የፌደራል ፍርድ ቤቶች በጎ የተገልጋይ ምላሽ ካገኙባቸው አገልግሎቶች በሻገር ዝቅተኛ ዕርካታ የሚስተዋልባቸውን ተከላካይ ጠበቃና አስተርጓሚዎችን በአፋጣኝ የመመደብ አገልግሎቶች ላይ ሊሠሩ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፌደራል ፍርድ ቤት ተገልጋዮች ላይ አገልግሎት ዕርካታ ላይ በገለልተኛ አማካሪ ድርጀት ያደረገውን የዳሰሳ ጥናት ሚያዚያ 26 ቀን 2014 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል፡፡
በዳሰሳ ጥናቱ 39,673 ተጠቃሚዎች በናሙና ዘዴ ተለይተው ከጥቅምት 15 እስከ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ውስጥ ባሉት ሁለት ሳምንታት በመጠይቅና 1,139 በቃለ መጠይቅ መረጃ እንዲሰጡ ተደርጓል ተብሏል፡፡
የዳሰሳ ጥናቱ በአምስት ዋና ምድቦች ላይ ትኩረት ማድረጉ የተገለጸ ሲሆን፣ እነዚህም ሥነ ምግባርና ገለልተኝነት፣ ተደራሽነትና ግልፅነት፣ የአገልግሎት ውጤታማነት ቅልጥፍናና ተገማችነት፣ ያለፉት ሦስት ዓመታት የፍርድ ቤቶች አፈፃፀም፣ እንዲሁም ተገልጋዮች ፍርድ ቤት የመጡበት ጉዳይ የመሳካት ሁኔታ እንደነበሩ ተገልጿል፡፡
ጥናቱ Customer Satisfaction Score (CSAT) በተሰኘ የውጤት መለኪያ የተነተነ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ በተሰበሰበው መረጃ መሠረት ከ75 በመቶና በላይ የተመዘገበባቸው አገልግሎቶች ዕርካታ የሚለውን ውጤት ሲያመላክቱ፣ በአንፃሩ ከዚህ አኃዝ በታች ውጤት የተመዘገበባቸው አግልግሎቶች ዝቅተኛ ዕርካታ የተገኘባቸው በሚል መደብ ውስጥ እንሚጠቃለሉ የጥናቱን ውጤት ያቀረቡት የፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተስፋዬ ንዋይ አስረድተዋል፡፡
ተጋላጭ ለሆኑ የኅብረተሰብ አካላት ተደራሽነት በሚለው ነጥብ ላይ እንዲሁም ነፃ የሕግ አገልግሎትና ተከላካይ ጠበቃ ማቅረብ አንዲሁም የፍርድ ቤት አስተርጓሚዎችን በአፋጣኝ መመደብ ላይ እስከ 37 በመቶ የደረሰ ዝቅተኛ የዕርካታ ውጤት እንደተገኝ የተደረገው የዳሰሳ ጥናት አሳይቷል፡፡
ተገልጋዮችን በእኩልነት ማስተናገድ እንዲሁም ዳኛ ወይም ችሎቱ ጉዳይን በትህትና በሚዛናዊነት የመስማት ደረጃ የሚሉት ሥነ ምግባርና ገለልተኝነት የትኩረት ነጥቦች ላይ የተገልጋዮች ዕርካታ ከ75 በመቶ በላይ ድምር ውጤት እንደተገኘ ጥናቱ አረጋግጧል፡፡
ወደ ችሎትና ፍርድ ቤቶች ተገልጋዮች በቀላሉ መግባት መቻላቸው እንዲሁም የፍርድ ቤቶች የደኅንነት ደረጃን በተመለከተ የተመዘገበው ድምር ውጤት ከ87 በመቶ እንደሆነ የተመላከተ ሲሆን፣ በመረጃ ማዕከል የሚቀርቡ መረጃዎች በቂነታቸው እንዲሁ 76 ከመቶ የዕርካታ ደረጃ አግኝቷል፡፡
በሌላ በኩል የአገልግሎት ውጤታማነት፣ ቅልጥፍና፣ ማስረጃና ክርክሮችን መርምሮ ውሳኔ የመስጠት ሒደት፣ ማስረጃና ክርክርን የሚመጥን ውሳኔ ማግኘት እንዲሁም የፍታብሔር ጉዳዮችን በዕርቅና ድርድር እንዲልቅ ዕድል የመስጠት ሁኔታ በተገልጋዮች የተሰጠው የዕርካታ ደረጃ ከ75 በመቶ በታች እንደሆነ ጥናቱ አመላክቷል፡፡
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ እንዳስታወቁት፣ የፌደራል ፍርድ ቤቶች ተገልጋዮች በዳኝነት አገልግሎቱ ላይ የላቸውን የዕርካታ ደረጃ ለማወቅ የተካሄደው ጥናት የራሱ ልዩ ባህሪ አለው፡፡ አንደኛ ጥናቱ ነፃ በሆነ ገለልተኛ አማካሪ የተካሄደ መሆኑ የጥናቱን ደረጃ ተዓሚነት ከፍ የሚያደርግ ሲሆን፣ በሌላ በኩል በጥናቱ ላይ የተገኙት ሐሳቦች በአንድ በኩል ራሱ ፍርድ ቤቱ በተለያየ መልኩ ካከናወናቸው መለስተኛ ጥናቶችና ግብረ መልሶች ጋር ተቀራራቢ ውጤቶችን ያሳየ መሆኑ ነው፡፡
‹‹ከዚህ በኋላ የጥናቱን ውጤት ግብረ መልስ እንደ ወሳኝ ግብዓት በመውሰድ በቀጣይ የሪፎርም ሥራዎቻችን ላይ እናውላቸዋለን፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቷ፣ ይህም መሠረታዊ የሆነ የመዋቅር ለውጥና ችሎታ ያለው የሰው ኃይል ለማደራጀት ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑትና ጥናቱን ያቀረቡት አቶ ተስፋዬ ንዋይ እንዳስረዱት፣ ዝቅተኛ ዕርካታ ከተገኘባቸው ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ማለትም አስተርጓሚ መመደብ፣ ጉዳዮችን በስምምነት እንዲያልቁ ማድረግ ላይ በመዋቅር የሚመለሱት እንደጠበቁ ሆነው በየፍርድ ቤቱ ግን እነዚህን ችግሮች ወይም የፍርድ ቤቶችን የተገልጋይነት ዕርካታ ከፍ ማደረግ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
በሒደት ላይ የሚገኙ ደንቦች በተለይም የፍርድ ቤት አስተዳደር ሠራተኞች ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደተላከ ያስታወቁት አቶ ተስፋዬ፣ ከጉዳዩ አስቸኳይነትና አንገብጋቢነት አንፃር፣ በተከታታይ ከአራት ሺሕ በላይ ሠራተኞች የሚያነሱት ስለሆነ ቅድሚያ ሰጥቶ ይህንን ደንብ እንዲያፀድቅ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡