Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየመንግሥት ባለሥልጣናት ስለአገራዊ ምክክሩ አስተያየት ከመስጠት እንዲቆጠቡ ተጠየቀ

የመንግሥት ባለሥልጣናት ስለአገራዊ ምክክሩ አስተያየት ከመስጠት እንዲቆጠቡ ተጠየቀ

ቀን:

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት የአገራዊ ምክክሩን ሒደት አስመልክቶ አስተያየት ከመስጠትና ጥርጣሬን የሚጭሩ መልዕክቶችን ከማስተላለፍ እንዲቆጠቡ ጠየቀ፡፡ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔውን ያደረገው ምክር ቤቱ፣ አገራዊ ምክክሩን አስመልክቶ ለሰዓታት የቆየና በአለመግባባቶች የታጀበ ውይይት ካደረገ በኋላ፣ በአብላጫ ድምፅ አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን እየደገፈ ለመቀጠል ወስኗል፡፡

ሐሙስ ሚያዝያ 17 ቀን 2014 ዓ.ም. 53 የፖለቲካ ፓርቲዎች በተገኙበት ጠቅላላ ጉባዔውን ያደረገው ምክር ቤቱ፣ በጉባዔው መጨረሻ በሰጠው የአቋም መግለጫ፣ ከአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ምሥረታ ማግስት ጀምሮ በመንግሥት አካላት በኩል የታዩ የግልጽነት ጉድለቶች በሒደቱ ላይ ጥርጣሬ እንዲፈጠር ማድረጋቸውን ገልጿል፡፡ ምክር ቤቱ አገራዊ ምክክሩን ከምርጫው አስቀድሞ ለማስጀመር ከፍተኛ ጥረት እንዳደረገ ጠቅሶ፣ ‹‹ይሁን እንጂ መንግሥት ለጉዳዩ በሰጠው ዝቅተኛ ቦታና ትኩረት፣ ብሔራዊ ምክክሩ ሳይጀመር ወደ ምርጫ ከመገባቱም ባሻገር፣ አገራችን ወደ ለየለት ጦርነት ገብታለች፤›› ብሏል፡፡

ባለፉት ወራት ውስጥም ኮሚሽኑን የማቋቋም ሥራን ሲያስተባብሩ የነበሩ የመንግሥት አካላት ለፖለቲካ ፓርቲዎች ሥጋትና ጥያቄ በቂ ትኩረት ሳይሰጡ፣ ኮሚሽኑን የማቋቋም ሥራውን በአጭር ጊዜ ማገባደዳቸውን ጠቁሟል፡፡ አንዳንድ  የመንግሥት ባለሥልጣናት የአገራዊ ውይይቱን ተሳታፊዎች፣ አጀንዳዎችና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ አስተያየት ከመስጠትና የሒደቱን ገለልተኝነት አስመልክቶ ጥርጣሬ ሊጭሩ የሚችሉ መልዕክቶችን ከማስተላለፍ እንዲቆጠቡ ጠይቋል፡፡

አክሎም፣ ‹‹የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ባለበትና ኮሚሽነሮች ተመድበው ሥራ በጀመሩበት በአሁኑ ወቅት፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሒደቱን አስመልክቶ የሚሰጡት አስተያየት እንዲቆም፤›› በማለት አሳስቧል፡፡

ምክር ቤቱ ለአንድ ቀን ባደረገው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ዓመታዊ ሪፖርት ከማቅረብና አገራዊ ምክክሩን አስመልክቶ አቋም ከመያዝ ባሻገር፣ አዲስ የሥራ አስፈጻሚዎችን ለመምረጥ ዕቅድ ይዞ ነበር፡፡ ይሁንና አገራዊ ምክክሩ ላይ አቋም ለመያዝ የተደረገው ውይይት አብዛኛውን ጊዜ በመውሰዱ አዲስ ሥራ አስፈጻሚ አባላት ሳይመረጡ ጉባዔው ተበትኗል፡፡

የምክር ቤቱ አባል የሆኑት የፖለቲካ ፓርቲዎች አገራዊ ውይይቱን አስመልክቶ ያደረጉት ውይይት ያጠነጠነው፣ ምክር ቤቱ የኮሚሽኑን ሥራና የምክክሩን ሒደት ተቀብሎ ዕርማት እያደረጉ መቀጠልና ከአዋጁ ጀምሮ ሁሉንም ሥራ በድጋሚ መጀመር የሚለው ላይ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ተወካይ አቶ አበባ አካሉ፣ ፓርቲያቸው የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን ማቋቋሚያ አዋጅም ሆነ ኮሚሽኑን የማቋቋም ሒደት ችግር አለበት ብሎ እንደሚያምን ገልጸው፣ ይኼም ቢሆን ግን ኮሚሽኑን ‹‹ከእነ ችግሩ ተቀብሎ መሄድ›› አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ከብሔራዊ ምክክር ውጪ ምን አማራጭ አለ የዚህችን አገር ችግር ለመፍታት የሚለውን ተቋም ብለን ማሰብ አለብን፡፡ ተመልሰን ወደ ጦርነት ቀጣና የምንገባ ከሆነ አገሪቷን በታትነናት ነው ቁጭ የምንለው፤›› በማለት ሐሳባቸውን አጠናክረዋል፡፡

ሒደቱ ቆሞ እንደ አዲስ እንዲጀምር ከጠየቁ ፓርቲዎች ውስጥ አንዱ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ሲሆን፣ ፓርቲውን የወከሉት አቶ ጄሳቤ ገቢሳ ፓርቲያቸው የአገራዊ ምክክር አስፈላጊነት ላይ ምንም ጥያቄ እንደሌለው ተናግረዋል፡፡ ብሔራዊ ምክክር ተቀባይነት እንዲኖረው ገለልተኛ፣ አሳታፊና ግልጽ መሆን እንዳለበት የገለጹት አቶ ጄቢሳ፣ የተጀመረው የብሔራዊ ምክክር ሒደት ግን ሦስቱንም እንደማያሟላ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ብሔራዊ ምክክር የሚያስፈልገው የበደለና የተበደለ አንድ ጠረጴዛ ላይ ተነጋግረው መፍትሔ እንዲያስገኙ ነው፡፡ አሁን ግን የበደለ ብቻ ነው አገራዊ ምክክር እያደረገ ያለው፤›› ካሉ በኋላ፣ ‹‹ወደኋላ ተመልሰን ዕርምጃችንን አስተካክለን እንደ አዲስ መጀመር ያስፈልገናል፤›› ብለዋል፡፡

ለሰዓታት የቀጠለው ውይይት የተቋጨው በጉዳዩ ላይ ምክር ቤቱ አቋም እንዲይዝ ድምፅ በመስጠት ነው፡፡ በጉባዔው ላይ ድምፅ ከሰጡ 53 የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ 40 ያህሉ መንግሥት ጣልቃ እስካልገባ ድረስ ውይይቱ እንዲቀጥል ሲወስኑ፣ 13 ፓርቲዎች ከአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጁ አንስቶ ሒደቱ እንደገና እንዲጀመር ድምፃቸውን ሰጥተዋል፡፡ በዚህም መሠረት ከዚህ ቀደም የምክክሩ ሒደት ለጊዜው ተገትቶ ውይይት እንዲደረግ የጠየቀው የጋራ ምክር ቤቱ የአገራዊ ምክክሩን ደግፎ ለመቀጠል ወስኗል፡፡

ምክር ቤቱ አገራዊ ምክክሩን የሚደግፈው ስህተቶች እንዲታረሙ ግፊት በማድረግ እንደሆነ ለሪፖርተር የተናገሩት የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ራሔል ባፌ (ዶ/ር)፣ ምክር ቤቱ አባላት ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ከመንግሥትና ከኮሚሽኑ ጋር ባደረገው ውይይት፣ መንግሥት የተነሱ ችግሮችን ለመፍታት ቃል እንደገባ ገልጸዋል፡፡ አክለውም ‹‹በጣም ጠባብ በሆነ መንገድ እየሄድን ቢሆንም፣ ለአገርና ለሕዝባችን ስንል ጠባቧንም ዕድል ቢሆን መያዝ አለብን፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...