Tuesday, December 5, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በሚያዚያ ወር ብቻ ከ12.8 ቢሊዮን ብር በላይ ለነዳጅ ድጎማ እንደተደረገ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአሥር ወራት ድጎማው ከ73.5 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል

የዓለም ነዳጅ ዋጋ ባሻቀበበት በዚህ ወቅት መንግሥት በሚያዚያ ወር ብቻ የነዳጅ ዋጋን ለማረጋጋት ከ12.8 ቢሊዮን ብር በላይ ድጎማ ማድረጉ ተገለጸ፡፡

እስከ ሚያዚያ ወር ማጠናቀቂያ ድረስ በአንድ ወር ብቻ ከ12.8 ቢሊዮን ብር በላይ የነዳጅ ድጎማ መደረጉ የታወቀ ሲሆን፣ ከሐምሌ 2014 ዓ.ም. አንስቶ በጠቅላላው ባለፉት አሥር ወራት በመንግሥት የተደረገው የተመዘገበ የድጎማ መጠን ከ73.5 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷ ተብሏል፡፡

የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አህመድ ቱሳ እንደተናገሩት፣ ለማነጻጸር ያህል ቤንዚን ከዓለም አቀፉ ዋጋ ጋር በተገናኘ በሰኔ 2013 ዓ.ም. መሸጥ የነበረበት በ42.74 ብር ቢሆንም፣ ሆኖም እስከ ኅዳር 2014 ዓ.ም. ድረስ ሲሸጥ የቆየው በ25.80 ብር እንደነበር ተናግረዋል፡፡ በታኅሳስ ከአምስት እስከ ስድስት ብር የሚደርስ ጭማሪ ተደርጎ 31.74 ብር እንደተሸጠ አቶ አህመድ ተናግረዋል፡፡

እስከ ተያዘው ሚያዚያ ወር ማጠናቀቂያ ድረስ ኩባንያዎች ወይም ነዳጅ አመላላሾች በዝቅተኛ የትርፍ ህዳግ እየሠሩ የዓለም የቤንዚን ዋጋ 68 ብር ቢደርስም መንግሥት ዝቅተኛውን ታክስና ሌሎች ነገሮችን ሳይጨምር በ31.30 ብር እያቀረበ እንደሚገኝ ያስታወቁት አቶ አህመድ፣ ይህም በሊትር  35.30 ብር ወይም ከግማሽ በላይ ድጎማ እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

ከዚህ በፊት ነዳጅ በዓለም አቀፉ ዋጋና በአገር ውስጥ በሚሸጥበት ዋጋ ላይ ይሸጥበት የነበረው ልዩነት ወይም መንግሥት የሚደጉመው በጣም ትንሽ የሚባልና ከአምስት እስከ ስድስት ብር እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፣ በዚህ ወቅት ከግማሽ አልፎ መንግሥት ተሸክሞ መሄድ የማይችልበት ደረጃ ላይ እንደደረሰ ተጠቅሷል፡፡ በመሆኑም ይህንን ጉዳይ ሕዝቡ ሊጋራው እንደሚገባ ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

በድጎማ መልክ በሚከፈለው ዋጋ በሐምሌ 2013 ዓ.ም. ብቻ ተጠቃሚው ሊከፍል የሚገባውን 5.7 ቢሊዮን ብር መንግሥት እንደሸፈነ ያስታወቁት አቶ አህመድ፣ የዓለም ዋጋ እየጨመረ ሲሄድ የኢትዮጵያ ዋጋ ባለበት መቆየቱን ተናግዋል፡፡

‹‹የነዳጅ ዋጋ ቀንሶ ይህንን ዋጋ እንከፍላለን የምንልበት ሁኔታ ላይ አይደለንም›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ የዓለም የነዳጅ ዋጋ ወደ ታች የሚመለስበት ዕድል ስለሌለ ቀስ በቀስ የታለመ ድጎማ ወይም የዋጋ ማስተካካያን ወደ ተጠቃሚው የሚተላለፍበት ተግባር ውስጥ መግባት አለበት ብለዋል፡፡

ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮች አስመልክቶ ምን ሊደረግ ይገባል? የሚለው እስከ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ የታየ ጉዳይ እንደሆነ የተናገሩት አቶ አህመድ፣ የነዳጅ ዋጋው ዓለም ላይ በጣም እየጨመረ በመምጣቱ መንግሥት ለዚህ የሚመድበው በጀት የለውም ብለዋል፡፡

የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት ባየለበት፣ በእንደዚህ ዓይነት አጣብቂኝ ጊዜ ውስጥ እንዴት ነው በጋራ ከሕዝብ ጋር ተጠቃሚው በተወሰነ ደረጃ እየከፈለ፣ መንግሥትም እየደገፈ፣ በጊዜ ሒደት ውስጥ ችግሩን መሻገር የሚቻለው? የሚለው ላይ፣ ከዋጋ ጋር በተያያዘ በኪሳራ እየቀረበ ያለውን የነዳጅ ዋጋ የዓለም ዋጋን በሚያንፃባርቅ ደረጃ በጊዜ ሒደት እንዴት ማምጣት ይቻላል? የሚለው ጉዳይ እንደሆነ ዋና ዳይሬክተሩ የተናገሩ ሲሆን፣ ከዚህ በኋላ የሚኖረው ጉዳይ ድጎማን ማስቀጠል ሳይሆን አሁን ካለው ድጎማ እንዴት በሒደት እንወጣለን የሚል ነው ብለዋል፡፡

መንግሥት ሕገ ወጥነትንና ብክነትን ማስቀረት ዓላማው እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ከዚህ ሌላ ከመጪው የሐምሌ ወር አንስቶ ድጎማን ቀስ በቀስ ለማስቀረት የተጠናው ጥናት ሌላ በመፍትሔ ሐሳብነት የተያዘ ጉዳይ እንደሆነ ሚያዚያ 27 ቀን 2014 ዓ.ም. የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ስለ አዲሱ የታለመ የነዳጅ ድጎማና ዋጋ ማሻሻያ በተመለከተ ለሚዲያ አካላት በተዘጋጀ ውይይት ላይ ተብራርቷል፡፡ 

በዓለም አቀፍና በአገር ውስጥ የሚሸጠው የነዳጅ ዋጋ ልዩነት የነዳጅ ኮንትሮባንድ ንግድ እንዲስፋፋ ዋነኛ ምክንያት መሆኑ በውይይቱ ወቅት የተገለጸ ሲሆን፣ የመንግሥት ትኩረት በጦርነትና በሌሎች ጉዳዮች ላይ መሆኑ፣ የክልልና የፌዴራል ተቋማት ተቀናጅተው መሥራት አለመቻላቸው፣ የአገር ውስጥ ጥቁር ገበያው መስፋፋት፣ ማደያዎች በበቂ ሁኔታ በአገሪቱ ውስጥ አለመኖራቸው ሌላው ችግር እንደሆነ ተመላክቷል፡፡

በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የፕሮጀክት አስተባባሪ የሆኑት አቶ ኑረዲን መሐመድ እንዳስታወቁት፣ መንግሥት በጥር 2013 ዓ.ም. የነዳጅ ዋጋ ግንባታና የትርፍ ህዳግን በተመለከተ ጥናት አጥንቶ የሚያቀርብ ኮሚቴ እንደተዋቀረ ተናግረዋል፡፡

ነዳጅ በ1988 ዓ.ም. መመርያ ሲወጣለት በ1993 ዓ.ም. የነዳጅ ዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ የሚባል አዋጅ እንደወጣለት ገልጸዋል፡፡ ይህ የዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ 247/1993 ያስቀመጠው የዓለም የነዳጅ ዋጋን የሚገዛው መንግሥት ነው፡፡ መንግሥት ሲገዛ ከገዛበት ዋጋና የሚሸጥበት ዋጋ ጋር እያየና እያስተያየ ቅንስናሽ ሳንቲሞችን ወደ ማረጋጊያ ፈንድ ያስገባል፡፡ ለምሳሌ ቤንዚን በወቅቱ በነበረው የዓለም ዋጋ 12.10 ብር ይገዛል፡፡ በዚህ የገንዘብ መጠን ተገዝቶ ትራንስፖርትና ትርፉ ተጨምሮ 12.90 ብር ከሆነ የመጣው 13 ብር ተተምኖ አሥሯ ሳንቲም ወደ ማረጋጊያ ፈንድ ትገባለች፡፡ የሚቀጥለው ወር ላይ 13.05 ከመጣ አምስት ሳንቲሟ ቀርታ በ13 ብር ይቀጥላል፣ ክፍቱን የሚያረጋጋበት ፈንድ ያስተካክለዋል የሚል ዕምነት ተይዞ በአዋጅ የተቋቋመና ተጠሪነቱ ለገንዘብ ሚኒስቴር የሆነ ፈንድ እንደተቋቋመ አቶ ኑረዲን አስታውሰዋል፡፡

ይህ ከ1993 እስከ 2003 ዓ.ም. በጥሩ ሁኔታ ትንንሽ ሳንቲሞችን ከትርፍ የሚወጡ ህዳጎችን እየሰበሰበ እስከ 14 ቢሊዮን ብር ድረስ በማረጋጊያ ፈንድ ውስጥ እንዳስቀመጠ ያስታወሱት አቶ ኑረዲን፣ በ2002 ዓ.ም. ላይ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ሲያሻቅብ መንግሥት ከዋጋ ማረጋጊያ ፈንዱ በላይ ሊወስድ እንደሚችል ስለተረዳ ታክስና ቫትን ወደ ታች እንዳወረደው፣ ነዳጅ ዋጋ ቢጨምር ኅብረተሰቡ ስለሚጎዳ  በሚል 15 እና 30 በመቶ የነበረው በሊትር 2.98 ብር እና 3.45 ብር ይሁን ብሎ ውሳኔ ማሳለፉን ተናግረዋል፡፡

አቶ አህመድ በበኩላቸው እስከ 2012 ዓ.ም. ድረስ የነበረው በዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ ላይ የተከማቸ ዕዳ 14.5 ቢሊዮን እንደነበር ያስታወቁ ሲሆን፣ በ2013 ዓ.ም. ደግሞ የነበረው ድጎማ  36 ቢሊዮን መሆኑን ጨምረው ገልፀዋል፡፡

በተያዘው ዓመት እስከ ሚያዚያ ወር ድረስ መንግሥት የደጎመው ገንዘብ 124 ቢሊዮን እንደደረሰ ያስታወቁት አቶ አህመድ፣ ይህም አንድ አምስተኛውን የኢትዮጵያን በጀት የሚሸፍን እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

መንግሥት ነዳጅን እየደጎመ ይቀጥል ከተባለ ይህንን መጠን ያለው ገንዘብ ከሌሎች የልማት ሥራዎች ቀንሶ ወደዚህ ማምጣት እንደሚገባው የተገለጸ ሲሆን፣ ነዳጅ እየተደጎመ ይሂድ ከተባለ ይህ ገንዘብ ሊከፈል እንደሚገባው ተገልጿል፡፡

ነዳጅ በጎረቤት አገሮች ያለው ዋጋ ሲታይ በተለይ ቤንዚን በጅቡቲ 90 ብር፣ በኬንያ 60 ብር 79 ብር እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ 72 ብር እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ አንድ ሊትር በሚያዚያ ወር መሸጥ የነበረበት 68.10 ብር እንደነበር ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች