Wednesday, October 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኅብረት ሥራ ኮሚሽን ለበጋ መስኖ ስንዴ የሚያስፍልገውን 3.3 ቢሊዮን ብር ሳያገኝ የምርት ጊዜ አለፈ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን በመንግሥት ትኩረት ተሰጥቶበት የተመረተው የበጋ መስኖ ስንዴ፣ በኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል ለገበያ እንዲቀርብ ለማኅበራቱ ሊያቀርብ ያቀደውን 3.3 ቢሊዮን ብር ሳያገኝ የምርት መሰብሰቢያ ጊዜ እንዳለፈ አስታወቀ፡፡  

ኮሚሽኑ ማኅበራቱ የበጋ መስኖ ስንዴን ለመሰብሰብ የሚያጋጥማቸውን የፋይናንስ እጥረት ለመቅረፍ ጉዳያቸው በተለየ ሁኔታ እንዲታይ ለብሔራዊ ማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ ጥያቄ ቢያቀርብም ውሳኔ እንዳልተላለፈ ገልጿል፡፡ በዚህም ምክንያት ማኅበራቱ የበጋ ስንዴ ለማቅረብ በሚፈለገው መጠን ገንዘብ ማግኘት ሳይችሉ የመኸር ወቅት መድረሱን፣ በኮሚሽኑ የኅብረት ሥራ ግብይት ዳይሬክተር ወ/ሮ ይርጋዓለም እንየው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በ2014 ዓ.ም. የበጋ መስኖ ስንዴ ምርት ዘመን በምርት ከተሸፈነው 404,900 ሔክታር መሬት፣ በመጀመሪያ ዙር 16 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት እንደሚገኝ፣ ከምርቱ 9.63 ሚሊዮን ኩንታል ለገበያ እንደሚቀርብ ተገልጾ ነበር፡፡ ለገበያ ከሚቀርበው ስንዴ ውስጥም 2.4 ሚሊዮን ኩንታል በኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል እንዲቀርብ ኮሚሽኑ ዕቅድ ይዞ ነበር፡፡

እንደ ኮሚሽኑ ገለጻ፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራቱ ለገበያ የሚያቀርቡትን ስንዴ ከአርሶ አደሮች የሚገዙበት 3.56 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋቸዋል፡፡ ኮሚሽኑ ባደረገው ጥናት መሠረት ማኅበራቱ 188.4 ሚሊዮን ብር አቅም ያላቸው ሲሆን፣ ከገንዘብ ቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማኅበራት ደግሞ 38.5 ሚሊዮን ብር ማግኘት ይችላሉ፡፡ ይሁንና ኮሚሽኑ ትልቁን ድርሻ የሚይዘውን 3.3 ቢሊዮን ብር ለማሟላት አቅዶ የነበረው ከባንኮች በሚገኝ ብድር ነበር፡፡

የኅብረት ሥራ ማኅበራት የበጋ መስኖ ስንዴን ለመሰብሰብ ፋይናንስን ጨምሮ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት፣ በግብርና ሚኒስትር ደኤታው ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር)፣እንዲሁም በኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽነር ወ/ሮ ፍሬዓለም ሽባባው የሚመራ ብሔራዊ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ነበር፡፡ ይህ ግብረ ኃይል 3.3 ቢሊዮን ብር ከአበዳሪ ባንኮች ለማግኘት ንግግር ጀምሮ እንደነበር ወ/ሮ ይርጋዓለም ተናግረዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ አዋሽ ባንክ፣ ኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ፣ ዓባይ ባንክ፣ አንዲሁም ሌሎች የግል ባንኮች ብድር ይገኝባቸዋል ተብለው የታሰቡ የፋይናንስ ተቋማት ነበሩ፡፡ ይሁንና ከባንኮቹ ውስጥም አንዳቸውም በተለያዩ ምክንያቶች ብድር እንዳላቀረቡ የተናገሩት ዳሬክተሯ፣ ባንኮች ማስያዣ በመፈለጋቸው የኅብረት ሥራ ማኅበራቱ ደግሞ ሊያስይዙት የሚችሉት ንብረት አለመኖሩ ችግር መፍጠሩን አስረድተዋል፡፡

ወ/ሮ ይርጋለም በአማራ ክልል ላሉ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ብድር ያቀርባል ተብሎ ታስቦ ከነበረው ዓባይ ባንክ ጋር የነበረውን ንግግር በምሳሌነት አውስተዋል፡፡ ባንኩ የአማራ ክልል መንግሥት ማስያዣ ካላመጣ ብድር እንደማይሰጥ ሲገልጽ፣ የክልሉ መንግሥት ደግሞ ከዚህ ቀደም ለማኅበራቱ ያቀረበው ገንዘብ ስላለ ይህንን ማድረግ እንደማይችል ማስታወቁን አስረድተዋል፡፡

ከባንኮቹ የተደረገው ንግግር ፍሬ ባለማፍራቱ በበጋ መስኖ የተመረተውና በማኅበራቱ እንዲቀርብ የታቀደው ስንዴ፣ ከውጭ የሚመጣውን ስንዴ የሚተካ መሆኑ ተገልጾ፣ የማኅበራቱ ፋይናንስ ችግር በልዩ ሁኔታ እንዲታይ ለብሔራዊ ማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ ጥያቄ ቢቀርብም ችግሩ እንዳልተፈታ ተናግረዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ስንዴውን እንዲገዛ በሚል ለንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርና ለገንዘብ ሚኒስቴር በደብዳቤ የቀረበው ጥያቄም፣ እስካሁን ውሳኔ እንዳልተሰጠበት ገልጸዋል፡፡

የኅብረት ሥራ ማኅበራቱም በመጋዘናቸው ውስጥ የተለያዩ ክምችቶች በእጃቸው ላይ ስለነበሩ፣ ተጨማሪ ግዥ ለመፈጸም የሚያስችል የፋይናንስ አቅም እንዳልነበራቸው ያስረዱት ወ/ሮ ይርጋለም፣ አርሶ አደሮችም በቀጥታ ገንዘብ ለሚያቀርብላቸው ነጋዴ መሸጣቸውን አስረድተዋል፡፡ በማኅበራቱ የተሰበሰበው ስንዴ አነስተኛ መሆኑን በመጥቀስም ‹‹የምንፈልገው ሥራ አልተጀመረም፣ ይኼ ወቅት አልተሳካልንም፤›› ብለዋል፡፡ አክለውም ለሚቀጥለው የምርት ወቅት ይኼንን ችግር ማለፍ የሚያስችል አዲስ አሠራር መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ የበጋ መስኖ ስንዴ ምርት ላይ ትኩረት አድርጎ የነበረው ከሌሎች የምርት ወቅቶች ይልቅ አብዛኛው ምርት ለገበያ የሚቀርበበት ወቅት በመሆኑ ነው፡፡ እንደ ኮሚሽኑ ገለጻ፣ አርሶ አደሮች በመኸር ጊዜ ከምርታቸው ውስጥ ለገበያ የሚያቀርቡት 28 በመቶውን ብቻ ሲሆን፣ ከበጋ መስኖ ምርታቸው ውስጥ ግን 60 በመቶውን ይሸጡታል፡፡

ይሁንና ኮሚሽኑ ‹‹የገበያ ሰንሰለቱን ያራዝማሉ›› የሚል ክስ የሚቀርብባቸውን ደላላዎች የስንዴ ገበያ ሰንሰለት ውስጥ ሲኖሩ፣ የዋጋ መናርና ሰው ሠራሽ የምርት እጥረት ይፈጥራሉ የሚል ሥጋት አለው፡፡ የሥራ ማኅበራቱ ስንዴውን የሚሰበሰቡ ከሆነ ግን እንደ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ እህል ንግድ ድርጅትና የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት የመሳሰሉ የመንግሥት ተቋማትና የዱቄት ማቀነባበሪያ ያላቸው ፋብሪካዎች በቀጥታ መግዛት እንደሚችሉ ኮሚሽኑ አስረድቷል፡፡

‹‹በሌሎች የሚሰበሰበው ስንዴ ለኮንትሮባንድ ገበያ ሊዳረግ ይችላል፣ ለታለመለት ዓላማ ላይውል ይችላል፣ ማኅበራቱ የሚሰበስቡት ከሆነ ግን መንግሥት ይቆጣጠረዋል፡፡ ከውጭ የሚመጣውን ስንዴ ለመተካትና ዕርዳታ ለመስጠትም ቢሆን ማኅበራት ዘንድ ያለንን ስንዴ ማንቀሳቀስ ይችላል፣ በየግለሰቡ እጅ ከገባ በኋላ ግን መቆጣጠር አይቻልም፣ የት እንደገባ አይታወቅም፤›› ሲሉ ወ/ሮ ይርጋዓለም ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች