Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየቴክኒክና ሙያ ምዘናን ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያሸጋግር ስምምነት ተፈረመ

የቴክኒክና ሙያ ምዘናን ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያሸጋግር ስምምነት ተፈረመ

ቀን:

በኢትዮጵያ፣ በኬንያና በታንዛኒያ መካከል ሲደረግ የነበረው የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ምዘናን፣ ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያሳድጋል የተባለው ፕሮጀክት በሦስቱ አገሮች ተፈርሞ ፀደቀ፡፡

በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና የሚመረቁ ተማሪዎችም ሆኑ መምህራን፣ በሦስቱ አገሮች እንደ ልብ ተንቀሳቅሰው የመሥራት ዕድል ይፈጠርላቸዋል ተብሏል፡፡

ስምምነቱ ከዚህ በተጨማሪ በዘርፉ ቀጣናዊ፣ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት ያላቸው ምሁራንን ለማፍራት ያስችላል ተብሏል፡፡

የሦስቱ አገሮችን የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ለማሳደግ በዓለም ባንክ ድጋፍ፣ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የክህሎት ሽግግር (EASTRIP) የተባለ ፕሮጀክት ተቀርፆ ወደ ሥራ መገባቱ ተነግሯል፡፡ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ባዘጋጀው ዓውደ ጥናት ላይ እንደተብራራው፣ በዚህ ፕሮጀክት አማካይነት ሦስቱ አገሮች የተስማሙበት ወጥ የሆነ የጋራ የምዘና ሥርዓት ሲሠራ ቆይቷል፡፡

ይህ ወጥ ምዘና የማዘጋጀት ሥራም መገባደዱ የተነገረ ሲሆን፣ የኬንያና የታንዛኒያ አቻ ሚኒስትሮች በተገኙበት ስምምነት ሆኖ በሦስቱ አገሮች ተፈርሞ ፀድቋል፡፡

ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አሰግድ ጌታቸው፣ ‹‹ስምምነቱ በዘርፉ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ያላቸው ሙያተኞችን ለማፍራት የሚያስችል ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ከዚህ በፊት በአንዳንድ የቴክኒክና ሙያ ዘርፎች ምዘናና ዕውቅና ለማግኘት መምህራኖቻችንን ጭምር ውጭ አገሮች ለመላክ እንገደድ ነበር፣ ይህ ፕሮጀክት ይህንን ያስቀርልናል፤›› ሲሉ አቶ አሰግድ አክለዋል፡፡

ስምምነት በተደረገበት ፕሮጀክት መሠረት ኢትዮጵያ በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ‹‹ቀጣናዊ የምዘና መስጫ ማዕከል›› ትሆናለች ሲሉ ነው ሚኒስትር ደኤታው የተናገሩት፡፡ ዓለም አቀፍ የቴክኒክና ሙያ ምዘና መስጫ ማዕከል በኢትዮጵያ ለመገንባትም የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጥረት እያደረገ መሆኑን አቶ አሰግድ ጠቅሰዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ዕውን እንዲሆን ሲያስተባብር የቆየው የኢትዮጵያ ጥናት ቡድን መሪ  ገነነ አበበ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በሦስቱ አገሮች የተፈረመው ስምምነት በኢትዮጵያ የሚሰጡ ደረጃዎችን ቁጥር እንደሚያሳድግ ገልጸዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ እስካሁን በቴክኒክና ሙያ እስከ ደረጃ ስምንት ብቻ ነው ሥልጠና የምትሰጠው፡፡ ስምምነቱ እስከ 10 እና 11 ደረጃዎች ከሚሰጡ አገሮች ጋር በመደረጉ፣ ይህን ለማሳደግ ያግዘናል፤›› ብለዋል፡፡ ዜጎች በተለያየ የዓለም አገሮች ተንቀሳቅሶ የመማር ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳድሮ የመሥራት ዕድል እንደሚያገኙም ገነነ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

‹‹በዘርፉ የሚሰጠው የሙያና ክህሎት ሥልጠና ዓለም አቀፍ ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን የሚያስችል ነው፤›› ሲሉ ስምምነቱን ገልጸውታል፡፡ ኢትዮጵያ በቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ዘርፍ ዓለም አቀፍ ጥራት ያለው ሥልጠናና ምዘና እንዲኖራት ለረዥም ጊዜ ጥረት ስታደርግ መቆየቷንም አመልክተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...