Sunday, February 5, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ቁጥጥር የማይደረግበት የፍራንኮ ቫሉታ ንግድ መዘዞች

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥት በመሠረታዊ የፍጆታ ሸቀጣ ሸቀጦች ላይ የሚታየውን የአቅርቦትና የፍላጎት አለመጣጣም ለማጥበብና የውጭ ምንዛሪ እጥረት የፈጠረውን ጫና በመጠኑ ለማቅለል በማሰብ, የፍራንኮ ቫሉታ ንግድን ከጥቂት ሳምንታት በፊት መፍቀዱ ይታወሳል። 

ቁጥጥር የማይደረግበት የፍራንኮ ቫሉታ ንግድ መዘዞች | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር ቁጥጥር የማይደረግበት የፍራንኮ ቫሉታ ንግድ መዘዞች | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር 

ይህንን ተከትሎም በመደበኛው የውጭ ምንዛሪ ገበያና በጥቁር ገበያው መካከል የነበረው የዶላር መግዣ ዋጋ በከፍተኛ ምጣኔ ማሻቀቡ እየተስተዋለ ነው። 

መንግሥት የፍራንኮ ቫሉታ የንግድ ዕድልን በፈቀደበት ወቅት አንድ የአሜሪካን ዶላር በመደበኛው የውጭ ምንዛሪ ገበያ ላይ ይሸጥ የነበረው 52 ብር ገደማ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ወቅት በጥቁር ገበያው የነበረው የአንድ ዶላር ዋጋ 63 ብር ገደማ እንደነበር ሪፖርተር የሰበሰባቸው መረጃዎች ያመለክታሉ። 

በመደበኛው የውጭ ምንዛሪ ገበያ የአንድ ዶላር መሸጫ ዋጋ በአነተስተኛ ምጣኔ ጨመሩን ቢቀጥልም፣ በአሁኑ ወቅት ያለው የመሸጫ ዋጋ ከ52 ብር ዘሎ አልሄደም። ይሁን እንጂ የፍራንኮ ቫሉታ ንግድ መፈቀዱን ተከትሎ የጥቁር ገበያው የመሸጫ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ እያሻቀበ በመሄድ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ አንድ ዶላር ከ70 ብር እስከ 71 ብር በመሸጥ ላይ መሆኑን ሪፖርተር ማረጋገጥ ችሏል። 

ከዚህም ባለፈ ሕገወጥ የዶላር ዝውውር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ሲሆን፣ በጉምሩክ ኮሚሽንና በፌዴራል ፖሊስ ሰሞኑን በሕገወጥ መንገድ ከአገር ሊወጡ ሲሉ የተያዙ የውጭ ገንዘቦች በመጠን መጨመራቸው ተስተውሏል።

በጥቁር ገበያው እየታየ ያለው የምንዛሪ ዋጋ ተመን መጨመርና በሕገወጥ የውጭ ምንዛሪ ዝውውር ከተያዙት ተጠርጣሪዎች በአንድ ጊዜ የተገኘው የውጭ ገንዘብ መጠን መጨመር መንግሥት ከፈቀደው የፍራንኮ ቫሉታ ንግድ ጋር ቀጥትኛ ግንኙነት ያለው መሆኑን ለማረጋገጥ አስቸጋሪ ቢሆንም፣ የፍራንኮ ቫሉታ ንግድ አሠራር ጥንቃቄና ቁጥጥር ካልተደረገበት ይህንን መሰል ችግር ሊያመጣ እንደሚችል የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይመክራሉ።

አንዳንድ ምግብ ነክ ምርቶችን በፍራንኮ ቫሉታ እንዲገቡ መፍቀዱ ተገቢ ቢሆንም፣ ይህ ውሳኔ በጥቁር ገበያውና በመደበኛው የውጭ ምንዛሪ ዋጋ መካከል ሰፊ ልዩነት እየፈጠረ ከሄደ በኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ላይ ተፅዕኖ ሊያሳርፍ እንደሚችል ባሉሙያዎቹ ያነሳሉ።

በተለይ ፍራንኮ ቫሉታን ያላግባብ ትርጉም በመስጠት ከጥቁር ገበያ ዶላር በመግዛት ዕቃ ለማስመጣት የሚደረጉ ጥረቶች ከቀጠሉ፣ በሕጋዊ መንገድ ወደ አገር የሚገባ የውጭ ምንዛሪ እንዲቀንስ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ጭምር በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየታቸውን የሰጡ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡ 

በዚህ ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡት የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያው ቴዎድሮስ መኮንን (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በፍራንኮ ቫሉታ ምርትን ማስገባት የተለመደ አሠራር ቢሆንም፣ ከጥቁር ገበያ በተገዛ ዶላር ከሆነ፣ ፍራንኮ ቫሉታ የሚሰጠውን ጥቅም ከማዛባት ባለፈ ኢኮኖሚው ላይ ተፅዕኖ ያሳርፋል፡፡ 

በመሆኑም ከጥቁር ገበያ የውጭ ምንዛሪ በመግዛት ዕቃ ለማስገባት የሚደረገው ሙከራ ቁጥጥር ሊደረግበትና በመደበኛው የምንዛሪ ዋጋና በጥቁር ገበያው መካከል ያለውን የምንዛሪ ዋጋ በጥብቅ መከታተል የሚሻ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡  

እንደ ዶ/ር ቴዎድሮስ ገለጻ፣ ‹‹ሰዎች ፍራንኮ ቫሉታ ተፈቅዷል ሲባል፣ መጀመርያ የሚያደርጉት ወደ ጥቁር ገበያ በመሄድ የውጭ ምንዛሪ መግዛት ነው፤››  ይህ ፈፅሞ ትክክል ያለመሆኑን፣ ነገር ግን እየታየ ያለ ጉዳይ መሆኑ እንደሚያሳስባቸው አመልክተዋል፡፡ ምክንያቱም በፍራንኮ ቫሉታ ዕቃ ለማስመጣት ከጥቁር ገበያ የሚገዛው የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት እየጨመረ በሄደ ቁጥር በጥቁር ገበያ የምንዛሪ ዋጋው ከፍ ይላል፡፡ ስለዚህ በፍራንኮ ቫሉታ ዕቃ ለማስገባት ባልተገባ መንገድ የጥቁር ገበያው ዋጋ ከፍ እያለ መምጣት ደግሞ ከመደበኛው የምንዛሪ ዋጋ ጋር ያለውን ልዩነት እያሰፋው እንደሚሄድ ጠቁመዋል፡፡ የልዩነቱ መስፋት ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ችግር ሊያስከትል ይችላል የሚል ምልከታቸውን ቴዎድሮስ (ዶ/ር) አንፀባርቀዋል፡፡ በጥቁር ገበያውና በመደበኛው የውጭ ምንዛሪ ዋጋ መካከል የልዩነቱ መስፋት ከሚያስከትለው ችግር አንዱ ከውጭ በሕጋዊ መንገድ የሚገባውን የውጭ ምንዛሪ እንዲቀንስ ስለሚያደርግ ነው፡፡ 

ምክንያቱም በጥቁር ገበያና በመደበኛው የምንዛሪ ዋጋ መካከል ያለው ልዩነት ከሰፋ ከውጭ ገንዘብ የሚልኩ ሰዎች በጥቁር ገበያው ያለው ዋጋ ከፍ በማለቱ ዓይናቸውን ወደ ጥቁር ገበያው እንዲጥሉ የሚያስገድዳቸው መሆኑን ቴዎድሮስ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡ ስለዚህ በመደበኛውና በጥቁር ገበያው መካከል ልዩነቱ እየሰፋ ከመጣ መንግሥት ይህንን ልዩነት ማቀራረብ ወይም የጥቁር ገበያው የምንዛሪ ዋጋ እንዲወርድ መውሰድ የሚገባውን ዕርምጃ መውሰድ እንዳለበት ይመክራሉ፡፡

‹‹በጥቅል ሲታይ ፍራንኮ ቫሉታ በራሱ ምንም ችግር የሌለበት የፖሊሲ ውሳኔ አይደለም፤›› ያሉት ቴዎድሮስ (ዶ/ር)፣ ፍራንኮ ቫሉታ የቱንም ያህል ጠቃሚ ነው ቢባልም ውስብስብ እንደሆነ ማወቅ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው ሌላው የኢኮኖሚው ባለሙያ ለማ ጉዲሳ (ዶ/ር)፣ ‹‹ፍራንኮ ቫሉታ ያለ ውጭ ምንዛሪ ዕቃን ማስገባት እንጂ ለጥቁር ገበያ ዕውቅና መስጠት አይደለም፡፡ ነገር ግን ፍራንኮ ቫሉታ ማለት ጥቁር ገበያ ተፈቀደ ማለት ነው በሚል ወደ ጥቁር ገበያ መሄድ ትክክል አይደለም፤›› በማለት የቴዎድሮስ (ዶ/ር)ን ሐሳብ ይጋራሉ፡፡ 

መንግሥት ፍራንኮ ቫሉታን ሲፈቅድ የውጭ ምንዛሪ ያላቸው አካላት የባንክ ፈቃድ ሳይጠየቁ ዕቃ ገዝተው ወደ አገር ውስጥ ማስገባት ይችላሉ በሚል እንጂ፣ ከጥቁር ገበያው ዶላር አይደለም፡፡ ይህ ከሆነ ግን ሕገወጥ ተግባር ነው፣ መንግሥትም የማይፈቅድ መሆኑን ለማ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡ ይህ አካሄድ በመንግሥት ተቆጣጣሪነት ዕርምት እንደሚገባውም ሳያሳስቡ አላለፉም፡፡  

ከፍራንኮ ቫሉታ ጋር በተያያዘ ሌላም አሳሳቢ ችግር እንዳለ የጠቆሙት ለማ (ዶ/ር)፣ ይህም ከሕገወጥ የኮንትሮባንድ ንግድ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ሕገወጥ የኮንትሮባንድ ንግድ ከሌላው ጊዜ በተለየ ቁጥጥር የማይደረግበት ከሆነም ኢኮኖሚያዊ ችግር ያስከትላል ይላሉ፡፡ ፍራንኮ ቫሉታ ሕገወጥ የኮንትሮባንድ ንግድ እንዲስፋፋ ምክንያት ሊሆን ስለሚችል፣ በሕገወጥ የኮንትሮባንድ ንግድ ላይ መደረግ ያለበት ቁጥጥር ጠንከር ሊል ይገባል፡፡ 

እንደ ወርቅ፣ ቡና፣ የቀንድ ከብትና የመሳሰሉትን የወጪ ንግድ ምርቶች በመላክ የተሰማሩ ነጋዴዎችና ሌሎችም ምርቶቹን በሕገወጥ መንገድ (በኮንትሮባንድ) በማስወጣት የሚያገኙትን የውጭ ምንዛሪ ደግሞ የተፈቀደውን የፍራንኮ ቫሉታ ዕድል ተጠቅመው ምርቶችን ለማስገባት እንዲሳቡ ያደርጋል፡፡ በመሆኑም ፍራንኮ ቫሉታ ጥንቃቄ ካላተደረገበት የኮንትሮባንድ ንግድ ሊያስፋፋና የንግድ ዕድሉም ያልተገባ ጥቅም ማግኛ ሊሆን እንደሚችል ባለሙያው ለማ (ዶ/ር) አሳስበዋል።

ይህ ደግሞ የወጪ ንግዱ ላይ ተፅዕኖ ከማሳደር በላይ ፍራንኮ ቫሉታ የታሰበለትን ግብ እንዳይመታ ያደርጋል የሚል አስተያየታቸውንም ሰጥተዋል፡፡ 

‹‹የፍራንኮ ቫሉታ ጉዳይ ውስብሰብ መሆኑን ማወቅ ይገባል፤›› የሚሉት ቴዎድሮስ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በፍራንኮ ቫሉታ የጥቁር ገበያው የምንዛሪ ዋጋ እንዲሰፋ በማድረግ ሌላ ትልቅ ችግር ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ጠቁመዋል። ይኼውም የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሪ ሚዛን ማዛባት እንደሆነ አስረድተዋል።

የውጭ ምንዛሪ ሚዛን ተዛባ ማለት ደግሞ የማክሮ ኢኮኖሚው ላይ ጫና በመፍጠር፣ የውጭ ምንዛሪ ክምችቱ እንዲቀንስ እንደሚያደርግ፣ የውጭ ምንዛሪ ክምችቱ ቀነሰ ማለት ደግሞ ከውጭ የሚገባው ምርት በዚያው ልክ እንዲቀንስና እንደገና ገበያ ውስጥ የምርቶች እጥረት እንዲከሰት የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም መንግሥት ፍራንኮ ቫሉታን ሲፈቅድ በጥቁር ገበያውና በመደበኛው የምንዛሪ ገበያ መካከል ያለውን የዋጋ ልዩነት በተለየ ትኩረት መቆጣጠር ይገባዋል ብለዋል።

በፍራንኮ ቫሉታ ላይ ተጨማሪ አስተያየት የሰጡት ደግዬ ጎሹ (ዶ/ር)፣ የፍራንኮ ቫሉታ የተፈቀደበት ምክንያት ማዛባት እንደማይገባ አመልክተዋል፡፡ አብዛኛውን የቴዎድሮስ (ዶ/ር) እና የዶ/ር ለማን ሐሳብን ይጋራሉ፡፡ 

በተለይ ፍራንኮ ቫሉታንና ጥቁር ገበያን ማገናኘት ፈፅሞ ስህተት መሆኑን አስረድተው፣ አሁን ከተፈቀዱት ምግብ ነክ ምርቶች ሌላ ሌሎች ምርቶችንም በፍራንኮ ቫሉታ ማስገባት ጠቃሚ ነው ባይ ናቸው፡፡ በተለይ መድኃኒት ነክ ምርቶች በፍራንኮ ቫሉታ ቢገቡ ጠቃሚ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ይህንንም እየተቆጣጠሩ ማስገባት ያለውን ጫና በማቃለል ረገድ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል የሚል ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች