Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ኧረ እየተናበብን!

እነሆ ከሜክሲኮ ወደ ፒያሳ ልንጓዝ ነው። ትናንት የበረደው ዛሬ እየወበቀው፣ ከጥጋብ ወደ ረሃብ እየተንሸራተተ፣ ከመፅዋችነት ወደ ተመፅዋችነት እየተንፏቀቀ፣ ከአፋፉ ወደ ቁልቁለቱ ሲንደረደር እናያለን። መኖር የማያሳየን የለም። እግር ይራመድ እንጂ እስትንፋስ እስካለ ብዙ ይታያል። ወዲህ በሳቅ ፍርስ ስንል ወዲያ ደግሞ ተንሰቅስቀን ስናለቅስ፣ በተቃራኒ ስሜቶችና ሁነቶች የተገነባች ዓለም ውስጥ የሞት ሽረት ትግል እናደርጋለን። ታክሲያችን እየሞላች ነው። የአንገታቸው ቆዳ መሟሸሽና አስተጣጠፍ ያስተክዛል። እርጅና ብርታት ነፍጓቸው ሳያበቃ ጡንቻቸው ምርኩዛቸውን አጥብቆ አልይዘው እያለ ከእጃቸው ያፈተልካል። አዛውንቷ በሁለት ወጣቶች ተደግፈው ታክሲዋ ላይ ወጡ። ሦስት ተሳፋሪዎች ይቀሯታል። ጋቢና ሁለት መልከ መልካም ሴቶች፣ ከሾፌሩ ጀርባ አዛውንቷ፣ ቀጥሎ እኔና አንድ ጎልማሳ፣ ሦስተኛው ረድፍ ላይ አዛውንቷን ደግፈው ያሳፈሩት ወጣቶች ተሰይመዋል። መጨረሻ ወንበር አንዲት ወይዘሮና የማኅበራዊ ድረ ገጽ ማማ ላይ ቀልቧ የተረሳት ወጣት አሉ። ወያላው በአንድ እጁ ትኩስ ሻይ ይዞ ፉት እያለ፣ በግራው በዘይት የወዛ ፓስቲ እየገመጠ ከንፈሩን አሞጥሙጦ ብቻ ግቡ ይላል። የህልውና ትግል!

“አይ ጉድ እህል ክብሩን ጣለ። ለነገሩ ዘንድሮ ምን ክብሩን ያልጣለ ነገር አለ?” ይላሉ አዛውንቷ። ጎልማሳው ብዙ እንዲያወሩ ፈልጎ ፈገግታ ያሳያቸዋል። “እንዲህ መንገድ ላይ የጎረሱት አንጀት ጠብ ይላል? ምናለበት ዘወር ብሎ ቢበላ?” ብለው፣ “ሁሉም ነገር መንገድ ለመንገድ የሆነበት ጊዜ። እንዲያው እንዲህ ያለ ዘመን…” ብለው ከራሳቸው ጋር የተጣሉ መስለው፣ “ተመሥገን ነው መብላት መቻሉም። በኋላ እኮ ዕዳው ለእኛ ነው…” አላቸው ወያላውን እያስተዋለ ጎልማሳው። “አሁንስ መቼ ይቀርልናል? እውነትህን ነው፣ አፍና እጅ መገናኘት ሲያቅታቸው አደጋው ለእኛ ነው…” ብለው ትንሽ አሰብ አድርገው ቀጠሉ። “ለነገሩ የሚበላ ከተገኝ ለምን መንገድ ላይ ተበላ ማለት ልክ አይደለም፡፡ ያው የድሮው አለቅ ብሎኝ እንጂ እኔማ ምን አግብቶኝ ልጄ? የሚያሳዝነኝ ግን በአግባቡ የሚበላ ሳይኖረን የምናመነዥከው አጀንዳ መብዛቱ ነው። የአጀንዳው ብዛት ሠርተን እንድንለወጥ ቢጠቅመን እኮ ጥሩ ነበር፡፡ ግን እርስ በርስ እየተናቆርን ሽቅብና ቁልቁል እየተያየን እንድንበላላ ማድረጉ ነው የሚቆጨው…” ብለው አዛውንቷ እንደ ማዘን አሉ። እሳቸው በየጊዜው የሚፈጠርልንን አጀንዳ ከወቅታዊ ጭቅጭቃችን ጋር ለማዛመድ እንደፈለጉ ተሸራርፎ ሲገባን፣ ‘አይ የገባቸው እናት’ አልን። እንዲያ ነው!

ከአዛውንቷ አጠገብ ሲናገር የሚጣደፍና የሚኮላተፍ ጎረምሳ ገብቶ ከመቀመጡ፣  መጨረሻ ወንበር ሁለት ኮረዶች ከመሰየማቸው፣ ወያላው እጁ ላይ የተቅለጠለጠውን ዘይት በፊቱና በፀጉሩ እየጠረገ “ሳበው” ብሎ በሩን ዘጋ። ታክሲያችን መንቀሳቀስ ጀመረ። ሲናገር የሚጣደፈው ከአዛውንቷ አጠገብ የተሰየመው ኮልታፋ ተሳፋሪ፣ “እኛ ከተማው በግራጫ ቀለም ሊወለወል ነው እያልን የሳምንቱን አጀንዳችንን እናወራርዳለን፣ አንተ ደግሞ በፓስቲ ዘይት ራስህን ታወዛለህ…” ሲል ወያላውን ያናግረዋል። “ግድ ነዋ በዚህ ኑሮ ላይ የቅባት ወጪ ተጨምሮ ይቻላል ታዲያ? ከተማው ግራጫ ቀለም ይቀባል የሚል ወሬ ሲናፈስብህ ወይ ቀለሙን አቅርብ፣ ወይ ፋብሪካ ክፈትና ቢዝነሱን ተቀላቀል አትፍዘዝ፡፡ ልክ አይደለሁ እንዴ?” እያለ ወያላው ጋቢና ወደ ተቀመጡት ቆነጃጅት አስግጎ ይጠይቃል። ትከሻቸውን ሰብቀው ዝም ሲሉት ከፍቶት “ሒሳብ ወጣ… ወጣ…” ብሎ ፊቱን ዘፈዘፈው። ችኩሉ አሁንም በቸኮለ አነጋገር፣ “ኧረ አረጋጋው በግራጫ የተጀመረውን ጨዋታ በቀይ ካላቀላሁ ትላለህ እንዴ?” ሲለው ወያላው ሳቀ። ይኼን ጊዜ ጎልማሳው ቀበል አድርጎ፣ “ጊዜው አወዛጋቢ ነው። ነገሩ ፈጣን፣ ጭቅጭቁ ፈጣን፣ ዕድገቱ ፈጣን፣ ውድቀቱ ፈጣን፣ ጋብቻው ፈጣን፣ ፍቺው ፈጣን፣ ሁሉም ነገር ፈጣን። ኧረ ተጨማሪ 30 ደቂቃ ናፈቀን። አልናፈቀህም ሁለተኛ ዕድል?” አለ ወደ እኔ ዞሮ። “ምን ታረጊዋለሽ?’ የሚለውን ዘፈን መስማት ነው…” አለ ኮልታፋው ፊቱን አዙሮ። “ቆይ ግን እኛ ዘፈን ብቻ እየተገባበዝን እስከ መቼ?” አለ ጎልማሳው የሞቀ ፈገግታ እየለገሰው። “በየሳምንቱ አዳዲስ አጀንዳ እየተገባበዝን እኮ ነው ግራጫ ላይ የደረስነው…” አለ ኮልታፋው። ይናገረዋል!

ይኼኔ “እንዲህ ነው ነገሩ?!” ብለው አዛውንቷ አፋቸውን በመዳፋቸው ሲጋርዱ ሁላችንም ፈገግ አልን። “ምነው እማማ?” ጠየቃቸው ጎልማሳው። “አይ ተወኝ ወዲህ ነው…” አሉት። “ፖለቲካ ይፈራሉ?” ብሎ ኮልታፋው ሲጠይቃቸው፣ “እኔ ፖለቲካና ሰይጣን አልፈራም፣ ፈጣሪ አምላኬን እንጂ። እንዲያው የሰማዩንም የምድሩንም መጠየቅ አቁመን የት ልንደርስ እንደምንችል ግራ ገብቶኝ ነው…” ብለው ዝም ሲሉ ለጊዜው ዝምታ ሰፈነ። ጋቢና ከተቀመጡት ቆነጃጅት አንዷ፣ “አንቺ ይህች ልጅ ግን አታፍርም? በእኔ ቀለመ ደማቅ ሹራቦች ነው አሥር ጊዜ ፎቶ እየተነሳች ‘ፖስት’ የምታደርገው? እኔማ እጽፍላታለሁ…” ብላ ለ‘ኮሜንት’ ስትንደረደር ሁሉም ካቀረቀረበት ቀና ብሎ ወደ ጋቢና ያይ ጀመር። “ኧረ ነውር ነው። ምን ነክቶሻል? ‘እጀ ጠባብህን ቢወስድብህ መጎናፀፊያህን አትከልክለው’ እያለ መጽሐፉ አንቺ ለጨርቅ አብረሻት ትገመቻለሽ፣ ተይው ይመርባት። የሁለታችሁም የቀለም ተመሳሳይነት አይገርምም ግን? ቀይ፣ ሰማያዊ፣ ነጭና ጥቁር ያስደስታችኋል…” ብላ ጓደኛዋ ልታረጋጋት ስትጥር፣ “ታዲያስ አንዳንዴ ግን ቢጫና ግራጫ እየቀላቀለች ታናድደኛለች…” አለችና ‘ኮሜንት’ መጻፍ ጀመረች። ጎልማሳው ወደ ጆሮዬ ጠጋ ብሎ፣ “የሰው ሕይወት እኮ በዘመኑ የፖለቲካ አጀንዳ እየተጠለፈ ነው። በሰው ላብ የሚሸለመው፣ በሰው ፕሮፖዛል ጨረታ የሚያሸንፈው፣ በሰው ደም እጁን እየተለቃለቀ ለልጅ ልጆቹ የደም ዕዳ የሚያወርሰውን እያየን እንዳላየን ስናልፈው መኖራችን አያበሳጭም? ዕድሜ ለ‘ፌስቡክ’ ግን ቢያንስ አየህ ማንም የሚሰማን ባይኖር፣ ማንም ኮሜንታችን መስጦት ‘ላይክ’ ባያደርገው ተናግሮ እንደ መተንፈስ ያለ ፈውስ የለም…” ይለኛል። ‘ኮሜንቱ’ ሁሉ በስድብ ጀምሮ በስድብ ባያልቅ መልካም ነበር!

ጉዟችን ቀጥሏል። ጥቁር ሻሽ ያሰረች አንዲት የገጠር ደርባባ ታክሲያችንን አስቁማ ገባች። ስልክ እያወራች ነው። ስለወዳጅ ዘመዶቿ ጤንነት ጥቂት ስትጠያይቅ ቆየች። ወዲያው አንድ የቅርቧ ሰው መሞቱን ተረዳች መሰል ጩኸቷን አቀለጠችው። ገሚሱ ማባበል ጀመረ። ሌላው “ተዋት! ማልቀስ እኮ ሰብዓዊ መብቷ ነው…” ይላል። እዬዬው አልበቃን ብሎ የመብት ክርክሩ ጦፈ። “ኧረ እንዲያውም ከቻለች የእኛን ጨምራ ታልቅስ። ሐዘን የበዛበት ኑሮአችን ዕንባችንንና ደመወዛችንን ጨረሰው…” ሲል አንዱ፣ “የማንን ዕንባ ማን ያፈሳል? የማንን ፍርድ ማን ይቀበላል? የዘራነውንማ እንጨድ እንጂ ተውን…” ይላል ሌላው። ሾፌሩ ጭቅጭቁን ከምንጩ አደርቃለሁ ብሎ፣ “ሃሎ ከአንድ እስከ ሦስት እስክቆጥር ማልቀስ ካላቆምሽ ታሪፉን እጥፍ የሚያስከፍል ማዕቀብ ይጣልብሻል…” ሲላት፣ “ለምን ደግሞ በገዛ ዕንባዬ?” ብላ አንባረቀችበት። ሾፌሩ ‘እውነት ይህች ልጅ ከዩክሬን ናት ወይስ ከሩሲያ?’ ሳይል ቀረ? ይኼኔ ጎልማሳው፣ “አይ የሰው ልጅ ለእንጀራው ሲባክን የወዳጅ ዘመዱን ሞት መንገድ ለመንገድ ይረዳ ጀመር?” ሲለኝ ከጀርባችን ከተቀመጡት ወጣቶች አንዱ፣ “ኧረ ታልቅስበት? እኛስ ከተማው ግራጫ በግራጫ ሊሆን ነው ብለን እየተላቀስን አይደለም እንዴ…” እያለ ሲስቅ ጓደኞቹ አጀቡት፡፡ ለማጀብ ማን ሰንፎ!

ወደ መዳረሻችን እየተቃረብን ነው። ጫጫታው ቀንሷል። ወያላው መልስ እየመለሰ ደርሶ እንባዋ ኩልል እያለ ለሚያስቸግራት ልጅ የሶፍት መዋጮ ያመላልሳል። መጨረሻ ወንበር ድምጿ ሳይሰማ የተቀመጠችው ወይዘሮ፣ “ይኼኔ የሰውን ሕይወት፣ የአገርን የድህነት ታሪክ የሚቀይር መዋጮ አስፈልጎ ቢሆን ኖሮ የአሁኑን ያህል ባልሆንን ነበር…” አለች። “ምን ነካሽ? የእኛ ሰው የምር ለውጥ ቢወድ ከኋላው ተነስተው ጃፓንና ቻይና ጥለውት ይሄዱ ነበር?” አለ ሦስተኛው ረድፍ ላይ ከተቀመጡት ወጣቶች አንዱ። “ምን ይደረግ? ሲበልጡን አንወድ። ከቀደሙን አንማር። ደርሶ ሰው ቁልቁል ስናይ ነው መንፈሳችን የሚረካው። ይኼ ቁልቁል ለመተያየት ስንከፋፋ፣ ስንዳማና ስንነፋፈግ ኖረን ኖረን ይኼው ዛሬ የሚወረር መሬት እናያለን፣ መሬት የግል እንደሆነ ሁሉ…” አለ ኮልታፋው። “እንዲያው በምን ቀን ብንፈጠር ይሆን?” ስትል አዛውንቷ ቀበል አድርገው፣ “በሰኔና በሰኞ…” አሉ። ወያላው “መጨረሻ” ብሎ በሩን ሲከፍተው “ሰኔና ሰኞ ቢሆን ነው ልጄ ካልጠፋ አጀንዳ ቀለም የሚያነታርከን፣ ግራ ሲገባን እኮ ነው ትናንት የተናገርነውን ዛሬ ሽምጥጥ አድርገን እየካድን ትዝብት የምናተርፈው፡፡ ኧረ ወገኖቼ እየተናበብን…” እያሉ አዛውንቷ ወርደው ተሰናብተውን ሲሄዱ እኛም በየአቅጣጫው ተበታተንን፡፡ መልካም ጉዞ! 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት