Wednesday, May 29, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ምርት ገበያ ስለታሰሩበት ሠራተኞቹና የታሸጉ ቅርንጫፎቹ መንግሥትን መፍትሔ ጠየቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሚያዝያ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. በኦሮሚያ የፀጥታ አካላት ከሥራ ገበታቸው ላይ ተይዘው የታሰሩ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የስድስት ቅርንጫፎች ሠራተኞች፣ አሁንም በእስር ላይ ሲሆኑ ሰባተኛ ቅርጫፉም መታሸጉ ተገለጸ፡፡

ምርት ገበያ ስለታሰሩበት ሠራተኞቹና የታሸጉ ቅርንጫፎቹ መንግሥትን መፍትሔ ጠየቀ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

የሠራተኞቹ የታሠሩበትንና ቅርጫፎቹ የታሸጉበትን ምክንያት እስካሁን ማወቅ አለመቻሉን የተናገረው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ፣ ‹‹ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ በመሆኑ›› ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት በደብዳቤ ስለሁኔታው ማሳወቁን ለሪፖርተር ገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በተለይ ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል በጻፈው ደብዳቤ፣ ቅርንጫፎቹ መዘጋታቸውን ጠቁሞ ሠራተኞቹ ምክንያቱ ባልተገለጸ ሁኔታ መታሰራቸውንም አመልክቷል፡፡

በምርት ገበያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድማገኝ ነገራ ተፈርሞ ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የተላከው ደብዳቤ፣ ሠራተኞቹ በድንገት በመታሰራቸው ቤተሰቦቻቸው በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ መግባታቸውን በመጠቆም፣ ኮሚሽኑ ጉዳዩን ትኩረት ሰጥቶ አስፈላጊውን ማጣራት በማድረግ በተቻለ ፍጥነት መፍትሔ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ነፃነት ተስፋዬ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሠራተኞቹ ስለታሰሩበት ምክንያትም ሆነ ስለቅርንጫፎቹ መታሸግ እስካሁን ተቋማቸው ምንም ዓይነት ማብራሪያም ሆነ መረጃ አላገኘም፡፡ ሆኖም ከታሰሩት ሠራተኞች ውስጥ የተወሰኑት ስለመለቀቃቸው መስማታቸውን፣ ነገር ግን ሠራተኞቹ የታሰሩበትን ምክንያትም ሆነ ስለተወሰደው አጠቃላይ ዕርምጃ ማብራሪያም ሆነ መረጃ ማግኘት መቸገራቸውን ገልጸዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት ከታሸጉት ከስድስቱ ቅርንጫፎች ሌላ አንድ ተጨማሪ ቅርንጫፍ እንደታሸገና ይህም የታሸጉበትን ቅርንጫፎች ቁጥር ሰባት እንደደረሰው አቶ ነፃነት ገልጸዋል፡፡

በክልሉ የፀጥታ ኃይል ታሽጓል የተባለው ሰባተኛው ቅርንጫፍ በቡሌ ሆራ የሚገኝ ሲሆን፣ በዚህ ቅርንጫፍ የሚሠሩ ሠራተኞች ግን አለመታሰራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

የምርት ገበያው ሰባት ቅርንጫፎች በመታሸጋቸው አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴዎቻቸው መቋረጡን፣ ይህም በምርት ገበያው የግብይት ሒደት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ መፍጠሩም ታውቋል፡፡ ከእነዚህ ቅርንጫፎች ወደ ምርት ገበያው የሚገቡ ምርቶች መቋረጣቸውን፣ በተመሳሳይም ወደ ቅርንጫፎቹ የሚገቡ ምርቶች መቆማቸውም ታውቋል፡፡ 

በክልሉ መንግሥት የተወሰደው ዕርምጃ በአጠቃላይ የምርት ገበያውን የሥራ እንቅስቃሴ ያስተጓጎለበት እንደሆነም ከምርት ገበያው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ከሠራተኞች መታሰር በተጨማሪ፣ በታሸጉት ቅርንጫፎች መጋዘኖች ውስጥ ያሉ ምርቶች ለብልሽት እየተጋለጡ መሆኑ እንዳሳሰበው ምርት ገበያው ለሪፖርተር ገልጿል፡፡ በታሸጉት ቅርንጫፎች መጋዘኖች ውስጥ ያለው የምርት መጠን ምን ያህል እንደሆነ ባይታወቅም፣ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች ሳይቀሩ ለብልሽት ሊጋለጡ ይችላል የሚል ሥጋት እንዳለበት አስታውቋል፡፡ በመሆኑም የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጣልቃ ገብተው ለጉዳዩ መፍትሔ እንዲሰጡ ጠይቋል፡፡ 

ከዚህም ሌላ በመጋዘኖቹ ይገቡ የነበሩ ምርቶች መቋረጥ አጠቃላይ የግብይት ሒደቱንና የወጪ ንግድ ገበያውን በማስተጓጎል፣ በኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል አሳስቧል፡፡ 

ላኪዎች ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የገዙትን ምርት ሳይረከቡ መጋዘኖቹ በመታሸጋቸው ችግር ውስጥ መግባታቸውንም ምርት ገበያው አስታውቋል፡፡ አርሶ አደሮችና አቅራቢዎችም ገቢ እናገኝበታለን ብለው ለእነዚህ ቅርንጫፎች ያቀረቡት ምርት የታሸገበት በመሆኑ፣ ክፍያቸውን ለማግኘት እንዳልቻሉም ተገልጿል፡፡ አዲስ ምርት ለማስገባት ቅርንጫፎች ሥራ በማቆማቸው በምርት ገበያው ቀጣይ ገቢ ላይ ጥላ ማጥላቱም ጠቁሟል፡፡ በመጋዘኖቹ ያሉ ለግብይት ተሰናድተው የነበሩ ምርቶች ከፍተኛ መጠን ያላቸው ሲሆን ከእነዚህም ቡና፣ ጥራጥሬ፣ ሰሊጥ፣ ቅመማ ቅመሞችና የመሳሰሉት ምርቶች ይገኙበታል ተብሏል፡፡

እነዚህ ምርቶች በመጋዘኑ ውስጥ ተዘግተው መቀመጣቸው የምርቶቹ ጥራት ላይ ችግር እንደሚፈጥር ጭምር እየተገለጸ ሲሆን፣ ችግሩ በዚህ ደረጃ እየታየ እስካሁን መፍትሔ ያለመገኘቱ ብዙዎችን እያነጋገረ ነው፡፡ 

ለብዙዎች እንቆቅልሽ የሆነው የኦሮሚያ ክልል ዕርምጃ ምክንያቱ ራሱ አለመታወቁና ምርት ገበያውም ስለጉዳዩ ምንም አላውቅም ማለቱ ደግሞ ጉዳዩን የበለጠ ውስብሰብ አድርጎታል፡፡

ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተሉ ያሉ ወገኖች በበኩላቸው፣ ችግር እንኳን ቢኖር በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች ላይ ማሸግ ተገቢ አለመሆኑን ይገልጻሉ።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከፌዴራል መንግሥታዊ ተቋማት መካከል አንዱ ሲሆን፣ በቀጥታ ተጠሪ የሆነው ለንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ነው፡፡ ሰሞኑን የተከሰተውን ችግር በተመለከተም የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ለሚኒስቴሩ በደብዳቤ በማሳወቅ በጉዳዩ ላይ ክትትል በማድረግ መፍትሔ እንዲያፈላልግ መጠየቁን ሪፖርተር ለመረዳት ችሏል፡፡ ሪፖርተር ጉዳዩን አስመልክቶ ከኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

በኢትዮጵያ ዘመናዊ ግብይትን በመጀመር ከ14 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያለው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በአሁኑ ወቅት በመላ አገሪቱ ከ25 በላይ ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን፣ በየዓመቱ የግብይት መጠኑን በመጨመር እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በአሁኑ ወቅት ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ የሚያወጡ በጥቅል መጠናቸው እስከ 700 ሺሕ ቶን የሚደርሱ ምርቶችን የሚያገበያይ ድርጅት- ነው፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች