Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊመንግሥት  ለወጠናቸው የአዳሪ ትምህርት ቤቶች በሞዴልነት የታጨው ኃይሌ መናስ አካዴሚ

መንግሥት  ለወጠናቸው የአዳሪ ትምህርት ቤቶች በሞዴልነት የታጨው ኃይሌ መናስ አካዴሚ

ቀን:

ከአዲስ አበባ 130 ኪሎ ሜትርን ከተጓዙ በኋላ በሰሜን ሸዋ ዞን ዋና ከተማ ደብረ ብርሃን የሚገኘውና በልዩነት የሚጠቀሰው የአዳሪ ትምህርት ቤት ስለመገንባቱ መረጃው በበቂ ሁኔታ ተዳርሷል ለማለት አያስደፍርም፡፡

ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ኢንቨስትመንትን የጠየቀው የኃይሌ መናስ አካዴሚ ልዩ የሚያደርገው የአዳሪ ትምህርት ቤት መሆኑ ሳይሆን፣ ከተለያዩ አካባቢ የመጡ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን ከንድፈ ሐሳብ ይልቅ ተግባራዊ በሆነ መንገድ እንዲማሩ የዘረጋው የማስተማር ሥነ ዘዴ እንደሆነ ተማሪዎቹና የአካዴሚው ማኅበረሰብ ያስረዳሉ፡፡

እ.ኤ.አ. በ2018 ግንባታው በሁለት ምዕራፎች የተጀመረው ኃይሌ መናስ አካዴሚ ባሁኑ ወቅት ሁለተኛውን ምዕራፍ በማገባደድ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ የተቋቋመውም በወ/ሮ ርብቃ ኃይሌና በባለቤታቸው ዠን መናስ አማካይነት ነው፡፡

- Advertisement -

ይህ አካዴሚ መጠሪያውን ከሁለቱ ጥንዶች የአባት መጠሪያ በመውሰድ፣ ‹‹ኃይሌ መናስ›› በሚል ስያሜ ከዓምና አንስቶ የአዳሪ ትምህርት ቤት አገልግሎት በመስጠት ላይ ነው፡፡

በስምንት ሔክታር ወይም 80,000 ስኩዌር ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው አካዴሚው በውስጡ 23 ሕንፃዎች አሉት፡፡ እነዚህ ሕንፃዎች የተማሪዎችና የመምህራን መኖሪያዎች፣ የስፖርት ፋሲሊቲዎች፣ የሳይንስ ቤተ ሙከራ፣ የመማሪያና የመመገቢያ ክፍሎች፣ ቤተ መጻሕፍት፣ የእግር ኳስ ሜዳና የመሮጫ ትራክ ያካተቱ ናቸው፡፡ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው ሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ ከነ ሙሉ ግብዓቱ 12 ሚሊዮን ዶላር ወይም ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ መፍጀቱ ተገልጿል፡፡

የአካዴሚው ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ክፍሌ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ አካዴሚው ሲቋቋም ዋናው ዓላማው የነገዋን ኢትዮጵያ መሪዎች ማፍራት ነው፡፡ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የመጡ ተማሪዎች በደንብ ተምረው፣ ለዓለም ዝግጁ ሆነው፣ ኢትዮጵያን እንዲያገለግሉ በማሰብ መቋቋሙን ያስረዱት አቶ ተስፋዬ፣ ለትርፍ ያልተቋቋመ የግል አዳሪ ትምህርት ቤት ብቻ ሳይሆን፣ ለኢትዮጵያም ሞዴል ይሆናል ተብሎ ታሳቢ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

ከ2013 ዓ.ም. አጋማሽ አንስቶ 72 የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎቹ በመመልመል እያስተማረ የሚገኘው የኃይሌ መናስ አካዴሚ፣ በትምህርት ሚኒስቴር በቅርቡ ይገነባሉ ተብሎ ለታቀዱት የአዳሪ ትምህርት ቤቶች በሞዴልነት እንደሚያገለግል ትምህርት ቤቱን የጎበኙ የትምህርት ባለሙያዎች ጭምር ይናገራሉ፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) የአዳሪ ትምህርት ቤቱን በቅርቡ በአካል እንደጎበኙት የተገለጸ ሲሆን፣ ትምህርት ሚኒስቴር በቀጣይ አምስት ዓመታት 50 የአዳሪ ትምህርት ቤቶችን በአገሪቱ ለመገንባት መወሰኑን በማስታወስ፣ በተለይም በሚቀጥለው ዓመት ለመገንባት ዕቅድ በተያዘላቸው 13 የአዳሪ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚያስተምሩ መምህራንና ዳይሬክተሮችን ለማሠልጠን ኃይሌ መናስ ይሁንታ እንዳገኘ  ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት 72 ተማሪዎች በትምህርት ቤቱ እየተማሩ የሚገኙት  37 የ9ኛና 35 የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው፡፡ የመጀመርያው ዙር ተማሪዎች ትምህርት ቤቱን የተቀላቀሉት በጥር 2013 ዓ.ም. ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ከዘጠኝ ወር በፊት የገቡ ናቸው፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ትምህርት ወደቀ›› ሲባል ከሥርዓተ ትምህርት ጋር ተያይዞ የሚሰነዘር አስተያየት መሆኑን የተናገሩት አቶ ተስፋዬ፣ ነገር ግን ችግሩ የተቀረፀው ሥርዓተ ትምህርት ላይ ሳይሆን፣ ሥርዓተ ትምህርቱ እንዴት ተደርጎ ነው ለተማሪዎች የሚቀርበው? የሚለው ላይ በደንብ ባለመሠራቱ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ኃይሌ መናስ በዋናነት የሚሠራው ተግባራዊ በሆነው የሥርዓተ ትምህርት አተገባበር ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአካዴሚው እያንዳንዱ ትምህርት ተግባር ተኮር በሆነ መንገድ እንደሚሰጥ ተገልጾ፣ የመምህራን ሚናም ተማሪ ተኮር የሆነውን የትምህርት ሒደት ማገዝ ብቻ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ብሩክ ክብረት ከአዲስ አበባ የመጣ ተማሪ ሲሆን፣ ቀደም ሲል በመደበኛ ይማርበት ከነበረው ትምህርት ቤት ጋር በማነፃፀር በአዳሪ ትምህርት ቤቱ የሚሰጠውን ትምህርት ገልጿል፡፡ በዚህ ወቅት የሚማረው ትምህርት የተጻፈን ነገር ሸምድዶ ማቅረብ ሳይሆን፣ የተላለፈው ትምህርት እንዴት ሊመጣ ቻለ? (ምንም ነገር ቢሠራ እንዴት ሊሆን ቻለ?) የሚለው ላይ የሚያተኩር መሆኑንም ይናገራል፡፡

ወደ አካዴሚው ሲመጣ ከቤተሰቡ በመለየቱ የሐዘን ስሜት እንደተሰማው የተናገው ብሩክ፣ ነገር ግን ውሎ ሲያድር ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከመጡ ተማሪዎች ጋር ሲላመድ ሌላ ዕውቀትና ክህሎት ብቻ ሳይሆን ቤተሰባዊነትንም መመሥረቱን ገልጿል፡፡

የኮምፒዩተርና ስፔስ ሳይንስ ላይ እንደሚያዘነብል የሚናገረው ብሩክ፣ ኢትዮጵያ ያላትን ነባር ዕውቀትንም አዳብሎ አዲስ ግኝቶችን የመፍጠር ዕቅድ እንዳለው አስታውቋል፡፡

በሌላ በኩል ጽዮን ዓብይ ዘንድሮ በኃይሌ መናስ መማር የጀመረች የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን፣ ከተለያዩ አካባቢዎች ከመጡ ተማሪዎች ጋር መማር መጀመሯ የመተሳሰብና የመቻቻል ባህሪ ማሳያ መሆኑን ተናግራለች፡፡

በትምህርት ቤቱ እንዴት ማሰብ እንዳለባት እንጂ ምን ማሰብ እንዳለባት እንደማይነገራት ገልጻ፣ ይህም በራሷ እንድታስብ፣ ነገሮችን እንድትፈጥርና ነገሮችን እንድትመራመር እንዳስቻላት ገልጻለች፡፡

ከዚህ ቀደም ስትማር የቆየችበት የትምህርት አሰጣጥ ደብተር ላይ መሠረት ያደረገ እንደነበር ያስታወሰቸው ጽዮን፣ በዚህ ወቅት እሷን ጨምሮ ሁሉም ተማሪዎች በቴክኖሎጂ መሣሪያ (አይፓድ) ብቻ ስለሚማሩ ሁሉንም መረጃ ከዚያ ላይ እንደሚያገኙ አስረድታለች፡፡

የኃይሌ መናስ አካዴሚ መሥራች ወ/ሮ ርብቃ ኃይሌ ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ እንዲሁም በሒዩማኒቲስ የትምህርት ይዘት ብቻ ሳይሆን፣ ከተሰጣቸው ፍንጭ በመነሳት በሁሉም መስኮች ምን ሊደረግ ይገባል? የሚለውን ወደ ተግባር የሚቀይሩ ተማሪዎችን ለማፍራት በማሰብ ትምህርት ቤቱ መቋቋሙን ተናግረዋል፡፡

ለትምህርት ቤቱ የአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን የውጭ አገሮች መምህራንን ማምጣት ያስፈለገበት ምክንያት በኢትዮጵያ የትምህርት አሰጣጥ ወይም ተማሪዎች ላይ ምንድነው የሚያስፈልገው ለውጥ? የሚለውን በማየት በዚያ ላይ አተኩሮ ለመሥራት ከማሰብ በመነጨ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ትምህርት በዜጎች ላይ የሚሠራ የወደፊት ኢንቨስትመንት መሆኑን የሚናገሩት ወ/ሮ ርብቃ፣ ትምህርት ቤቱ እንደ ሌሎች ኢንቨስትመንቶች የወል መጠሪያ ስያሜ ይሰጠው እንጂ ትርፍን በማሰብ የተቋቋመ አይደለም ብለዋል፡፡ መክፈል የሚችል የተማሪ ቤተሰብ ትምህርት ቤቱ የሚጠይቀውን ክፍያ እንደሚከፍል የተገለጸ ሲሆን፣ ነገር ግን ተሰጥኦ ያላቸውና የትምህርት ቤቱ የመቀበያ መሥፈርት የሚያሟሉትን ተማሪዎች የነፃ ዕድል የሚመቻችላቸው መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

ትምህርት ቤቱ የተማሪዎችን የመክፈል አቅም ላለማየት ይሞክራል ያሉት የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ፣ ለትርፍ ሳይሆን በመማር ማስተማር ሒደት ላይ የሚወጣውን ወጪ ለመሸፈን በዓመት የሚያስከፍለው አሥር ሺሕ ዶላር መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ይህ ክፍያም የተማሪዎችን ዩኒፎርም፣ ምግብ፣ የቴክኖሎጂ መማሪያ አይፓዶችና ሌሎች የተለያዩ ወጪዎችን የሚሸፍን ነው ተብሏል፡፡

የደብረ ብርሃን መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ምክትል ዲን መብዓ ፈጠነ (ፕሮፌሰር) በበኩላቸው፣ ትምህርት በግልም ሆነ በመንግሥት ተቋማት በንድፈ ሐሳብ ሲቀርብ የተለየ ልዩነት ባይኖረውም፣ ነገር ግን በተግባር ሲተረጎም ማየት ትልቁ የለውጥ አስኳል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኮሌጁ በራሱ መውሰድ የሚገባውን ተሞክሮ ከአዳሪ ትምህርት ቤቱ እንዳገኘ ያስታወቁት ምክትል ዲኑ፣ ምክንያቱም ተማሪዎችን የሚቀርፁ መምህራን የሚፈሩበት እንደመሆኑ በርካታ የሚቀሰሙ ተግባራትን መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡

አቶ ተስፋዬ እንዳስረዱት፣ ትምህርት ቤቱ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በቅርበት የሚሠራ ሲሆን፣ ሞዴል ትምህርት ቤት መሆንን ያለመ እንደመሆኑ መጠን፣ በደብረ ብርሃን ከተማ ውስጥ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች፣ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲና የመምህራን ኮሌጅ ጋር በቅርበት መሥራት ጀምሯል፡፡ በተጨማሪም አካዴሚው በሚገኝበት አካባቢ በሚገኘው የሳተላይት ትምህርት ቤት ውስጥ የሚማሩ የአካባቢው ማኅበረሰብ ተማሪዎችን፣ የኃይሌ መናስ ተማሪዎች በተለያየ መልኩ ድጋፍ ማድረግ መጀመራቸው ተመላክቷል፡፡

ተማሪዎች ወደ ኃይሌ መናስ አካዳሚ ለመግባት ከሚጠበቅባቸው መለኪያዎች አንዱ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ መሆንን ነው፡፡ ማንኛውም ተማሪ የስድስተኛና ሰባተኛ ክፍል ሪፖርት ካርዱን በዲጂታል ዘዴ አስተካክሎ (ስካን አድርጎ) ለትምህርት ቤቱ በሚልከው መረጃ መሠረት፣ የትምህርት ቤቱ አድሚሽን ቢሮ የመምረጥ ሥራ እንደሚሠራ ተገልጿል፡፡ ያንንም ተከትሎ የተማሪ መቀበያ ፈተና በትምህርት ቤቱ ይሰጣል፡፡

ትምህርት ቤቱ በዓመት የሚቀበለው የተማሪ ቁጥር 100 እንደሆነና በውስጡ የሚገኙ መምህራንም ሆነ የአስተዳደር ባለሙያዎች ከኢትዮጵያና ከውጭ አገሮች የተውጣጡ መሆናቸውም ተነግሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...