Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናከስድስት ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን ከየመን ወደ አገራቸው ሊመለሱ ነው

ከስድስት ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን ከየመን ወደ አገራቸው ሊመለሱ ነው

ቀን:

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) ጦርነት ውስጥ ባለችው የመን የሚገኙና ለመመለስ ፈቃደኛ የሆኑ 6,750 ኢትዮጵያውያንን ወደ አገራቸው ሊመልስ መሆኑን አስታወቀ፡፡ ድርጅቱ እስካሁን ድረስ 600 ስደተኞችን ከየመን ወደ ኢትዮጵያ እንደመለሰ ያስታወቀ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ወላጅ ወይም አሳዳጊ የሌላቸው 60 ስደተኛ ሕፃናት እንደሚገኙበት ገልጿል፡፡

ተቋርጦ የነበረውን ፈቃደኛ ስደተኞችን ወደ አገራቸው የመመለስ ፕሮግራም በተያዘው ወር ማስጀመሩን ማክሰኞ ግንቦት 16 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ያስታወቀው ድርጅቱ፣ እስካሁን ሦስት በረራዎችን ማድረጉን ጠቁሟል፡፡ በቀጣዮቹ ሳምንታት ተጨማሪ በረራዎችን ለማድረግ መርሐ ግብር እንደያዘም አክሏል፡፡

በመግለጫው ላይ የተጠቀሱት የድርጅቱ የየመን ተልዕኮ ኃላፊ ክሪስታ ሮተንስታይነር፣ የመንን አቋርጠው የሚያልፉ ወይም በአገሪቱ አጣብቂኝ ሁኔታ ውስጥ የገቡ ስደተኞች በየመን እየተባባሰ በመጣው ሁኔታ ችግር ውስጥ ከወደቁት መካከል መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ስደተኞቹ እንደ የዘፈቀደ እስራት፣ የግዳጅ ዝውውር፣ ብዝበዛ፣ ማሰቃየትና የመሳሰሉ ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ተፈጽመውባቸው ሕይወታቸው አደጋ ላይ ሲወድቅ ወደ ድርጅቱ ማዕከላት እንደሚመጡ አስረድተዋል፡፡

በእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ውስጥ በመሆናቸው ወደ አገራቸው ለመመለስ ፈቃደኛ የሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ፍላጎታቸውን እንደገለጹለት ያስታወቀው ድርጅቱ፣ ነገር ግን ይህንን ለማድረግ ድጋፍ እንደሚፈልግ አስረድቷል፡፡ ተመላሾቹን ደኅንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ ለመመለስና የጤና ድጋፍ ለማቅረብ እንዲችል የ7.5 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

በየመን የሚገኘው የድርጅቱ ቅርንጫፍ ተመላሾቹ ወደ አገራቸው ለመመለስ የሚያስችላቸውን የጉዞ ሰነድ ማዘጋጀት፣ በረራ የማመቻቸትና ከባለሥልጣናት ጋር ንግግር የማድረግ ሥራ የሚያከናውን ሲሆን፣ ስደተኞቹም ከመምጣታቸው በፊት የምክር አገልግሎት ያገኛሉ ተብሏል፡፡ ከየመን ተነስተው ኢትዮጵያ ሲደርሱ ደግሞ ምግብ፣ ጊዜያዊ መጠለያ፣ ሕክምና እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶችን እንደሚያገኙ መግለጫው አስታውቋል፡፡

የዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በኤደን ባህረ ሰላጤ በኩል ወደ ስደት ያመራሉ፡፡ እ.ኤ..አ. በ2011 ቀውስ ከመከሰቱ በፊት የመን ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን ታስተናግድ የነበረ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ ኢትጵያውያንና ሱዳናውያን ናቸው፡፡ በየመን ቀውስ ከተከሰተ በኋላ ደግሞ እነዚህ ስደተኞች አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መግባታቸውን ድርጅቱ አስታውቋል፡፡

በየመን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የመጠለያ ጣብያቸው የመቃጠል፣ የመታፈንና ተገዶ የሁቲ አማፅያንን የመቀላቀል አደጋ የሚያጋጥማቸው ሲሆን፣ በየመን በኩል ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ዱባይና ሌሎች የቀጣናው አገሮች ለማለፍ የሚደረግ ሙከራ ስደተኞቹን ለዚህ አደጋና ሞት የሚያጋልጣቸው ዋነኛ ምክንያት ነው፡፡

በጂቡቲ በኩል ወደ የመን ከሚጓዙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መካከል ሁለት ሦስተኛው በየመን ጦርነት ስለመኖሩ እንደማያውቁም የድርጅቱ ጥናት ያመላክታል፡፡ ወደ የመን ከሄዱ በኋላ በታጣቂዎች ተገደው የመግባት ዕድላቸው ከፍተኛ በመሆኑም፣ በርካታ ወጣት ኢትዮጵያውያን ግቡንና ዓላማውን ባልተረዱት ጦርነት ውስጥ እየተዋጉ መሆኑን ድርጅቱ አስታውቋል፡፡ የኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ከፍተኛ ተጋላጭነት ያላቸው በመሆኑ እንደ አልሸባብ፣ አልቃይዳና ሁቲ በመሳሰሉ ታጣቂዎች የመቀጠር ዕድላቸው እንደጨመረ ተገልጿል፡፡

የዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት ከኢትዮጵያ፣ ከጂቡቲ፣ ከሶማሊያና ከየመን መንግሥታት፣ እንዲሁም ሌሎች አገሮች ጋር በመተባበር በየመን የሚገኙና ከአፍሪካ ቀንድ ለተሰደዱ ግማሽ ሚሊዮን ፍልሰተኞች ዕርዳታ የማቅረብ ዕቅድ አለው፡፡ ይህንን ዕቅድ ለማሳካት 67 ሚሊዮን ዶላር በጀት ይጠይቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...