በጦርነቱ ምክንያት አገልግሎት ለአንድ ዓመት ለተቋረጠባት ላሊበላ ከተማ ከሌላ የኤሌክትሪክ መስመር ጥቅም ላይ ሊውል መሆኑን፣ የአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።
በላሊበላ ከተማ ከሐምሌ ወር 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የተቋረጠ ሲሆን፣ ከተማዋ እስካሁንም አገልግሎት እያገኘች አለመሆኑን የአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰለሞን ጣሰው ለሪፖርተር ገልጸዋል።
ለከተማዋ አገልግሎት የሚሰጠው የኤሌክትሪክ መስመር መነሻውን አላማጣ አድርጎ ወደ ተከዜ የሚደርስ በመሆኑና በእነዚህ አካባቢዎች ያለውን የመስመር ችግር መፍታት ባለመቻሉ፣ አገልግሎቱ ተቋርጦ መቆየቱን አክለዋል።
ላለፉት አሥር ወራት ገደማ ተቋርጦ የቆየውን አገልግሎት በሌላ አማራጭ ለመተካት ጄኔሬተሮችን ለመጠቀም ቢሞከርም፣ በነዳጅ እጥረት ምክንያት መቀጠል አለመቻሉን አቶ ሰለሞን ተናግረዋል። ጄኔሬተር ለመጠቀም ተሞክሮም ነዳጅ ማግኘት የተቻለው ከአንድ ወር ላልበለጠ ጊዜ ብቻ መሆኑን አክለዋል።
የላሊበላ ከተማ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ማዕከል ሥራ አስኪያጅ አቶ እንዳልኬ ሙሉሰው፣ ከላሊበላ በተጨማሪ የአገልግሎት ማዕከል የሆነችው ላሊበላና የሌሎች በርካታ ወረዳዎች ኃይል እንደተቋረጠባቸው ገልጸዋል።
የላሊበላ ከተማ የኤሌክትሪክ አገልግሎት መስመር የተዘረጋባቸው በርካታ ቦታዎች በሕወሓት ቁጥጥር ሥር በመሆናቸው፣ አሁን ባለው መስመር ጥገና አድርጎ ለማስቀጠል አለመቻሉን የገለጹት አቶ ሰለሞን፣ አዲስ መስመር ለመዘርጋትም ከወጪና ጊዜ አንፃር አዋጭ አለመሆኑን ጠቁመዋል።
በመሆኑም ከዚህ በፊት ጥቅም ላይ ሲውል የነበረና መነሻውን ከወልድያ ከተማ ያደረገ የኤሌክትሪክ መስመር በመኖሩ፣ በቀጣይ ይህንን መስመር በመጠቀም ወደ ላሊበላ ከተማ የኤሌክትሪክ መስመር ለመዘርጋት ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል።
ነባሩ መስመር አገልግሎት እየሰጠ እንዳልነበረና አንዳንድ ቦታዎች ላይ ጉዳት የደረሰበት በመሆኑ፣ ጥገና ተደርጎለት ወደ አገልግሎት ይመለሳል ብለዋል። የጥገና ሥራው መጀመሩን የገለጹት አቶ ሰለሞን፣ ‹‹ከሁለት ወራት በኋላ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ የላሊበላ ከተማ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት እንድታገኝ ዕቅድ ይዘን እየሠራን ነው፤›› ብለዋል።