አማራ ባንክ የሥራ መጀመሪያ ፈቃድ ለማግኘት ለብሔራዊ ባንክ ጥያቄ ማቅረቡን አስታወቀ፡፡
በብሔራዊ ባንክ ሕግ መሠረት የመመሥረቻ ፈቃድ ከተሰጠ በኋላ ወደ ሥራ ሲገባ የሥራ ማስጀመርያ ፈቃድ (ኦፕሬሽን ላይሰንስ) ስለሚያስፈልግ አማራ ባንክ ባለፈው ሳምንት ለብሔራዊ ባንክ ጥያቄ ማቅረባቸውን ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ የቀድሞ የባንኩ ፕሮጀክት ማናጀር ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ባንኩ ከሁለት ሳምንት በኋላ ማለትም ግንቦት 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ዋና መሥሪያ ቤቱን ለመክፈት በዝግጅት ላይ መሆኑን ወ/ሮ መሰንበት ገጸዋል፡፡
የተሟላ የሰው ኃይል፣ ለሠራተኞች ምቹ የሆነ ቦታና የባንኩ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ከተሟላ በኋላ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ እንዲሰጠው ይጠየቃል፡፡
ከወር በፊት በነበረው አጠቃላይ የአማራ ባንክ የመሥራቾች ጉባዔ እስከ ግንቦት 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ወደ ሥራ መግባት የሚያስችለውን ተግባር በሙሉ ማከናወን እንዳለበት አቅጣጫ መሰጠቱን ወ/ሮ መሰንበት ተናግረዋል፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ባንኩ ሥራ መጀመሩንና ሌሎች ስለባንኩ የሚገለጹ በሙሉ የሐሰት መረጃዎች ናቸው ሲሉ ወ/ሮ መሰንበት ገልጸዋል፡፡
በኮቪድ-19 ወረርሽኝና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት ስብሰባዎች መከልከሉ የባንኩ ወደ ሥራ የሚገባበት ቀን እንዲዘገይ አድርጎታል፡፡ በተጨማሪም ከ185 ሺሕ በላይ ባለአክሲዮኖች መረጃዎች ለብሔራዊ ባንክ ሲላክ፣ የብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ የሆነ ቁጥጥር ማድረጉና ባለአክሲዮኖች የሚሞሉት ፎርም በትክክል አለመሞላት እንዲዘገይ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳሉ፤›› ሲሉ ወ/ሮ መሰንበት ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያን የፖለቲካ አለመረጋጋት ጨምሮ ከላይ የተጠቀሱት ምክንያቶች ቢፈጠሩም፣ ከሌሎች በምሥረታ ላይ ከሚገኙ ባንኮች አንፃር ዘገየ የሚባል አይደለም በማለት የተናገሩ ደግሞ አቶ አስቻለው ታምሩ የባንኩ የብራንዲንግና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ናቸው፡፡
በብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት ባንኮች የሥራ እንቅስቃሴ ለመጀመር ጥያቄ ሲያቀርቡ ለሥራው ዝግጁ ናቸው ወይ የሚለውን የማረጋገጥ ሥራ እንደሚሠራ አቶ ፍሬዘር አያሌው የብሔራዊ ባንክ ሱፐር ቪዥን ዳይሬክተር ገልጸዋል፡፡
የብሔራዊ ባንክ መሥፈርት ከተሟላ ሥራ ለመጀመር የሚያስችለውን ፈቃድ ከሁለት እስከ ሦስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ አቶ ፍሬዘር ተናግረዋል፡፡
የዘገየ የመሰለው ለመጀመርያ ጊዜ ትልቅ የሀብት ምንጭ አሰባስቦ ወደ ሥራ የገባ ትልቅ ባንክ ስለሆነ፣ በርካታ ባለአክሲዮኖች ባንኮችና ባለድርሻ አካላት እየጠበቁት ስለሆነ መሆኑን አቶ አስቻለው ተናግረዋል፡፡
በአብዛኛው በአማራ ክልል ቅርንጫፍ ይከፍታል የሚሉ ቢኖሩም፣ በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ቅርንጫፎቹን ለማስፋት፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ በርካታ ቅርንጫፍ እንደሚከፍት አቶ አስቻለው ገልጸዋል፡፡
በባንኩ የአደራጅ ኮሚቴ ሪፖርት መሠረት፣ ከነሐሴ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ሽያጩ እስከ ቆመበት ኅዳር 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ 188 ሺሕ ከሚሆኑ ባለአክሲዮኖቹ 5.90 ቢሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል አክሲዮን ሽያጭ አሰባስቧል፡፡ የተፈቀደ ካፒታሉ ደግሞ 7.9 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ተገልጿል፡፡