Saturday, December 9, 2023

ኢትዮጵያን ከገባችበት ቀውስ ለማውጣት ምን ይደረግ?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 25 ቀን 1991 የአውሮፓውያኑ ገና በሚከበርበት ዕለት፣ ሚካኤል ጎርባቾቭ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው ከሶቭዬት ኅብረት ፕሬዚዳንትነት መልቀቃቸውን በይፋ አወጁ፡፡ ይህ አጋጣሚ የታላቂቱ አገር ሶቭዬት ኅብረት መፈራረስን አስከተለ፡፡ በዚህም ወደ 15 አገሮች ተከፋፈለች፡፡ በቅርቡ የተለቀቀው ባለሁለት ክፍል የዶቼ ቬሌ “The red Army” ወይም ‹‹ቀዩ ጦር›› የተባለ ዶክመንተሪ እንደተረከው፣ በሶቪዬት ኅብረት መፈራረስ የተነሳ 25 ሚሊዮን የሩሲያ ተወላጆች (የሩሲያ ቋንቋ ተናጋሪዎች) በወጡበት የሌላ አገር ዜጋ ተብለው ቀሩ፡፡

ዛሬ በዩክሬን የተፈጠረውና ዓለምን እያወዛገበ ያለው ግጭት የሶቭየት ኅብረት መፈራረስ ውጤት ነው ይባላል፡፡ ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ጦር የተማዘዘችው በዩክሬን ባሉ የሩሲያ ቋንቋ ተናጋሪዎች ላይ በደል ይፈጸማል በሚል መሆኑን ብዙዎች ያወሱታል፡፡ ሶቭዬት ኅብረት ስትፈራርስና ብዙ አገሮች ነፃ ሲወጡ ሰላምና ነፃነት በተሻለ ሁኔታ እናገኛለን የሚል ምኞት ቢኖራቸውም፣ ብዙዎቹ የተመኙትን ማግኘታቸው ግን ያጠራጥራል፡፡ በአዋጅ የፈረሱት የሶቭዬት አካል የነበሩ አገሮች ዛሬም ቢሆን የኢኮኖሚ ዕድገትና መረጋጋት ለመፍጠር እንደሚቸገሩ ነው የዶቼ ቬሌ ‹‹ቀዩ ጦር›› ዶክመንተሪ ከሊቱኒያ እስከ ዩክሬንና ሩሲያ እያዟዟረ ሊያሳይ የሚሞክረው፡፡

አያድርስና ታላቋ ኢትዮጵያ የሆነ ቀን ፈረሰች ቢባልስ? እንደ ሶቪዬት ኅብረት ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ1922 የተፈጠረች አገር ባለመሆኗ፣ በአዋጅ አትፈርስም ቢባልም ነገር ግን ጨርሶ አይፈጠርም ብሎ ማሰብ እንደማይቻል ብዙዎች ሥጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ከምትገኝበት ሁኔታ አኳያ አይመጣም ብሎ ነገሮችን ከመዝጋት፣ የከፋ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል ብሎ ማሰብም ተገቢ መሆኑን ነው የሚያሳስቡት፡፡

ይህን ሥጋት ከሚጋሩ ወገኖች አንዱ የሆኑት የሕግ ባለሙያው አቶ መንግሥቱ አሰፋ፣ ‹‹የሶቪዬት ኅብረት ባለሥልጣናት በቅንነት ለለውጥ ብለው ሊሆን ይችላል አገር ያፈረሱት፡፡ እኛ አገር ግን ሆን ብሎ አገር የማፍረስ ዝንባሌ ይታያል፤›› በማለት ነው የኢትዮጵያ አካሄድ ከሶቭዬት ኅብረትም የባሰ መሆኑን የሚያስረዱት፡፡

‹‹ሚካኤል ጎርባቾቭ ፕሮስትሬይካ ባለው ለውጥ ሕዝቡን ከጦር ሠራዊቱና ከስለላ መዋቅሩ ጭፍለቃ ለማውጣት ጣረ፡፡ የለውጡ ዓላማ ዴሞክራሲን ለማምጣት ስለነበር አገር ቢያፈርስም እኔ ለእሱ ይቅርታ አለኝ፡፡ እኛ አገር ግን ሆን ብሎ የማይነካካ የአገር ምሰሶ ሁሉ አየነቀነቀ አገር ለማፍረስ ሙከራ ይደረጋል፤›› በማለት የሚናገሩት የሕግ ባለሙያው አቶ መንግሥቱ፣ አገሪቱ ቀስ በቀስ እንዳትበተን እንደሚፈሩ ሐሳባቸውን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የገጠማት ፖለቲካዊ ቀውስ ብዙኃኑን ዜጋ ማሥጋቱ አልቀረም፡፡ በሕዝቡ የረዥም ዘመን ተቻችሎና ተፈቃቅሮ የመኖር ጠንካራ ብሂል እንጂ፣ አገሪቱ አንድነቷን የሚፈታተን ከባድ ችግር ከገጠማት መከራረሙ ይነገራል፡፡ ከሰሞኑ መልኩን ቀይሮ ወደ ሃይማኖቶች የዞረው ግጭትና አለመረጋጋት ደግሞ አዲስ ሥጋት መፍጠሩ ይነገራል፡፡ በዚሁ በወቅታዊው አሳሳቢ ጉዳይ ላይ ሐሳባቸውን ለፋና ኤፍኤም ሬዲዮ ያጋሩ ምሁራንም አገሪቱ ያለችበትን አሳሳቢ ሁኔታ ለማሳየት ሞክረዋል፡፡

የሕግ ባለሙያው አቶ አንዷለም በዕውቀቱ፣ ‹‹መስጊድና ቤተ ክርስቲያን መቃጠሉ አዲስ ላይሆን ይችላል፡፡ አሁን የገጠመን ሁኔታ ግን ከውስጥም ከውጭም እየተደገፉ በተደራጀ ሁኔታ አገር የማፍረስ ሙከራ ነው፡፡ አገሪቱ እከሌና እከሌ ብለን በስም ልንጠቅሳቸው የምንችላቸው ጠላቶች አሏት፤›› በማለት ወቅታዊው ምስቅልቅል ምን ዓይነት ገጽታ እንዳለው ለማስቀመጥ ሞክረዋል፡፡

በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ምሁር የሆኑት አቶ መሐመድ ሰይድ በበኩላቸው፣ ‹‹አንድ ቦታ ቤተ ክርስቲያን ወይም መስጊድ ተቃጥሏልና ሌላ ቦታ ላቃጥል ወይም ልግደል ማለት በፍፁም መወገዝ ያለበት ነው፡፡ ጥቃት አድራሾችን ለሕግ በማቅረብ፣ ለተጎጂዎች ካሳ በመክፈልና የተጎዳውን በመጠገን ነው መፍትሔ መፍጠር ያለብን፤›› በማለት ቀውሱ እንዳይባባስ መደረግ የሚኖርበትን ነጥብ ያነሳሉ፡፡

የሥነ ማኅበረሰብ ሳይንስ ምሁሩ አቶ ኢስማኤል ነጋሽ በበኩላቸው፣ ‹‹እንደ ከረሩ የፖለቲካ ዕሳቤዎችና መጠላለፎች ሳይሆን፣ ማኅበረሰቡ ካለው ተሳስቦ የመኖር ባህልና በሃይማኖቶቻችን በጎ የመቻቻል እሴት የተነሳ እስካሁን ዘልቀናል፡፡ ብዙ የፖለቲካ መጠላለፎች ቢኖሩም ኢትዮጵያ ግን ሴራና ተንኮል የሚያከሽፉ ሕዝቦች አገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ለቆየው አብሮነትና አንድነት ሃይማኖቶች ያደረጉት አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም፤›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡ አሁን ግን እነዚህ የአገር ባለውለታ የሆኑ የእምነት ተቋማት ጭምር በፖለቲካው ቀውስ እየተናጡ መሆኑን ነው ባለሙያው የሚያመለክቱት፡፡

ኢትዮጵያ በመረጋጋት ከቀውስ ውስጥ መውጣት ካልቻለች የከፋ አደጋ ይገጥማታል የሚለው ሥጋት የብዙዎች ነው፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ የሕግና የሥነ ማኅበረሰብ ምሁራን ብቻ ሳይሆን፣ የፖለቲካ ሳይንስ አዋቂዎችንም እንደሚያሳስብ ይናገራሉ፡፡ አገሪቱ ከቀውስ ልትወጣበት ትችላለች የሚሉትን ሐሳብም በማቅረብ ላይ ናቸው፡፡

በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር የሆኑት ንጉሥ  በላይ (ዶ/ር)፣ ‹‹አሁን ከገባንበት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለመውጣት በመጀመርያ ወደ ቀውስ የከተቱንን የችግር ምንጮች መለየት ይኖርብናል፤›› ይላሉ፡፡ የቀውሱን መፍትሔ ለማወቅ የቀውሱን ምንጭ ማወቅ እንደሚጠቅም የሚጠቅሱት ንጉሥ (ዶ/ር)፣ መፍትሔ ነው ከሚሉት አማራጭ ጋር በማከል ለአገር ይበጃል የሚሉትን ሐሳብ አጋርተዋል፡፡

‹‹በቅርብ ጊዜያት የሃይማኖት ይዘት እየያዙ የመጡት የአገራችን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋቶች ምንጫቸው ብዙ ነው፡፡ አንዱና በመንግሥትም ሆነ በምሁራን የማይተኮርበት ጤናማ ያልሆነ የሕዝብ ቁጥር ዕድገት ነው፡፡ ኢኮኖሚያችን መሸከም ከሚችለው በላይ የሆነ የሕዝብ ቁጥር ዕድገት አለ፡፡ ሕዝቡ በጨመረ ቁጥር የምርት አቅርቦት፣ መሠረታዊ አገልግሎትና የሥራ አቅርቦት ሁሉ አብሮ ካላደገ በአገር ላይ አደጋ ነው የሚደቅነው፡፡ ብዙ ወጣት ሥራ ጠባቂ በመሆኑ ለጥፋት ሊያሰማራው ለፈለገም ተጋላጭ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ጤናማ ያልሆነ የሕዝብ ቁጥር ዕድገት በፈጠረው ችግር ለውጭ ዕርዳታ ጠባቂነት ተዳርገናል፤›› በማለት የሚናገሩት ንጉሥ (ዶ/ር)፣ ይህ ጉዳይ ብዙ ልብ የማይባል መሠረታዊ የቀውስ ምንጭ መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡

‹‹አስደንጋጭና በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የኑሮ ውድነት ይታያል፡፡ የዋጋ ንረቱ ዜጎች መሠረታዊ ሕይወት ለመምራት የሚያቅታቸው ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ በዚህ የተነሳ ብዙዎች በተስፋ መቁረጥ ውስጥ በመውደቅ ለግጭትና ለቀውስ ተጋላጭ እየሆኑ ይገኛሉ፤›› ሲሉ የሚገልጹት ንጉሥ (ዶ/ር)፣ የአገሪቱ ቀውስ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት እንዳለውም ያስረዳሉ፡፡

ምሁሩ የአገሪቱን የቀውስ ምንጮች መዘርዘራቸውን ሲቀጥሉ ፅንፈኝነት ሦስተኛው መሠረታዊ ችግር መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ ‹‹በብሔርና በሃይማኖት ፅንፍ የወጣ አመለካከት በዝቷል፡፡ የፖለቲካ አመለካከት ልዩነትን ማቻቻል አለመቻል የፅንፈኝነት መሠረት ሆኗል፡፡ በሠለጠነ ሁኔታና በምክንያታዊነት ፖለቲካን ማራመድ አለመቻል ፅንፈኝነትና መገፋፋትን እየወለደ የቀውስ ምንጭ ሆኖብናል፤›› በማለት በዚህ በኩል ያላቸውን ዕይታ ያብራራሉ፡፡

በሌላ በኩል፣ ‹‹አለመተማመንና መጠራጠር እንደ አገር ችግር ውስጥ ከቶናል፤›› በማለት በአራተኝነት ያስቀመጡታል፡፡ ‹‹አንዱ ብሔር ሌላውን ብሔር፣ አንዱ ሃይማኖት ሌላውን ይጠራጠራል፡፡ በመካከል መፈራራትና ሥጋት እየተፈጠረ ይገኛል፡፡ በክልሎች መካከል እርስ በርስ መጠራጠር አለ፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል መጠራጠርና ሥጋት አለ፡፡ በገዥውም ሆነ በተፎካካሪ ፓርቲዎች ውስጥ በአመራሮች መካከል መጠራጠር እንዳለ እናያለን፡፡ ይህ ሁሉ አለመተማመንና መጠራጠር የፈጠረው ችግር ነው፡፡ በኢኮኖሚውና በፖለቲካው ላይ መሪ በሚባሉ ኃይሎች ውስጥ መከፋፈልና ግጭቶች ሲፈጥር እናስተውላለን፤›› ሲሉ የሚያስረዱት ንጉሥ (ዶ/ር)፣ ይህ ሁኔታ ደግሞ ወደ ሕዝቡ እየተሠራጨ አገር አቀፍ ቀውስ እንደሚወልድ ገልጸዋል፡፡

ባለፉት 30 ዓመታት በተለይ ከ1984 ዓ.ም. ወዲህ እነዚህ ችግሮች በሒደት እያደጉ መምጣታቸውን በመግለጽ፣ ‹‹በታዳጊ አገሮች ቀውስ በመነገድ ለማትረፍ በሚፈልጉ ዓለም አቀፍ ተዋንያን እንዲሁም በውጭ ጠላቶች ዕገዛ ችግሮቹ የበለጠ እንዲባባሱ ይደረጋል፡፡ ኢትዮጵያ ሁልጊዜ እንዳትረጋጋና ከግጭት እንዳትወጣ የሚፈልጉ ኃይሎች የራሳቸውን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካ ጥቅም ለማስጠበቅ ሲሉ ቀውስን የማባባስ ሚና ይጫወታሉ፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ችግር ከሚፈጥሩ ኃይሎች ጀርባ ከቀውሱ ለማትረፍ ያሰፈሰፉ ኃይሎች መኖራቸው ሊታወቅ ይገባል፤›› ብለዋል ‹‹የውጭ ግጭት አትራፊዎች በደንብ እየተጠቀሙብን ይገኛል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

ከቀውሱ ለመውጣት ምን መደረግ አለበት? ለሚለው መሠረታዊ ጥያቄም ዝርዝር ማብራሪያ የሰጡት ንጉሥ (ዶ/ር)፣ ብሔራዊ ምክክር የመፍትሔው አንዱ አካል መሆን እንደሚችል ያሰምሩበታል፡፡ ነገር ግን ብሔራዊ ምክክር አንዱ የመፍትሔ አማራጭ እንጂ ብቸኛው አለመሆኑን፣ እንዲሁም ከብሔራዊ ምክክር በፊት ኅብረተሰቡ በሚገባ ዝግጅት ማድረግ እንዳለበት ያስረዳሉ፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት ከሁሉ በፊት የኢትዮጵያ ሕዝብ ከስሜታዊነት መውጣትና መስከን አለበት፡፡ ግራና ቀኝ፣ እንዲሁም ከበስተጀርባ ያለውን ሁኔታ ማየት አለብን፡፡ በብሔርም ሆነ በእምነት ስሜታዊ ከሆኑ እንቅስቃሴዎች በመቆጠብ ከደመ ነፍሳዊ ጉዞ መውጣት አለብን፡፡ ሰከን ካልን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ከምንፈጥረው ጥፋት እንቆጠባለን፡፡ አክቲቪስቱ፣ የሃይማኖት መሪው፣ ፖለቲከኛው፣ ምሁሩ፣ ያልተማረውና ሁሉም ወገን፣ በተለይ ወጣቱ በአሁኑ ወቅት መስከንና መረጋጋት በእጅጉ ያስፈልገናል፤›› በማለት የተናገሩት የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲው ምሁር ንጉሥ (ዶ/ር)፣ ከሁሉ ነገር በፊት መቅደም አለበት የሚሉት ለመደማመጥና ለመነጋገር የሚረዳ ስክነት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ አሁን በብሔር ፖለቲካ ውጥረት ውስጥ ገብታለች የሚለው የብዙዎች እምነት ነው፡፡ በክልሎች መካከል የድንበር ውዝግብ ደጋግሞ ይከሰታል፡፡ ብሔር ተኮር ጥቃት በየአቅጣጫው ይፈጸማል፡፡ በሁሉም የአገሪቱ ክፍል በነፃነት ተንቀሳቅሶ፣ ሠርቶና ንብረት አፍርቶ መኖር ፈተና ሆኗል፡፡ አሁን አሁን ደግሞ ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች ማቆጥቆጥ ጀምረዋል፡፡ ይህን ሁሉ ማሳያ የሚያደርጉ አንዳንድ ምሁራን ቀውሱ እየሰፋ ሄዶ አገሪቱን ለመፍረስ ሊዳርግ ይችላል የሚል ከባድ ሥጋት ያነሳሉ፡፡

አንዳንድ ወገኖች በበኩላቸው ግን ከመፈራረስ ወይም መበታተን እኩል፣ በቀውስ አዙሪት ውስጥ መዳከርም ሊፈጠር የሚችለውን አደጋ በመጠቆም ላይ ናቸው፡፡ በሊባኖስ የተፈጠረውን ሁኔታ ምሳሌ በማድረግ የኢትዮጵያ ችግርም የቀውስ አዙሪት ሊሆን እንደሚችል የሚጠቁም ጽሑፍ በማኅበራዊ የትስስር ገጻቸው ላይ ያስነበቡት ዓብይ ሰይድ፣ በሊባኖስ ሃይማኖት ተኮር ፖለቲካ ፈጥሮት የቆየውን ችግር ማነፃፀሪያ አድርገው አቅርበዋል፡፡

ሊባኖስ የመካከለኛው ምሥራው ስዊዘርላንድ፣ ዋና ከተማዋ ቤሩት ደግሞ ትንሿ ፓሪስ እየተባለች እስከ እ.ኤ.አ. 1975 ስትሞካሽ እንደነበር ጸሐፊው ያስታውሳሉ፡፡ በ1975 በአንድ አውቶብስ ላይ በተፈጸመ ጥቃት ወደ እርስ በርስ ጦርነት ገባች፡፡ ሊባኖሳዊያን ክርስቲያን፣ ዱርዝ፣ ሺአ፣ ሱኒ፣ ወዘተ እየተባባሉ በሃይማኖት ፖለቲካ ተገዳደሉ፡፡ እስራኤል፣ ሶሪያ፣ አሜሪካ፣ ፈረንሣይ፣ ኢራንና ሌሎች የውጭ ኃይሎች ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ በቀውሱ ላይ ቤንዚን እየረጩ የበለጠ አባሏቸው በማለት ዓብይ ሰይድ ጽሑፋቸውን ይቀጥላሉ፡፡

ሊባኖሳውያን ከብዙ መጨፋጨፍ በኋላ 150 ሺሕ ዜጎች አጥተውና ከአንድ ሚሊዮን በላይ ከአገር ተሰደው እ.ኤ.አ. በ1990 ለመታረቅ በቁ፡፡ ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ የሥልጣን ክፍፍል በማድረግ አዲስ ፖለቲካ ቀረፁ፡፡ ሙስሊሞችና ክርስቲኖች 50 በመቶ እኩል የፓርላማ ወንበርን ተከፋፈሉ፡፡ ፕሬዚዳንቱ ክርስቲያን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደግሞ ሙስሊም እንዲሆን ቃል ተገባቡ፡፡ አዲሱ ፖለቲካ ዘላቂ መፍትሔ ያመጣ መሰለ፡፡ በአገሪቱ ለተወሰኑ ዓመታትም ዕድገት ተመዘገበ፡፡ ሃይማኖት ላይ ያጠነጠነው ፖለቲካ ግን በሒደት ሌላ ዓይነት ቀውስ ወለደ ይላሉ ጸሐፊው ሲቀጥሉ፡፡

በሊባኖስ የሃይማኖትና የፖለቲካ ክፍፍል ሰፋ፣ ሙስናና ምዝበራ በእጅጉ ተስፋፋ የሚሉት ዓብይ፣ እ.ኤ.አ. በ2018 እና በ2019 ብቻ ከአገሪቱ 20 ቢሊዮን ዶላር ወደ ውጭ መውጣቱን ያስረዳሉ፡፡ በ2020 በቤሩት ወደብ በደረሰ ፍንዳታ 200 ሰዎች ሞተው 300 ሺሕ ዜጎች ቤት አልባ ሆኑ፡፡ ፍንዳታው ከ15 ቢሊዮን ዶላር በላይ ኪሳራ አስከተለ፡፡ የሊባኖስ ፖለቲከኞች ንቅዘትና ፖለቲካዊ ልዩነት አገሪቱን ከዚህም በላይ መስዋዕት አስከፍሏታል ይላሉ ጸሐፊው ሲቀጥሉ፡፡

ዛሬ በሊባኖስ የዋጋ ግሽበት 1000 ፐርሰንት አሻቅቧል፡፡ ወደ 100 የአሜሪካን ዶላር ለመመንዘር 900 ሺሕ የሊባኖስ ሊሬ ያስፈልጋል፡፡ ጥቁር ገበያ በሁሉም ዘርፍ ደርቷል፡፡ እንደ ነዳጅና መድኃኒት ያሉ የድጎማ ሸቀጦች በኮንትሮባንድ ወደ ጎረቤት አገር ይሸጣሉ፡፡ የአገሪቱ የውጪ ብድር ዕዳም 95 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል በማለት የሚዘረዝረው የዓብይ ጽሑፍ፣ የሊባኖስ ውድቀት ልክ እንደ መስተዋት የኢትዮጵያን ቀውስ የሚያሳይ ነው ይለዋል፡፡ ሊባኖስ አልተበታተነችም፣ ነገር ግን በፖለቲከኞቿ አለመግባባትና ንቅዘት ሳቢያ ከመፍረስ ያልተሻለ ሁኔታ ላይ ትገኛለች ይላል፡፡ ፖለቲከኞቿ የሃይማኖትና የፖለቲካ ቁርሾ በመፍጠር ከግጭቱ ለማትረፍ እንጂ፣ ዘለቄታዊ መፍትሔ አይፈልጉም በማለትም ኢትዮጵያ ከዚህ መሰሉ የቀውስ አዙሪት እንድትማር ያሳስባል ጽሑፉ፡፡

ከሌሎች አገሮች ውድቀት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ከራሷ ያለፈ ታሪክ መማር እንዳለባት አስፈላጊ መሆኑን ብዙዎች ያሳስባሉ፡፡ ሐሙስ ሚያዝያ 27 ቀን 2014 ዓ.ም. በተከበረው 81ኛው የአርበኞች ድል በዓል ዕለት የተላለፉ መልዕክቶች ይህንኑ የሚያስተጋቡ ነበሩ፡፡

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ‹‹ዘር፣ ሃይማኖትና ቀለምን ለሌላ ፍላጎት ሳናውል ከቁጥር ሳንጎድል መኖር እንችላለን፡፡ በአባቶቻችን ደምና አጥንት ተጠብቃ የኖረች አገራችንን ማስቀጠልም እንችላለን፤›› ሲሉ ነበር በዕለቱ የተናገሩት፡፡

የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር የበላይ ጠባቂ ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን በበኩላቸው፣ ‹‹አባቶቻችን የፈረስ ሽንትና የጠላት መርዝ ጋዝ እየጠጡ በዱር በገደሉ ለአምስት ዓመታት ሞተው ያቆዩዋትን ይህችን አገር፣ ነፃነቷና አንድነቷ በቀላል ዋጋ እንዳልተገኘ እናስታውስ፤›› በማለት ነበር ጠንከር ያለ ማሳሰቢያ ያስተላለፉት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -