Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

ጊዜውን የጠበቀ ሕክምና በአዳዲስ ዕውቀት የማጀብ ትልም

አታክልቲ ባራኪ (ዶ/ር) በአለርት ሆስፒታል የፕላስቲክና ሪኮንስትራክሽን ቀዶ ሕክምና ባለሙያና የኢትዮጵያ ቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ የመጀመርያና የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ የተከታተሉት አታክልቲ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በመግባት በሕክምና የመጀመርያ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡ በዚሁ ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ቀዶ ሕክምናን (ጄኔራል ሰርጀሪ) አጥንተዋል፡፡ ኖርዌይ በሚገኘው በርገን ዩኒቨርሲቲ የፕላስቲክና የሀንድ ሰርጀሪ ተምረዋል፡፡ እንዲሁም በግላስኮ፣ በለንደንና ህንድ ኢንተርናሽናል ማሟያ ኮርስ ተከታትለዋል፡፡ በማኅበሩ እንቅስቃሴና በተያያዥ የሕክምና ጉዳዮች ላይ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ የሚገኙ የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች ብዙ ናቸው፡፡ በማኅበሩ በአባልነት የታቀፉት ግን ያን ያህል አይደሉም፡፡ ምክንያቱ ምን ይሆን?

ዶ/ር አታክልቲ፡- ማኅበሩ ከተመሠረተ 26 ዓመታት ሆኖታል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በመላ ኢትዮጵያ ያሉት የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች ወደ አንድ ሺሕ የሚጠጉ ሲሆን፣ በማኅበሩ የታቀፉት ደግሞ ከ300 በላይ ናቸው፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት ብዙ አዳዲስ የሜዲካል ትምህርት ቤቶች ተከፍተው በርካታ ተመራቂዎች ወጥተዋል፡፡ ይህም ቢሆን ማኅበሩ ምን ይጠቅመናል? በሚል የተሳሳተ አመለካከት በአባልነት ሳይመዘገቡ የቀሩ አሉ፡፡ በሙያ ማኅበር መሰባሰብ ወይም መደራጀት የሚያስገኘውን ጥቅም በስፋት ማስረዳት እንዳለብን እንገነዘባለን፡፡ የሙያ ማኅበር አባል መሆን ኩራት ነው፡፡ ማኅበሩ ምን ያደርግልኛል የሚለው ጥያቄ መነሳት የሚችለውም በአባልነት ታቅፎ ማኅበሩ ላይ አስተዋጽኦ ሲደረግ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የሚቀድመው አባል መሆን ነው፡፡ ይህ ከሆነ በኋላ እጅ ለእጅ ተያይዞ ማኅበሩን ከፍ ወዳለ ቦታ ማድረስ ነው፡፡ አባል በመሆን ሰፋ ያለ ዕድል ይገኛል፡፡ በማኅበሩ የመመረጥ፣ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ የማድረግ መብትና ሌሎችንም ጥቅም ያስገኛል፡፡ ውስጡ ሲኮን የማኅበሩን አስተዋጽኦ በግልጽ መረዳት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ አባል ያልሆኑትን የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች ለማሳተፍ ምን እያደረገ ነው?

ዶ/ር አታክልቲ፡- ማኅበሩ በአሁኑ ጊዜ አባል ያልሆኑ የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎችን የሚሰበስብበትን መንገድ በማመቻቸት ላይ ይገኛል፡፡ የማመቻቸቱም እንቅስቃሴ ያተኮረው የግለሰብ ዕድገትን በማፋጠን ላይ ነው፡፡ ይህም ማለት ቀጣይነት ያለው የሕክምና ትምህርት ወይም ሥልጠና መስጠትን ይመለከታል፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን ከጤና ሚኒስቴር ተገቢው ፈቃድ እንዲሰጠን ጠይቀናል፡፡ ጥያቄያችንም በቅርቡ መልስ ያገኛል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድ ደግሞ ማኅበሩ በአባልነት ለመታቀፍ የሚፈልጉ ባለሙያዎችን ለመሳብ በእጅጉ ይጠቅመዋል፡፡ ምክንያቱም ማንኛውም የጤና ባለሙያ ሥልጠና ካልወሰደ በስተቀር ፈቃዱ አይታደስለትም፡፡

ሪፖርተር፡- ስለ ፈቃድ ዕድሳቱ ቢያብራሩልን?

ዶ/ር አታክልቲ፡- ማንኛውም የጤና ባለሙያ ፈቃዱን በየአምስት ዓመቱ ማሳደስ አለበት፡፡ ግዴታም ነው፡፡ ቀደም ሲል የፈቃዱ መቆያ ጊዜ አልፏል? የሚለው ብቻ እየታየ ነበር የሚታደሰው፡፡ አሁን ግን ይህ ዓይነቱ አካሄድ ቀርቶ ባለሙያው በአምስት ዓመቱ ውስጥ የወሰደው ሥልጠና እየታየ ነው የሚታደስለት፡፡ ይህም ማለት ሥልጠና መወሰዱ ከተረጋገጠ ይታደስለታል፡፡ ሥልጠና ካልወሰደ ግን በምንም ዓይነት መንገድ አይታደስለትም፡፡ ፈቃድ ካላሳደሰ ወይም ጭራሽኑ ከሌለው ደግሞ ሥራ መሥራት አይቻልም፡፡ ይህ ዓይነቱ ፖሊሲ የወጣውም በቅርቡ ነው፡፡ ሥልጠና መከታተሉና ፈቃድ የማሳደስ እንቅስቃሴ የጤና ሙያተኛው ወደ ማኅበሩ እንዲገባ ያደርገዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- የማኅበሩን የወደፊት ዕቅድ ምንድን ነው?

ዶ/ር አታክልቲ፡- ማኅበሩ ብዙ ዕቅዶች አሉት፡፡ አንዱና ዋነኛው ዕቅድ የአባላቱን ክህሎትና ዕውቀት ማሻሻል ነው፡፡ በተለይ የሕዝብ ደኅንነት ወይም ጤና የሚረጋገጠው ደረጃውንና ጊዜውን የጠበቀ የሕክምና አገልግሎት ሲሰጥ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በቂ ዕውቀት፣ ክህሎትና ሥነ ምግባር ያስፈልጋል፡፡ የዛሬ አምስት ዓመት የነበረው ዕውቀት አሁን በአዲስና በተሻለ ሊተካ ይችላል፡፡ ስለዚህ የጤና ባለሙያዎች ሁሉ ዕውቀታቸውንና ክህሎቶቻቸውን በማሳደግ ሕክምናቸውን ማከናወን ይገባቸዋል፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን ማኅበሩ አስፈላጊ ዕቃዎችን የማዘጋጀት፣ ሕጋዊ የሆነውን ፈቃድ ማግኘትና ሥራዎችን መጨረስ፣ በወጣው ፖሊሲ መሠረት ለሥልጠናው የሚያስፈልጉ መሥፈርቶችን ማሟላትና ቦታዎችን ማዘጋጀት ይጠበቅበታል፡፡ ሥልጠናው የሚሰጠው እርስ በርስ ስለሆነ ሻል ያለው ሰው ሌላውን ማስተማር ይጠበቅበታል፡፡

ሪፖርተር፡- በተለያዩ የጤና ተቋማት ውስጥ ለቀዶ ሕክምና አገልግሎት የሚውሉ የአላቂና ቋሚ ዕቃዎች እጥረት እንዳለ ይነገራል፡፡ ይህንን በተመለከተ አስተያየት ሊሰጡን ይችላሉ?

ዶ/ር አታክልቲ፡- ሕክምና ገና ሲጀመር በጣም ውድ የሆነ አገልግሎት ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃም ቢሆን ለሕክምና የሚወጣው ብር በጣም ብዙ ነው፡፡ ለሕክምና የሚያስፈልገው እያንዳንዱ አላቂም ሆነ ቋሚ ዕቃም ቢሆን ውድ ነው፡፡ ታደጊ ከ110 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ለሚያስተናግድና የሕክምናውን ዘርፍ ከከተማ በተጨማሪ ወደ ገጠር ለማዳረስ የሚሞክር አገር አንዱ የሚገጥመው ችግር የአቅም ነው፡፡ የአቅም ማነስ ይኖራል፡፡ የአቅም ማነሱ ደግሞ በሰው ሀብት፣ በአላቂና በቋሚ ዕቃዎች ይመነዘራል፡፡ በተለይ ቋሚ ዕቃዎችን በሚመለከት ከመሰበሩ በፊት መንከባከብ፣ ከተሰበረ ደግሞ መጠገን ይጠይቃል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሠለጠኑ ባለሙያዎችና ሥርዓት ያስፈልጋል፡፡ ይህን ሁሉ ለማሟላት ታዳጊ አገር እንደመሆናችን መጠን የገንዘብ አቅም ያስፈልጋል፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ ችግሩ ከገንዘብ አቅምና ከሰለጠነ ባለሙያ እጥረት ጋር ይያያዛል፡፡

ሪፖርተር፡- የሕክምና ቁሳቁስ ጥገና ለማከናወን የሚችሉ ባዮሜዲካል ኢንጂነሮች ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በየዓመቱ እየተመረቁ አይደለም እንዴ?

ዶ/ር አታክልቲ፡- አዎ ይመረቃሉ፡፡ በጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታል ውስጥ አንድ ባዮሜዲካል ኢንጂነር ማዕከል ነበር፡፡ በደርግ ዘመን የተሠራው ማዕከል ከ20 ዓመታት በላይ አገልግሎ ነበር፡፡ በኋላ ማዕከሉ ከሆስፒታሉ ወጥቶ በየክልሉ እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡ ከዚያም በኋላ ለብዙ ጊዜ ሥልጠና አልነበረም፡፡ ሥልጠናው የተጀመረው በቅርብ ጊዜ ነው፡፡ የመጀመርያዎቹ ባዮሜዲካል ኢንጂነሮች ተመርቀው የወጡት የዛሬ አምስት ዓመት ይመስለኛል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ብዙ ኢንስቲትዩቶች ተቋቁመዋል፡፡ ይህም ሆኖ ግን ሥልጠናው እየተካሄደ ያለው እንደፍላጎታችን መጠን አይደለም፡፡ በየዓመቱ በባዮሜዲካል ኢንጂሪንግ የሚሠለጥኑ ሰዎች ቁጥርም አናሳ ነው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት የማስተማር አቅማችን ወይም የሚያስተምሩት ተቋማት ቁጥር አነስተኛ በመሆናቸው ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ክፍተት ለመሙላት እንዲቻል በየቦታው ሥልጠናው እንዲስፋፋ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህም ጥራትን በጠበቀ መልኩ መሆን አለበት፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን የማሠልጠኛው ቦታ ደረጃውን የጠበቀ ሊሆን ይገባዋል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

አሜሪካ ሕወሓትን በማሳመንና በመጫን በሰላም ሒደቱ ትልቅ ሚና መጫወቷን የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ አስታወቁ

የተመድና የአውሮፓ ኅብረት አበርክቶ አሉታዊ እንደነበር ጠቁመዋል በመንግሥትና በሕወሓት መካከል...

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...

አገር የሚገቡ የግል ዕቃዎችን በሚገድበው መመርያ ምክንያት በርካታ ንብረቶች በጉምሩክ መያዛቸው ተገለጸ

በአየር መንገድ ተጓዦች ወደ አገር የሚገቡትን የግል መገልገያ ዕቃዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለጥቃቅንና አነስተኛ ብድሮች ዋስትና መስጠት ሊጀምር ነው

ኢንተርፕራይዞችን ብቻ የሚያገለግል የፋይናንስ ማዕከል ሥራ ጀመረ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ...