ክረምት ከመግባቱ በፊት ሙሉ ለሙሉ እንደሚመለሱ የክልሉ መንግሥት አስታውቋል
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በግጭት ምክንያት ተፈናቅለው የሚገኙ ከ400 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች በአስቸኳይ ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ፣ የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቦዴፓ) ጠየቀ፡፡ ተፈናቃዮቹ ክረምት ከመግባቱ በፊት ሙሉ ለሙሉ እንደሚመለሱ የክልሉ መንግሥት አስታውቋል፡፡
በክልሉ ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ በነበሩ ግጭቶች የተፈናቀሉ ሰዎች በአሁኑ ወቅት በካምፕና በተለያዩ ቦታዎች መኖራቸውንና ክረምት ከመግባቱ በፊት ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ ፓርቲው ጠይቋል። ተፈናቃዮቹ በቂ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንዳልሆነና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ፣ የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የጥናትና ምርምር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሙሉቀን ብርሃኑ ለሪፖርተር ገልጸዋል።
በክልሉ በተወሰደ የሰላም ማስከበር ዘመቻ አንፃራዊ ሰላም መገኘቱን ገልጸው፣ ነገር ግን ተፈናቃዮችን ወደ ቦታቸው የመመለሱ ሒደት መዘግየቱንና በአስቸኳይ የመመለስ ሥራው ሊከናወን ይገባል ብለዋል።
በርካታ ንብረቶችም በመውደማቸው ተፈናቃዮቹን ወደ ቀዬአቸው ከመመለስ በተጨማሪ፣ እንዲቋቋሙ ዕገዛ ሊደረግ ይገባል ሲሉ አክለዋል። ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት በርካታ ሰዎች ከእርሻ ሥራ ውጪ ሆነው መቆየታቸውንና ይህም በዚህ ዓመት የሚቀጥል ከሆነ ለከፍተኛ ረሃብ ሊያጋልጥ የሚችል በመሆኑ፣ የክረምት ወቅቱ ከመምጣቱ በፊት ወደ ቀዬአቸው ተመልሰው ወደ እርሻ ሥራ ማሰማራት ያስፈልጋል ብለዋል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሚገኙ የተለያዩ ዞኖች የሚገኙ ተፈናቃዮችን በተመለከተ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር አቶ ታረቀኝ ተሲሳ፣ በክልሉ በአጠቃላይ 442 ሺሕ ተፈናቃዮች መኖራቸውንና ይህም ቁጥር ከክልሉ ሕዝብ አንድ ሦስተኛ እንደሚሆን ገልጸዋል።
በመተከል፣ በካማሺና በአሶሳ ዞኖች ተፈናቃዮች በብዛት እንደሚገኙ ገልጸው፣ እስካሁን የሰባዓዊ ዕርዳታ በበቂ ሁኔታ እየደረሰ ነው ብለዋል። ለዚህም በተለይም መንግሥት እስከ 70 በመቶ የሚሆነውን ዕርዳታ እየሸፈነ መሆኑን፣ ለእያንዳንዱ ተፈናቃዮች በወር 15 ኪሎ ምግብ ነክ ዕርዳታ እየደረሰ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ነገር ግን ዕርዳታውን በማድረስ በኩል ምዕራብ ወለጋ አካባቢ መንገድ በመዘጋቱ መቸገራቸውን ገልጸዋል። በግጭቱ በርካታ የግል ንብረቶች፣ እንዲሁም 189 የጤና ተቋማትና ከ250 በላይ ትምህርት ቤቶች መውደማቸውን ገልጸዋል። በመሆኑም ተፈናቃዮችን ወደ ቦታቸው መልሶ ለማቋቋም ፈታኝ መሆኑን ጠቁመው፣ ሁሉም የበኩሉን ዕገዛ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
በክልሉ የእርሻ ወቅት ከመድረሱ ጋር ተያይዞ ማዳበሪያና ሌሎች ግብዓቶች በሚፈለገው ደረጃ ባይሆንም መገኘቱን ገልጸው፣ ሥርጭት እየተደረገ ነው ብለዋል። ተፈናቅለው የሚገኙ ሰዎችን መጪው የክረምት ወቅት ከመግባቱ በፊት፣ ወደ ቀዬአቸው እንደሚመለሱ አቶ ታረቀኝ አክለዋል፡፡