Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምአፍሪካ የተጋረጠባትን የምግብ ቀውስ ለመታደግ የአፍሪካ ልማት ባንክ ውጥን

አፍሪካ የተጋረጠባትን የምግብ ቀውስ ለመታደግ የአፍሪካ ልማት ባንክ ውጥን

ቀን:

አፍሪካውያን የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ከመጀመሩ በፊት በምግብ ራሳቸውን ለመቻል የሚያበቃ ደረጃ ላይ አለመድረሳቸው፣ አሁን ላይ ከፍተኛ የምግብ ቀውስ እንዲጋረጥባቸው አድርጓል፡፡

ይህንን መቀልበስ አለብን ያለው የአፍሪካ ልማት ባንክ ሃያ ሚሊዮን የአፍሪካ ገበሬዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ያለውን ኢንሽየቲቭ ባለፈው ሳምንት አስታውቋል፡፡

በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት አፍሪካ የገጠማትን የምግብ ቀውስ ለመቀልበስ የአፍሪካ ልማት ባንክ ቦርድ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍም አፅድቋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በዩክሬንና ሩሲያ ጦርነት ምክንያት የምግብ ቀውስ በመከሰቱ በአፍሪካ የ30 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ምግብ በተለይም የስንዴ፣ በቆሎና አኩሪ አተር እጥረት ተፈጥሯል፡፡

አፍሪካ እነዚህን ምግቦች ከዩክሬንና ሩሲያ ስታስገባ ነበር ያለው ባንኩ፣ ይህ በመቋረጡ የአስቸኳይ ጊዜ ምግብ ምርት ላይ መሥራት እንደሚያስፈልግ ገልጿል፡፡ ለአፍሪካ ገበሬዎች ከፍተኛ ጥራት ያላቸው የእህል ዘሮችና የግብርና ግብዓት በማቅረብም አነስተኛ ገበሬዎች የተከሰተውን የምግብ እጥረት እንዲሞሉ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

ለሃያ ሚሊዮን አነስተኛ ገበሬዎች ደረጃቸውን የጠበቁ ዘሮችና የግብርና ግብዓቶችን በመደገፍ 38 ሚሊዮን ቶን ምግብ በአስቸኳይ እንዲያመርቱ ይደረጋልም ብሏል፡፡ ይህ በሁለት ዓመታት ውስጥ የምግብ ምርቱን በ12 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያሳድገውም ጠቁሟል፡፡

የባንኩ ግሩፕ ፕሬዚዳንት አኪንውሚ አዲሲና እንደሚሉት፣ የምግብ ዕርዳታ አፍሪካን ሊመግባት አይችልም፡፡ አፍሪካም የበሰለ ምግብ በእጇ እንዲቀርብላት አትፈልግም፡፡ አፍሪካ የሚያስፈልጋት ዘርና በቴክኖሎጂ የታገዘ ግብርና ነው፡፡

አፍሪካውያን ዘርና የግብርና ግብዓት ካገኙ በአገራቸው ምግብ ማምረት ይችላሉ ያሉት አዲሲና  (ዶ/ር)፣ ምግብ በመለመን ክብር እንደሌለና አፍሪካ በኩራት ራሷን መመገብ እንዳለባት ጠቁመዋል፡፡

ከማዳበሪያ አምራቾች፣ ከአፍሪካ ኅብረት የግብርናና ፋይናንስ ሚኒስትሮች ጋር ውይይት ከተደረገ በኋላ የአፍሪካ የአስቸኳይ ጊዜ ምግብ ምርት ተግባራዊ እንዲሆን መወሰኑን የሚናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ ሚኒስትሮቹ የግብርናው ዘርፍ እንዳያድግ ማነቆ የሆኑበትን ዘመናዊ ግብዓቶች ችግር ለመፍታት ሪፎርም እንደሚያደርጉ ተስማምተዋል ብለዋል፡፡

የአፍሪካ ልማት ባንክ እንዳለው፣ በዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ በአፍሪካ የስንዴ ዋጋ በ45 በመቶ ጨምሯል፡፡ የማዳበሪያ ዋጋ በ300 በመቶ አሻቅቧል፡፡  አኅጉሪቷ የሁለት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የማዳበሪያ እጥረት ገጥሟታል፡፡ በርካታ የአፍሪካ አገሮች የዳቦና የሌሎች የምግብ ዓይነቶች ዋጋ ውድነት ገጥሟቸዋል፡ ይህ ክፍተት ካልተሞላ በአፍሪካ የምግብ ምርት በሃያ በመቶ ይቀንሳል፡፡ አኅጉሪቷም ከ11 ቢሊዮን ዶላር በላይ የምግብ ምርት ታጣለች፡፡

ይህንን ለመቀልበስ የታለመው የአፍሪካ ልማት ባንክ የ1.5 ቢሊዮን ዶላር ስትራጂ፣ 11 ሚሊዮን ቶን ስንዴ፣ 18 ሚሊዮን ቶን በቆሎ፣ ስድስት ሚሊዮን ቶን ሩዝና 2.5 ሚሊዮን ቶን አኩሪ አተር ለማምረት የሚያስችል ነው፡፡

ገበሬዎች ከዘርና ማዳበሪያ በተጨማሪ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት የሚያገኙ ሲሆን፣ የገበያና ከምርት በኋላ የምርት አስተዳደር ድጋፍም ያገኛሉ፡፡

በቀጣዮቹ አራት የእርሻ ወቅቶች ባንኩ ለአነስተኛ መሬት ገበሬዎች ማዳበሪያ የሚያቀርብ ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ወሳኝ የፖሊሲ ሪፎርም እንዲደረግ መደላድል (ፕላትፎር) የሚፈጥር ሲሆን፣ ይህም አገራዊ ተቋማትን ማጠናከርንና የግብዓት ገበያ መቃኘትን ያካትታል፡፡

ከተለያዩ የልማት አጋሮች ጋር መሥራት፣ በፍጥነት ወደ ትግበራ መግባትና ውጤታማነትን ለማረጋገጥ ባንኩ የሚሠራ ሲሆን፣ ድጋፉ የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ዕርምጃዎችን በመውሰድም፣ የአሁኑን የምግብ ቀውስ በአስቸኳይ ለመፍታት እንዲሁም በረዥም ጊዜ ዘላቂነት ያለውና ችግርን የሚቋቋም የአፍሪካ የምግብ ሥርዓት ወደ መዘርጋትም ይገባል፡፡

የአፍሪካ ልማት ባንክ ባለፉት ሦስት ዓመታት ‹‹በቴክኖሎጂ ፎር አፍሪካ አግሪካልቸራል ትራንስፎርሜሽን›› ኢንሽየቲቭ በኩል በሰባት አገሮች ለሚገኙ 1.8 ሚሊዮን ገበሬዎች ሙቀት የሚቋቋም የስንዴ ዝርያ በማቅረብ 2.7 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ መመረት መቻሉን አስታውቋል፡፡

የአፍሪካ የአስቸኳይ ጊዜ ምግብ ምርት ፕሮግራም ለቀጣይ ሁለት ዓመታት የሚተገበር ሲሆን፣ ለአምስት ዓመታት የሚቆይ ፕሮግራም ይከተላል፡፡ ይህ የረዥም ጊዜ ዕቅድ አፍሪካ ከውጭ የምታስገባቸውን ስንዴና ሌሎች የምግብ ዓይነቶችን ለማስቀረትና በአኅጉሪቷ ለማምረት ያለመ ነው፡፡

የአምስት ዓመቱ ዕቅድ ለ40 ሚሊዮን ገበሬዎች ዘርና የግብርና ግብዓት ማቅረብን የሚያካትት ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...