እነሆ መንገድ። ጊዜና ሥፍራ ተጋግዘው በውስነንት ይዘውናል። መፍጠን ያቃተው ‹የጊዜ እንጂ የሰው ጀግና የለውም› እያለ እጁን ሰጥቶና አንገቱን ደፍቶ ይኖራል። ስለደጉ ጊዜ ይዘምራል፡፡ ክፉውን ይኮንናል። ጊዜን የቀደመው ደግሞ በእጆቹ ሥራ ኮርቶ ይጀግናል፡፡ አንዳንዱም ሰው ከማያየው ህሊናው ጋር እንደተሟገተ ‹የፍጥነት እንጂ የጊዜ ጀግና የለውም ያለው ሳይንቲስት ለዘለዓለም ይኑር› እያለ በወኔ ይጣደፋል። በመሀል በጊዜም በፍጥነትም ነገር ያልገባው፣ ቀኔም ውሎዬም ስሜም እኔም እንደተጻፈልኝ እንጂ፣ እንደምጽፈው የምኖረው አይደለም በሚል ስሜት፣ የሚያየውንና የማያየውን ለአንድ ታላቅ አምላክ አስገዝቶ ውረድ ሲሉት ይወርዳል፣ ተሳፈር ሲሉት ይሳፈራል። አይስቅም፣ አያለቅስም፣ አይደሰትም፣ አያዝንም። ይህም እንደ ተጻፈለት እንጂ እንደ ጻፈው አይደለምና። ከላይ ሰማይ አለ። ከሰማዩ በታች አልፎ አልፎ ደመና፣ አልፎ አልፎ ብርሃን፣ አልፎ አልፎ ጨለማ፣ ከአልፎ አልፎዎቹ በታች ተራራ፣ ወንዝ፣ ባህርና የብስ አለ። በወንዞቹ፣ በተራራዎቹ፣ በየብሳቱ መካከል ክልልና ኬላ፣ ከተማና ገጠር፣ ቀበሌና መንደር አሉ። አንዳንዱ የተጨናነቀ፣ አንዳንዱ ነፃ የሆነ መንገድ መኖሩ ሳይዘነጋ። አንዳንዱ ሕይወት፣ ትዳር፣ እምነት፣ ፅናት የሚያፈርስ ሌላው የልኬቱን ብቻ ታሪፍ የሚቀበል ጎዳና። ከእዚህ ጎዳና በአንዱ እንደ አበቃቀላችንና ኑሯችን የማናምን ተሰብስበን ታክሲ ይዘናል። አቀማመጣችን በሒሳባዊ ቀመር መገለጽ ቢችል ወይም ባይችል የማንደነግጥና የማንደመም፣ ብቻ ወያላው ‹ዛሬ ሒሳብ በእኔ ነው› ቢለን ጮቤ የምንረግጥ ታካች መንገደኞች ነን። በቅርበትና በርቀት ከአዕምሯችን በላይ በሆኑ ጥበቦችና ሐሳቦች ከተሠራው ዓለማችን በላይ ተጋፍተን ወንበር መያዛችን የሚያስፈነድቀን ምስኪን የሕይወት እስረኞች ነን። መንገድ የሌለበት የለምና ከደመናው በላይ ባንጓዝ ከደመናው በታችን መጓዝ አላቋረጥም። መንገድ ውሎ ይግባና!
‹‹ሾፌር ንዳዋ ጊዜያችንን ገደልከው እኮ…›› ጋቢና የተቀመጠ ወጣት ሾፌራችንን ይጠዘጥዘዋል። ‹‹ምን ጊዜ አለ ደግሞ እዚህ አገር?›› አለው ከጎኑ የተቀመጠ ሌላ ተሳፈሪ። ‹‹እንዴት?›› ግራ ተጋብቶ ዞሮ አየው። ሾፌሩ ወያላውን እየጠቀሰ ትርፍ እንዲጭን ያበረታታዋል። ‹‹ኧረ ተወኝ አንዳችንም የለንም…›› መለሰ ‘ምን ጊዜ አለ’ ባዩ። ‹‹ከማንና ከማን?›› ጠየቀው የቸኮለው ወጣት። ‹‹ከጊዜና ከእኛ አንዳችን እዚህ አገር ላይ የለንም ብዬ ነው የማምነው…›› አለው ኮስተር ብሎ ሐሳቡን ለምጡቅ የፊዚክስ ሊቅ እንደሚያቀርብ ታታሪ ተማሪ። ‹‹ታዲያ እንደ እሱ አትለኝም። መጀመርያውኑም ‘ብዬ ነው የማምነው’ ብለህ ሐሳብህን አቅርበህ ቢሆን ኖሮ ይኼው ገና አሁን ቁርሴን በልቼ ከመውጣቴ ደንግጬ ረሃብ አይሰማኝም ነበር…›› አለ በጎን ሾፌሩን እንሂድ እያለ እየወተወተው። እንዲያ ነው!
‹‹አልገባኝም›› አለው ደግሞ በተራው ያኛው ግራ ተጋብቶ። ‹‹ጊዜ የሚባል ነገር እኛ ዘንድ የለም አልክ። ቀጠልክና ወይ እኛ ወይ እሱ አንዳችን የለንም አልከኝ። ማስረጃ ያለህ መስሎኝ ደግሞ ምን ተዓምር አመለጠኝ ብዬ እህ ብዬ ሳዳምጥም አገር፣ ጊዜና ሕዝብ የመገነጣጠል መላምታዊ ሐሳብህ በእምነት ላይ እንደተመሠረተ ነገርከኝ። እንኳን በተጨበጠ የፍጥረት ሕግና ቁጥር ላይ አልተመሠረተ እንጂ፣ በሐሳብና በእምነት ላይ የተመሠረተ የመነጠልና የመገንጠል ቲዮሪ ፍርኃት አይዞህ ለቆናል…›› እያለ ይባስ ግራ አጋባው። ‹‹ማነው ስለአንቀጽ 39 የሚያወራው?›› ብሎ ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጠ ሳቂታ ሰውዬ ጣልቃ ሲገባ፣ ‹‹ምናለበት አንቀጽ መቁጠሩን ትታችሁ ዕድሜያችሁን ብትቆጥሩ? አዳሜ ከ39 ዓመት በላይ መኖር በማይችልበት አገር አሁንም አንቀጹ ላይ ነው?›› ብላ ከሰውዬው አጠገብ የተሰየመች ወጣት ሳቀች። እንዲያው የአንዳንዱን ሳቅ ዓይነት ለመግለጽ የሆነ የሳቅ መለኪያ ‹ዩኒት› በኖረ ያስብላል፡፡ አንዳንዴ!
ወያላው ሒሳቡን ሰብስቦ መልስ ያከፋፍላል። መጨረሻ ወንበር የተየሰመ ወጣት ስለሰብዓዊነት ይተረተራል። ‹‹ሌላው ቢቀር ጓደኛዬ ሠፈር ውኃ የለም እያልን እኛ ሁለት ሰዓት ሙሉ ሻወር ስንወስድ ትንሽ አናፍርም?›› አለ። ‹‹ማነን እኛ?›› አለች መሀል መቀመጫ ላይ ወይዘሮዋ። ‹‹ኧረ ቆይ ተይው፣ አሁን ይኼን ከሰብዓዊ አስተሳሰብ ጋር ምን ያገናኘዋል? ውኃ የሚጠፋው ስለማያልፍልን። ሻወር የምንወስደው ስላለፈልን። ቆይ ምን ለማለት ነው?›› ብሎ ሦስተኛው ረድፍ ላይ አጠገቤ የተሰየመው ጎልማሳ አፈጠጠበት። ‹‹በሉ በሉ ውኃ ፈረቃ ገባን ብለን ያልተጣላን ሰዎች በሻወር ልንጣላ ነው?›› ሲል አንዱ፣ ‹‹ካላችሁስ ዘመኑ ብዙ ሻወር የሚያስወስድ ነው…›› አለ ሌላው። ‹‹እንዴት?›› ሲባል፣ ‹‹ታጥቦ የማይጠራው በዝቷላ። ተነግሮት የማይለወጠው፣ ተመክሮ የማይሰማው፣ ተለምኖ የማይራራው እኮ ነው መንገዱን አጓጉል እያደረገ ፍዳችንን የሚያሳየን። ዛሬ ብንነቃ ነገ ፈዘን እንውላለን። እውነቱና ሀቁ እዚህ አፍንጫችን ሥር ተኝቶ አናስተውለውም። ሙሰኛው አጠገባችን እየበላ እየጠጣ ቆይቶ ጋባዥ እኛው ነን። እንዲያው በአጠቃላይ አይደለም የሁለት የ24 ሰዓት ሻወር ብንወስድ ያንሰናል?›› ብሎ እንዳበቃ፣ ‹‹የምሩን ነው? በውኃ እጥረትና በመዋጮ በአበደች አገር ተቀምጦ 24 ሰዓት ሻወር ሲል አያፍርም?›› ይለኛል። ወዬው በሆነልንና ውኃው በባከነ ብዬ በልቤ ዝም። አያሰኝም እንዴ? የአስተሳሰብ ውዝግባችን ብዛቱ?
ጉዟችን ቀጥሏል። መሀል ረድፍ ላይ ከወይዘሮዋ ጋር የተሰየመች ሠርቶ አዳሪ ከት ብላ ሳቀች። ‹‹እንዴ ምንድነው እንዲህ ያለ ማስጠንቀቂያ የምትስቂው?›› ስትላት ጨመረችው። ‹‹ወይ አዲስ አቤ አያ፣ ሳቅም በማስጠንቀቂያ ነው ደግሞ? ኧሯ…›› እያለች ከላይ እስከ ታች እያንዳንዳችንን ታነሳ ትጥለን ጀመር። ‹‹የየት አገር ልጅ ነሽ?›› ወይዘሮዋ ናት የምትጠይቃት። ‹‹ባህር ዳር። ፓስፖርት ላወጣ መጥቼ ነፍሴ ልትወጣ ነው…›› ብላ ታከተች። ‹‹ወዴት ልትሄጂ ነው?›› ከማለቷ ሴትዮዋ፣ ‹‹አልተማርኩ፣ አልነገድኩ፣ አቅም የለኝ፣ ዘመድ የለኝ። አንዱ አገር ሄጄ የአርባ ቀን ዕድሌ እንደሚያደርገኝ ለመሆን ነዋ…›› ስትላት ወይዘሮዋ ቆጣ ብላ፣ ‹‹እኛ ምንሽ ነን? ይኼ አገር ምንሽ ነው? ቤትሽ እኮ ነው። እኛም ዘመዶሽች ነን። ለምን ስደት?›› ብላ ሰቀዘቻት። ‹‹ኧረ ይተውኝማ። ‹መኒ› ነው አሉ ጨዋታው ዘንድሮ። ያለ ‹መኒ› የለም ‹ፈኒ› ይላሉ። በዚያ ላይ ሴት ነኝ። ወንድ ብሆን ባጃጂቷንም ቢሆን ተበዳድሬ ገዝቼ እሯሯጥ ነበር። ማጀት ለማጀት ከመሯሯጥ ሸጋ ጥቅም ያለበት አገር ሄጄ ጭስ የማያውቀው ማጀት ብገባ እመርጣለሁ፣ ይተውኝማ…›› ብላ ቆዘመች። ‹‹ወይ አንቺ አገሬ፣ አንድ አገር ውስጥ ሆነን ለካ ማዶ ለማዶ ነን…›› ሲል ጎልማሳው፣ ‹‹ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም›› ብላ ወይዘሮዋ መልካሙን ሁሉ ተመኘችላት። ከመመኘት በቀር መከወንማ የጥቂቶች ፀጋ ሆኗል እንግዲህ!
ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። መጨረሻ ወንበር ከተቀመጡት ወጣቶች መካከል ስለሰብዓዊነትና ስለመተዛዘን ሲሰብክ የነበረው ወራጅ ብሎ አስቆመን። ሲወርድ መሀል መቀመጫ በአነጋገር ዘዬዋና በቀናነቷ ቀልባችን ስትስብ የቆየችውን ምስኪን ሠርቶ አዳሪን ረገጣት። ‹‹ኧረ ኡኡኡኡ፣ ኧረ ገደለኝ እናንተ፣ ኧረ እኔስ እንጃልኝ ወዬው፣ ኡሁሁሁሁ!›› እያለች አቀለጠችው። ተሳፋሪዎች ከመደንገጥና ምን ሆንሽ ከማለት ይልቅ ባደገችበት የቋንቋ አገላለጽ ልማድ አጋና ስታቀርበው፣ እንደ ቴአትረኛ ፈዘው እያዩዋት በሳቅ አሽካኩ። እሷም አፍራ በነጠላዋ ዓይኗን ሸፈነች። ያ ወጣት ግን መለስ ብሎ ‹እኔን› ሳይል ‹ይቅርታ› ሳይል ቀጥ ብሎ ሄደ። ‹‹አይዞሽ!›› አለች ወይዘሮዋ። ‹‹ኧረ እኔስ ተርፌያለሁ እሱ ነው እንጂ፣ ቅድም እንዲያ ሲደሰኩር እንዳልነበር እንደ ኮርማ መለስ ብሎ ሳያየኝ የሄደው። ኧረ፣ ወይ አዲስ አበባ አያ…›› እያለች ንፅፅር ጀመረች። ‹‹እንዴ ቅድም እንዲያ ስለሰውና ሰብዓዊነት ሲደሰኩር እንዳልነበር ምናለበት አሁን ቢያንስ ትዝብቱን ፈርቶ ይቅርታ ብሏት ቢወርድ?›› ወይዘሮዋ ነገር ለኮሰች። ደግሞ ለነገር!
‹‹ካወራን አይበቃም ብለሽ ነው። ዘመኑ እኮ የወሬ እንጂ የተግባር አይደለም። ከማን አንሼ ‹በቶክ› ሆኗል። ሥራማ ድሮ ቀረ…›› እያለ ተሳፋሪዎች መቀባበል ጀመሩ። ‹‹ያም ሆነ ይህ ቃል የእምነት ዕዳ ነው። መቼም ልናበዛውና ልናሳንሰው እንችላለን እንጂ ምንም ነገር እንዲያው ሳናምንበት አናወራም። አይደለም እንዴ?›› ሲል ጎልማሳው ‹‹ተወው እሱን። ዘንድሮ ከልብ ሳይሆን ከፌስቡክና ከዩቲብ የቃረመውን ነው የሚያወራው። ለዚያም እኮ ነው በተግባር የማያሳየውን ነገር ሲዘባርቅ መዋል የበዛው። ሌብነትም ይባል የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ የፍትሕ ይሁን የዴሞክራሲ ዕጦት የመሳሰሉት አላስኖሩን አሉ እያልን፣ ስንትና ስንት የአገር ሸክሞች በእኛው በግለሰቦች ደረጃ ሊቃለሉ የሚችሉ እያሉ፣ ወሬያችንና ትችታችን እንዳበቃ ሀሞታችን ይፈሳል። ደግሞ ለሌላ የቃል የዲስኩር ሐሜትና ትችት አጠራቅመን እንመለሳለን…›› ብሎ ከመጨረሻዎቹ አንዱ የልቡ እስኪደርስ አወራ። ወያላው ‹‹መጨረሻ!›› ብሎ በሩን ከፈተው። እኛም ‹የወሬ ማብቂያ የተግባራዊነት መጀመርያ ዘመን የትኛው ፌርማታ ላይ ይሳፈርብን ይሆን?› እየተባባልን ወረድን። አንዳችን በሌላችን ላይ እያላከክን ዘመኑ እንዴት ይገፋ ይሆን? ያ ወጣት እንዳለው አንድ አገር ውስጥ ሆነን ማዶ ለማዶ መሆናችን አይገርምም? ኧረ አንገፋፋ! መልካም ጉዞ!