Friday, September 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሲሚንቶ ፋብሪካዎች አከፋፋይ ወኪሎቻቸውን ከግብይት ሥርዓቱ እንዲያስወጡ ታዘዙ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ምርቶቻቸውን የሚያከፋፍሉላቸውን ወኪሎች (ኤጀንት) ከገበያ ሥርዓት ውስጥ አስወጥተው ምርታቸው በቀጥታ እንዲሸጡ አዘዘ፡፡ ሚኒስቴሩ ለአሥር የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በጻፈው ደብዳቤ ፋብሪካዎቹ ያስወጧቸውን የሲሚንቶ አከፋፋይ ኤጀንቶች ብዛትና ስም ዝርዝር በደብዳቤ እንዲያሳውቁትም አሳስቧል፡፡

ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ሚያዝያ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. የተጻፈውና በሚኒስትር ደኤታው ሐሰን ሙሐመድ የተፈረመው ደብዳቤ፣ ‹‹በሲሚንቶ ፋብሪካዎች በኤጀንትነት ተመልምለናል›› የሚሉና የጅምላ ንግድ ፈቃድ የያዙ ነጋዴዎች ሲሚንቶውን ለሌሎች ጅምላ ነጋዴዎች እየሸጡ ስለመሆናቸው መታወቁን ያስረዳል፡፡ ይኼም ጅምላ ከጅምላ የሚደረግን የጎንዮሽ ንግድ የሚከለክለውን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 980/2008 እንደሚጥስ በደብዳቤው ላይ ተገልጿል፡፡ ስለሆነም ፋብሪካዎቹ ደብዳቤው ከደረሳቸው ቀን ጀምሮ የሲሚንቶ አከፋፋይ ኤጀንቶችን አስወጥተው ለሚኒስቴሩ እንዲያሳውቁ ታዘዋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ደኤታው አቶ ሐሰን፣ ሚኒስቴሩ ሲሚንቶ ላይ ያለውን የግብይት ሰንሰለት ለማሳጠር እየሠራ መሆኑን ገልጸው ኤጀንቶች የግብይት ስንሰለቱን ከሚያራዝሙት አንዱና በሕግም የማይደገፉ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ አክለውም ከአሁን በኋላ ሲሚንቶን ለማከፋፈል ኤጀንቶችን የሚጠቀም የሲሚንቶ ፋብሪካ ከተገኘ ጥብቅ የሆነ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸዋል፡፡

ከዚህም በተጨሪም ሚኒስቴሩ የገበያውን ሒደት ለማየትና ለመቆጣጣር ሲል የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ምን ያህል ምርት እንዳመረቱና ለማን እንዳከፋፈሉ የሚገልጽ መረጃ እንዲያቀርቡ መታዘዙን ሚኒስትር ደኤታው ተናግረዋል፡፡

አቶ ሐሰን እንደተናገሩት፣ ከአሁን በኋላ የሲሚንቶ ግብይቱ የማንም ጣልቃ ገብነት ሳይኖርበት ጅምላ ነጋዴዎች ቀጥታ ከፋብሪካዎች መረከብ የሚያስችል ይሆናል፡፡ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችና ሌሎች የመንግሥት ግንባታ ፕሮጀክቶች ደግሞ በተለየ መልኩ እንደሚታዩ አስረድተዋል፡፡   

ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር ፋብሪካዎች ምርቶቻቸውን ወደሚፈልጉት አካባቢ የሚያሠራጩላቸውን ወኪሎች የሚመርጡ ሲሆን ከእነዚህ ወኪሎች ውጪ ያሉ ጅምላ ነጋዴች ሲሚንቶን ቀጥታ ከፋብሪካዎቹ አይገዙም ነበር፡፡ ይሁንና ኤጀንቶቹ ከፋብሪካዎቹ የሚረከቡትን ሲሚንቶ ዋጋ ጨምረው ለጅምላ አከፋፋዮች ስለሚሸጡ ሰንሰለቱን ከማርዘሙ በላይ ከፋብሪካ የሚወጣው ሲሚንቶ ተጠቃሚው ጋር እስኪደርስ በሦስት ደረጃ የዋጋ ጭማሪ እንዲደረግበት ምክንያት ሆኗል፡፡

የማዕድን ሚኒስቴር ኅዳር 2014 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና ከንግድ ሚኒስቴር ጋር በመሆን በሲሚንቶ ዘርፍ ላይ ከምርት እስከ ግብይት ሰንሰለቱ ድረስ ያለውን ችግር በተመለከተ ያስጠናው ጥናት የግብይት ሥርዓቱ ጤናማ ባልሆነ የግብይት ሰንሰለት የተዋቀረ መሆኑን አሳይቷል፡፡

ከፋብሪካዎች ሲሚንቶውን ተረክበው ኤጀንቶች በጊዜው በነበረው የገበያ ዋጋ ከአንድ ኩንታል ሲሚንቶ ላይ በትንሹ ከ115 እስከ 230 ብር አትርፈው እንደሚሸጡና ከፍተኛ የዋጋ ንረት በተከሰተበት ጊዜ በፋብሪካው የመሸጫ ዋጋና በኤጀንቶቹ የማከፋፈያ ዋጋ መካከል እስከ 400 ብር የደረሰ ልዩነት እንደነበር የጥናቱ ቡድን አባል የሆኑት የማዕድን ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር የሆኑት ፍሬሕይወት ፈቃዱ ለሪፖርተር ተናግረው ነበር፡፡

የንግድ ወኪል ተብለው ከፋብሪካዎቹ ጋር የሚሠሩት በአንድ በኩል ቤተሰባዊ ግንኙነት ያላቸው እንዲሁም አልፎ አልፎም የፋብሪካዎቹ ሰዎች ከበስተጀርባ የሚታዩባቸው መሆናቸውንም ጥናቱ አሳይቷል፡፡

ከዚህም ባሻገር የማዕድን ሚኒስቴር ኃላፊዎች የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ምርቱን ሳያመርቱ ከኤጀንቶቻቸው ገንዘብ በመውሰድ በመሀላቸው ያለው ውል የሚቋረጥበትን መንገድ ለመዝጋት ይሞክራሉ የሚል ጥርጣሬ አላቸው፡፡ ሚኒስቴሩ ከዚህ ቀደም አራት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ገንዘብ ወስደው ለአከፋፋዮች ያልሰጡት ውዝፍ የሲሚንቶ ዕዳ 2,633,863.26 ቶን ሲሚንቶ መድረሱን አስታውቆ ነበር። ይኼንን ተከትሎም ሚኒስቴሩ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው በማምረት ውዝፍ የሲሚንቶ ሽያጭ ዕዳቸውን ከምርታቸው ጋር በማመሳከር እንዲያስተካክሉ ማሳሰቢያ ሰጥቷቸዋል።

በተጨማሪም ኅዳር 2014 ዓ.ም. ፋብሪካዎቹ የሲሚንቶ ምርታቸውን በወኪልነት የሚያከፋፍሉላቸው ኩባንያዎችን ስም ዝርዝርና የሚገኙበትን አድራሻ እንዲያሳውቁ እንዲሁም አዲስ መመርያ እስኪዘጋጅ ለአዲስ የምርት አከፋፋይ ወኪሎች ፋብሪካዎች ፈቃድ እንዳይሰጡ ታዘው ነበር፡፡

ሲሚንቶ ከነፃ ገበያ እንዲወጣ የግብይት መመርያ እያዘጋጀ ያለው ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሲሚንቶ እንደ መሠረታዊ ሸቀጥ ተቆጥሮ ዋጋው ቁጥጥር እንዲደረግበት ይፈልጋል፡፡ እያዘጋጀው ያለው መመርያ ሲፀድቅም ጅምላና ችርቻሮ ነጋዴዎች ላይ የትርፍ ህዳግን ለመወሰን አቅዷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች