- እንደምታውቁት በምግብ ዘይት ላይ ያልተገባ የዋጋ ንረት ሰሞኑን በገበያው ተስተውሏል።
- ልክ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ልክ አይደለም።
- እ…
- አዎ፣ የጠራናችሁ በዘይት ላይ የታየው የዋጋ ንረት ልክ ስላልሆነ ነው፣ ተገቢ አይደለም።
- ክቡር ሚኒስትር ምን መሰለዎት…
- ቆይ ልጨርስ፣ በመጀመሪያ የዋጋ ንረቱ ትክልል አለመሆኑን ማመን አለባችሁ።
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- እንዴት ጭራሽ?
- እንዴት አልኩኝ እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
- ለዚያውም ቁጣ የተቀላቀለበት ነዋ፡፡
- ለማለት የፈለግኩት ግን ‹‹እንዴት?›› ለማለት አልነበረም ክቡር ሚኒስትር።
- ታዲያ ምን ለማለት ፈልገህ ነበር?
- እንዴት በዘይት ዋጋ ንረት ላይ አንወያይም? መወያየት አለብን ለማለት ነበር፡፡
- ማን አንወያይም አለ?
- እ… የተባለ መስሎኝ ነው ክበር ሚኒስትር፣ ይቅርታ ይደረግልኝ።
- ለማንኛውም ዓመት በዓሉ ይለፍ ብለን ነው ውይይቱን ያዘገየነው፣ ዛሬ ግን የግድ መወያየት አለብን።
- ትክክል ነው ክቡር ሚኒስትር መወያየት አለብን፣ እንዲያውም ዘግይቷል።
- ጥሩ፣ አብዛኞቻችሁ የምግብ ዘይት ለማምረት ፈቃድ ስትጠይቁን ያቀረባችሁት ፕሮፖዛል ላይ የአገር ውስጥ የዘይት ምርት ፍላጎትን ለማሟላትና ዋጋን ለማረጋጋት ነበር።
- ልክ ነው፣ አሁንም ዕቅዳችን ያው ነው ክቡር ሚኒስትር።
- ያው አይደለም፣ ከወራት በፊት ሦስት መቶና አራት መቶ ብር ይሸጥ የነበረውን ዘይት በአንድ ጊዜ አንድ ሺሕ ብር አስገብታችሁታል።
- ክቡር ሚኒስትር ችግሩ የተፈጠረው…
- የተፈጠረ ችግር የለም፣ አብዛኞቻችሁ ፈቃድ ስትወስዱ የገባችሁትን ቃል አትዘንጉ። ለምሳሌ አንተ እዚያ ጋር ያለኸው…?
- አቤት… እኔን ነው?
- አንተም ያው ነህ፣ ግን ቅድም ልናገር ልናገር ስትል የነበርከው… እዚያ ጋ…
- እኔን ነው ክቡር ሚኒስትር?
- አዎ አንተ።
- አቤት ክቡር ሚኒስትር?
- ለምሳሌ አንተ በቅርቡ ነው ወደ ምርት የገባኸው፣ አይደለም?
- ትክክል ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ወደ እዚህ ሥራ ስትገባ ከመንግሥት የጠየቅከው ድጋፍ ብዙ እንደነበረ አስታውሳለሁ።
- እውነት ነው ክቡር ሚኒስትር።
- ለምሳሌ መሬት በአነስተኛ የሊዝ ዋጋ ሊፈቀድልኝ ይገባል ብለህ ተፈቅዶልሃል።
- እውነት ነው።
- የኤሌክትሪክ ኃይል በአካባቢው የለም ብለህ ከረዥም ርቀት ተስቦ እንድታገኝ ተደርጓል አይደለም?
- እውነት ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የውጭ ምንዛሪ ወረፋ መጠበቅ የለብኝም ብለህ ቅድሚያ እንድታገኝ ተደርጓል፣ አይደለም?
- ልክ ነው፡፡
- የካፒታል ብድርም እንድታገኝ ተደርጓል፣ አይደለም?
- እውነት ነው፡፡
- ታዲያ አንተ በምን ምክንያት ነው ዘይት በአንድ ጊዜ አንድ ሺሕ ብር ለመሸጥ የወሰንከው?
- ክቡር ሚኒስትር…
- ክቡር ሚኒስትር ማለቱን ተውና የወሰንክበትን ምክንያት አስረዳኝ፡፡
- እ… በውሳኔ አይደለም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እና ምን ሆነህ ነው?
- ባርቆብኝ ነው፡፡
- ምን?
- ክቡር ሚኒስትር በስህተት… ባረቀብኝ፡፡
- መጀመሪያ ካልተቀባበለ እንዴት ይባርቃል?
- እሱማ ተቀባብሎ ነበር።
- ተቀባብሎ ነበር? እንዴት?
- ክቡር ሚኒስትር ምን ማድረግ እችላለሁ?
- እንዴት?
- ሁሉም ተቀባብሎ ነው ያለው፣ እኔ ብቻዬን ጉዳት ከሚደርስብኝ ብዬ ባቀባብል ድንገት ባረቀብኝ።
- እህ… እንደዚያ ነው?
- እንደዚያ ነው ክቡር ሚኒስትር።
- አንተ ያን ሁሉ ድጋፍ ከመንግሥት አግኝተህ ከባረቀብህ ሌሎቹማ አነጣጥረዋል ማለት ነው።
- እሱን መንግሥት ቢያጣራው ይሻላል… መፍትሔው ግን…
- እሺ… መፍትሔው ምን?
- የተቀባበለ ነገር ሁሉ ወደ ቦታው መመለስ አለበት!
[ክቡር ሚኒስትር ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥኑ መስኮት ላይ ትኩረታቸው ተስቦ አላስተዋሏቸውም ነበር]
- ኧረ እንዴት አመሻችሁ እያልኩ ነው?
- ውይ… ውይ… በሞትኩት፣ ደህና አመሸህ?
- ምንድነው እንደዚህ ትኩረትሽን የሳበው ነገር?
- አንተው ነሃ… ሌላ ምን ይሆናል ብለህ ነው?
- ኦ… በኑሮ ውድነት ላይ ያደረግኩት ንግግር እየተላለፈ ነው እንዴ?
- እህ… ግርም ብሎኝ እየተከታተልኩ ነበር።
- ምንድነው ያስገረመሽ?
- እርግጠኝነትህ ነዋ? መቼም ደፋር ነህ፡፡
- እንዴት? ምንድነው እሱ?
- ዘንድሮ የበጋ ስንዴ ባናመርት ኖሮ በግብፅ የሆነው እዚህም መደገሙ አይቀርም ነበር እንዴት ይባላል?
- እንዴት አይባልም? ምን ችግር አለው?
- እንዴት ይባላል?
- በእኔ ዕይታ እንደዚያ ማለቴ ችግር የለውም።
- በአንተ ዕይታማ ችግር ስለሌለው ነው እንደዚያ ያልከው፣ እኔን የገረመኝ ለማስተላለፍ የፈለግከው መልዕክት ነው።
- እኔ ምንም መልዕክት ማስተላለፍ ፈልጌ አይደለም እንደዚያ ያልኩት።
- እና ምን ማስተላለፍ ፈልገህ ነው? ሕዝቡ እንደ ግብፅ ሕዝብ ባለማድረጉ ማመስገን ፈልገህ ነው? ወይስ እንደ ግብፅ ስንዴ አጣሁ፣ የምበላው አጣሁ ብሎ አደባባይ ስላልወጣ እያሾፍከበት ነው።
- ምንድነው የምታወሪው? እንዴት እንደዚያ ዓይነት መልዕክት አስተላልፋለሁ?
- የበጋ ስንዴ ባይደርስ በግብፅ የሆነው እዚህም መምጣቱ አይቀርም ነበር ማለት ለምን አስፈለገ፣ የስንዴ ችግር ሙሉ በሙሉ ተቀርፎ ነው?
- አልተቀረፈም፣ ግን የበጋ ስንዴ መድረሱ ችግሩን አቅሎታል።
- እሺ ክረምቱን የበጋ ስንዴ ከየት ልታመጡ ነው? ክረምቱ እንደሆነ ይኸው እየገባ ነው።
- ከተናገርኩት በኋላ ቆይቼ ሳስበው ነው ክረምት መምጣቱን ያስታወስኩት።
- አየህ እንዲህ ዓይነት ኃላፊነት ላይ ስትቀመጥ ከመናገርህ በፊት በጥልቀት ማሰላሰል ጥሩ ብቻ ሳይሆን የግድ ነው።
- እሱስ ልክ ነሽ።
- እና ስለመፍትሔው እያሰብክ ነው?
- ስለምኑ?
- የተመካህበት የበጋ ስንዴ ክረምቱን ያሻግረናል?
- ሰሞኑን ወደ ውጭ ተጉዘው ከነበሩ የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር ስለዚህ ጉዳይ እየተወያየሁ ነበር።
- ምን አሉህ? መፍትሔ አለው?
- አታስብ ብለውኛል።
- አታስብ ማለት?
- አጋሮቻችን ቃል ገብተዋል፣ የእኛ ባይደርስ የእነሱ ይደርሳል ብለውኛል።
- የእነርሱ ምን?
- የበጋ ስንዴ!