- እሺ ዛሬ ውሎሽ እንዴት ነበር?
- ያው እንደተለመደው ነው?
- እንደተለመደው ማለት?
- ያው አንዱ ቢሮ ስሄድ እዚህ አይደለም እዚያኛው ነው ይላሉ። እዚያም ስሄድ እዚያኛው ነው ይላሉ…
- ምንድነው ችግሩ?
- እኔን ነው የጠየከኝ?
- ሌላ ማን አለ?
- ሚኒስትሩ አንተ ነህ ብዬ ነዋ?
- እስኪ ነገር ማጣመሙን ትተሽ ተቋሙ የሚለውን ንገሪኝ ምን ችግር ገጠመኝ ነው የምትይው?
- የተሽከርካሪ ሰሌዳ ነው ችግሩ። አቤት የሚጉላላው ሕዝብ ብዛቱ?
- ስም ማዘዋወሩን ጨርሰሻል?
- እሱማ ካለቀ ቆየ። የተሽከርካሪ ሰሌዳ ነው ማግኘት ያልታቻለው።
- እንዴት የተሽከርካሪ ሰሌዳ ችግር ይፈጠራል?
- እኔ ምን አውቄ ታርጋ ቁጥሩ የሚጻፍበት ሰማያዊ ቀለም የለም ነው የሚሉት?
- ቀለም?
- አዎ። ሰማያዊ ቀለም እጥረት በመፈጠሩ የተሽከርካሪ ሰሌዳ ማተም አልተቻለም ነው የሚሉት።
- እና ችግሩ መቼ ይፈታል አሉ?
- ሲደርስ እንደውላለን ነው የሚሉት።
- ወይ ጉድ?
- እኔማ ቢቸግረኝ በሰሞኑ ቀለም ስጡን አልኳቸው?
- የሰሞኑ ቀለም ደግሞ ምንድነው?
- ግራጫ!
[ክቡር ሚኒስትሩ በፍትሕ ዘርፍ ማሻሻያ የተገኙ ውጤቶችን በተመለከተ ከአማካሪያቸው ጋር እየተወያዩ ነው]
- ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር ይኸው በቀጠሮአችን መሠረት ተገኝቻለሁ።
- መልካም። የዛሬ አጀንዳችን የሚሆነው የፍትሕ ዘርፍ ማሻሻያ ፕሮግራማችን ያስገኛቸውን ውጤቶች ለመዳሰስና ለተወካዮች ምክር ቤት በምናቀርበው ሪፖርት ውስጥ ቢካተቱ የምንላቸውን ለመለየት ነው።
- ክቡር ሚኒስትር ለምክር ቤት የሚቀርበውን ሪፖርት ማዘግየት አይቻልም?
- ለምን?
- ወይም የፍትሕ ዘርፍ ማሻሻያ ፕሮግራማችንን አፈጻጸም ብቻ ለሌላ ጊዜ ብናቆየውስ?
- እንዴት ያልተሟላ ሪፖርት ይዘን እንቀርባለን? በዚያ ላይ የፍትሕ ዘርፍ ማሻሻያ የተቋማችን ዓብይ ተግባር አይደለም እንዴ?
- እሱማ ልክ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ታዲያ ምንድነው የምትለው?
- ከፍተኛ ወቀሳ እንዳይቀርብብን ሠግቼ ነው?
- የተገልጋዮች እርካታን በተመለከተ ሰሞኑን ያደረግነው ጥናት ከፍተኛ ውጤት መገኘቱን አረጋግጧል ብላችሁ ሪፖርት አቅርባችሁ አልነበረም?
- ልክ ነው ክቡር ሚኒስትር የተገልጋዮች እርካታ 80 በመቶ መሆኑን በጥናት አረጋግጠናል።
- እና ምንድነው ያሠጋህ?
- አንዱ ሥጋቴ በመቶኛ ያስቀመጥነውን የተገልጋዮች እርካታ ውጤት በቁጥር አስቀምጡ እንዳንባል ነው።
- ቢባል ምን ችግር አለው?
- የተገልጋዩቹን ብዛት በቁጥር ከተጠየቅን አነስተኛ ነው። ይህ ደግሞ ተቋማችንን ያስወቅሳል።
- ስለዚህ እሱን በጥናቱ እንደቀረበው በመቶኛ እናስቀምጣለን።
- የግድ በቁጥር ግለጹ ብንባልስ?
- መቶኛም እኮ ቁጥር ነው እንላለን ካልሆነም…
- ካልሆነ ምን ክቡር ሚኒስትር?
- ጥናቱን ያካሄደው አማካሪ ውጤቱን ያቀረበው በመቶኛ ነው እንላለን።
- እንደዛ ማለት ይቻላል?
- ለምን አይቻልም?
- አማካሪው ውጤቱን በቁጥር እንዲገልጽ እንዴት አላደረጋችሁም ተብለን ብንጠየቅስ?
- በቁጥር እንዲገለጽ በጀት ስላልተያዘ ነው እንላለን።
- እንደዛ ይቻላል?
- ለምን አይቻልም?
- እንዴት በጀት አልተያዘም ተብለን ብንጠየቅስ?
- ከህልውና ዘመቻው ጋር በተያያዘ ነው እንላለን።
- ከህልውና ዘመቻው ጋር ምን አገናኘው ብንባልስ?
- በህልውና ዘመቻው ምክንያት ሁሉም ተቋማት በጀት እንዲቆጥቡ መንግሥት በማዘዙ መሆኑን እንገልጻለን።
- እንደዛ ማድረግ ከተቻለ ጥሩ ነው። ነገር ግን…
- ነገር ግን ምን?
- አሁንም ሪፖርቱን ካላዘገየነው ከወቀሳ የምንድን አይመስለኝም፡፡
- ለምን?
- ምክንያቱም በፍትሕ ዘርፍ ማሻሻያ ቃል ከገባናቸው በርካታ ጉዳዮች መካከል በዋናው ጉዳይ ላይ ምን ለውጥ አልመጣም።
- ምን ነበር ዋናው ጉዳይ?
- ሳናጣራ አናስርም፣ እያሰርን አንመረምርም የሚለው ነው።
- እና ምንም የተገኘ ለውጥ የለም?
- ምንም ለውጥ የለም ወደ እርስዎ ቢሮ ከመግባቴ በፊትም በዚህ ጉዳይ ላይ ከፍተኛ ወቀሳ ደርሶኛል።
- የምን ወቀሳ! ማነው ያቀረበው?
- የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ነው።
- ምንድነው የሚሉት እነሱ ደግሞ?
- በየአካባቢው ሰዎች ተይዘው እየተሰወሩ ነው። ቤተሰቦቻቸው ብቻ ሳይሆኑ የኮሚሽኑ መርማሪዎችም የታሰሩትን ዜጎች ፈልገው ማግኘት አልቻሉም ነው የሚለው።
- የት የት ፈልግን ነው የሚለው ኮሚሽኑ?
- በፌዴራልም ሆነ በየክልሉ የሕግ አስከባሪ ተቋማት ዞረን ማግኘት አልቻልንም ነው የሚለው ኮሚሽኑ።
- እዚያ ምን አዞራቸው እነሱ?
- ተጠርጣሪዎች የሚታሰሩት በነዚህ ተቋማት ስለሆነ ነዋ ክቡር ሚኒስትር?
- በነዚህ ተቋማት ብቻ አይደለም፡፡
- ከነዚህ ተቋማት ውጪ ሰዎችን የማሰር ሥልጣን ያለው ሌላ አካል አለ ክቡር ሚኒስትር?
- በፍትሕ ዘርፍ ማሻሻያው ሌላ ተጨምሯል!