Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበማኅበራዊ ሚዲያ ወንጀል የሚፈጽሙ የውጭ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ እንደሚገኝ ተገለጸ

በማኅበራዊ ሚዲያ ወንጀል የሚፈጽሙ የውጭ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ እንደሚገኝ ተገለጸ

ቀን:

የተለያዩ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን በመጠቀም ወንጀል የሚፈጽሙ የውጭ ዜጎች ቁጥራቸው እየጨመረ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡

የማጭበርበር ወንጀሎቹ በዋናነት የሚፈጸሙት በውጭ አገር በሚኖሩ፣ በቱሪስት ቪዛ ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ የውጭ አገር ዜግነት ባላቸው ግለሰቦች ከመሆኑ ባሻገር፣ ከግለሰብ እስከ ተቋማት የሚደርስ የማወናበጃ ሥልት የሚተገበርበት መሆኑን፣ በብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት እና የፋይናስ ደኅንነት አገልግሎት የተዋቀረው የጋራ ግብረ ኃይል አስታውቋል፡፡

በፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት የፋይናንስ ወንጀሎች ትንተና ኃላፊ አቶ ዮናስ ማሞ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ የማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም የሚደረገው የማጭበርበር ድርጊት ካለፉት ሁለት ዓመታት አንስቶ ሲፈጸም የቆየ ቢሆንም፣  ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰና ዓይነቱንም እየቀየረ መጥቶ በማኅበረሰቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል ብለዋል፡፡

ጉዳዩን ከስሩ ለማጥናት ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት እና ከፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት የተወጣጣ ግብረ ኃይል  እንቅስቃሴ መጀመሩ ተገልጾ፣ የኅብረተሰቡን የግንዛቤ ደረጃ በማየት በአገር ውስጥ ከሚገኙ ግለሰቦች ጋር በመመሳጠር የተለያዩ የማጭበርበሪያ ሥልቶችን የሚተገብሩ የውጭ አገር ዜጎች ቁጥራቸው መበራከቱን ማረጋገጡ ተመላክቷል፡፡

በተለይ በዚህ ዓይነቱ ወንጀል በብዛት ተጠቂ ሆነው የተገኙት ሴቶች ናቸው ተብሏል፡፡ የውጭ አገር ዜጎች የማኅበራዊ የትስስር ገፆችን በመጠቀም የረዥም ጊዜ መግባባት በመፍጠር፣ ‹‹ዕቃ እንልካችኋለን›› እና ‹‹ልናገባችሁ እንመጣለን›› የሚሉ አጓጊ መደለያዎችን በማቅረብ የማጭበርበር ሥራውን እንሚፈጽሙ ተገልጿል፡፡

የተለያዩ ዕቃዎችን እንልካለን በማለት ሐሰተኛ ፎቶዎች በመላክ በአገር ውስጥ ለሚገኙ ግብረ አበሮቻቸው ስሞችን በማስተላለፍ፣ አንዳንዴም ዕቃውን ይዘን መጥተናል፣ ነገር ግን የኢትዮጵያን ብር ስላልያዝን ለቀረጥ የሚሆን ገንዘብ ላኩልን በማለት በወኪሎቻቸው በኩል ድርጊቱን እንደሚፈጽሙ በጥናት ተለይቷል ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል በኢንቨስትመንት ስም ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ በማሳወቅ ትላልቅ ባለሀብቶችን የሚያጠምዱ የውጭ አገሮች ዜጎች እንደሚገኙ ያስረዱት አቶ ዮናስ፣ ሐሰተኛ ሰነዶችን ኢሜይል በማድረግ በጋራ ኢንቨስት እናድርግ የሚል ትስስር እንደሚፈጥሩ ገልጸዋል፡፡

ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ እንደያዙ፣ ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አስፈላጊውን ጉዳይ እንዳጠናቀቁ በማሳየት ስምምነት በማሰር፣ ማሽነሪዎችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ገንዘብ ያስፈልጋል በሚል ምዝበራ የፈጸሙ የውጭ አገር ዜጎች መገኘታቸው ተጠቅሷል፡፡

ድርጊቶቹ ወደ ኢትዮጵያ በተለያየ ጊዜ በሚመጡ የውጭ አገር ዜጎች፣ ነዋሪነታቸውን ረዥም ጊዜ በኢትዮጵያ ባደረጉ፣ ለጉብኝት በሚል ነገር ግን ለዚህ ዓላማ በሚመጡ፣ የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎችና  የገንዘብ ማተም ሥራ ላይ በተሰማሩ ዜጎች የሚፈጸም እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በዚህ ወንጀል የበርካታ አገሮች ዜጎች ተሳታፊ ቢሆኑም፣ ነገር ግን የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ በዚህ ዓይነቱ ወንጀል ጠርጥሯቸው ከአገር እንዲወጡ የተደረጉትና በማረሚያ ቤት የሚገኙት ዜጎች ከናይጄሪያ፣ ካሜሮን ሌሎች የምዕራብ አፍሪካ አገሮች የተወጣጡ ናቸው ተብሏል፡፡

የወንጀል ድርጊቱ ሰላባ የሆኑ ሰዎች ድርጊቱን ከቤተሰብና ከትዳር አጋር በመደበቅ እንደማድረጋቸው መጠን፣ ወደ ፖሊስና የሕግ አካላት መሄድ የሚያስፈራቸው መሆኑ ተመላክቶ፣ ነገር ግን በፖሊስ ተይዘው በምርመራ ላይ የሚገኙት ምርመራዎች ቁጥራቸው ቀላል የሚባል እንዳልሆነ ተመላክቷል፡፡

በቅርብ ጊዜ በተደረገ ጥናት በተለያዩ የፖሊስ ጣቢዎች በቀን 40 የሚደርሱ መሰል ወንጀሎች የሚስተናገዱ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም ድርጊቱ በመላ አገሪቱ እየተስፋፋ ለመሆኑ አመላካች ነው ተብሏል፡፡

የግብረ ኃይሉ ዋና ዓላማ በአገሪቱ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ የሚገኙ ወንጀለኞችን ተከታትሎ ለሚመለከተው የሕግ አካል ማቅረብ እንደሆነ ያስታወቁት አቶ ዮናስ፣ ድርጊቱ ግለሰቦችን በመያዝ ብቻ የሚቆም ስላልሆነ የግንዛቤ ማስጨበጫዎችን በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን  ማሳወቅ ተገቢ ሆኖ መገኘቱን አብራርተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...