Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርአደገኛው የበቀል ባህልና የኢትዮጵያ ዕጣ ፋንታ

አደገኛው የበቀል ባህልና የኢትዮጵያ ዕጣ ፋንታ

ቀን:

በጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ

በቅድሚያ በተለያየ መንገድ ሕይወታቸው ያላግባብ ለተቀጠፉ ወገኖች ቸሩ እግዚአብሔር ነፍሳቸውን ይማር፣ ቤተሰብን ወዳጅ ዘመድንም ያፅናና።

‹‹ጠንካራው ኃላፊነት የተሞላበት ዕርምጃ በመውሰዱ፣ ደካማ የሚመስልበትና ደካማው ደግሞ በሚወስደው ኃላፊነት የጎደለው ዕርምጃ ጠንካራ የሚመስለበት አስገራሚ ወቅት ላይ እንገኛለን፤›› የቀድሞው የጀርመን ቻንስለር ኦቶ ቮን ቢስማርክ፡፡

በቀል በኢትዮጵያ ባህል ውስጥ የተገመደና ለዘመናት አንዱን ከአንዱ ጋር ሲያገዳድል የኖረ አደገኛ ባህላዊ ክስተት ነው። ሌላው ቀርቶ ልጅ ሲወለድ የሚሰጡ ስሞችና አንዳንድ ምሳሌያዊ አነጋገሮቻችን በቀልን የሚያወድሱና በቀልን የሚያበረታቱ ናቸው። በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች በቀል ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍና በማኅበረሰቡ ውስጥ ከፍተኛ ጉዳት ሲያመጣም ለዓመታት አስተውለናል። ‹‹ብድሩን የማይመልስ ወንድ ልጅ አይወለድ›› የሚል ዓይነት ብሂልና ‹‹ደም መላሽ›› የሚል ዓይነት ስም በባህላችንና በማኅበረሰባችን በቀል ያለውን ተቀባይነት ያንፀባርቃሉ። ይህ የበቀል ባህል ፖለቲካችንን፣ ሃይማኖታችንን፣ ማኅበራዊ ኑሯችንንና የምጣኔ ሀብታችንን ጨምሮ አቃውሷል። እስካሁንም ትኩረት ተሰጥቶበት በጥናት የተደገፈ መፍትሔ ለማምጣት ብዙ ባይሞከርም፣ የበቀል ባህልን ከሥሩ ለመንቀል ከመጣር ይልቅ፣ ስለሰላምና ዕርቅ መስበኩ ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ ቆይቷል። ይህ ጸሐፊ የበቀል ባህልን ከሥሩ እስካልነቀልን ድረስ በአገራችን ሰላምና ዕርቅ ይኖራል ብሎ ለመገመት ያዳግተዋል።

እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያ ከቀውስ አዙሪት ያልወጣችው የፖለቲካ ባህላችን በበቀል አስተሳሰብ የተመረዘ በመሆኑ ነው። ትናንትም ሆነ ዛሬም እየተገዳደልን የምንኖረው ውስጣችን በበቀል ስሜት ስለጨቀየና ይህን የበቀል ባህል ለመቀየር ይህ ነው የሚባል ሥራ ባለመሥራታችን ነው። አገራችን ብዙ ብርቅዬ ልጆቿን ያጣችው፣ ባልተቋረጠው በቀል በወለደው የግጭትና የዓመፅ አዙሪት ለመሆኑ ታሪክ ተንታኝ አያስፈልገንም።

ለዘመናት ያካሄድናቸው የእርስ በርስ ግጭቶች መሠረታቸው በቀል ነው። ሌላው ቀርቶ የፈጣሪን ፍቅር ማስተማር የሚገባቸው የሃይማኖት አባቶች፣ በበቀል ስሜት ታውረው የሃይማኖት ተከታዮቻቸውን ለመግራት እንኳን ተነሳሽነት አያሳዩም። ምንም እንኳን በቃል በአደባባይ ስለሰላም ቢሰብኩም፣ ከመጋረጃ ጀርባ ግን በቀልን የሚያራምዱና የጥፋት ሴራ የሚጎነጉኑ ለመሆናቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው። ሃይማኖቶች ከአፈጣጠራቸው ጀምረው የፖለቲካ መሣሪያ ነበሩ፣ አሁንም ናቸው። ለዚህም ነው ዛሬ መስጊድ ሲቃጠል በአደባባይ ውግዘት፣ ከጀርባ ደግሞ የበቀል ዕርምጃ ግፊት የምናየው። በስልጤ ዞን ቤተ ክርስቲያን የተቃጠለው መስጊድ ውስጥ ፀሎታቸውን አጠናቀው ከመስጊድ በወጡ ሰዎች መሆኑ መምህራኑ ‘በቀል አያዋጣም፣ ከፈጣሪም ያጣላል’ ብለው አፅንተው ባለ መምከራቸው ነው። ይህ ባይሆን ኖሮ ከፈጣሪው ጋር በቤተ እምነቱ ተነጋግሮ (ፀልዮ) የወጣ ሰው ምንም ቢሆን ወደ ጥፋት ጎዳና ባልሄደ ነበር።

በጎንደርም የተከሰተው ከዚህ የተለየ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ስጡ እንጂ ንፉግ ሁኑ ብሎ አያስተምርም። ሕይወታቸው ላለፈው ሙስሊም አባት ቀብር ድንጋይ ከተፈለገ፣ ቤተ ክርስቲያኗም ሆነ ‹‹አማኝ›› ነን የሚሉት ሰዎች ድንጋዩን መስጠት ብቻ ሳይሆን፣ ቀብሩ በሥርዓት እንዲያልቅ ማገዝ ነበረባቸው። የሃይማኖቱም ትክክለኛ አስተምህሮ ይህ ይመስለኛል። ይህ በሃይማኖት ስም የተሠራ ሸፍጥ እንጂ ከሃይማኖቱ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። የተነሳውንም ግጭት ከማብረድና ለችግሩ መንስዔ የሆኑ ሰዎችን ከመገሰፅ ይልቅ፣ በውስጥ ያለው የበቀል ስሜት ያነሳሳቸው ‹‹የሃይማኖት መሪ ነን›› ባዮች ሁኔታዎችን ማባባሳቸው፣ ከክርስቶስ ትምህርትና ከክርስቲያን መርህ ያፈነገጠ ለመሆኑ ፈላስፋ መሆንን አይጠይቅም። ድንጋይ አትርፎ የእግዚአብሔር ፍጡር የሆነውን ክቡሩን የሰው ሕይወት የሚያጠፋስ በየትኛው ሃይማኖታዊ ትምህርት ታንፆ ነው? እኔ እንደሚገባኝ ችግሩ የሃይማኖቶቹ መርህ ሳይሆን፣ ችግሩ የሃይማኖቱን አስተምህሮ ለምዕመናን በተሳሳተ መንገድ ከማስጨበጥ የመነጨ ነው።

በሰበታ ውስጥ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ባዋጣቸው መሬትና ከሙስሊሙ ማኅበረሰብ በተዋጣ ገንዘብ ትምህርት ቤት መገንባቱ ያኮራንን ያህል በጎንደር፣ በስልጤና በሌሎች አካባቢዎች በሃይማኖት ተቋማት ላይ የተፈጸመው ጥቃትና ከዚያም ጋር ተያይዞ በጠፋው ሕይወትና በወደመው ንብረት ሁላችንም ልናፍር ይገባናል። ማፈር ብቻ ሳይሆን፣ የበቀል ባህላችን ከሥሩ ሊበጠስ የሚችልበትንም መንገድ ማቀድና መተግበርም ይኖርብናል። እኔ እስከማቀው ድረስ የየትኛውም ሃይማኖት የተቀደሰ መጽሐፍ የሰውን ሕይወት በከንቱ አጥፋ፣ ንብረት አውድም አይልም።

በሁለቱም ወገን ለደረሰው ጥፋት ዋና ተጠያቂዎቹ የሃይማኖቶቹ መሪዎች ናቸው። የሃይማኖት መሪዎች ምዕመኖቻቸውን የሚያስተምሩት ምንድነው? ይህ መልስ ማግኘት ያለበት ጥያቄ ነው። ፈጣሪ ሁሉንም የሰው ልጅ የሚያየው እኩል ነው። ሙስሊም፣ ክርስቲያን፣ ወዘተ የሚለውን ክፍፍል የፈጠርነው እኛ ነን። አላህና እግዚአብሔር አንድ ናቸው። ‹‹አላህ›› ዓረብኛ እንጂ ‹‹እስላምኛ›› አይደለም። በአማርኛ እግዚአብሔር፣ በእንግሊዝኛ (God)፣ በፈረንሣይ (Dieu)፣ በእብራይስጥ (elo’ah)፣ በዓረብኛ ደግሞ አላህ ነው። በዓረብ አገሮች የሚኖሩ ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን የሚጠሩት ‹‹አላህ›› ብለው ነው። የሰው ልጆች የተለያየ ስም ቢሰጡትም፣ ፈጣሪያችን ግን አንድና አንድ ብቻ ነው። ሁሉም ሃይማኖቶች ክቡሩ የሰው ልጅ የአንድ ፈጣሪ ፍጥረት መሆኑን እንደ ማስተማርና ፍቅርን እንደመስበክ፣ ለየራሳቸው ‹‹የሃይማኖት ችርቻሮ›› ሲሉ፣ በሰዎች መካከል ልዩነትን በመፍጠር፣ በማስፋትና አንዳንድ ተከታዮቻቸው በበቀል እንዲታወሩ በማድረግ ለማያባራ ግጭት እየዳረጉን ለመሆኑ በግልጽ፣ በድፍረትና በተደጋጋሚ ሊነገር ይገባል።

በአንድ አገር በሰላም ልንኖር የምንችለው አንዳችን ሌላችንን እንደ ሰው ስናከብር፣ አንዳችን የሌላችንን እምነት ሳንጋፋና ስንከባበር ነው። አባላት ለማብዛት በሚደረግ ፉክክር ውስጥ በዚህም በሚገመድ ተንኮል ማንም አያተርፍም፣ ማንም አይፀድቅም። መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹እሱ እንዳደረገብኝ እንዲሁ አደርግበታለሁ፣ አፀፋውን እመልሳለሁ አትበል›› ይላል (ምሳሌ 24:29)። ቅዱስ ቁርዓን በበኩሉ ‹‹ለዲያብሎሳዊ ሥራ የምትሰጠው የበቀል ምላሽ ራሱ ዲያቢሎሳዊ ነው፡፡ ሆኖም ማንም ይቅር የሚል ካሳውን የሚያገኘው ከአላህ ነው›› ይላል (ቁርዓን 42፡40)።

የየሃይማኖቶቹ የተቀደሱ መጽሐፍት የሚያስተምሩን ይቅር ባይነትን ነው። ጥያቄው ግን የየሃይማኖቶቹ መሪዎችና አስተማሪዎች ይህንን ያስተምራሉ ወይ ነው። በየሃይማኖቶቹ የተሰገሰጉትን ጽንፈኞችና ሃይማኖትን ለራሳቸው ፖለቲካ መጠቀሚያ የሚያደርጉትንስ የየሃይማኖቱ መሪዎች እንዴት ማፅዳት አቃታቸው? የማፅዳትስ ፍላጎት አላቸው ወይ? እነዚህ ጥያቄዎች በጥናት መልስ ሊገኝላቸው ይገባል። አንዱ ከሌላው የበላይ ለመሆን የሚያደርገው ፉክክርና የአባላቶቻችውን የበቀል ስሜት በመቆስቆስ እየፈጠሩ ያሉት የማያቋርጥ የግጭት አዙሪት መፍትሔው በሃይማኖት መሪዎቹ እንጂ በመንግሥት እጅ ብቻ አይደለም።

በተደጋጋሚ እንደምንሰማውም ከተራ ‹‹የኅብረተሰብ አንቂ›› ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የሃይማኖትና የፖለቲካ መሪዎች ሁሌም የሚሉት አስገራሚ ነገር አለ። ‹‹መንግሥት ዋና ኃላፊነቱ የዜጎችን ሰላም የማስጠበቅ ነው፡፡ መንግሥት ኃላፊነቱን ይወጣ›› የሚል ነው። የመንግሥት ዋና ኃላፊነት ሰላም ማስጠበቅ ነው ማለት፣ ሁሌም መንግሥት ችግር ከመፈጠሩ በፊት፣ ችግሮችን ማስቆም ይችላል ማለት አይደለም። የሃይማኖት መሪውም፣ የፖለቲካ መሪውም ሆነ አንቂው በየቦታው እሳት እየለኮሰ፣ መንግሥት እሳቱ እንዳይነሳ ማድረግ አልቻለም ብሎ መክሰስ ተገቢ አይደለም። በየትኛውም ዓለም ያለ መንግሥት ሙሉ ለሙሉ ችግሮች ከመነሳታቸው በፊት ሊያስቆም አይችልም። ችግሮች ከተከሰቱ በኋላ ግን መንግሥት አጥፊዎች ላይ ዕርምጃ የመውሰድ ግዴታና ኃላፊነት አለበት። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ችግሩ ከመከሰቱ በፊት፣ ችግሩ እንዳይነሳ የማድረግ ኃላፊነቱ የማነው? በሃይማኖት መምህራንና አመራሮች ያልተገራ አጥፊ ለሚያጠፋው ጥፋት ተጠያቂ መሆን ያለበት የሃይማኖት መምህሩና አመራሩ ነው፣ በፖለቲካውም እንዲሁ። የፖለቲካ ድርጅቶች አባላቶቻቸውን በተገቢው ሁኔታ በመግራት በነውጥ እንዳይሳተፉ ከማድረግ ይልቅ፣ ነውጥን እየሰበኩ አባላቶቻቸውና ደጋፊዎቻቸው ጥፋት ሲፈጽሙ መንግሥት ላይ ጣት መጠቆም ተገቢ አይሆንም።

ኢትዮጵያ የሁላችንም ነች፡፡ ሰላሟን የማስጠበቅ ግዴታ የሁላችንም ነው። የመግሥት አካላት ከመሀላችን የወጡ እንጂ ከሰማይ የመጡ ተዓምር ሠሪዎች አይደሉም። ሕወሓት ሥልጣን ከተቆናጠጠበት ጊዜ ጀምሮ ከሥልጣን እስከ ተወገደበት ጊዜ ድረስ፣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ተቋማት ያዳከመና በተለይም የፀጥታ መዋቅሩ ለአንድ ፓርቲ ብቻ እንዲቆም ሆኖ የተገነባ እንደነበር መረዳት አለብን። ከለውጡ በኋላ ግንባታው እንደ አዲስ የተጀመረ በመሆኑ ጠንካራ ሆኖ ለመውጣት ብዙ ይቀረዋል። ተቋም ለመገንባት ጊዜ ወሳኝ ነው። በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች ሽብር ለመፍጠር፣ የጅምላ ጭፍጨፋዎችን ለማካሄድና ሰላም ለመንሳት ቆርጠው የተነሱ የሽብርና የአጥፊ ኃይሎች መኖራቸውም የተዘነጋ ይመስላል። እነዚህን ኃይሎች መንግሥት ሊቋቋምና ሊያጠፋ የሚችለው በኅብረተሰቡ ትብብር ነው። እኛስ ችግር ከመፈጠሩ በፊት ችግር እንዳይፈጠር የማድረግ ኃላፊነት የለብንም ወይ? ችግር ከተፈጠረስ በኋላ ችግር ፈጣሪዎችን ለሕግ አካላት አሳልፈን የመስጠት ግዴታ የለብንም ወይ? ፋኖ አጠፋ ሲባል ተከራካሪው አማራ ብቻ ከሆነ፣ ሸኔ አጠፋ ሲባል ተከራካሪው ኦሮሞ ብቻ ከሆነ፣ ይህ አካሄዳችን በእውነት ለአገራችን ይበጃል ወይ? ለሙስሊሙ ክርስቲያኑ ካልተከራከረ፣ ለክርስቲያኑ ሙስሊሙ ካልተከራከረ የጋራ አገር ውስጥ በሰላም መኖር እንችላለን ወይ?

መንግሥትን መውቀስ ቀላል ነው፡፡ ራሳችንንስ በመስተዋት ማየት የለብንም ወይ? ኃላፊነት እንደሚሰማው ዜጋ ሁላችንም ለአገራችን ዘብ መቆም የለብንም ወይ? ወይስ በበቀል ደዌ ታመን፣ ‹‹የእኔ›› የማንለውን ኃይል ለመጣል በምናደርገው እኩይ ድርጊት አገርን በመጉዳት ዘላቂ ሰላም እናመጣለን ብለን እናስባለን?

ዛሬ አዲስ አበባ ተቀምጠው ወንበር የሚያሞቁና ‹‹ጭብጨባ ፍለጋ›› በመግለጫ የሚያደነቁሩን የፖለቲካ ኃይሎች ምን እየሠሩ ነው? መንግሥት የተቸገረውን እንዲረዳ የወቀሳ አለንጋቸውን ከመሞረድ ይልቅ፣ ሕዝቡን በማስተባበር ለተቸገረውና ከየቀዬው ለተፈናቀለው ኅብረተሰብ ዕርዳታ ለምን አያደርሱም? ሕዝብን ለማገልገል፣ ከልብ ለማገልገል የግድ ቤተ መንግሥት መገባት አለበት የሚል አስተሳሰብ ከየት ነው የመጣው? ኢትዮጵያ ውስጥ በጦርነት ሕዝብ ሲፈናቀል ይህ የመጀመርያው አይደለም። ከሶማሌ ጋር በተደረገ ጦርነት በደረሰው ጉዳትና መፈናቅል በግል አነሳሽነት፣ ዕርዳታ ስናሰባስብ ለነበርን ሰዎች አሁን በተሻለ ቴክኖሎጂ፣ የተሻለ ጥረት የማይደረግበት ምክንያቱ ግራ አጋብቶናል። በወሎ ረሃብ ጊዜ በወቅቱ የወጣት መሪዎች የነበሩት እነ ረዘነ በየነ ገብረ እግዚአብሔር በብሔራዊ ሎተሪ አዳራሽ ዕርዳታ ያሰባሰቡበት የኢትዮጵያዊነት መንፈስ የት ገባ? በጋሽ ጳውሎስ ኞኞ አስተባባሪነት አባቴም የተሳተፈበት የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች በራሳቸው አነሳሽነት ለወሎና ለትግራይ ረሃብተኞች ያሰባሰቡት ዕርዳታስ መንፈሱ የታለ? ከእነዚህ ልምዶች እንዴት ትምህርት አልተወሰደም? አንዳንድ የዛሬ ‹‹ጋዜጠኞቻችን›› ስለተቸገረው ሕዝብ የአዞ ዕንባ እያፈሰሱ ስህተት ፍለጋ ከማነፍነፍና አንዱን ብሔር ከሌላው ጋር ለማጋጨት፣ ተግተው ከመሥራት ይልቅና ስብለታለን ለሚሉት ተፈናቃይ ሕዝብ ምን ሠሩ? እነዚህ ኃይሎች በበቀል ስሜት የታመሙ በመሆናቸው፣ የመገናኛ ብዙኃንን ለራሳቸው ጠባብ ፍላጎት ሲጠቅሙብት እያየንና እያበረታታን መፍትሔ ማግኘት እንዴት እንችላለን?

ለዚህ ሁሉ የሰው ሕይወት መጥፋት፣ ንብረት መውደም ምክንያቱ የበቀል ባህላችን ነው። ችግሩን ካባባስነው ስለመንግሥት ጥፋት ነጋ ጠባ ካወራን፣ መንግሥትን ብቻ ተጠያቂ ካደረግን የማንፈልገው ቡድን ከሥልጣን ይነሳል በሚል የበቀል ስሜት የተገመደ አገር አጥፊ የበቀል ባህል በመንግሥት በኩል ያሉ ጥፋቶችን ተገቢና ገንቢ በሆነ መንገድ ከማረም ይልቅ፣ ‹‹ልጁንም፣ የታጠበበትንም ቆሻሻ ውኃ›› የመድፋት የቂም አስተሳሰብ አገራችንን እየጎዳ ነው።

አመራር ላይ ያሉ ሰዎችን በአስተሳሰባቸው ወይም በሥራቸው ሳይሆን፣ የምንመዝናቸው በሃይማኖታቸውና በዘራቸው በመሆኑ የእኔ አካል ናቸው እንደግፋቸዋለን፡፡ የእኔ ካላልናቸው ደግሞ አምርረን እንጠላቸዋልን። ስንጠላቸው ደግሞ በሥራቸው ስኬታማ እንዳይሁኑ ግጭት እናራግባለን። መልሰን ስለሰላም የምንጠይቀው ደግሞ እኛው እንሆናለን።

‹‹ትኋንን ለማጥፋት ቤትን የማቃጠል›› ዕርምጃ በሃይማኖቱም፣ በፖለቲካውም የምናየው የአገር ጠንቅ ሊወገድ የሚችለው የበቀል ባህላችንን ከሥሩ ነቅለን ስንጥል ብቻ ነው። በአንድ ጉንጭ ስለሰላም እየሰበኩ፣ በሌላ ጉንጭ ጥፋትን ማስተማር የሚያጠፋው ሁላችንንም መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። እንደዚህ ጸሐፊ እምነት የወደፊት አብሮነታችንንና ዘላቂ ሰላም ልናሰፍን የምንችለው አደገኛውን የበቀል ባህል ለመቀየር፣ በጥናት የተደገፈ መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጣ ሥራ ስንሠራ ብቻ ነው። በተለይም የተቋቋመው የሰላምና የዕርቅ ኮሚሽን የበቀል ባህላችንን ለመለወጥ ተግቶ ካልሠራ፣ ስብሰባ ብቻውን ለውጥ ያመጣል ብሎ ማመን አስቸጋሪ ነው። ገና ከጅምሩ በርካታ የፖለቲካ ኃይሎች እንቅፋት ሲፈጥሩ የምናየው፣ ውስጣቸው ባለው የበቀል ስሜት ነው።

ዛሬም ዓላማቸው የአገር ፅናት ሳይሆን በአቋራጭ ሥልጣን መያዝ ነው። ሐሳብ አቅርበው በሐሳብ ተሟግተው የሕዝብን ልብ ለማሸነፍ አቅም የሌላቸው፣ ገና ከ70ዎቹ የበቀል የፖለቲካ አስተሳሰብ ያልተላቀቁና የሙሾ ፖለቲካ ላይ የተቸነከሩ ፖለቲከኞች አርቀው የሚያዩት እስከ ሥልጣናቸው እንጂ፣ ከሥልጣን ባሻገር ለአገር ዘላቂ ሰላምና ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገር ሥልተ ሥርዓት የመገንባት አዎንታዊ ሥራ ላይ አይደለም። ይህም የሆነው ውስጣቸው በበቀል የተሞላ በመሆኑ ነው። ለዚህም ነው አገራችንን በጥናት በተደገፈ ከፍተኛ ሥራ የበቀል ባህልን ከአገራችን ማፅዳት ያለብን። ለዚህም ነው ከበቀል የፀዳ ኅብረተሰብ ስንገነባ አገራችን ኢትዮጵያ ከግጭት አዙሪት የምትወጣበት ዕጣ ፈንታ የሚሆነው።

ሰላም ለኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን እግዚአብሔር ይጠብቅ፣ ይባርክ።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...