የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በተለያዩ አካባቢዎች በመፈጸም ላይ ያሉ የጋዜጠኞች፣ የማኅበረሰብ አንቂዎችና የሌሎች ሰዎች እስራትን በተመለከተ በሰጠው መግለጫ፣ የፌዴራልም ሆኑ የክልል የፀጥታ ኃይሎች ተጠርጣሪዎችን ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጪ ከማሰር እንዲታቀቡ አሳሰበ።
የተወሰኑት ተጠርጣሪ ታሳሪዎች በቤተሰቦቻቸው የተጎበኙና በተለያየ የጊዜ መጠን ወደ ፍርድ ቤት የቀረቡ ቢሆንም፣ በርካታ ታሳሪዎች ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጪ መታሰራቸውን፣ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውንና በቤተሰብ አለመጎብኘታቸውን መመልከቱን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
የፌዴራል መንግሥትና የክልል የፀጥታ ኃይሎች ‹‹በተቀናጀ መንገድ የሕግ በላይነትን ማስከበር›› በሚል፣ ባለፉት ጥቂት ቀናት መውሰድ በጀመሩት ዕርምጃ፣ ጋዜጠኞችና የማኅበረሰብ አንቂዎችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች መታሰራቸውን ገልጿል፡፡
ኮሚሽኑ ሁኔታዎችን በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን በተለይም በአማራ ክልል በርካታ ታሳሪዎች ከመደበኛ መኖሪያ አካባቢያቸውና ከመደበኛ እስር ቦታዎች ውጪ ጭምር በመታሰራቸው፣ ቤተሰቦቻቸው ያሉበትን እንኳን ለማወቅ መቸገራቸውን ማወቁን በመግለጫው አብራርቷል።
በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር መንግሥት በሕጋዊ መንገድ ሊወስድ የሚችላቸውን ዕርምጃዎች እንገነዘባለን ያሉት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፣ ‹‹የዚህ ዓይነት የሰብዓዊ መብቶች መርሆዎችን ያልተከተለና የተስፋፋ እስር ተገቢ አይደለም፤›› ብለዋል።
በተለይም የፌዴራልም ሆነ የክልል የፀጥታ ኃይሎች ተጠርጣሪዎችን ከወንጀል ምርመራ በፊት ከማሰር፣ ጋዜጠኞችን በሥራቸው ምክንያትና ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ ሰዎችን ከማሰር ሊታቀቡ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በተጨማሪም በማናቸውም ዓይነት ሁኔታ የታሰሩ ሰዎች ሁሉ ቤተሰቦቻቸው ወዲያውኑ እንዲያውቁ እንዲደረግና ወደ ፍርድ ቤትም ሊቀርቡ ይገባል ብለዋል፡፡ በማናቸውም ሥፍራ በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎችን ሁኔታ በድንገተኛ ጉብኝት ለመከታተል በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት፣ ክትትል በማድረግ ላይ ስለሆነ፣ ሁሉም የፌዴራልና የክልል መንግሥታት አካላት ለኮሚሽኑ ሥራ የመተባበር ግዴታቸውን በአግባቡ እንዲወጡም ኮሚሽነር ዳንኤል (ዶ/ር) አሳስበዋል፡፡