Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበጦርነቱ የወደሙ የመንግሥታዊ ተቋማት መረጃዎች እንደገና እየተደራጁ መሆናቸው ተገለጸ

በጦርነቱ የወደሙ የመንግሥታዊ ተቋማት መረጃዎች እንደገና እየተደራጁ መሆናቸው ተገለጸ

ቀን:

በሰሜን ኢትዮጵያ በአማራና በአፋር ክልሎች ሲካሄድ በነበረው ጦርነት፣ በሕወሓት ታጣቂዎች ወድመዋል የተባሉትን የተቋማት መረጃ እንደገና ለማደራጀት የሚረዳ ጥናት እንዳደረገ ያስታወቀው የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን፣ በክልሎቹ ተቋማት የወደመውን መረጃ መልሶ የማደራጀት ሥራ መጀመሩን አስታወቀ፡፡

በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የክልሎች ድጋፍ ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው መኩሪያ ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ በሦስት ቡድን የተደራጀ አጥኚ ቡድን በአማራና በአፋር ክልሎች ተሰማርቶ ጥናት አድርጎ ተመልሷል፡፡ በአጥኚ ቡድኑ የቀረበው ሪፖርት ኮሚሽኑ ምን ዓይነት ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት ያሳየ እንደሆነ ያስታወቁት አቶ ግዛቸው፣ ሪፖርቱ ኮሚሽነሮቹ ባሉበት ቀርቦ በራሱ በተቋሙ አቅም መጠን መቅረብ ያለበት ድጋፍ ምንድነው? ሌሎች የፌዴራል ተቋማት በማስተባበር የሚሠሩዋቸው ምንድናቸው? የሚሉት ጉዳዮች ተለይተው የባለሙያዎቹን ምክረ ሐሳብ ወደ ተግባር መቀየር እንደተጀመረ ገልጸዋል፡፡

የጥናት ቡድን ባደረገው ምርመራ ውስጥ ውድመቱ የደረሰባቸው የአማራና የአፋር ክልሎች ያቀረቧቸው ጥያቄዎች እንደተለዩ ያስረዱት አቶ ግዛቸው፣ በአፋር ክልል በዋናነት የወደሙ የፈርኒቸር፣ የኮምፒዩተርና መሰል ድጋፎች ጨምሮ የተሽከርካሪ እጥረት ጥያቄዎችን ለማሟላት ወይም ባላቸው ላይ ድጋፍ ለማድረግ እንቅስቃሴ እንደተጀመረ ተገልጿል፡፡

ከዚህ በፊት በኮሚሽኑ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚተገበር ወረዳዎች ላይ የሚገኙ የሰው ሀብትን የተመለከቱ መረጃዎችን በኦንላይን ለማደራጀት የተዘጋጀ ሶፍትዌር እንዳለ የተገለጸ ሲሆን፣ በዚህ መሠረት ከዚህ ቀደም መረጃቸው የገባና ሲስተም ላይ የተቀመጠ ስላለ እሱ ጥቅም ላይ የሚውል እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ በአንፃሩ ይህንን ሲስተም ሳይተገብሩ የቀሩና ፋይላቸው የጠፉትን ተቋማት መረጃዎች ከክልሎቹ ጋር በመሆን ከፋይናንስ ላይ የደመወዝ ፔሮል ላይ የሰፈረውን የሠራተኞችን ስም በመውሰድ፣ እንዲሁም በሠራተኞች እጅ ላይ የሚገኘውን መረጃ በመውሰድ መልሶ የማደራጀት ሥራ እንደተጀመረ ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡

ተቋማቱን መልሶ ማደራጀትና አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ የሚለውን ለመመለስ መጀመርያ አገልግሎቱን ለማቅረብ አስፈላጊ የሆኑት የቢሮ ቁሶች መሟላት እንዳለባቸው የተገለጸ ሲሆን፣ እስከ ዞን ድረስ በኮሚሽኑ ተለይቶ ምን ያህል የቴክኖሎጂና የፈርኒቸር መሣሪያዎች ይገኛሉ የሚለው ተጠንቶ ሥርጭት ለማድረግ ዝግጅቶች እየተደረገ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡

ግብዓቶቹን ማሟላት ብቻውን በራሱ አገልግሎት ለመስጠት ስለማያስችል በቀጣይ ለሠራተኞች የማገገሚያ ሥልጠና መስጠት ታሳቢ መደረጉን የተናገሩት አቶ ግዛቸው፣ ይህም እስከ መጪው ሰኔ ወር ድረስ በተለይም በሁለቱ ክልሎች ላይ ትኩረት ተደርጎ ይሠራበታል ብለዋል፡፡

ኮሚሽኑ የላከው አጥኚ ቡድን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በአፋር ክልል ከተለቀቁት በቁጥር ስድስት ከሚደርሱት ወረዳዎች በተጨማሪ፣ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ 12 ያህል ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ ተቋማት በሙሉ እንደወደሙ በጥናት አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡

በአማራ ክልል ውስጥ የሚገኙት ወረዳዎች ቁጥር በርካታ ስለሆነ የኮሚሽኑ ትኩረት ከሜትሮፖሊያን ከተሞች ካልሆነ በስተቀር ለማየት የተሞከረው በዞን ደረጃ የሚገኙ ከተሞች ላይ እንደነበር ያስታወቁት አቶ ግዛቸው፣ ይህም ታሳቢ የተደረገው ኮሚሽኑ እስከ ዞን ደረጃ ላሉት ድጋፍ የሚያደርግ ከሆነ ዞኖች ወረዳዎችን በመለየት ድጋፍ እያደረጉ የመልሶ ግንባታውን በጋራ ለማድረግ በመታሰቡ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ በአማራ ክልል የጥናቱ ወሰን ያካተተው በሦስት ዞኖች ማለትም ሰሜንና ደቡብ ወሎ እንዲሁም ሰሜን ሸዋ እንደሆነ ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

የመልሶ ግንባታ ድጋፉን ከሚያግዙ አካላት አንዱና ዋነኛው የገንዘብ ሚኒስቴር እንደሆነ ተጠቁሞ፣ በሌላ በኩል በክልሎች የሚደረገውን ድጋፍ የሚመራው የሰላም ሚኒስቴርና የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር ዋና ዓቢይ ኮሚቴ ሆነው እንደሚሠሩ ታውቋል፡፡ በተጨማሪም ሌሎች ተቋማትም በራሳቸው ዘርፍ የሚሠሩት እንደሚኖር ተመላክቷል፡፡

በአጠቃላይ ኮሚሽኑ በሚመራው የመልሶ ማደራጀት እንቅስቃሴ በአጭር ጊዜ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ እንቅስቃሴ የተጀመረው ተግባር እስከ ዞን ደረጃ ያሉትንና ዋና ዋና የሚባሉትን የመንግሥት ተቋማትን ቶሎ ሥራ ማስጀመር እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም የቁሳቁስና የሥልጠና ሥራዎችን በአፋጣኝ በመስጠት የሚተገበር እንደሆነ ተመላክቷል፡፡

በረዥም ጊዜ ደግሞ የዓለም ባንክና ዩኤንዲፒ፣ እንዲሁም የገንዘብ ሚኒስቴር እያስጠኑ የሚገኙትን ጥናት መሠረት በማድረግ የሚተገበሩ ፕሮጀክቶችን ወደ ሥራ ማስገባት እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ‹‹ሆኖም ከሁሉ በላይ የያዘን የገንዘብ እጥረት ነው፤›› ያሉት አቶ ግዛቸው፣ ስለዚህ ይህ ጥናት ተቀርፎ ወደ ድጋፍ መግባት የቀጣይ ዓመት የኮሚሽኑ ዋነኛ ዕቅድ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...