Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹ታሪክ እርግማን መሆኑ ቀርቶ በረከት እንዲሆን ሁላችንም መሀል መንገድ ላይ ለመገናኘት መጣር...

‹‹ታሪክ እርግማን መሆኑ ቀርቶ በረከት እንዲሆን ሁላችንም መሀል መንገድ ላይ ለመገናኘት መጣር ይኖርብናል››

ቀን:

ባህሩ ዘውዴ (ፕሮፌሰር)፣ የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ፕሬዚዳንት

የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማኅበር ባካሄደው ዓውደ ጥናት ላይ ንግግር ያደረጉት የታሪክ ተመራማሪውና የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማኅበርና ፕሬዚዳንት ባህሩ ዘውዴ (ፕሮፌሰር)፣ ዘመናዊት ኢትዮጵያን ለመፍጠር የተሄደበት ጉዞ አባጣ ጎርባጣ እንደነበር አስታውሰው፣ የታሪክ ባለሙያዎችም ከማንም ባልተናነሰ ዘግበውታል አሉ፡፡

‹‹ልዩነቱ የሚመጣው ያን አባጣ ጎርባጣውን ስናሰላስል እንኑር? ወይስ እሱን ዘግበን ወደ ተሻለ ሥርዓት እንሸጋገር የሚለው ላይ ነው፡፡ ስለሆነም ታሪክ እርግማን መሆኑ ቀርቶ በረከት እንዲሆን፣ ሁላችንም መሀል መንገድ ላይ ለመገናኘት መጣር ይኖርብናል፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማኅበር ‹‹አገራዊ መግባባት ለመፍጠር ታሪክ ያለው ሚና›› በሚል ርዕስ፣ የተለያዩ የታሪክ ምሁራን ለአገራዊ መግባባት ያግዛሉ ያሏቸውን የጥናት ጽሑፎች የሚያቀርቡበት የሁለት ቀናት ዓውደ ጥናት ማክሰኞ ግንቦት 16 ቀን 2014 ዓ.ም. በአምባሳደር ሆቴል አስጀምሯል፡፡

የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ባህሩ ዘውዴ (ፕሮፌሰር) እንዳስታወቁት፣ ዓውደ ጥናቱ የማኅበሩን ዳግም ምሥረታ ከማክበር ጎን ለጎን በዓበይት የታሪክ ጉዳዮች ላይ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ጥልቅ ውይይት ይካሄድበታል ነው፡፡

የኢትዮጵያ ታሪክ አጻጻፍ ጉዞ፣ የታሪክ ባለሙያዎች ማኅበርን ለማቋቋም ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ጀምሮ የተደረጉ ጥረቶች፣ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችን ታሪክ በምልዓት ለመጻፍ የታቀደው ፕሮጀክት፣ ለከፍተኛ ትምህርት ጀማሪ ተማሪዎች እንደገና መስጠት የታሰበው አጠቃላይ የኢትዮጵያ ታሪክ መርሐ ግብር ዕጣ ፈንታ፣ በአገራዊ ታሪክና ብሔረሳባዊ ታሪክ መካከል ስለተፈጠረው አላስፈላጊ ተቃርኖና ሌሎችም ርዕሰ ጉዳዮችን የተመለከቱ ጽሑፎች በዓውደ ጥናቱ ላይ ቀርበዋል፡፡

ባህሩ (ፕሮፌሰር) እንደሚሉት፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ያለው የተቃርኖ መንስዔ የተለያየ የታሪክ አተረጓጎምና  አረዳድ መኖሩ ነው፡፡

በባለሙያዎች የተደረሰበት የታሪክ ድምዳሜ በአንድ በኩል ሲኖር፣ በሌላ በኩል ለተወሰነ የፖለቲካ ዓላማ በማሰብ ወይም መረጃ በማጣት፣ ወይም መረጃ መርጦ ከመጠቀም ፍላጎት በመነሳት ታሪክ ለየት ብሎ የሚቀርብበት አጋጣሚም ይስተዋላል ብለዋል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ደግሞ ለተቃርኖም ሆነ ለግጭት መሠረት መሆናቸውን የታሪክ ተመራማሪው አስረድተዋል፡፡

የታሪክ ባለሙያዎች ማኅበር መኖር፣ ማደግና መጠናከር በታቃርኖ የሚነሱ ጉዳዮችን ለመዳኘት እንደሚመች ተገልጾ ታሪክ ምን እንደሆነ፣ እንዴት እንደሚጻፍ፣ ልክ የሆነውንና ያልሆነውን ለመመልከት ያግዛል ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ያለፈው ታሪክ ብዙ ውጣ ውረድ ያለው እንደሆነ ያስረዱት ባህሩ (ፕሮፌሰር)፣ ይህም ብዙ በጎ ጎኖችና በዚያው ልክ መጥፎ ጎኖችም ያሉት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የታሪክ ጸሐፊዎች የሚያቀርቡት ሁለቱንም እንደሆነ፣ በሌላ በኩል መጥፎውን ብቻ ለማቅረብ የሚፈልጉና በዚያ ላይ የሚተጉ አሉ ብለዋል፡፡

አንድ ዓይነት ገጽታ ከሚያሳይ የታሪክ አቀራረብ መላቀቅ አስፈላጊ እንደሆነ ያስረዱት የታሪክ ተመራማሪው፣ አሉታዊውም ሆነ አዎንታዊው ጉዳይ በሚዛን ተለክተው መቅረባቸው ምናልባት አገራዊ መግባባቱን ሊያመጣ ይችላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ከታሪክ ተቃርኖ ጋር የሚያያዙት ችግሮች የሚፈቱት በምክክርና በውይይት እንደሆነ በዓውደ ጥናቱ ላይ የተገለጸ ሲሆን፣ ለዚያም ዝግጁ መሆንን የሚጠይቅ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

‹‹ታሪክ አሁናዊው የሰዎች ሕይወት ላይ ብዙ ጫና ሊያደርግ አይገባም፤›› ያሉት የታሪክ ምሁሩ፣ ምክንያቱ ደግሞ በዚህ ወቅት ከምንም በላይ እንዲፈታ የሚያስያስፈልግ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ተግዳሮት ስላለ ነው ሲሉ አክለዋል፡፡

በዓውደ ጥናቱ መክፈቻ ላይ የተገኙት የሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዷለም ከታች ከሥርዓተ ትምህርት ጀምሮ በሁሉም ደረጃ ያለው ዜጋ በታሪኩ ላይ ጥልቅ ግንዛቤ እንዲይዝ ካልተደረገ በዚህ ወቅት በአገሪቱ ላይ የሚታዩት ሁኔታዎች በቀላሉ የሚቀረፉ አይደሉም ብለዋል፡፡

ለታሪክ ባለሙያዎች የተመቸ ሁኔታ መፍጠርና የተፈጠሩትን ችግሮች ለመቅረፍ በጋራ መሥራት ይጠበቃል ያሉት ሚኒስትሩ፣ አገሪቱ በዚህ ወቅት ለምትገኝበት ችግር ዋነኞቹ ምክንያቶች ታሪክ በትርክት መተካቱና የዜጎች የታሪክ አረዳድ የተዛባ መሆን ተጠቃሾቹ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ታሪክ የልዩነት ሳይሆን የመግባባትና የመቀራረብ ምንጭ ሊሆን ይገባል ያሉት አቶ ብናልፍ፣ አገሪቱ የገባችባቸውን የታሪክ አረዳድ ችግሮች እንዲፈቱ የመሪነቱን ሚና መጫወት የሚገባቸው የታሪክ ምሁራን መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማኅበር የተመሠረተው በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት እንደነበር፣ ነገር ግን በአብዮቱ ምክንያት መዳከሙን፣ ከዚያም መልሶ ለማቋቋም የተደረገው ጥረት ለረዥም ጊዜ ሳይሳካ ቆይቷል ተብሏል፡፡ የሰላም ሚኒስቴር የታሪክ ምሁራንን ለአራት ቀናት በተለያዩ ጉዳዮች በዝግ እንዲመክሩ ካደረገ በኋላ፣ ዳግም ማኅበሩ ከአንድ ዓመት በፊት መቋቋሙ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...