየቦታው መክፈትና ማስፋፋትን በመገደብ ለጥራት እየሠራን ነው የምንገኘው፡፡ ለማስፋፋት አስተማሪ፣ የመማሪያ ክፍል፣ የትምህርት ቁሳቁስና ሌላውንም ግብዓት ማሳደግ የሚጠይቅ ትልቅ ሥራ በመሆኑ፣ ይህን ስናደርግ ደግሞ ጥራትን ሊያወርድ ስለሚችል በውስን ካምፓሶች ጥራት ያለው ትምህርት ማቅረብን መርጠናል፡፡

ሪፖርተር፡- በቴክኖሎጂ ዕገዛ የተደራሽነትና የጥራት መጣጣምን መፍጠር አይቻልም?

አረጋ (ዶ/ር)፡- ይህ የአቅርቦት ሥርዓት መዘርጋትን የሚመለከት ነው፡፡ በኢንተርኔት (ኦንላይን) ትምህርት ለመስጠት የዲጂታል ቴክኖሎጂውን ጥራትና ተደራሽነት ይጠይቃል፡፡ እንደኛ ዓይነት ታዳጊ አገር ደግሞ በዚህ ዘርፍ ይቸገራል፡፡ ለምሳሌ እኛ ወልዲያ ላይ በኦንላይን ትምህርት እንስጥ ብንል፣ ወልዲያ ከተማ ያለው የኔትወርክ አቅርቦትና ሌላው የዲጂታል ቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ወሳኝነት ይኖረዋል፡፡ ዘርፉ ጥራት ያለው ካልሆነ ደግሞ የምሰጠውን የኢንተርኔት ትምህርት ጥራትም ይጎዳዋል፡፡ ጥራት የአንድ ነገር ብቻ ሳይሆን የብዙ ነገሮች ስብስብ ነው፡፡ ተማሪና አስተማሪውን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን፣ የትምህርት ጥራት የብዙ መስኮች ጥራትን የመጠበቅ ውጤት ነው፡፡ በትምህርት መስክ ጥራትን ስንገመግም የግል ወይም የመንግሥት ትምህርት በማለት ፈንታ፣ ሁሉንም የዘርፉን ጥራት የሚያሳድጉ ጉዳዮች በሚዛናዊነት መፈተሽና ለማሻሻል መትጋት ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ ያልተማረ ባለ ሰርተፊኬት አምራች ሆነዋል ይባላል፡፡ የግል ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ገንዘብ መሰብሰብና ጥራቱን ያልጠበቀ ትምህርት እየሰጡ ሰርተፊኬት ማደል ላይ አተኩረዋል የሚል ብያኔ ይሰማልና ይህ ከምን የመጣ ነው የሚለውን ቢያብራሩልን?

አረጋ (ዶ/ር)፡- ማንኛውም ሰው ሲሠራ መመሥገን ይፈልጋል፡፡ ማንም ሰው ለመሥራት ሲነሳ በአብዛኛው በጎ ነገር እሠራለሁ ብሎ ነው የሚነሳው፡፡ ይህ ሒትለርንም ሊጨምር ይችላል፡፡ ነገር ግን ሥራ የሚበላሸውና ችግር የሚፈጠረው በሒደት ነው፡፡ አንዳንዶች በውጤቱ ስኬታማ የማይሆኑትም ለዚህ ነው፡፡ ለምሳሌ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ቡሽ ሁለተኛ ለአገሬ ብዙ ነገር እሠራለሁ ብለው ቃል ገብተው ምርጫ አሸንፈው ወደ ሥልጣን መጡ፡፡ ወዲያው ግን የመስከረም 11 ቀን ጥቃት አሜሪካ ላይ ደረሰ፡፡ ይህ አጋጣሚ አጠቃላይ ቆይታቸውን ቀየረው፡፡ የፀረ ሽብር ዘመቻ፣ የአፍጋኒስታንና የኢራቅ ጦርነት እየተባለ ቆይታቸው የጦርነት ሆነ፡፡ አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ዓይነት አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡ ማንኛውም የግልም ሆነ የመንግሥት ተቋም ሲቋቋም በአቅሜ ጥሩ ነገር ሠርቼ እመሠገናለሁ ማለቱ አይቀርም፡፡ መጥፎ ነገር እየሠራሁ ደመወዜን ልብላ ወይም ልመሥገን የሚል ሰው አለ ብዬ አላምንም፡፡ ሁልጊዜም ቢሆን በሰዎች ማመን አለብን፡፡ ሰዎች ጥሩ ነገር ለማድረግ ነው በተፈጥሯቸው የሚያስቡት፡፡ ችግሩ የሚፈጠረው ግን ወደ ሥራ ውስጥ ሲገባ ነው፡፡ አንዳንድ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጥሩ ነገር እንሠራለን ብለው ቢነሱም፣ ነገር ግን በሒደት ተገቢውን አገልግሎት ሳያቀርቡ ብዙ ገንዘብ ማግኘትን ሊያስቀድሙ ይችላሉ፡፡ ይህ ከምን የመጣ ነው ብሎ መመርመር ያስፈልጋል፡፡ መጀመርያውኑ መቋቋም አልነበረባቸውም? ወይስ በቂ አቅም የላቸውም? መጣራት አለበት፡፡ ይህንን በተገቢው መንገድ በማጠያየቅ ጎደሏቸውን መሙላትና ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት እንዲያቀርቡ ማገዝ እንጂ፣ ጥራት የላቸውም ብሎ በጅምላ መፈረጅ አማራጭ ላይሆን ይችላል፡፡ ትምህርት ቤቶች ወረቀት እያራቡ ነው የሚሰጡት ከተባለ፣ ዘርፉን የሚመራው አሁን የትምህርትና የሥልጠና ኤጀንሲ የሚባለው ተቋም ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል በግል ተቋማት ላይ ስለሚያደርግ፣ መሥፈርቱንና ጥራትን ባጓደሉ ላይ ተገቢ የዕርምት ዕርምጃ መውሰድ አለበት፡፡ ነገር ግን የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጥራት ያለው ትምህርት አያቀርቡም የሚል ጥቅል ድምዳሜ ካለ ግን የተሳሳተ ግምት ነው የሚሆነው፡፡ ሁሉም እንደዚያ ስላልሆኑ በጅምላ ሊፈረጅ አይችልም፡፡

በአንድ ዓውደ ውጊያ የሚካፈሉ ሠራዊቶች እንኳ አንዱ ከሌላው ብርጌድ የተለየ ጀግንነትና ተዋጊነት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ስለዚህ ጥሩ የሆኑትን በማበረታታት፣ ደካማ የሆኑትን እንዲሻሻሉ ማገዝ ጠቃሚ ነው፡፡ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግብር ከፋይ ናቸው፡፡ ፈቃድ ለማግኘት እንዲያሟሉ የሚጠየቁት የፈቃድ መሥፈርትም እጅግ ጠንካራ ነው፡፡ ይህን ሁሉ አልፈው ወደ ሥራ ሲገቡ ችግር ከገጠማቸው እንዲያርሙ ማገዝ አዋጭ ነው የሚሆነው፡፡ ‹‹በግል የትምህርት ተቋማት ዲፕሎማ ይታደላል›› እያሉ አንዳንድ ወገኖች ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ይህን የሚያደርገው እከሌ ነው ለምን አይሉንም፡፡ ፖለቲካው ላይ ያሉ ሰዎች በግል ተቋማት ሰርተፊኬት እየተራባ ነው ሲሉ ብሰማም፣ ነገር ግን ይህንን ሲያደርጉ አግኝተን ይህን ዓይነት ዕርምጃ ወስደናል ሲሉ አይታዩም፡፡ ዩኒቲን ብትወሰድ ዲግሪያችንን የምናሳትመው ካሊፎርኒያ ልከን ነው፡፡ እዚህ አገር እንዳይራባ ልዩ መለያ ቁጥር ተሰጥቶት በውድ ገንዘብ ነው የምናሳትመው፡፡ ይህ ጥራት ለማስጠበቅ ከምናረገው አንዱ ጥረት ሊሆን ቢችልም፣ ነገር ግን ይህ በቂ እንዳልሆነ እንገነዘባለን፡፡ በጎ ተሞክሮ ያላቸውን ተቋማት ሌሎች ይገልገሉበት ማለት እየተቻለ፣ ሁሉንም በአንድ ላይ ዲግሪ የሚያራቡ ማለት ተገቢ አይደለም የምለው ለዚህ ነው፡፡

በአሁን ዘመን የምመለከተው ግን ዘራፍነት የበዛበትና ክብራችንን የሚነካ ንግግር ነው፡፡ ትልልቅ ኃላፊነት ላይ ያሉ ሰዎች ከኢትዮጵያ ሕዝብ ባህል ጋር የማይሄድ ንግግር ይናገራሉ፡፡ ከተማሩ ሰዎች ሊወጣ የማይገባ ቃላትን እንሰማለን፡፡ አንድን ዘርፍ በጅምላ ላለመፍረድ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ የግል ትምህርት ተቋምን ለ12 ዓመታት መርቻለሁ፡፡ እኛ እንቀርፀዋለን የምንለው ትውልድ መጥፎ ቃላትን ካቀበልነው፣ እየተቀረፀበት ስለሚሄድ በዚያም ረገድ ጥራት ይወርዳልና መጠንቀቅ አለብን፡፡ አንዳንዶች ሆን ብለው ሊያጠፉ እንደሚችሉ እረዳለሁ፡፡ ሆኖም የግሎቹ ብቻ ሳይሆኑ የመንግሥት ተቋማትም እኮ ኦዲት ሲደረጉ ብዙ ቢሊዮን ገንዘብ ጠፍቶባቸው እንደተገኙ ማወቅ አለብን፡፡ የግሎቹ ግብር ከፋይ በመሆናችን ቢያንስ የኦዲት ችግራችን አይታለፍም፡፡ የግል ስለሆነ ምዝበራ አለበት ማለት አያስኬድም፡፡ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለአገር ያስፈልጋሉ ተብሎ እንዲከፈቱ ፈቃድ እስከተሰጠ ድረስ፣ በሥራ ላይም ችግራቸውን እያረሙ እንዲሄዱ ማገዝ እንጂ ጥራት የለሽ ብሎ ማጣጣል ፍሬ የለውም፡፡

ሪፖርተር፡- ትምህርትን የወላጆች በማድረግ ወይም የ‹ፐብሊክ ፕራይቬት› ቅንጅታዊ አሠራርን በማስፋት የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ ይቻላል የሚል አማራጭ የሚያቀርቡ ባለሙያዎች አሉ፡፡ ከውጭ አገሮች ልምድም ሆነ በዘርፉ ካለፉት ቆይታ በመነሳት በዚህ ላይ ምን ማብራሪያ ይሰጣሉ?

አረጋ (ዶ/ር)፡- ሁሉም አገር ጥራት ያለው ትምህርት ለሕዝቡ መስጠት ያስችለኛል፣ እንዲሁም ከአገሩ ሁኔታ ጋር የተዛመደ ነው የሚለው የየራሱ የትምህርት ሥርዓት አለው፡፡ የአሜሪካና የእኛ አገር የትምህርት ፖሊሲ ፍላጎት አንድ ሊሆን አይችልም፡፡ አሜሪካኖቹ ከደረሱበት የዕድገት ደረጃ ጋር አብሮ የሚሄድ የትምህርት ሥርዓት እንደሚያስፈልጋቸው ሁሉ፣ እኛም የሚያስፈልገን ከደረስንበት የዕድገት ደረጃ ጋር የሚሄድ ትምህርት ነው፡፡ የእኛ አንዱ ዋና ችግር የሌሎች አገሮችን ትምህርት ሥርዓት መቅዳታችንና እንደወረደ እንገልገልበት ማለታችን ነው፡፡ የቀዳነውን ፖሊሲ ከእኛ አገር ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ማጣጣምና አብሮን እንዲሄድ ለማድረግ መሞከር ነው፡፡ አንዱ ጀርመን ስለተማረ ቲቬት ይዞ ይመጣል፡፡ ሌላው አሜሪካ ስለተማረ ሌላ ነገር ይዞ ይመጣል፡፡ አሁን ባለንበት የዕድገት ሁኔታ ለመጪዎቹ 20 እና 30 ዓመታት ያስፈልገናል የምንለውን የትምህርት ፖሊሲ መቅረፅ ነው የሚያዋጣው፡፡ ለዕድገት ቅድሚያ የሰጠነው መስክ ምን እንደሆነ መለየትና ትምህርቱንም የበለጠ በእሱ ላይ ያተኮረ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ የኔትወርክ መሠረተ ልማት ወይም የዲጂታል ቴክኖሎጂ ባላደገበት ሁኔታ፣ ሁሉንም ተማሪ በአይቲ ካልተመረቀ ካልን አስቸጋሪ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በተጨባጭ የገበሬዎች አገር እንደ መሆኗ መጠን ግብርናውን ከበሬ ማረስ ለማሻሻልና ለማዘመን የሚያስችሉ ትምህርቶች ያስፈልጉናል፡፡ ከበሬ ጫንቃ እርሻ የምንወጣው የዛሬ 20 ዓመት ነው ወይ? የግብርና መስክን ማዘመን ያለብን አይቲ ወይም ሌላ ቴክኖሎጂ ከጨረስን በኋላ ነው? የቴክኖሎጂ ወይም ኢንዱስትሪ ትምህርቶችን እየጠላሁ አይደለም፡፡ ነገር ግን ከእነዚህ ጎን ለጎን ግብርናውን የሚያዘምን የትምህርት ሥርዓት ቀርፀናል ወይ የሚለው ያስጨንቀኛል፡፡ ካሪኩለምን ከእነ መጽሐፉ ጭምር ከውጭ እያመጡ ማስተማር አደገኛ ሊሆን ይችላል የሚል ሥጋት አለኝ፡፡

ለእኛ የሚሆነውን የትምህርት ፖሊሲ መቅረፅ ከቻልን ሥራችን የአስተዳደር ነው የሚሆነው፡፡ በዚህ በኩል ደግሞ በግልም ሆነ በመንግሥት በተለይ ታዳጊ ወጣቶችን በሚያስተምሩ በሁለተኛና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ወላጆች በባለቤትነት ቢሳተፉ ጥሩ ቢሆንም፣ ነገር ግን ወጣቶቹ በራሳቸው ኃላፊነት መሸከምን እየለመዱ ቢያድጉም ጠቃሚና አማራጭ መሆኑ ሊታሰብ ይገባል፡፡ ሆኖም በአንደኛና በመዋዕለ ሕፃናት ትምህርቶች በዕድሜ ትንንሽ ተማሪዎች ስለሆኑ ሁለት ወላጅ ኖሯቸው ቢያድጉ የተሻለ ሊሆን ይችላል፡፡ በእነዚህ የትምህርት እርከኖች አስተማሪዎችም ወላጆችም እኩል ሚና አላቸው፡፡ ሁለቱ ጠንከር ባለ ዝምድና በእነዚህ የትምህርት ዕርከኖች እኩል በባለቤትነት ቢሠሩ አዋጪ ሊሆን ይችላል ማለት ነው፡፡ ፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነርሺፕ (ፒፒፒ) እየተባለ በሁሉም መስክና በሁሉም ደረጃ አዋጭ አሠራር ነው በሚል የሚቀርቡ መፍትሔዎች ሁሌም ትክክል ናቸው ማለት አይደለም፡፡ ነገሩን በሁሉም ቦታና ሁኔታ በጅምላ የምንጠቀምበት አድርጎ ማሰብ ስህተት ነው፡፡ አሜሪካም ብትሄድ ኤለመንተሪና ሃይስኩል አካባቢ አጥንተው ለተወሰነ ጊዜ ወላጆች በባለቤትነት የሚሳተፉባቸው ቻርተር ትምህርት ቤቶችን ፈጥረው ያውቃሉ፡፡ ነገር ግን አሠራሩ እንደ አካባቢው፣ እንደ ደረጃውና እንደ ሁኔታው የተለያየ ይዘት ኖሮት መሠራት ያለበት ነው፡፡ በዚህ ዓይነት አቀራረብ ከሆነ ወላጆች በትምህርት ቢሳተፉ ገንቢ ነው የሚሆነው፡፡

ነገር ግን ወላጆች ብቻ ሳይሆኑ በትምህርት ዘርፍ ላይ መሰማራት ያለባቸው በርካታ ባለድርሻዎች አሉ፡፡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ሲቪክ ማኅበራት  ሊሆኑም ይችላሉ፡፡ ሌሎችም ባለድርሻዎች አሉ፡፡ አሠራሩን ለተወሰነ ጊዜ፣ ለተወሰነ ቦታ ወይም ለተወሰነ ዓላማ ብሎ አጥንቶ መተግበር አስፈላጊ እንደሆነ አምንበታለሁ፡፡ ነገር ግን በጅምላ ይህ አቀራረብ ካልተተገበረ ማለት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡

ፐብሊክ ፕራይቬት ቅንጅት ያስፈልጋል፡፡ ወላጆች የትምህርት ባለቤት መሆን አለባቸው ብሎ በፖሊሲ አዘጋጅቶ በጅምላ ይተግበር ማለት አደጋ አለው፡፡ አንድ ነገር ብቅ ሲል ተሻምቶ የመቅለብ ነገር ይታያል፡፡ በየዩኒቨርሲቲው ሲኬድ ፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነርሺፕ ፈጥረናል ይባላል፡፡ ይህንን ለማስፈጸም የሚያስተባብር ቢሮ ሁሉ በአገር ደረጃ ሳይኖር አይቀርም፡፡ ወላጆች ብቻ እኮ አይደሉም አንድን የትምህርት ተቋማት ከኢንዱስትሪዎች ጋር በማስተሳሳር ውጤታማ ሥራ መሥራት እንደሚቻል በግሌ ሞክሬ አውቃለሁ፡፡ ለምሳሌ እኔ የምመራቸውን ሚድሮክ ጎልድና ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲን በማስተሳሰር ጥሩ ውጤት አምጥተን እናውቃለን፡፡ ሚድሮክ ወርቅን በምመራበት ጊዜ ብዙዎቹ ሠራተኞቻችን የውጭ ሠራተኞች በመሆኑ፣ አገሪቱ በዘርፉ ባለሙያዎች ልታፈራ ይገባል ብለን በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ የማዕድን ሳይንስ ትምህርት በመጀመር ከኢንዱስትሪው ጋር አስተሳሰርነው፡፡ አገሪቱ የማዕድን ምህንድስና ባለሙያ በሰፊው ያስፈልጋታል ብለን ካሪኩለም ቀርፀን ትምህርቱን መስጠት ጀመርን፡፡ ከማዕድን ሚኒስቴርና ከሚድሮክ ጎልድ ጋር አስተሳስረን የቀረፅነው የትምህርት ክፍል፣ ለሦስት ተከታታይ ዙሮች የተማሩ ወጣቶችን በዘርፉ በማስመረቅ ለአገር አበርክቷል፡፡ በክፍል ውስጥ የቀሰሙትን ትምህርት ለገደንቢ ወርደው ከባለሙያዎች ጋር ሠርተው በተግባር እንዲያውቁ በማመቻቸት ጥሩ ጥምረት ፈጠርን፡፡ ይህ በተጨባጭ ኢንዱስትሪና የትምህርት ተቋማትን የፈጠረ ሲሆን፣ ዛሬ  በብዙ የመንግሥት ተቋማት የማዕድን ሳይንስ ከመሰጠቱ ቀድመን ውጤታማ ሥራ የሠራንበት ተሞክሮ ነበር፡፡ የዚህ ዓይነቱን አሠራር ሁሉም መስክ ላይ መተግበር አይቻልም፡፡ ነገር ግን አሠራሩ ውጤታማ ነው በሚል በፖሊሲ አስደግፎ በሁሉም ቦታ ካልተተገበረ ካልን፣ ለማለት ብቻ እንጂ በተጨባጭ ውጤታማ የምንሆንበት ዕድል ጠባብ ነው፡፡ ፒፒፒ ተብሎ ማን ከማን ጋር ተቀናጀ ወይም ውጤት አመጣ የሚለውን መመለስ አለብን፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ዩኒቨርሲቲዎች ችግር ፈቺ የምርምር ውጤቶችን ማበርከት አለባቸው ይባላል፡፡ የትምህርት ተቋማት አንዱ ሚና መመራመርና ጥናት ማድረግ በመሆኑ፣ ይህንን ግምት ውስጥ ከቶ ነው ብዙኃኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሚሠራው፡፡

ይህን በተመለከተ ግን ችግር ፈቺ ጥናት ታቀርባለህ ወይ እየተባለ መጠየቁ አስቸጋሪ ነው፡፡ ለምሳሌ ከ20 ሺሕ ተመራቂ ተማሪዎች ውስጥ ብዙኃኑ ዲግሪ ለማግኘት የሚቀርቡ ጥናቶች እንጂ ችግር ፈቺ መሆን አለባቸው ማለት ስህተት ነው፡፡ አንዳንዶቹ አዳዲስ ሐሳብ የሚያፈልቁ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ በቀጣይ የሚጎለብቱ፣ ሌሎቹ ደግሞ አዳዲስ ሐሳብ ያላቸውና አንዳንድ ደግሞ ዓለም አቀፍ ችግሮችን ከኢትዮጵያ ሁኔታ አያይዘው የሚያነሱ ይሆናሉ፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እኮ ዓለም አቀፋዊ አስተሳሰብ ያለው ነው፡፡ የሚቀርቡ ጥናቶች በሙሉ አሁን የገጠመንን ችግር የሚፈቱና ግዴታ መሆን አለባቸው ሊባል አይችልም፡፡ መጀመርያ የገጠሙን ችግሮች ጥናት የሚፈልጉ ናቸው ወይ የሚለውን ከመለስን በኋላ ነው ችግር ፈቺ ጥናት ማድረግ የምንችለው፡፡ እኛ በበሬ ነው የምናርሰው፡፡ ህንድ አገር በበሬ ያርሳሉ፣ ነገር ግን በሬው ጭነት እንዳይበዛበት ደጋፊ መሽከርከሪያ ጎማ ከማረሻው ጎን ሲጨምሩለት ይታያል፡፡ እኛ አገር እነዚህን መሠረታዊ ችግሮቻችን የሚፈቱ ቀላል የሚመስሉ መፍትሔዎችን ለማፍለቅ ጥናት ማድረግ ነው ያለብን፡፡

ሪፖርተር፡- የግሉ ትምህርት ዘርፍ እንደ አንድ ኢንቨስትመንት ተገቢውን ትኩረትና ማበረታቻ ምን ይመስላል?

አረጋ (ዶ/ር)፡- ትምህርት ዘርፍ በዋናነት የሚያስፈልገው ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ መሆን ነው፡፡ ዘርፉ ለትውልድ ግንባታ ጠቃሚ መሆኑ ታምኖበት ሁሉም ወገን የየራሱን አስተዋጽኦና ድጋፍ የሚያደርግበት መሆን አለበት እንጂ፣ የበዛ ተፅዕኖ ወይም የተንሸዋረረ አተያይ አይሻም፡፡ ትምህርት ወደቀ የሚሉ ወቃሾች ጭምር የትምህርት ውጤት ናቸውና ከወቀሳ ወጥተው ዘርፉን ቢያግዙ ነው የምለው፡፡ ወጣት አመራሮች እየተፈጠሩ ነው ስንል እኮ የዚሁ ዘርፍ ውጤት ናቸው፡፡ በመጀመርያ ወጥነት ያለው ለረዥም ጊዜ የሚያገለግል ፖሊሲ ያስፈልገናል፡፡ ለውጥ ስናደርግ ደግሞ የሚያናጋ ዕርምጃ መውሰድ የለብንም፡፡ ዲግሪ በሦስት ዓመት፣ በአራት ወይም በአምስት ይሰጥ እያሉ የተደበላለቀ ዕውቀት ያለው ትውልድ መፍጠር ተገቢነት የለውም፡፡ በቁጥጥር ጥራትን አመጣለሁ የሚለው አተያይም የተሳሳተ ነው እላለሁ፡፡ እኔ የአቪዬሽን ሰው ነኝ፡፡ አውሮፕላን ጥገና ሲደረግለት ያኔ እያንዳንዱ ነገር የተጻፈ ሕግ ተቀርፆለትና በየአንዳንዱ የሥራ ሒደት ጥብቅ ቁጥጥር በተቆጣጣሪዎች እየተደረገ ነበር የሚካሄደው፡፡ አንድ ብሎን እንዴት ይፈታል? ይጠብቃል? የሚለው ሳይቀር የተጻፈ ሕግ አለው፡፡ ከጠበቀና ከተፈታ በኋላ ቴክኒሻኑና ተቆጣጣሪው ሁለቱም ፈርመው ነው ሥራውን የሚረካከቡት፡፡ ይህ ዘመን ግን ውጤታማ በሆነ አሠራር ተተካ፡፡ ሰዎችን ማለትም የሥራው ባለቤት የሆኑ ሙያተኞችን ኃላፊነት በመስጠት ጥራትም ውጤታማነትም መመዝገብ ጀመረ፡፡ ሥራህና ድርሻህ ነው ብለህ ባለሙያዎችን ኃላፊነት ስትሰጣቸው ውጤታማ ይሆናሉ፣ ጥራትም ይጠበቃል፡፡ 150 ተቆጣጣሪ ከጀርባ በማቆም ግን የሥራ ውጤትም ሆነ ጥራት እንደማይገኝ፣ አሁን ካለው የትራፊክና አሽከርካሪዎች ድብብቆሽ ጨዋታ መመልከት ይቻላል፡፡

ቀይ ሲበራ ማቆም ግዴታዬ ነው የሚል ሾፌር መፍጠር አለብህ፡፡ እኛ አገር ግን ችግር አለ ተብሎ ሲነገር በአንድ ሌሊት መቆጣጠሪያ አዋጅ ይወጣል፡፡ ችግሩ እንዳይፈጠር ለማድረግ ጥረት ሳናደርግ አዋጁ ቢወጣም የሚፈለገውን ግብ አይመታም፡፡ ሁልጊዜ ችግርን ወይም ኔጌቲቭ ነገርን ከምናሳድድ ጥቂት የአስተሳሰብ ለውጥ በማድረግ በጎ ባህልን ብንገነባ ነው የሚሻለው፡፡ የሰው ልጅ አይጨመቅም፣ ማበረታታትና ድጋፍን ነው የሚፈልገው፡፡ ስትጨምቀውና ስታስጨንቀው በከፋ ሁኔታ ነው አፀፋ የሚሰጠው፡፡ ከዚያ ይልቅ አምንሃለሁ፣ ኃላፊነት እሰጥሃለሁ፣ የምትሠራበት መመርያም ይህ ነው ብለህ አብቃው፡፡ ችግር ካለ ዕርዳታህን እንደሚያገኝ ነግረህ አሰማራው፣ ጥራት ያለው ውጤት ታገኛለህ፡፡ አየር መንገድ እዚህ አጠገባችን አለ፡፡ በየዓመቱ የሚያድጉበት ሚስጥር ምንድነው ብለን ለምን አንጠይቅም? ውጤታማ የሆኑት በጥራት ላይ ጥራት የሚጨምር ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሚያደርጋቸውን ውጤታማ አሠራር ለረዥም ጊዜ ስለገነቡና እንደ አስፈላጊነቱ ራሳቸውን ስላሻሻሉ ነው፡፡ ወደ ግል ተቋማት ስንመጣ ገቢያችን ከተማሪዎች የሚገኝ የመማሪያ ክፍያ ነው፡፡ የመንግሥቶቹ ገቢያቸው ከሕዝብ ታክስና ግብር የሚገኝ ገንዘብ ነው፡፡ አመጣጡ በተለያየ አቅጣጫ ቢሆንም፣ ሁለቱም ከሕዝብ የሚገኝ ነውና አንዱ ቅዱስ ሌላው እርኩስ ገቢ ነው ሊባል አይችልም፡፡ ሁለቱም አገልግሎት መስጠት (ማስተማር) ነው ሥራቸው፡፡ መንግሥት ቤት ያሉም ሆነ የግል ተቋማት የሚያስተምሩ መምህራን ሁለቱም ከአንድ የትምህርት ሥርዓት ባህር የወጡ ናቸው፡፡

የግሉ ከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ እንዲያድግ ከተፈለገና ለኢትዮጵያ አስፈላጊ ነው ከተባለ ዘርፉን ማበረታታት አስፈላጊ ነው፡፡ የግሉ ትምህርት ልዩ ባህሪ ያለው ሲሆን፣ የመንግሥት ሊያቀርባቸው የማይችላቸውን ሥራዎች ይሠራል፡፡ በተፈለገው ጊዜ አገልግሎቱ ይገኛል፡፡ በሥራ ላይ ያሉ ሰዎችን ያስተምራል፡፡ በቦታም ሆነ በገንዘብ ሰዎች አማርጠው ሊማሩ የሚችሉበትን ዕድል ይፈጥራል፡፡ ዋናው ነገር ለታለመው ዓላማ አገልግሎት መስጠቱን ማረጋገጥ ነው፡፡ አንድ ኢንቨስትመንት ወደ አገራችን ሲመጣ የታክስ ዕፎይታና ሌላም ጥቅማ ጥቅም ይሰጣል፡፡ ትምህርትም ልክ እንደ አንዱ ኢንቨስትመንት ታይቶ ማበረታቻ ሊደረግለት ይገባል፡፡ ትምህርት በልዩ ሁኔታ መታየት አለበት እየተባለ፣ የግል ትምህርት ተቋማትን አለማበረታታት ግን ይጋጫል፡፡ ግብርና ታክስ እየከፈሉ የሚሠሩ ተቋማት ናቸው፡፡ ሌሎች ዘርፎች እንዲቋቋሙ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ሁሉ፣ የትምህርት ተቋማትን ማበረታታት አለብን፡፡ ለትርፍ ብቻ ነው የተቋቋሙት ወይም ሌላ ዓይነት ገቢ አላቸው ብለህ ከድጋፍ ውጪ ካደረካቸው ግን፣ ዘርፉን ለማስፋፋትም ሆነ ጥራት ያለው አገልግሎት ለማቅረብ ይቸገራሉ፡፡ በዓመት የተወሰኑ መጻሕፍትን ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ መፍቀድ ቀላል ዕገዛ አይደለም፡፡ የላቦራቶሪ ቁሳቁሶችን ማስገባትም እንደ አስፈላጊነቱ ቢፈቀድ ለዘርፉ ትልቅ ነገር ነው፡፡ መምህራንን ከውጭ ማምጣት ግዴታ ሲሆንብኝ ለምን የተለየ ድጋፍ ካልተደረገልኝና ሁሉንም ነገር ግብርና ቀረጥ እየከፈልክ ከተባልኩ፣ ዞሮ ዞሮ ወጪውን በተማሪዎች ክፍያ ላይ ነው የምጭነው፡፡ ፈቃድ ማግኘት ላይ ያለው ውጣ ውረድ ለግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አስጨናቂ ነው፡፡ ብድር ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ የሚሠለጥኑ ሰዎችን በተለይ ፒኤችዲ ምሁራንን በመንግሥት ተቋማት ለማሠልጠን የምናገኘው ዕድል ጠባብ ነው፡፡ ትምህርት ልዩ ነው እየተባለ ከሌላው ዘርፍ እኩል ነው ታክስም ቀረጥም የምንከፍለው፡፡

ሪፖርትር፡- አንዳንድ የኮሌጅ ባለቤቶች ግን የማበረታቻ ሕጎቹ ቢኖሩም በተግባር አይተረጎሙም ይላሉ፡፡

አረጋ (ዶ/ር)፡- ሕጎቹ የሉም፡፡ ለምሳሌ እኔ ዩኒቲን ላስፋፋ ብል ቁጥር አንድ የሚቸግረኝ መምህር ነው፡፡ ኮሌጅ ስትከፍት ወይም አዲስ ፕሮግራም ስትጀምር ሕጉ ይህን ያህል ዶክትሬት፣ ይህን ያህል ማስተርስና ዲግሪ መምህራን ቅጠር ብሎ ጣሪያ ያስቀምጣል፡፡ ይህን ለማሟላት ስለማንችል ግዴታ በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች በዶክትሬት መምህራን እንዲሠለጥኑ እንጠይቃለን፡፡ ነገር ግን ተቋማቱ በፍላጎታቸው ካልሆነ በስተቀር አሠራሩ ሕግ አልተበጀለትም፡፡ አማራጭ ስታጣ ከመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች አስተማሪዎችን በትርፍ ሰዓት ልቅጠር ትላለህ፣ ነገር ግን ሕጉ በቋሚ ቅጥር አሟላ ይልሃል፡፡ ከውጭ አገሮች መምህራንን ለማምጣት ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ይጠይቃል፡፡ እሱ ደግሞ እንደ አገር ከባድ ችግር ነው፡፡ የግል ተቋማትን የመስፋፋት ፍላጎት የገደበው የመምህራን እጥረት ነው፡፡ አንድ መምህር በሁለት ኢንስቲትዩቶች ማስተማር የለበትም የሚል ሕግ መኖሩ ይገድባል፡፡ ይህ አሠራር የተቀረፀበት ምክንያት ቢገባኝም፣ በተጨባጭ ኢትዮጵያ ካለችበት ሁኔታ ጋር የተጣጣመ አይደለም፡፡ ሐኪም ቢሆን በግል አትሥራ ሊባል አይችልም፡፡ ብዙ ዶክተሮች ከሆስፒታል ውጪ በግል በየክሊኒኩ ባያገለግሉ ኖሮ የሕክምና ሽፋናችን እጅግ ኋላቀር ይሆን ነበር፡፡ ትምህርት ሲሆን ግን ልዩ ነው ይባላል፣ ጥራት ያስፈልጋል ይባላል፡፡ ሕክምናና ሌላውም እኮ ጥራት ይፈልጋል፡፡ የግል ትምህርት ላይ ያሉ ሕጎች ከጊዜውና ካለው ሁኔታ ጋር መሻሻል አለባቸው፡፡ ዘርፉን የሚቆጣጠሩ አካላት ጥራት አጓደሉ ባሏቸው ተቋማት ላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዕርምጃ መውሰዳቸውን እኛ በበጎ ብንቀበለውም፣ መዝጋት ግን አሁንም ቢሆን መፍትሔ ይሆናል ብለን አናምንም፡፡ ከመዝጋት ያጎደሉትን ነገር መሙላት ይሻላል እንላለን፡፡ ጥራት የሚያጓድሉ አሉ፡፡ ሆኖም መዝጋት ግን የኅብረተሰቡን ትምህርት የማግኘት ዕድል ነው የሚገድበው፡፡

ሪፖርተር፡- ስለአመራርነት (ስለሊደርሺፕ) አስፈላጊነት እናንሳ፡፡ ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ ተቋማት፣ አልፎም በአገር ደረጃ የብቁ አመራር ዘርፍን አስፈላጊነት እንዴት ይመለከቱታል?

አረጋ (ዶ/ር)፡- ለምሳሌ ዛሬ በማኔጅመንት የምናስተምራቸውን ተመራቂ ተማሪዎች ከሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ተግባር ተኮር የሆነ የአመራርነት ሥልጠና ስንሰጥ ነበር፡፡ ተማሪዎቹ ሲወጡ ከተግባሩ ጋር አንፃራዊ ትውውቅ በዘርፉ ይዘው እንዲወጡ ያግዛል፡፡ አመራር ስንል በመሠረታዊነት ቤተ መንግሥትም ይሁን፣ የሃይማኖት ተቋማት ወይ የሚሊታሪ ትንሽም ይሁን ትልቅ ወሳኝ ነው፡፡ ከቡና ቤት እስከ ሚኒስቴር ተቋማት በየዘርፉ ግንባር ቀደሙ ተጠሪ አመራር ነው፡፡ አመራር ስንል ሳይንስም፣ እንዲሁም ጥበብም ይጠይቃል፡፡ መሪ ሲባል ገንዘብ ስላለው ብቻ አመራሩ ጥሩ፣ ገንዘብ ስለሌለው አመራሩ መጥፎ ይሆናል ማለት አይደለም፡፡ አመራር የራሱ መለኪያ ያለው ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ አጥንቻለሁ፡፡ ትልቅ የሚባል 27 ድርጅቶች ያሉት ኩባንያም መርቻለሁ፡፡ የአመራርን ምንነት ለማሳወቅ በሬክታንግል ቅርፅ ወይም በፒራሚድ ምሥል የምናቀርበው ብዙ ሐሳቦችን ስለሚሰጥ ነው፡፡ ፒራሚዱ ከታች መቆሚያው ሰፊ ሲሆን፣ አናቱ ግን እየጠበበ ነው የሚሄደው፡፡ ተመሪው ለአመራርነት መሠረት ስለሆነ፣ ሰፊና ጠንካራ ሆኖ ወደ ላይ ሲሄድ ደግሞ እየጠበበ ነው አናቱ ላይ የሚደርሰው፡፡ መሪነት ሁሉንም ነገር ማወቅ ወይም ሁሉም ቦታ መገኘት አይደለም፡፡ መሪነት ተመሪዎችን ኃላፊነታቸውን አውቀው እንዲሠሩ መፍቀድ ነው፡፡ መሪ ሁሉንም ነገር ይመለከተዋል ማለት አይደለም፡፡ በየክፍሉ ራሳቸውን ችለው የሚሠሩ አመራሮችና ተመሪዎች ሊኖሩት ይገባል፡፡ ፒራሚዱን ገልብጠን ተመሪውን ከላይ መሪውን ከታች እናድርገው ካልንም ፒራሚዱ ችሎ ስለማይቆም ይወድቃል፡፡ ይህ በተቋማትም ሆነ በአገር የሚሠራ ጉዳይ ነው፡፡

ሊደርሺፕ/አመራር ብለን የምናስቀምጠው ሰው ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ አመራሩ የሚቀመጠው በሀብቱ፣ በዕውቀቱና በብቃቱ ነው? ወይስ በዘሩና በፖለቲካ ቀረቤታው የሚለው መፈተሽ አለበት፡፡ በአገራችን መታዘብ እንደሚቻለው ብዙ አመራሮች መሪ የሚሆኑት በአመራር ብቃታቸው አይደለም፡፡ ይህ የሚሆነው በዘርፉ ብዙ ሰዎችን ባለማፍራታችን ወይም ልምድ ያለው ለማግኘት ስለምንቸገርም ጭምር ነው፡፡ በእኛ አገር በብዛት ያሉት ማኔጅ የሚያደርጉ ሰዎች እንጂ መሪዎች አይደሉም፡፡

ማኔጅመንትና መሪነት የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ በመርከብ ብንመስለው መሪው የተወሰኑ የሥራ መመርያዎችን የሚሰጥ ወይም የሚሾፍረው ካፒቴን ይሆናል፡፡ ማኔጅመንቱ ግን መርከቡ ውኃ እንዳያስገባ ከሚቆጣጠረው ጀምሮ በየዘርፉ መደበኛ የቁጥጥር ሥራዎችን የሚሠራ ሰው ነው፡፡ እኛ አገር ችግር የሚፈጠረው ሁለቱን እየደባለቅን ነው፡፡ በፖለቲካውም ሆነ በትምህርቱና በሌላው የሚፈጠሩ ችግሮች ማኔጅመንትንና መሪነትን ለይቶ ካለመረዳት፣ እንዲሁም በአመራርነት የበቁ ሰዎችን ካለማፍራት የሚመነጭ ነው፡፡ ኢትዮጵያ 120 ሚሊዮን ሕዝብ ነው ያላት፡፡ ባለፉት 50 ዓመታት እኔ ራሴን ፊደል ከቆጠሩት ጨምሬ እጅግ ብዙ ተጣጥራ ያፈራቻቸው ትንሽ ምሁራንን ነው፡፡ በዚህ መንገድ የወጡ ምሁራን ግን ተተኪ ምሁራንን ለማፍራት የሚጠበቅባቸውን አልሠሩም፡፡ አገሬ ዕድል ሰጥታኛለችና ሌሎች በእኔ እግር እንዲተኩ ላድርግ ብሎ መሥራት ባህላችን አይደለም፡፡ ከዚህ ይልቅ ምሁርነትንና ፊደል መቁጠርን ልክ እንደ ትልቅ መኩራሪያ በመቁጠር አውቅላቹኋለሁና እኔ የምላችሁን አድርጉ ወደ የሚል ጎጂ ልማድ ነው የገባነው፡፡ እንድማር አድርጋችሁኛልና የእናንተ ጥፋት ነው ስለዚህ ከላያችሁ ሆኜ እንደፈለግኩ ላድርጋችሁ የሚለው ብሂል ጎድቶናል፡፡ 

ለመምራትና አገር ለመቀየር ቀድሞ እንደ መሠለፍ ጥቂት የሚጣጣሩ ሰዎች ብቅ ሲሉ፣ ከጀርባ ሆኖ መተቸትን የመምረጥ ዝንባሌ በምሁራኑ ይታያል፡፡ ስለተመቸህ ተቀምጠህ ስትተች መዋል፣ የበኩልህን ከማድረግ ይልቅ ሌሎችን ማጣጣል በግልጽ የሚያሳፍር ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ደሃ ከሆነች አገር ዲግሪ ተሰጥቶህ ኃላፊነትህን ከመወጣት፣ ከሚሠሩ ሰዎች ጋር ከመተጋገዝ፣ እያጠፉና እያስተካከሉ በጎ ሥራዎችን ከማበርከት ይልቅ ተቀምጦ በትችት ብቻ ማሳለፍ እየገደለን ነው፡፡ የሚሠሩ ሰዎችን ስህተት ማጉላትና መተቸት ድሮም ነበረ፣ ነገር ግን አሁን ሚዲያውም ተጨምሮበት ብዙ እየጎዳን ነው፡፡ ሚዲያው በጎውን ትቶ መጥፎው ነገር ላይ ማተኮሩ ለዚህ ችግር መስፋት የበለጠ በር ከፍቷል፡፡ ብርጭቆው ጎደለ ከምትል ብርጭቆው በግማሽ የሞላ ነው ማለት በእጅጉ ገንቢ ነው፡፡ መማር ትሁትነት ነው፣ መማር ባገኘኸው ክቡር የመማር ዕድል ተጠቅመህ ሌላው ያልተማረውን ማሳወቅና መርዳት ነው፡፡ እኔ አውቅልሃለሁ አንተ ዝም በል ልትል ወይም ለራስህ ልትጠቀምበት ብቻ አይደለም፡፡ ይህ በሃይማኖቱም ብንሄድ ይሠራል፡፡ ለምሳሌ በክርስትናው ክርስቶስ መጥቶ ሲያስተምር ሌሎችን ዕርዱ፣ አስተምሩ ነው ያለው፡፡

ሪፖርተር፡- በብዙ መስኮች በአገር ደረጃ አመራርነት ላይ አልሳካልን ያለው ለምን ይመስልዎታል?

አረጋ (ዶ/ር)፡- ዋናው ጀምሮ የመተው ችግር ስላለብን ነው፡፡ የምንሠራው ነገር በሙሉ ሳያልቅ ማቆም የለብንም፡፡ በተለይ ፕሮጀክት ከሆነ እስከ መጨረሻው ሄደን መፈጸም አለብን፡፡ የምንሠራቸው ነገሮች በሙሉ ደግሞ የትንንሽ ፕሮጀክቶች ጥርቅሞች ናቸው፡፡ የዛሬ ስብሰባዬን አገባድጄ ካልሄድኩ ነገ ችግር ነው፡፡ እኛ አገር ፕሮጀክቶች ይጀመራሉ ይተዋሉ፡፡ ጀምሮ አለመጨረስ ደግሞ ለድርጅት ብቻ ሳይሆን እንደ አገርም ብዙ ኪሳራ የሚያደርግ ነው፡፡ ፋይል ከፋፍቶ ሳይዘጉ መተው ለሥራ እንቅፋት እንደሆነ ሁሉ፣ ሳር ከበቀለበት በኋላ የጀመሩትን ግንባታ ልቀጥል ማለት ወጪው ከባድ ነው፡፡ ሌላው ሥራውን የጀመሩ ሰዎች ጅምራቸው ጥሩ ከሆነ እስከ መጨረሻው እንዲቀጥሉት ማድረግም ጠቃሚ ነው፡፡ ቡፌ እንደሚቀምስ ሰው ትንሽ የስኬት ፍንጭ ሲያሳዩ ወደ ሌላ ነገር ማዛወር ችግር አለው፡፡ ለውጥ አይኑር አልልም፣ ነገር ግን መፍትሔ የምናገኘው ሰውን በመቀያየር አይደለም፡፡ ስኬት አልመጣ ቢል ራሱ ሰዎችን ባሉበት ቦታ በማብቃት ማጎልበት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡        

ሪፖርተር፡- አገራችን አሁን ለምትገኝበት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የተዳረገችው ምን ጠፍቶ ነው? ከአመራር ጉድለት በተጨማሪ የሚቆጣና የሚመክር ባለመኖሩ ነው ወይ?

አረጋ (ዶ/ር)፡- አሁን የገጠመንን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግር አንዳንዶች ቀውስ ቢሉትም፣ በእኔ እምነት ግን ፈተና (ቻሌንጅ) ነው የምለው፡፡ ሰው የተማረው፣ የሚያስበውም ሆነ የተፈጠረው በሙሉ ችግሮችን ለመፍታትና ምቹ የኑሮ ሁኔታን ለመፍጠር ነው፡፡ ችግር ለምን ተፈጠረ ሊባል አይቻልም፡፡ አንድ ሰው/አመራር የሚለካው ለተፈጠረ ችግር በሚሰጠው መፍትሔ ነው፡፡ መሪ ሥራው ቀውሱ ለምን ተፈጠረ? እነማን ፈጠሩት? ወይም ከየት መጣ? ማለት ሳይሆን፣ የመጀመርያ ሥራው መፍትሔ ማፍለቅ ነው፡፡ መሪዎች የተፈጠሩት ለመምራትና መፍትሔ ለመስጠት ነው፡፡ ችግር ሲፈጠር የመጀመርያው ሥራቸው ቅደም ተከተልን በመለየት ለችግሮች መፍትሔ መስጠት እንጂ፣ እነማንና እንዴት እያሉ ከቀውሱ በስተጀርባ ያሉ ውስብስብ ነገሮችን መልስ ማፈላለግ መሆን የለበትም፡፡ በኢትዮጵያ ከዕድር ጀምሮ እስከ እኛ ኩባንያ የትም ቦታ በብዛት የማየው ነገር፣ አንድ እንቅፋት ሲያጋጥም እንዴትና ማን አመጣው እያሉ ምንም የማይጠቅም ጊዜ አባካኝ ልምምድ ነው፡፡ ማንም ያምጣው እንዴት እውነታው ችግሩ አፍጥጦ መጥቷል፡፡ መሪ እስከሆንኩ የመጀመርያው ሥራዬ በአስቸኳይ ችግሩን መፍታትና መረጋጋት መፍጠር ነው፡፡ ማን አመጣው? ለምን መጣ? የሚሉ ዝርዝሮችን ማወቅ ጠቃሚ ነው፡፡ ነገር ግን መቅደም ያለበት ችግሩን ማስቆም ነው፡፡ ችግሩን በመፍታት ፈንታ ምክንያትና ማማካኛ የምንፈልግ ከሆነ፣ መደበቂያ የምንፈልግ ባለሙያ እንጂ መሪ አይደለንም፡፡ ባጀት ስለሌለ ነው፣ እንትን ስለሌለ ነው እየተባለ ሰዎች ምክንያት ይደረድራሉ፡፡ የመሪዎች ሚና መሆን ያለበት ግን ለችግሩ መፍቻ ምን ዓይነት የመፍትሔ ዕርምጃ እንጠቀም መሆን አለበት፡፡ ከልደታ አያት ለመሄድ ስትነሳ በሰዓቱ መድረስ ካለብህ፣ የተሻለና በፍጥነት ሊያደርስህ በሚችለው መንገድ ትጠቀማለህ፡፡ በሰዓቱ ባትደርስ ግን መንገድ ተዘግቶብኝ፣ ትራፊክ በዝቶብኝ እያልክ ምክንያት መደርደር አያስፈልግም፡፡ መሄድና በሰዓቱ መድረስ እያለብህ መንገድ ስለተዘጋ ነው፣ ጥፋቱ የእኔ አይደለም አይባልም፡፡ በታክሲ፣ በባቡር፣ በመኪና፣ በቦሌ ወይም በመርካቶ አማራጭህን ወስነህ ካሰብክበት መድረስ እንጂ ምክንያት መፈለግ መፍትሔ አይሆንም፡፡

በአገራችን ያለውን ሁኔታ ብናየው ዋነኛ ችግራችን ለእንቅፋቶች መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ ምክንያት መደርደር ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በጀት አልተለቀቀም ሲባል ሁሉም ነገር ይቆማል፡፡ የሆነ ቦታ የሆነ ነገር ተፈጠረ ሲባል ብዙ ነገር አብሮ ይቆማል፡፡ በየዘርፉ ያሉ አመራሮች አማራጮችን ማማተር አለባቸው፡፡ በአገር ደረጃ ቀውስ ውስጥ የወደቅነው ምን ስለጎደለን ነው? ለተባለው ግን እንደ ፖለቲከኛ ሳይሆን እንደ አንድ ግለሰብ እኛ ሁሉም ነገር አለን ነው የምለው፡፡ የሃይማኖት መሪዎች አሉን፣ ወርቅ የሆነ እሴት አለን፣ ወርቅ የሆነ ታሪክ አለን፣ ከእነ አየር ንብረቱ ምርጥ የሆነች አገር አለችን፣ መሬት፣ ውኃው አለን፣ ሁሉም ነገር አለን፡፡ እኔ እንደምታዘበው ግን ቁጥር አንድ ችግራችን ያለንን ሀብት በሚገባ ማወቅ አልቻልንም፡፡ ሁሉም እያለን ነገር ግን እንዳለን ማወቅና ዕውቅና መስጠትም አልቻልንም፡፡ ሁለተኛው ችግራችን ያለንን ሀብት ጥቅም አለው ብሎ ከማመን ወደ ሌለን ነገር ማማተራችን ነው፡፡ ያለንን እሴት ስለማናይ፣ ብናይም ዕውቅና ስለማንሰጥ ይጠቅሙናል ብለን ለማሰብም እንቸገራለን፡፡ ሁሉም እያለን ሌላው ጋ ለችግሮቻችን መፍትሔ ለማፈላለግ እናማትራለን፡፡ መፍትሔ ለማፈላለግ የሚጠቅም ላናገኝ፣ ዓለምን እየዞርን ስንዳክር በመሀል ደግሞ እጃችን ያለው ሀብት ከእጃችን እየወጣ ከሁለቱም ሳንሆን እየዋለልን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከሌሎች አገሮች ምን እንማራለን?

አረጋ (ዶ/ር)፡- ከሌሎች ልምድ መማር አይከፋም፣ አንዳንዴ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ የእስያ ታይገሮች የሚባሉ አገሮች እንዴት አደጉ ብሎ መጠየቅ ጥሩ ነው፡፡ እኛ በምንገኝበት የዕድገት ደረጃ ላይ የነበሩ አገሮች ምን አድርገው ነው ከእኛ ወደ ተሻለ የዕድገት ደረጃ የተሻገሩት ብሎ መጠየቅ ጤናማ ነው፡፡ እየቀደሙን ያሉ አገሮች የተጠቀሙትን ልምድ መቅሰምና መተግበር ሊጠቅም ይችላል፡፡ የቀደሙን አገሮች ልምድ እኛ ካለንበት ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የማይያያዝ ከሆነ ግን ኩረጃው ንድፈ ሐሳባዊ ብቻ ነው፡፡ እዚህ ላይ የዓለም ልምዶችን ቀምሮና ከተጨባጭ ችግር ጋር አዛምዶ የመተግበር ጥበብ ይጠይቃል፡፡ የሌሎችን ችግር አፈታት መንገድ ማወቁ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነትም ሆነ በሌላ ታሪክ ያጋጠሙዋቸውን ችግሮች ከሥር ከመሠረቱ ለመፍታት የተጠቀሙትን መንገድ መማር ጠቃሚ ነው፡፡ ካንሰር ሆኖ ችግሩ ቁስሉን (ምንጩን) ሳታክም ማለፍ አደጋ እንዳለው ሁሉ፣ ችግርን ከሥረ መሠረት የሚቀርፍ መፍትሔ ከሌሎች ማፈላለግ ጠቃሚ ጎን አለው፡፡ አንዳንዴ አቅም ላይኖር ወይም ችግርን ከመሠረቱ ለመፍታት የሚያስችል ሁኔታ ላይመቻች ይችላል፡፡ ነገር ግን ካንሰሩን ለመንቀል ግብ ማስቀመጥና ደረጃ በደረጃ የሚተገበሩ የመፍትሔ ዕቅዶችን አስቀምጦ በቅደም ተከተል ችግሩን ለመቅረፍ መሥራት ነው የሚያስፈልገው፡፡

ከሌሎች የምንማረው እኛ ጋር ጎዶሎ ስላለን መሆኑን በቀዳሚነት ማወቅ አለብን፡፡ ከሌሎች ለመማር ደግሞ ትሁትና ሌሎችን አክባሪ መሆን አለብን፡፡ ለግለሰብም ቢሆን ይሠራል፡፡ የጎደለንና ከሌሎች አገሮች የምንፈልገው ነገር እስካለ ድረስ በጥበብና በብልጠት ነው መቅረብ ያለብን፡፡ ሌሎች እኛ መድረስ የምንመኘው ቦታ የደረሱት አንድ ነገር አድርገው መሆኑን መረዳት አለብን፡፡ እነሱ ከእኛ በምን ይበልጣሉ የምንል ከሆነ ምንም አንማርም፣ የምንመኘው ቦታም አንደርስም፡፡ የምንገኝበትን ተጨባጭ ቁመና ማወቅ ክብር መሸጥ አይደለም፡፡ ከሌሎች ዕውቀትም ሆነ ልምድ እስከፈለግን ድረስ ግን አቀራረባችን በጨዋነትና በአክብሮት መሆን ይኖርበታል፡፡ ከሌሎች መማሪያው ጥሩ መንገድ ይህ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ሌላው አገር የዕድገት ደረጃ ላይ የደረሰው በምትኃት ወይም በድንገት አለመሆኑን እንረዳ፡፡ ለድርጅትም ሆነ ለግለሰብ ይህ ይሠራል፡፡ ሌሎች ምርታማ የሆኑት በፈጣሪ ስጦታ ብቻ አለመሆኑን መገንዘብ አለብን፡፡ አዲስ ድርጅት ወይም ፋብሪካ ልከፍት ብፈልግ ወይም አዲስ ምርት ላስተዋውቅ ካሰብኩ፣ ሌሎች የሠሩትና ሥራና ምርት በማጤን ተጨማሪ እሴት ይዞ ለመምጣት መሞከር አለብኝ፡፡ ማዘመን ካለብኝ ወይም ለእኔ የሚሆነውን ነገር ለማወቅ ሌሎች የሠሩትን ሥራ ማወቅ ትልቅ ጥበብ ይጠይቃል፡፡ እነዚህን ነጥቦች ለማስረዳት ዩኒቲን ምሳሌ ብናደርገው አንተ ዩኒቲ የምትመጣው ለመማር፣ ዕውቀትና ዲግሪ ይዞ ለመውጣት ነው፡፡ እኔ የዩኒቲ አስተዳዳሪ በመሆኔ ባልመችህ ግን ግብህን መሳት የለብህም፡፡ ከእኔ ጋር በሰላም ተግባብቶ ግብን አሳክቶ ለመውጣት የሚያስችል ጥበብ መፍጠር ነው እንጂ ያለብህ፣ በመካከላችን ተጨማሪ ንትርክና ውዝግብ የሚከሰት ነገር ለመፍጠር መገፋፋት የለብህም፡፡ ይህ በፈለገው ቦታ የሚሠራ ሲሆን ከዚህ የተሻለ ምሳሌ መስጠት አልችልም፡፡

ችግር ዓይነት እንጂ የሚለያየው ችግር የሌለበት አገር እንደሌለ እንወቀው፡፡ ገነት መሬት ላይ የለችም፡፡ አሜሪካም ብንሄድ ችግር የሌለበት ቦታ የለም፡፡ አሜሪካ የጥቁሮች እኩልነት ጥያቄ ውዝግብ የሆነበት አገር ነው፡፡ ዛሬም በየጎዳናው የሚያድሩና የሚለምኑ ድሆች ያሉበት አገር ነው፡፡ የችግሩ ዓይነት እንጂ የሚለያየው የሞላለትና ፍፁም የተስተካከለ ቦታ የለም፡፡ ሁሉም አገር ሁሉም ተቋማት ችግር አለ፡፡ አሜሪካም ብንሄድ ስለፖለቲካ ተሳትፎ ብዙዎች ግድ የማይሰጣቸውና የተወሰኑ ሰዎች ብቻ ለብዙዎች እየተናገሩላቸው የሚኖሩበት አገር ነው፡፡ የተወሰኑ ሰዎች ብዙዎችን ፀጥ አድርገው የያዙበት አገር ነው፡፡ አሜሪካ ወይም አውሮፓ ስለሆኑ በሁሉ ነገር ንፁህ ናቸው ብሎ ማመን ትክክል አይሆንም፡፡ እነሱ የተማሩና ያወቁ ቢመስሉንም ችግር አፈታት ጥበባቸውን ግን በዩክሬን እያየነው ነው፡፡ አንድም ሰው ሳይገደል ችግሩን ማስቆም በቻሉ ነበር፡፡ የመጀመርያ ኃላፊነታቸው የሰው ልጅ እንዳይሞት ማድረግ በሆነ ነበር፡፡

የዩክሬንን ግጭት ብንወስደው የሩሲያው መሪ ቭላድሚር ፑቲን ከመጀመርያው፣ ወደ ጎረቤት አገር ዩክሬን ምዕራባዊያን ከገባችሁ ለደኅንነታችን እንሠጋለን በማለት ፍራቻቸውን ሲገልጹ ነበር፡፡ ታጠቁናላችሁና ጎረቤታችን መሣሪያ አታስገቡ ብለው ነበር፡፡ በተቃራኒው የቆሙት ግን ይህንን አልተቀበሉትም፡፡ ወደ ዩክሬን መሣሪያ ገባ ማለት ጦርነት ቀስቃሽ ሆነ፡፡ ሩሲያውያን ዋስትና በመስጠት ፈርሙልንና ጦራችንን እንመልሳለን ብለው ወደ ዩክሬን ድንበር ጦር አስጠጉ፡፡ የዩክሬኑ መሪ ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ግን አናደርግም አሉ፡፡ በዚህ የተነሳ ሩሲያውያን ወደ ዩክሬን ገቡ፡፡ የመጀመርያው የመሪነት ውድቀት በእኔ ግምት የመጣው የመጀመርያው ሰው ሕይወት የተቀጠፈ ቀን ነው፡፡ አንድም ሰው መሞት አልነበረበትም፡፡ መዓት ሰው ሞተ፡፡ የዩክሬን መሪ ግን ዕርዱኝና እዋጋለሁ እንዳለ ነው፡፡ የሚረዱት ሰዎች ግን እኛንም ስለሚጎዳን ታጥቀን ልንገባ አንችልም፣ መሣሪያ እንሰጥሃለን ራስህ ተጋፈጥ ነው ያሉት፡፡ የዩክሬን መሪ መጀመርያውኑ እንረዳሃለን የሚሉት ሰዎች ሊመጡለት እንደማይችሉ ማወቅ ነበረበት፡፡ ጦርነቱን ባላስጀምርና ሰው ባላስገድል ይሻላል ብሎ ማሰቡ አይቀርም፡፡ አሁን ከሩሲያውያን ጋር የሚደራደረው በምን ሁኔታ ነው? ሩሲያውያንን ውጡልኝ ቢል የሚወጡለት አይመስልም፡፡ የያዛችሁትን ያዙና እንደራደር ቢልም አጣብቂኝ ነው፡፡ በዚህ መሀል ሕዝቡ ምን ይላል? ወደ ጦርነት ሳንገባ አክስትና አጎት በጦርነቱ ሳይሞትብን ለምን የሰላም ስምምነት አልተፈራረምክም የሚል ቅሬታ መምጣቱ አይቀርም፡፡ የጦርነቱ የመጨረሻ ግብ ካልተሳካ ውጤቱ ሌላ ውዝግብና ግጭት ነው ይዞ የሚመጣው፡፡ ብዙ ጊዜ ከመጥፎ ድምዳሜ መነሳት ወይም በተዛባ ግምገማ ወደ ዕርምጃ መግባት ያልታሰበ ውጤት ነው የሚሰጠን፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን በኢትዮጵያ መጨካከን በዝቷል፣ ይህ ከምን የመጣ ነው?

አረጋ (ዶ/ር)፡- በዓለማችን በተለይም በአገራችን ጭካኔ እያየን ነው፡፡ መጨካከን በየቀኑ እያየን ነው፡፡ እንደ እኔ ያለው ሸምገል ያለ ሰው ደግሞ ያልነበረ ባህል ሲከሰት ከየት መጣ ማለቱ የሚጠበቅ ነው፡፡ ጭካኔው ሁሉም ሰው በየቤቱ የሚያወራውን ለምን ወደ እዚህ ደረጃ ደረስን የሚለው ነው፡፡ ነገር ግን በእኔ እምነት ጭካኔው የመጣው በመጀመርያ ሰው ክቡር ፍጡር መሆኑን ካለማመን የመነጨ ነው፡፡ ሰው ክቡር ፍጡር ነው፡፡ መኪና ወይም ብስክሌት፣ ሌላ ቁሳቁስ ሳይሆን፣ እኔ ራሴ ነኝ ክቡር የፈጣሪ ፍጡር ነኝ ብሎ ከማመን ይጀምራል፡፡ ሌላው የምዕራባዊያን በሽታ ቁሳዊነትም እየተጋባብን ነው፡፡ ከሌላው እኔ እበልጣለሁ፣ ከሌሎች የእኔ ይቀድማል የሚል የራስ ወዳድነት እምነት እያጠፋን ነው፡፡ ሌላው ይኑር አይኑር የራሱ ጉዳይ የሚለው ነገር መሠረታዊ ተፈጥሯችንን ወይም የሰዎች ማኅበራዊ ፍጡርነትን ይቃረናል፡፡ አንድ ሚሊዮን ሕዝብ ባለው ከተማ ሁሉም ሰው አልቆ አንድ ግለሰብ ብቻህን ኑር ቢባል አይችልም፡፡ ስለዚህ ሰው በመኖሩ ምንም ባያደርግልንም በአካባቢያችን በመኖሩ ብቻ ተጠቅመናል ብሎ ማሰብ ጠቃሚ ነው፡፡ ሰዎች በአካባቢያችን እንዲኖሩ መጣር እንጂ ሰዎች ከእኛ እንዲሸሹ መጣር የለብንም፡፡ ጭካኔ የሚመጣው እኔ እበልጣለሁ ከሚል መንፈስ ነው፡፡ እኔ ብቻ ልኑር ከማለት ነው፡፡ አንተ ባትኖር እኔ አድጋለሁ ወይም ሀብታም እሆናለሁ በሚል የምቀኝነት መንፈስ መጨካከን ይመጣል፡፡ ሌላው ደግሞ ትልቁ ችግር ጭካኔና ክፉ ድርጊት መለመዱን ነው፡፡ ጭካኔ፣ ሞትና ግድያ ይለመዳል፡፡ በፍፁም ተቀባይነት የለውም ወይም ስህተት ነው ብለን ከላይ እስከ ታች ካልጮህን በስተቀር ጭካኔ ልማድ ይሆናል፡፡ ሁላችንም ካልጮህንና መቆም አለበት ካላልን ነገሩ እየተደጋገመ ባህል ይሆናል፡፡ የጭካኔ ድርጊትን ወደኋላም ሆነ ወደፊት በመሄድ ፍትሐዊ አድርጎ ለማቅረብ መሞከር የለብንም፡፡ ጭካኔ ከተፈጸመ ምንም ዓይነት ምክንያት ሊቀርብ አይችልም፡፡ በዚህ ረገድ ላላ ብለናል ብዬ አስባለሁ፡፡ አንድ ወይም ሁለት ሰው ሲገደል ምንም ካልመሰለን እየደነዘዝን ነው ማለት ነው፡፡       

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የሥራ አጦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመርና መከማቸት ለትግራይ ክልል ሰላምና ደኅንነት ትልቅ ሥጋት ይፈጥራል›› አትክልቲ ኪሮስ (ዶ/ር)፣ የፋይናንስ ባለሙያ

በሰሜን ኢትዮጵያ የተደረገው ጦርነት ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል፡፡ ለማኅበራዊ ቀውስ ምክንያትም ሆኗል፡፡ በጦርነቱ ሕይወታቸውን ያጡ፣ ለአካል ጉዳት የተዳረጉና ሀብት ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ...

‹‹በሌሎች ክልሎች ያለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት ከትግራይ አንፃር አነስተኛ ነው ብዬ ለመግለጽ አልችልም›› ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር)፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይና የሰብዓዊ ዕርዳታ...

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያቀርቡ ዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶችና ሠራተኞች በአገሪቱ በሚከሰቱ የበሽታ ወረርሽኞች፣ ድርቅ፣ ጎርፍና ጦርነት ምክንያት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በእጅጉ ተፈትነው ነበር። በኮቪድ-19...

‹‹የውጭ ዜጎች ንብረት እንዲያፈሩ መፍቀድ ከፍተኛ ጥቅም አለው›› ቆስጠንጢኖስ በርሃ (ዶ/ር)፣ የኢኮኖሚ ባለሙያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተከታታይ ውይይት እያደረጉ ነው፡፡ ከእነዚህ የውይይት መድረኮች መካከል ከከፍተኛ የግብር ከፋዮች ወይም ታማኝ ግብር ከፋዮች...