ኮርፖሬሽኑ ካለበት ዕዳ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የመክፈል አቅም አለኝ አለ
የአዲስ አበባ ቤቶች ኮርፖሬሽን ግንባታቸው ያልተጠናቀቁ ከ19 ሺሕ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን እስከ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. አጠናቆ ለባለ ዕድለኞች እንደሚያስተላልፍ አስታወቀ፡፡
በቅርቡ ከባንኩ በተገኘ 2.5 ቢሊዮን ብር ብድር ለባለ ዕድለኞች ተላልፈው ያልተጠናቀቁ ቤቶችን ለማጠናቀቅ ዕቅድ መያዙን በኮርፖሬሽኑ የግንባታ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቶማስ ደበሌ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ጨምረው እንዳስረዱት፣ የአዲስ አበባ ቤቶች ኮርፖሬሽን ካለበት 54 ቢሊዮን ብር ዕዳ ውስጥ፣ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የመክፈል አቅም እንዳለው በጥናት አረጋግጧል፡፡
የአዲስ አበባ ቤቶች ኮርፖሬሽን በያዝነው ዓመት 54 ቢሊዮን ብር ዕዳ እንዳለበት መገለጹ ይታወሳል፡፡ ይህንንም ለመክፈል የሚችልበት አቅም እንዳለው ለማወቅ ጥናት ሲደረግ መቆየቱን አቶ ቶማስ ጠቁመው፣ የከተማዋ ቤቶች ኮርፖሬሽን ከባንክ የተበደረውን ገንዘብ መክፈል ስላልቻለ ተጨማሪ የቦንድ ብድር መበደር አይችልም የሚል አቋም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ተይዞ እንደነበር ገልጸው፣ ችግሩን ለመፍታት ጥናት ተደርጓል ብለዋል። ለስድስት ወራት ያህል ጥናት ሲደረግ የነበረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም የተሳተፈበትና ትኩረቱንም የኮርፖሬሽኑን የሀብት መጠን መለየት ላይ ማድረጉን አክለዋል።
በጥናቱ ግኝት መሠረትም በአሁኑ ወቅት በተለያየ ሁኔታ ላይ የሚገኙ የኮርፖሬሽኑ ሀብቶች መኖራቸውን፣ እነሱን ደግሞ ወደ ገንዘብ መቀየር እንደሚቻል ለማወቅ መቻሉን አቶ ቶማስ አስረድተዋል።
ኮርፖሬሽኑ በእጁ የሚገኙ ቤቶች ለባለ ዕድለኞች ሲተላለፉ የሚገኝ ገንዘብን ጨምሮ በርካታ ጥቅም ላይ ያልዋሉ ንብረቶች መኖራቸውን ጥናቱ ማመላከቱን፣ እነዚሁም ቢያንስ የዕዳውን ከ50 በመቶ በላይ መሸፈን የሚችሉ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል ብለዋል።
በቀጣይም ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመሆን ተጨማሪ ጥናቶችን በማድረግ ዕዳው የሚከፈልበትን ሁኔታ ውሳኔ እንደሚሰጥ አቶ ቶማስ ጠቁመዋል። በአሁኑ ወቅት ከ139 ሺሕ በላይ ቤቶችን በመገንባት ላይ እንደሚገኙ ገልጸው፣ ግንባታቸው ተጠናቆ ያልተላለፉ ቤቶች ደግሞ 80 ሺሕ እንደሚደርሱ ገልጸዋል።
ኮርፖሬሽኑ ባለፉት መቶ ቀናት ውስጥ ከ68,000 በላይ ቤቶችን ለማጠናቀቅ አቅዶ ከ60 ሺሕ በላይ ቤቶችን ማጠናቀቁን የገለጹት አቶ ቶማስ፣ ከ50 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ቁልፍ ማስረከቡን ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት ከዋጋ ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሙ ችግሮች ቤቶቹን ለማጠናቀቅ ፈታኝ እንዳደረገው ተናግረዋል፡፡
የቤቶቹ ግንባታ በጊዜው አለመጠናቀቅ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብድር ለማግኘት አስቸጋሪ እንዳደረገውና በመብራት፣ በፍሳሽና በውኃ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚከናወኑ ማጠናቀቂያዎች ረዥም ጊዜ እንዲወስዱ አድርጓል ብለዋል።
የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ በአዲስ አበባ ከተማ ከተጀመረበት ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ በቤት ልማት ፕሮግራሙ በአጠቃላይ ከ317 ሺሕ በላይ ቤቶች ተገንብተው ለገዥዎች መተላለፋቸውን፣ የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመለክታል።