Tuesday, April 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ክለሳ ረቂቅ መጠናቀቁ ታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ኢትዮጵያ ካዘጋጀችው የአሥር ዓመታት የልማት ዕቅድ ጋር ተጣጥሞ ለማስኬድ እንዲቻል፣ ከዚህ ቀደም የነበረውን የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ክለሳ አድርጎ ረቂቁን እንዳጠናቀቀ አስታወቀ፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከዚህ ቀድም የነበረው የዘርፉ ፖሊሲ የነበረበት ችግር ወይም ጉደለት ምንድነው የሚለውን ዝርዝር እንደሠራ በማስታወቅ፣ ከአሥር ዓመት የልማት ዕቅዱ ጋር ተጣጥሞ የሚሄድ የመነሻ ጥናት ወይም ረቂቅ ተዘጋጅቶ በዘርፉ ዕውቀት አላቸው ለሚባሉና ዘርፍን ሲመሩ ለቆዩ አካላትና የዩኒቨርሲቲ ምሁራን አቅርቦ አስተያየት እንደተሰጠበት፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ሺሰማ ገብረ ሥላሴ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ስትራቴጂ ክለሳ ሥራው በአፍሪካ ልማት ባንክ ድጋፍ፣ ዳልበርግ የተባለ የውጭ አማካሪ ድርጅት ተቀጥሮ የጥናት ሥራውን እንደሠራው ከዚህ በፊት መገለጹ ይታወሳል፡፡

የፖሊሲ ክለሳውን ማድረግ በዋናነት ማድረግ ካስፈለገባቸው ዋነኛ ምክንያቶች ውስጥ፣ ከዚህ ቀደም በአገልግሎትም ሆነ በኮንስትራክሽንና የንግድ ዘርፎች የተሰማሩ አካላት እንዴት ወደ አምራች ዘርፉ መሸጋገር ይችላሉ በሚለው ላይ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ታሳቢ ማድረግ አንዱ እንደሆነ ሚኒስትር ደኤታው አስታውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል ከግብርና ዘርፉም ሀብት እየፈጠሩ ወደ ተቀናጀ አግሮ ፕሮሰሲንግ የሚገቡ አካላት ብቻቸውን ሳይሆን፣ በዙሪያቸው ከሚገኙ የገጠር የትራንስፎርሜሽን ማዕከላት ጋር ተመጋግበው ኢንዱስትሪውን የሚያሳድጉበትን ሁኔታ እንዲፈጠር የሚያስችል እንደሆነ ተመላክቷል፡፡ ረቂቅ ፖሊሲው በመጠናቀቁ በቀጣይ ወደ ውይይትና ውሳኔ ወደ የሚያሳልፈው የመንግሥት አካል በሚሸጋገርበት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አቶ ሺሰማ ገልጸዋል፡፡

የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ የልማት ስትራቴጂ ከተዘጋጀበት ከ1994 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉት 19 ዓመታት በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ ለውጦች በመኖራቸው ምክንያት፣ ዘርፉ ከአዳዲስ ሁኔታዎች ጋር የተጣጣመና እንዲሆን ታስቦ ፖሊሲው እንደተሻሻለ ተገልጿል፡፡

ዋና ተዋናይ ከሆኑት የኢንዱስትሪ መሪዎችና ከተለያዩ የመንግሥት አካላት ጋር ውይይት ከተደረገበት በኋላ የሚፀድቅ እንደሆነ ያስታወቁት አቶ ሺሰማ፣ የፖሊሲ ክለሳው በዚህ ወቅት በረቂቅ ደረጃ ተዘጋጅቶ መጠናቀቁን አስታውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ካለፈው ጥር ወር ጀምሮ በይፋ የተሰረዘችበትን ከአሜሪካ መንግሥት የተሰጣታትን የንግድ ተጠቃሚነት ዕድል (አጎዋ) ለማስቀጥል፣ መንግሥት ከአሜሪካ ጋር ያለውን ግንኙነት የማሻሻል ሥራዎች እየሠራ እንደሚገኝ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቋል፡፡  

የኢትዮጵያ ከተጠቃሚነት ዕድሉ መሰረዝ ከሁሉም በላይ መንግሥት ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ገበያ (በዩሮ ቦንድ) አንድ ቢሊዮን ዶላር የዕዳ ሰነድ ለሽያጭ በማቅረብ የሰበሰበውን የውጭ ምንዛሪ ካፒታል፣ እንዲሁም ከዓለም ባንክ ያገኛቸውን ብድሮች በመጠቀም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በገነባቸው ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በሚገኙ የውጭ ባላሀብቶች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ሲገለጽ ቆይቷል፡፡

በተለይም ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ ምርት ተግባር ከተሸጋገሩት፣ እንዲሁም ብዙኃኑ በጨርቃ ጨርቅ ምርቶች ላይ የተሰማሩና የምርታቸው መዳረሻ ወደ አሜሪካ ያደረጉ ኩባንያዎች ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ለአንዳንድ ድርጅቶች መዘጋት፣ በተጨማሪም ለሠራተኞች መበተን ምክንያት እንደሆነ እየተገለጸ ነው፡፡

ሚኒስትር ደኤታው አቶ ሺሰማ እንዳስታወቁት፣ በአጎዋ ምክንያት ሥራ ያቆመ ወይም አቆማለሁ ብሎ የተናገሩ ድርጅቶች ከአንድ ወይም ከሁለት የማይበልጡ እንደሆነ ተናግረው፣ እነዚህም ከጨርቃ ጨርቅና ከቆዳ ጋር የተያያዙ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

ከቀረጥ ነፃ የማስገባት ዕድሉ ተከለከለ እንጂ ምርት ወደ አሜሪካ ታክስ ከፍሎ ማስገባት እንዳልተከለከለ ያስረዱት ሚኒስትር ደኤታው፣ ያም ሆኖ ግን ከዚህ በፊት በዕድሉ ምክንያት ይቀር የነበረው የታክስ ጥቅም ምን ያህል ነበር? የሚለው ተሠልቶ እንዴት መንግሥት የሚጋራበትና የሚደግፍበት ዕድል ይኖራል ወይም ይችላል የሚለው በዝርዝር እየተሠራበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አቶ ሺሰማ አስምረው እንደተናገሩት፣ ከሁሉም በላይ ግን በዋነኛነት የሁለቱ አገሮች ግንኙነት እየተሻሻለ እንዴት ዕድሉ ሊቀጥል ይችላል? የሚለውን መውሰድ የተሻለ ነው፡፡

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ለሚመረቱ ምርቶች ሌሎች የተለያዩ የገበያ አማራጮች እንዳሉ የተገለጸ ሲሆን፣ ዜጎች አልባሳትን ከውጭ በዶላር ገዝተው እንደሚለብሱ ሁሉ፣ በአገር ውስጥ የማምረት አቅምን በማጠናከር ጥራትን በማረጋገጥ መንግሥት በብዙ ሚሊዮን ዶላር አውጥቶ የሚገዛቸውን አልባሳት በአገር ውስጥ ለመተካት የሚያስችላቸውን ዕድል ለእነዚህም ተቋማት እየተሰጠ መሆኑ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች