Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርየጠቅላይ ሚኒስትሩ "የሙዝ ተመገቡ" ሐሳብ ለፌዝ ፍጆታ እንዴት ሊውል ቻለ? ጥፋቱስ ምን...

የጠቅላይ ሚኒስትሩ “የሙዝ ተመገቡ” ሐሳብ ለፌዝ ፍጆታ እንዴት ሊውል ቻለ? ጥፋቱስ ምን ነበር?

ቀን:

‹‹ሎሚ ካልመጠጡት እንቧይ ዳቦ ካልገመጡት ድንጋይ››

በያሬድ ነጋሽ

የእዚህ ጽሑፍ ዝግጅት አትኩሮቱን በውስን የምግብ አማራጭ ላይ ያደረገ ሕዝብ አንድም በድርቅ አሊያም በምግብ ዋጋ ንረት ሊጠቃ መቻሉን ከዓለም አቀፍ እውነታ ጋር አነፃፅሮ፣  የጠቅላይ ሚኒስትራችን የሙዝ ብሉ ሐሳብ በዜጋ ዘንድ ለማኅበራዊ ሚዲያ ፌዝ (ሚም) ፍጆታ እንዴት ዋለ? ጥፋቱስ ምንድን ነበር? የሚለውን ይመለከታል።

- Advertisement -

ቻይና ካሳለፈቻቸው ተደጋጋሚ የረሃብ ጊዜያት መካከል እ.ኤ.አ. ከ1959 እስከ 1961 የተከሰተውን ‹‹በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የተመለከትነው ትልቁ ረሃብ›› ተብሎ ይጠቀሳል። በእዚህ ወቅት 30 ሚሊዮን የሚሆኑ ቻይናውያን በረሃብ ሞተዋል። በሕይወት የተረፉ ሰዎችም ቢሆኑ ሕይወታቸው አስከፊ መንገድ ሲጓዝ፣ በርካታ ጨቅላ ሕፃናት ለመቀንጨር (Malnutrition) ተዳርገዋል። ረሃቡ የርዕዮተ ዓለም ለውጥ ወይም አብዮት ለመቀስቀሱ ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ መውሰድ የሚያስችል ነበር። ከሁለት ትውልዶች በኋላ ቻይና የረሃቡን መንስዔና መዘዝ በግልጽ ልትመረምር ተነሳች።

የረሃቡ መነሻ ማኦ ዜዱንግ በቻይና ኮሙዩኒስት ፓርቲ አመራር የተደገፈ ታላቁን ሊፕ (የጉዞ ዕቅድ) ወደፊት ለማስጀመር ባሳለፈው ውሳኔ ሲሆን፣ ይህ የአገሪቱ ግዙፍ ዕቅድ ዓላማ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ ነበር። በአሥር ሚሊዮን የሚቆጠሩ ገበሬዎች በእርሻ ላይ ከመሥራት ይልቅ በአካባቢው በሚገኙት የብረት፣ የኖራና የድንጋይ ከሰል ማውጣት ክንዋኔዎች ላይ እንዲሳተፉና ብረት አቅልጠው ለተለያየ አግልግሎት እንዲያውሉ ተደረገ። ይህ ውሳኔ ገበሬዎች ከግብርና እንዲፋቱ ቢያደርግም፣ አዲስ የተቋቋሙ የኮሚውናል ግብርና ማኅበራት በወቅቱ ከ80 በመቶ በላይ የቻይና የምግብ ፍላጎት እንዲሸፍኑ ተደረገ። ሆኖም ከ1958 በፊት የምግብ አቅርቦቱና ፍላጎቱ እኩል የነበረ ሲሆን፣ በ1959 የፀደይ ወቅት በቻይና አንድ ሦስተኛው ማኅበረሰብ ለረሃብ ተጋላጠ።

ረሃቡ ከመከሰቱም በላይ የቻይና ገዥዎች ዕውቅና ባለመስጠታቸውና የውጭ የምግብ ዕርዳታን በፍጥነት እንዲያገኙ ባለማስቻላቸው ረሃቡን አከፋው። የቻይና መንግሥት ለረሃቡ ዕውቅና ሰጥቶ ዕርምጃ እስኪወስድ ድረስ ወደ ሦስት ዓመታት ገደማ ፈጅቷል። ሁሉም የግለሰብ የምግብ ማምረቻዎች በመንግሥት ቁጥጥር ሥር መውደቃቸው፣ ገበሬዎችን በአግባቡ ባልተደራጁ ማኅበራት ውስጥ እንዲገቡ ማስገደዱና የአገር ውስጥ ፍጆታን ገሸሽ በማድረግ ምርት ወደ ውጭ ለመላክ መወሰናቸው ነገሮች እንዲከፉ አደረገው።

በመጨረሻ በአገር አቀፍ ደረጃ የሟቾች ቁጥር መበራከቱን ተከትሎ ከ1961 በኋላ ምክንያታዊ የኢኮኖሚና የፖሊሲ ለውጥ በማድረግ እህልን ከውጭ ማስገባት ጨምሮ፣ ረሃቡን ያቆማሉ የተባሉ ውሳኔዎች ተወሰኑ። ከእነዚህ ውሳኔዎች መሀል አንዱ ውስንነት የሚታይበትን የቻይና የምግብ ባህል መስበር ወይም አብዮት (Cultural Revolution) ማስነሳት ነበር። ይህም ትልቅ ለውጥ ማምጣት ከመጀመሩ ባለፈ ኢኮኖሚውንም ያነቃቃ ነበር። ምክንያቱም በርካታ ነገሮችን ወደ ምግብ ሰንሰለት ውስጥ አስገብቶ የምግብ ዋስትናን (Food Security) ማረጋገጥ በመቻሉ፣ ወደ ኢኮኖሚያዊ ግንባታ ፊታቸውን ማዞር እንዲቀል ጥሪጊያውን በመመቻቸቱ ነበር። ማኦ በሞተ ሦስት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በ1979 የኮሙዩኒስት ፓርቲ የለውጥ አራማጅ ቡድን የጀመረው የመጀመርያው ትልቅ ለውጥ የግብርና ማኅበራትን ችግር በመፍታቱ፣ የቻይና አማካይ የነፍስ ወከፍ የምግብ አቅርቦት ከጃፓን አማካይ ጋር እኩል በመሆን አምስት በመቶ ደረሰ።

ከእዚህ ዓለም አቀፍ ተሞክሮ በመነሳት ኢትዮጵያውያን ለረሃብ በተደጋጋሚ የምንጋለጥ በመሆናችን፣ አንደኛ የምግብ ምርጫችን ውስንነት በራሱ እጥረቱን ያባባሰው በመሆኑ፣ እንደ ቻይናዎቹ “ሳር ቅጠሉ፣ ውሻው ጓጉንቸሩ”ይበላ ባንልም፣ በፖሊሲ ማዕቀፍ ደረጃ የምግብ ባህል አብዮትን ማስነሳት ተገቢነት ያለውና መሪ ጉዳይ አድርጎ የመወያየት ግዴታ የለበትም? ታዲያ ጠቅላይ ሚኒስትራችን አማራጭ ምግብ እንድንጠቀም መምከራቸው በማኅበራዊ ሚዲያው ሊቀለድበት ይገባ ነበር? ጥፋቱስ የቱ ጋ ነበር? ይህንን ከመመልከታችን በፊት መንግሥት ትኩረት የነፈጋቸውን ሁለት ነገሮች ቀድመን እናንሳ።

በመጀመሪያ ለውጭ የምናቀርባቸው ምርቶች የአገር ውስጥ ፍላጎት ለማሟላት በተቸገርንበት ወቅት በመሆኑ ተገቢነት የሌለው፣ ለምግብ እጥረት ለተጋለጡ ሥፍራዎች መዋል የሚችል መሆኑንና በተጨማሪም ገበያው ውስጥ የአቅርቦት እጥረት በመፍጠር የዋጋ ንረቱን በማባባስ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ተገንዝቦ ልክ ቻይናውያን እንደተገበሩት አፋጣኝ መፍትሔ መፈለግ ይሻል (በሚያዝያ 2014 ዓ.ም. ላይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክ አሶስዬሽን ይህንን አሳስቧል)። በመቀጠል ድህነት ተንሰራፍቶባታል ከሚሰኙ አገሮች መሀል የሆነችውን ኔፓል የሚያስተዳድሩት አካላት፣ “ገበሬው በችግርና በረሃብ ወይም ሁለት ቅጣት በአንዴ መቀጣት የለበትም” በሚል ያመረተውን ሩዝ እንዳይሸጥ ወስነው ነበር። ይህም ውሳኔ ኔፓላውያንን ጠረጴዛ ሙሉ ሩዝ በፈለጉት ሰዓት እንዲመገቡ (የጠገበ ሌላውን ችግር ለመቋቋም አቅም ይኖረዋል ከሚለው በተጨማሪ ለችግሩ መፍትሔ ማፈላለጉም ላይ ግንባር ቀደም ይሆናል የሚለውም ከግንዛቤ ይገባል) እና በርካቶች ወደ ጎሮ ግብርና እንዲሳተፉ በር የከፈተ ነበር።

የኢትዮጵያ መንግሥት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክ ማኅበርን ማሳሰቢያን ችላ በማለት ወይም፣ ‹‹የውጭ ንግዱ የውጭ ምንዛሪ የማሰባሰቢያ መንገዴ ነው›› ቢልም፣ ማኅበሩ፣ ‹‹የውጭ ምንዛሪ መሰብሰብና የዋጋ ንረት ተያይዘው የሚያድጉ አይደሉም። ታዲያ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ?›› ለሚለው ግን መልስ መስጠት አልቻለም። የኔፓል ዓይነት ውሳኔ በመወሰን ማኅበረሰቡ የሚመገበውን በየጓሮ ወይም በቤቱም ጣሪያ ላይ ሳይቀር የማምረት ግዴታ ውስጥ እንደሚከተው መንግሥት ተገንዝቦ፣ ወደ ተግባር ለመግባት ጅምሩ እንኳን አይታይም። በኬንያ ከተሞች በአገራችን እንደ ቅንጦት ምግብ የምንቆጥረው ዶሮ እንደ ሳንቡሳ በየመንገዱ የሚሸጥበት ምክንያት፣ ማኅበረሰቡ በየጓሮው ከአንድ ሺሕ ያላነሱ ዶሮዎችን በማርባት ምርታማነትን በማሳደጉና ትርፍ ምርት ገበያ ውስጥ በመፈጠሩ ነበር። ይህም በኢትዮጵያ መንግሥት ዘንድ የተሰጠው ትኩረት እንብዛም ነው።

ወደ ነገራችን እንመለስና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሙዝ ብሉ ሐሳብ በጭራሽ እንደ ስህተት የሚቆጠር ባይሆንም፣ የሥርዓቱ ወይም ለሕዝብ ያስገነዘቡበት መንገድና አማራጭ ብለው ከጠቆሙት ምርት ጋር በተያያዘ ግን በሁለት ገጽታ የሚታይ ህፀፅ የተሸከመ ነበር። አንደኛው የሚተቸው የስርፀቱን መንገድ በተመለከተ፣ ለማኅበረሰቡ አማራጭ ምግብ መጠቆም ማለት የሦስት ሺሕ ዓመት ዕድሜ ካለው የምግብ ባህል ጋር የማፋታት ወይም ባህሉ ላይ አብዮት (Culture Revolution) ማስነሳት ስለሆነ፣  በአጋጣሚ ባገኙት መድረክ ከሚናገሩት ይልቅ ራሱን የቻለ አጀንዳ ሆኖ የግብርናና የኢኮኖሚ ጽንሰ ሐሳቦችን አስደግፈው በእሳቸው ወይም በባለሙያ ማቅረብና የፖሊሲ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ አቅጣጫ ሊቀመጥለት ይገባ ነበር።

የተጠቆመው አማራጭ ሙዝ ከሚሆን ይልቅ የግብርና ባለሙያዎችን በፓርላማም ይሁን በሚኒስትሮች ምክር ቤት አብረው አሳትፈው፣ ውስን የሆነው የምግብ ምርጫችን አንድም ለምግብ እጥረት ሲያልፍም የምግብ ይዘቱ ላነሰ (Poor Nutrients) አመጋገብ እንደዳረገን ማስገንዘብ ነበረባቸው፡፡ በፕሮቲን ይዘት የበለፀጉ የወርና የሦስት ወር የጥራ ጥሬ እህሎች ማለትም እንደ ቦሎቄ፣ አደንጓሬ፣ በንጥረ ነገሮች የተሞሉና ከፍተኛ የፕሮቲን ይዘት ስላላቸው በተለይ ሥጋና የወተት ተዋፅኦዎች በኢኮኖሚ ውስንነት ተደራሽ በማይሆኑባቸው ክልሎች ተስማሚ የፕሮቲን ምንጭ ያደርጋቸዋል፡፡ እንጉዳይ የመሳሰሉትን በተለይ ዘይት ሳያስፈልግ ማዘጋጀት የሚቻልበትን መንገድ ቢቀይሱ፣ ማኅበረሰቡ ባለችው ቦታ አምርቶ (ዶሮ ማርባት ጨምሮ) ለሽያጭ ሳይሆን ለቤት ፍጆታው እንዲያውል ቢያግባቡ፣ በቅናሽ ቢያቀርቡ፣ ሬስቶራንቶች ምርቶቹን በተለያዩ ዓይነት አማራጮች በቅናሽ ለተጠቃሚ የሚያቀርቡበትን መንገድ ቢያመቻቹ ይመረጣል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ሚኒስትሮቻቸው ከእነ ቤተሰባቸው በእዚህ ሁኔታ ምግቡን አሰናድተው እየተመገቡ ለሕዝቡ አርዓያ ቢሆኑና አልፎም ተርፎ በጓሯቸው ተክሎቹን አራብተው ቢታዩ ትክክለኛው መንገድ ይሆን ነበር። “ሎሚ ካልመጠጡት እንቧይ” እንዲሉ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም የነገሩን ዓላማ በቅጡ ባለማስገንዘባቸው፣ ማኅበረሰቡም እንደ ዋዛ ተቀብሎ ለቀልድ ፍጆታው አዋለው።

በሁለተኝነት የሚተቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩን የስርፀት መንገድ ከመመልከታችን በፊት፣ እኛም በደፈናው አንድ ሁለት የኢኮኖሚ ጽንሰ ሐሳቦችን ማንሳት ይገባናል። የመጀመርያው የኢኮኖሚ ጽንሰ ሐሳብ፣ የገንዘብ የመግዛት አቅም መቀነስ ወይም በአጠቃላይ በኢኮኖሚ ውስጥ የሸቀጦችና የአገልግሎት ዋጋ መጨመር፣ ወይም የሸቀጦችና አገልግሎቶች አጠቃላይ የዋጋ ደረጃ የሚጨምርበት ፍጥነት የሚል ትርጓሜን ለሚይዘው የዋጋ ግሽበት (Inflation) መነሻ መሠረት ተደርገው ከሚወሰዱ ዋነኛ ምክንያቶች መካከል አንደኛው፣ በማምረቻ ዋጋ መጨመር የሚከሰት (Cost-push Inflation) ሲሆን ለእዚህ ምሳሌ ሆኖ መቅረብ የሚችለው የነዳጅ ዋጋ በመወደዱ ትራንስፖርትን ጨምሮ ሌሎች ግብዓቶችም ተያይዘው በመወደዳቸው፣ በንግዱና በአገልግሎት ዘርፉ ላይ ያለው ግብይት እየናረና እየተወደደ መጥቷል የምንለው ነው። ይህንን ሁኔታ በአገራችን ባለው የዋጋ ግሽበት (Inflation) ዋነኛው ምክንያት ተደርጎ መወሰድ የሚችል ነው።

ሁለተኛው ምክንያት የሸቀጦችና የአገልግሎት አቅርቦቱ መቀነስና በፍላጎት ግሽበት ወይም መጨመር (Demand-pull Inflation) ምክንያት የሚቀሰቀስ የዋጋ ግሽበት (Inflation) በሚል ይጠቀሳል። ለዚህኛው ደግሞ እንደ ምሳሌ የምናነሳው አንደኛ የጤፍና የዘይት አቅርቦት (Supply) እጥረት በማጋጠሙ፣ የዘይትና የጤፍን ፍላጎት ለማሟላት ብዙ የከፈለ አሸናፊ እንደሚሆነው ወይም ነጋዴው ብዙ ለማስከፈል በራስ መተማመኑ እንደሚጨምረው ልንል እንችላለን። ሌላው ደግሞ ማኅበረሰቡ ዘይትና ጤፍ ላይ ያለው አጠቃላይ ፍላጎት ሲጨምር ወይም በከፍተኛ ደረጃ ያለ አማራጭ ጥገኛ ሲሆን፣ የዘይትና የጤፍ ዋጋ ለመጨመሩ ወይም ነጋዴው ዋጋ ቢጨምር እንኳን ዕቃውን ማኅበረሰቡ እንደሚያነሳለት የልብ ልብ ተሰምቶት ዋጋውን ለማናር ምቹ አጋጣሚ ሲሆንለት ማለት ነው።

ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አማራጭ ምግብ ለመጠቆም ማሰባቸው፣ ‹‹ማኅበረሰቡን በውስን ምግቦች ላይ ጥገኛ በመሆንህ ወይም ፍላጎትህ በመጨመሩ በአጠቃላይ ፍላጎት መጨመር ሳቢያ በሚከሰተው የዋጋ ንረት (Demand-pull Inflation) እየተጠቃህ ነው፣ ስለዚህ ፍላጎትህን ወደ ሌሎች የምግብ አማራጮች አዙር፤›› እያሉን ነው። ይህ ማለት ደግሞ ወደ ሌላ የኢኮኖሚ ጽንሰ ሐሳብ ያሻግረናል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተተኪ የፍጆታ ዕቃ ውጤት (Substitution Effect) በገበያው ውስጥ ወይም በአጠቃላይ የፍጆታ ዕቃ ፍላጎት ውስጥ መፍጠር አስበዋል፣ ወይም ማኅበረሰቡን በውጤቱ ተጠቃሚ ለማድረግ ቆርጠዋል፣ ማለት ነው።

የተተኪ የፍጆታ ዕቃ ውጤት (Substitution Effect) ምንድነው? የሚለውን ከማየታችን በፊት፣ የሚተካኩ ዕቃዎች (Substitute Goods) ምንድናቸው? የሚለውን መመልከት አለብን። ተተኪ ዕቃዎች በተመሳሳይ ሸማቾች ለተመሳሳይ ዓላማ ሊውሉ ወይም የደንበኞቹን ተመሳሳይ ፍላጎቶች ሙሉ በሙሉ፣ ወይም በከፊል ሊያሟሉ የሚችሉ ቢያንስ ሁለት ምርቶች ናቸው። የአንደኛው ምርት ዋጋ ቢጨምር ወይም ቢወድቅ፣ የተተኪው ዕቃ ፍላጎት ሊጨምር ወይም ሊቀንስ ይችላል።  ለምሳሌ ፔፕሲ ኮላና ኮካ ኮላ ካነሳን አንዱ ለአንዱ ሁነኛ ምትክ ነው። ይህ ማለት የኮካ ኮላ ዋጋ ሲጨምር፣ የፔፕሲ ኮላ ፍላጎት ከጊዜ በኋላ ይጨምራል (ፔፕሲ ዋጋውን ካላሳደገ)። በውጭው ዓለም ቅቤና ማርጋሪን የተለመዱ የተተካኪ ዕቃዎች ምሳሌዎች ናቸው። አንድ ሰው የታክሲ የጉዞ ዋጋ ቢወደድ በአውቶቡስ ወይም በብስክሌት መጓዝ ይችላል። ስለዚህ አውቶቡሶች ወይም ብስክሌቶች ለታክሲ ትራንስፖርት ምትክ የሚሆኑ ናቸው።

በእኛ አገር ሁኔታ የጤፍ፣ የገብስ፣ የስንዴ፣ የሩዝ እንጀራ ወይም በዘይት ተዘጋጅተው የሚበሉ ወይም ያለ ዘይት ተዘጋጅተው የሚቀርቡ ምግቦችን በምሳሌነት ማንሳት እንችላለን። ይህንን ካነሳን የተተኪ የፍጆታ ዕቃ ውጤት ለመረዳት ይቀለናል፡፡ ወይም አንድ የፍጆታ ዕቃ ከሌሎች ተተኪ ዕቃዎች ጋር ሲነፃፀር፣ በዕቃው ላይ በተመጣጣኝ የዋጋ ለውጥ ምክንያት የፍላጎት ለውጥን (Shift in Demand) እንደሚያመለክት እንገነዘባለን። ለምሳሌ የጤፍ እንጀራ ዋጋ እንዳለ ሆኖ  የገብስ፣ የስንዴና የሩዝ እንጀራ ዋጋ ዝቅ ቢል ፍላጎት ይጨምራል ማለት ነው።

ታዲያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለተወደዱብን የፍጆታ ዕቃዎች መነሻው ፍላጎታችን በውስን ምግቦች ላይ በማተኮሩ ወይም ከፍ ብሎ በመታየቱ ከመሆኑ የመነጨ (Demand Pull Inflation) መሆኑን ተገንዝበው ተተኪ ምርት (Substitute  Goods) በመጠቆም፣ የተተኪ ምርት ውጤት  (Substitution Effect) መፍጠር እንደፈለጉ ከተረዳን ሐሳባቸው ለምን መቀለጃ ሆነ? ለሚለው መልሱ አንደኛ ነገሩ እንደ ዋዛ በተገኘው አጋጣሚ የሚነገር ሳይሆን፣ ከላይ እንዳየነው የኢኮኖሚ ጽንሰ ሐሳቦችንና ባለሙያዎችን አቅርበው፣ እንዲሁም የፖሊሲ ማዕቀፍ አዘጋጅተው አቅጣጫ ሊያስቀምጡለትና ሐሳባቸውን ለዜጎች ማስረፅ ይገባቸው ነበር።

ሁለተኛ ለተተኪ ምርት ውጤቱ (Substitute Effect) ለመፍጠር ተተኪ ምርት ሆኖ የቀረበው ሙዝ በጭራሽ መነሳት እንኳን ያልነበረበት ነበር። ይልቁንም ተተኪውን ምርት በቅናሽ አቅርበው ‹‹የአገሬ ሕዝብ ጤፍ በአገርህ እየተመረተ ኪሎውን መቶ ብር እየገዛህ ያለኸው የሙጥኝ ስላልከው ነው። ስለዚህ የሰሜኑ የአገራችን ክፍል ስንዴንና ገብስን፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሩዝን አላምደው እንጀራ ያደረጉበትን መንገድ እየተጠቀምክ ብትመገብ ጤፍ ላይ የነበረው ከፍተኛ ፍላጎት ሲቀንስ ዋጋው አብሮ ይረክሳል፡፡ ባይረክስም የችግሩ ሰለባ አትሆንም፣ ወይም በዘይት የሚሠሩ ምግቦች ላይ ያለህን ልክ ያጣ የሚመስለው ፍላጎት በዘይት ወደ የማይዘጋጅ የአርሲ ሰው ገንፎና በሶ አድርጎ የሚጠቀመውን ገብስ ወይም በደቡብ ኢትዮጵያ እንደተለመደው በቆሎን ለገንፎም ይሁን ወደሌላ መልክ ቀይረህ መመገብ ብትችል፣ የዘይት ፍላጎት ይቀንሳል ዋጋው ይረክሳል፡፡ ባይረክስም የችግሩ ሰለባ አትሆንም፤›› ቢሉን መልካም ነበር፡፡ ይህም ቢሆን ጥንተ መሠረት ካለው የኢትዮጵያ የምግብ ባህል ጋር መላተም ወይም የባህል አብዮት ነውና በልዩ የፖሊሲ ማዕቀፍ ታግዞ የንግድ ማዕከላት ምርቶቹን በርካሽ እንዲያቀርቡ፣ ሬስቶራንቶች ምግብ አዘጋጅተውበት ለተጠቃሚ ተደራሽ እንዲያደርጉ ቢደረግ፣ አሁንም ጠቅላይ ሚኒስትሩና ሚኒስትሮቻቸው ከእነ ቤተሰባቸው በእዚህ ሁኔታ ምግቡን አሰናድተው እየተመገቡ ለሕዝቡ አርዓያ ቢሆኑ ሐሳቡ ሚዛን ይደፋና ግቡን ይመታ ነበር። ሆኖም ዳቦ ካልገመጡት ድንጋይ ነውና ምን እያሉ እንዳለ በግልጽ ያልሰረፀለት ዜጋ የገባውን ወስዶ ለፌዝ (ሚም) ፍጆታው አዋለው።

አንድ ሰው የደረሰበትን ውሳኔ ‹‹ልብ ያመላለሰውን፣ ኩላሊት ያጤሰውን›› ተብሎ መጠቀሱ፣ አገራዊ ውሳኔ የመሪውና ተመሪው ለአንድ ውጥን ሊኖራቸው ስለሚገባው ወጥ የሆነ ግንዛቤ በምሳሌነት የሚያበክር ቢሆንም፣ ስርፀቱ አግባቡን ሲስት ግን ውጤቱ ከመግባባት ይልቅ በአንድ ቋንቋ እንዳልተግባቡት የባቢሎን ሰዎችን እንደ መሆን ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል [email protected] አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...