Monday, March 4, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ባንኮች በጦርነትና በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች ተጨማሪ ብድርና የመክፈያ ጊዜ ማራዘሚያ እንዲሰጡ ተፈቀደ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በጦርነትና በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች ለሚገኙ ተበዳሪዎች ባንኮች የአንድ ዓመት የብድር መመለሻ የዕፎይታ ጊዜ እንዲሰጡና ተጨማሪ ብድር እንዲያመቻቹላቸው አሳሰበ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከትናንት ግንቦት 16 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ተፈጻሚ እንዲሆን በማለት ለሁሉም ባንኮች ባስተላለፈው መመርያው፣ በጦርነትና በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች ለሚገኙ ደንበኞቻቸው ለሰጡት ብድር የመክፈያ ጊዜ ማራዘሚያ እንዲፈቅዱ ከማለቱ ባሻገር፣ ተጨማሪ ብድርና የውጭ ምንዛሪ እንዲያመቻቹላቸውም አሳስቧል፡፡

የተባለውን የብድር ማራዘሚያ መስጠታቸውን አስመልክቶም በየሦስት ወሩ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሪፖርት እንዲያደርጉ አሳስቧል፡፡ ይህ መመርያ ተፈጻሚ የሚሆነው በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በአፋርና በሶማሌ ክልል በተፈጠሩ ግጭቶችና በድርቅ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ተበዳሪዎች ብቻ ነው፡፡ በዚህ ዕድል ተጠቃሚ የሚሆኑትም በግጭቱና በድርቁ ወቅት ለተሰጠው ብድር ብቻ እንደሆነ መመርያው ይጠቁማል፡፡ 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባንክ ዘርፍ ሱፐር ቪዥን ምክትል ገዥ አቶ ፍሬዘር አያሌው፣ በጦርነቱና በድርቁ ምክንያት ያለባቸውን ብድር መክፈል ላልቻሉ ተበዳሪዎች ባንኮች የራሳቸውን አሠራር ተጠቅመው፣ ብድሩ እንዲያገግምና መመለስ እንዲችል ለማድረግ ሲባል የወጣ መመርያ መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል። 

በዚህም ሒደት ባንኮች የሰጡትን ብድር እንዲመለስ ለማስቻል ከመመርያው አንፃር በባንኮች በኩል መደረግ ያለባቸውን ጥብቅ የሆኑ አንዳንድ አሠራሮችን እንዲያፍታቱ ለማድረግ ጭምር ታስቦ የወጣ መመርያ እንደሆነ አብራርተዋል።

በዚህ መመርያ መሠረት ዋና ተፈጻሚ እንዲሆን የሚፈለገው ከዚህ በፊት የባንክ ተበዳሪ ሆኖ፣ ግን በተቀሱት ችግሮች ምክንያት ያለባቸውን ብድር መክፈል ላልቻሉና በዚህም ችግር ውስጥ ለገቡ ተበዳሪዎች ብድሩን የሰጡ ባንኮች ድጋፍ አድርገው ብድራቸው እንዲመለስ ማስቻል እንደሆነ ከአቶ ፍሬዘር ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡  

ይህ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ ከማስተላለፉ በፊት የባንኮች የሥራ መሪዎችና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መክረውበታል፡፡ የባንኮች የሥራ መሪዎች ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጋር ከመምከራቸው ቀደም ብሎም በተለይ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢ የነበሩ ተበዳሪዎች ንብረታቸው በመውደሙና ሥራቸው በመስተጓጎሉ መልሰው ወደ ሥራ መግባት እንዳልቻሉ፣ በዚህም ምክንያት ያለባቸውን የባንክ ብድር ለመመለስ ድጋፍ እንዲደረግላቸው በደብዳቤ ጭምር ጠይቀው እንደነበረ ታውቋል፡፡ ይህንኑ ጥያቄያቸውን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አቅርበው ጉዳዩ ሲታይ መቆየቱንም ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡ 

የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንትና የዳሸን ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ጦርነት በነበረባቸው ቦታዎች ያሉ ተበዳሪዎች ለባንኮች በዋናነት ያቀረቡት ሁለት ጥያቄዎች እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡ 

አንደኛው ጥያቄ ‹‹የተበደርነውን ብድር መክፈል ስለማንችል የብድር የማራዘሚያ ጊዜ ይሰጠን›› የሚል ሲሆን፣ ሁለተኛው ጥያቄያቸው ደግሞ፣ ‹‹ሁሉም ነገር ስለወደመብንና ሥራችንን መልሰን ለመቀጠል ተጨማሪ ብድር ይሰጠን›› የሚል ነው፡፡ እንዲህ ካሉ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች በኋላም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና ባንኮች፣ ‹‹ጥያቄው በምን ዓይነት መንገድ በማስተናገድ መፍትሔ መስጠት ይቻላል›› በሚለው ላይ በመምከር ይህ መመርያ ሊወጣ መቻሉ ተጠቅሷል፡፡ 

እንደ አቶ አስፋው ገለጻ ብሔራዊ ባንክ ይህንን መመርያ ማውጣቱ አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት አቶ አስፋው፣ እንደ መፍትሔ መወሰድ ያለበት የብድር ማረዘሚያ ብቻ ሳይሆን፣ ተጨማሪ ብድርም የሚያስፈልግ መሆኑን ከግንዛቤ በማስገባት በመመርያው መካተቱ ተገቢ ነው ብለዋል። 

እነዚህ በተዳሪዎች ከአቅም በላይ የሆነ ችግር የመጣባቸው በመሆኑ ባንኮች እየተመለከቱ ሊቋቋሙ የሚችሉበትን ዕርምጃ ለመውሰድ ከብድር ማራዘሙ ሌላ እንደ ተሰጠው የብድር ዓይነት ሁኔታዎችን እያዩ ተጨማሪ ብድር መስጠት አስፈላጊ ይሆናልም ብለዋል፡፡

በጦርነት በተጎዱ አካባቢዎች ያሉ ተበዳሪዎችን ለመታደግ የብድር ማራዘሚያ ተጨማሪ ብድር ካልተሰጣቸው ሊቋቋሙ ስለማይቻል ባንኮች ተጨማሪ ብድር ሊሰጣቸው ይገባል ቢባልም፣ ይህንን የብድር አሰጣጥ በጥንቃቄ መያዝ የሚያስፈልግ መሆኑን ግን አቶ አስፋው ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ 

በግጭትና በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች ያሉ ተበዳሪዎች ምን ያህል ገንዘብ እንደተበደሩ አሁን ባለው ሁኔታ መጠኑ ባይታወቅም፣ ከፍተኛ እንደሚሆን ተጠቅሷል፡፡ ለዚህ የሚጠቀሰው ምክንያትም ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ቅርንጫፎች ያሏቸው ባንኮች በሙሉ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ብድር ሰጥተዋል ተብሎ መታመኑ ነው። አሁን የወጣው መመርያም ሁሉንም ባንኮች የሚመለከት እንደሆነ ታውቋል፡፡ ከላይ በተጠቀሱት አካባቢዎች ቅርንጫፍ የሌላቸው ባንኮች ግን መመርያው ላይመለከታቸው እንደሚችል ታውቋል።

ይህንን መመርያ ለማስፈጸም ሲባልም በብድር አሰጣጥና ብድር ማደስን የተመለከቱ ጥብቅ ሕጎች በተወሰነ ደረጃ እንዲለሳለሱ እንደሚደረግም ታውቋል፡፡ እንደ አቶ አስፋው ገለጻ፣ ሁሉም ባንኮች ለተበላሹ ብድሮቻቸው አስፈላጊውን መጠባበቂያ እንዲይዙ በብሔራዊ ባንክ የሚገድዱ ሲሆን፣ አሁን በወጣው መመርያ ግን የተወሰነ ማሻሻያ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ 

‹‹እነዚያ መመርያ ላይ ለምሳሌ ምንም ተስፋ የሌላቸውን ብድሮች ብታራዝሙ ትርጉም የለውም፡፡ ያ ብድር ሊከፈል ይችላል ተብሎ ነው የሚታመነው፡፡ ስለዚህ ባንኮች ብሔራዊ ባንክ ይህንን ነገር ባያመጣ እነዚህ ብድሮች የሞቱ ብድሮች ናቸው ብለው ሊፈርጃቸው ይችላል፡፡ ይህንን በማድረጋቸው ደግሞ መጠበቂያ ይዘው ያልፋሉ፡፡ አሁን ግን እነዚህ ብድሮች ላይ የደረሰው ጉዳት ከአቅም በላይ ስለሆነ በአንድ ዓመት ይህንን አድርጉ በመባሉ ባንኮች በዚሁ መንገድ መመርያውን ተፈጻሚ ያደርጋሉ፤›› ሲሉ አቶ አስፋው ተናግረዋል፡፡ 

በዚህ ጉዳይ ላይ የተጠየቁት አቶ ፍሬዘር፣ በዚህ መመርያ ላይ ባንኮች የተበላሸ ብድር ካጋጠማቸው የብድር መከፈያ ጊዜውን ለማራዘም ወይም ደግሞ አዲስ በድር ለመስጠት የሚያስቀምጧቸው ቅድመ ሁኔታዎች መኖራቸውን፣ ለአብነትም በብሔራዊ ባንክ ሕግ መሠረት ባልተከፈለው ብድር ላይ የተጠራቀመው ወለድ በቅድሚያ ማስከፈል ያለባቸው መሆኑንና በቀጣይ ያሉ ክፍያዎችን በመደበኛነት መክፈልን በቅድሚያ ማረጋገጥ እንዳለባቸው አስረድተዋል።

አሁን ግን እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ላይ የተወሰነ ማሻሻያ መድረጉንም ገልጸዋል፡፡

ይህ ተወሰነውም ባንኮች ይህንን ምክንያት አድርገው ብድር ማራዘሚያ ጥያቄን እንዳይከለክሉ የተወሰነ ማፍታቻ ለማድረግ መሆኑን ገልጸዋል። ‹‹ይህ መመርያ ዋናው ዓላማው ግን የባንኮችን ብድር አመላለስ ብቃት ለማጠናከር ነው፤›› ያሉት አቶ ፍሬዘር ደንበኞች፣ ‹‹እንዲህ ያለ ድጋፍ ካገኙ በተሰጣቸው ዕድል ተጠቅመው ብድራቸውን ከፍለው ወደ መደበኛ መስመር መመለስ ይችላሉ ተብሎ ስለታመነ ነው፤›› ብለዋል። 

ይህንን መመርያ ለማስፈጸም አንድ ዓመት በቂ አይደለም የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ያነጋገርናቸው አንድ የባንክ ባለሙያ ብድር አራዝሞ እንደገናም ተጨማሪ ብድር በመስጠት እንዲያገግሙ ለማድረግ ጊዜ ይወስዳልም ይላሉ፡፡ የብድር ዓይነቶቹም የተለያዩ በመሆኑ ይህም መታየት እንደሚኖርበት ይጠቅሳሉ፡፡

ለምሳሌ የፕሮጀክት ብድሮች አሉ፡፡ እነዚህ የፕሮጀክት ብድሮች ባህሪያቸው ይለያያል፡፡ ምን ደረጃ ላይ ነው ያሉት? ከውጭ የሚገቡ መሣሪያዎች ሊያስፈልጓቸው ይችላል፡፡ ለዚህ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ያስፈልጋል፡፡ መሣሪያውን አዝዞ የውጭ ምንዛሪን አዘጋጅቶ ዕቃውን አስመጥቶ ተክሎና ሥራ እስኪጀምር ጊዜ ወስዳልና የአንድ ዓመት ገደቡ ሊያዝ ይችላል የሚል ሥጋት አላቸው፡፡ 

አቶ ፍሬዘር ግን አንድ ዓመት የተሰጠው የብድር ስትራክቸሩን ለመሥራት ነው፡፡ ስለዚህ ሰርኩላሩን ለመተግበር አንድ ዓመት ከበቂ በላይ ነው ብለዋል፡፡ ባንኮች የራሳቸውን ጥናት አድርገው እያንዳንዱ ተበዳሪ ምን ዓይነት ድጋፍ ነው የሚፈልገው የሚለውን ለመለየት አንድ ዓመት በቂ ነው ብለዋል፡፡    

ከትናንት ጀምሮ ተግባራዊ ይደረግ የተባለው ይህ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ውሳኔ የትግራይ ክልል ውስጥ ያሉትን ተበዳሪዎች ያላካተተ አይደለም፡፡ ሆኖም ቢካተት የሚል ሐሳብ ቀርቦ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፣ አሁን ባለው ሁኔታ በክልሉ ባሉ ባንኮች የተሰጠው ብድርም ሆነ ማስያዣ ምን ደረጀ ላይ እንዳለ ባለመታወቁ ዕድሉን ለመስጠት አስቸጋሪ ሆኗል፡፡

በጦርነት በነበረባቸው አካባቢዎች በቢሊዮን የሚቆጠር ብሮች በብድር የተሰጡ ሲሆን፣ ባንኮች በእነዚህ አካባቢ የሰጧቸውን ብድሮችን ለማስመለስ ያልቻሉበት ሁኔታ ውስጥ ናቸው፡፡ በተለይ በትግራይ ክልልልና በአንዳንድ የአፋርና የአማራ ክልሎች የብድር ማስያዣ ንብረቶችን እንኳን ያሉበትን ሁኔታ እንኳን ለማወቅ አልተቻለም፡፡ 

ከዚያ አካባቢ የሚንቀሳቀሱ የነበሩ ባንኮች ምንም ዓይነት መረጃ የሌላቸው በመሆኑ ያበደሩትን ብድር ይመለስ አይመለስ ለማወቅ ያልተቻለ ሲሆን፣ በእነዚህ ብድሮች ላይ በመንግሥትም ሆነ በባንኮች በኩል የተወሰደ ዕርምጃ የለም፡፡ ጦርነቱ ባስከተለው ችግር ትግራይ ክልል ከፍተኛ የሆነ ብድር የነበራቸው እንደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ወጋገንና አንበሳ ባንኮች ብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት ከፍተኛ የመጠባበቂያ ገንዘብ እንዲይዙ አስገድዷቸዋል፡፡ በተለይ ወጋገንና አንበሳ ባንኮች ካለፈው ዓመት ጀምሮ መመለሳቸው አጠራጣሪ ለሆኑ ብድሮቻቸው ከፍተኛ የመጠባቂያ ማስቀመጥ በመገደዳቸው በትርፍ ምጣኔያቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳረፉ መገለጹ አይዘነጋም፡፡ የብድርና የተቀማጭ የገንዘብ አሰባሰብ ላይም በተመሳሳይ ችግር ፈጥሮባቸው ቆይቷል፡፡ በተለይ በትግራይ ክልል የሚገኙ ሁሉም ባንኮች ቅርንጫፎች ከሥራ ውጪ በመሆናቸው፣ ዳሸን ባንክ 1.7 ቢሊዮን ብር፣ ኅብረት ባንክ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ፣ አዋሽ ባንክ ደግሞ ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ የሰጡ ሲሆን፣ በእነዚህ ብድሮች ላይ ምንም መረጃ የላቸውም፡፡ ከግል ባንኮች የወጋገን ባንክና የአንበሳ ባንክ ግን ከዚህም በላይ የሚሆን ብድር በክልሉ ለሚገኙ ተበዳሪዎች በመስጠታቸው፣ ይህንን ብድር ለማስመለስ ባለመቻላቸው እየተፈተኑ ቆይተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች