Sunday, February 5, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ለአገር ህልውና ሲባል ሕግ ይከበር!

ከብሔር ወደ ሃይማኖት ለመሸጋገር እያቆበቆበ ያለው የወቅቱ አደገኛ ክስተት በጊዜ መፍትሔ ካልተፈለገለት፣ የት ሊደርስና ምን ያህል አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ለመተንበይ አዳጋች አይደለም፡፡ ከኢትዮጵያ ሕዝብ የአብሮነትና የጋራ ማንነት ታሪክ ጋር የሚላተሙ ነውረኛ ድርጊቶች እየበረከቱ ነው፡፡ ከህሊና ተጠየቅ፣ ከሕግ ድንጋጌዎችና ከእምነት አስተምህሮዎች የሚቃረኑ ኃላፊነት የጎደላቸው እንቅስቃሴዎች ካልተገቱ አገር ማፍረሳቸው ጥርጥር የለውም፡፡ በተለይ ምንጫቸው ወይም መነሻቸው የማይታወቁ አጀንዳዎች በቀናት ልዩነት በተከታታይ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች አማካይነት ሲለቀቁ፣ እነዚህን መሠረት በማድረግ ምክንያታዊነት የጎደላቸው ዕርምጃዎች ሲበረክቱ ነገን ለመተንበይ ነብይ መሆን አያስፈልግም፡፡ ሕግ የማክበርና የማስከበር ግዴታ ያለበት መንግሥት፣ መብቱ ተከብሮለት በሥርዓት መመራት ያለበት ሕዝብ፣ ቀናውን መንገድ የማያስያዝ ኃላፊነት ያለባቸው የእምነት ተቋማት፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ልሂቃንና ሌሎችም መናበብ ካልቻሉ ከዛሬ የከፋ አደጋ ነገ መከሰቱ አይቀሬ ነው፡፡ አሁን ከሚስተዋለው ነባራዊ ሁኔታ አኳያ የመጠላለፍ ፖለቲካው በሴራ ታጅቦ አገርን ዋጋ እያስከፈለ ነው፡፡ ፖለቲካና ሃይማኖት ያለ ዓውዳቸው አንዳቸው በሌላቸው ውስጥ እንዲመሽጉ ሲደረግ ደግሞ፣ ሕግ የማክበርም ሆነ የማስከበር ወጉ ይኮላሻል፡፡

የሕዝብ አደራ አለብኝ የሚል መንግሥት የአገር ኢኮኖሚን ከማሳደግና መሠረተ ልማቶችን ከማስፋፋት በተጨማሪ፣ ለሕዝቡ ማኅበራዊ ዋስትና ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህም መሠረታዊ አገልግሎቶችን በማቅረብ፣ የኑሮ ውድነትን በማርገብ፣ ፍትሐዊ የግብይት ሥርዓት በማስፈን፣ የዜጐችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በማስከበር፣ የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ፣ የፖለቲካ መጫወቻ ሜዳውን በማስፋት፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽና የመደራጀት መብት በማስከበርና በመሳሰሉት ጉዳዮች ይገለጻል፡፡ ማኅበራዊ ፍትሕ የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚኖረው ደግሞ መንግሥት አሠራሩ ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ሲታይበት ነው፡፡ ባለሥልጣናቱም በዚህ መሠረት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ሲደረግ ነው፡፡ ለዚህም ነው መንግሥት አገርን በሕግና በሥርዓት ለመምራት መቻሉ መመርመር ያለበት፡፡ የሕግ የበላይነት አለ በሚባልበት አገር ውስጥ ሕጉ ዜጎችን ካልታደገ፣ የፍትሕ ሥርዓቱ አካላት ሕዝቡን በታማኝነትና በቅንነት ካላገለገሉ፣ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት ሹማምንት ሕዝቡን በሥርዓት ካላስተዳደሩ፣ የገበያውን ጤናማነት እየተቆጣጠሩ ፍትሐዊ የግብይት ሥርዓት እንዲያሰፍኑ ኃላፊነት የተጣለባቸው ግዴታቸውን ካልተወጡ፣ ለሕዝቡ በሰላም ወጥቶ መግባት የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ካልተወጡ፣ ግዴለሽነትና ሕገወጥነትን የሚያስፋፉ አካላት እንደፈለጋቸው እንዲፈነጩ ከተደረገ መንግሥት አገርን በቅጡ እያስተዳደረ ለመሆኑ ማስረጃ አይኖርም፡፡

የኢኮኖሚና የሥነ መንግሥት ሊቁ ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ከ100 ዓመታት በፊት ቢቸግራቸው፣ “የእኛ የኢትዮጵያውያን ያለፈው ታሪክ እጅግ ያሳዝናል። ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ፍፁም የሆነ ሰላም አግኝተን አናውቅምና። የተወደደች አገራችን ዘወትር በጠላቶች ተከባ ስትኖር ነበረች፣ ትኖራለችም። ነገር ግን በእግዚአብሔር ቸርነት የውጭ ጠላት ከዚህ በፊት አላዋረደንም። አንድነትም ስንሆን ምንም የሚደፍረን እንደሌለ ታሪክ ይመሰክራል። ዘወትርም በስምምነት በፍቅር አድረን ብንሆን እስከ ዛሬ ድረስ ብዙውን ትልልቅ ነገር መፈጸም እንችል እንደነበር ጥርጥር የለውም። እግዚአብሔር ብዙ በረከት ሰጥቶናልና፣ ትምህርትን በቶሎ መቀበል የሚችል ልቦናና የጦረኛን ባህሪ፣ ማለፍያና ሀብታም አገርንም። ካለመስማማታችን የተነሳ ግን ሌሎች ሕዝቦች በአዕምሮና በጥበብ እየበረቱ ሲሄዱ እኛ ወደ ኋላ ቀረን። እንደ አረመኖች እስኪቆጥሩን ድረስ። የዱሮውም ያሁኑም ኑሮዋችን እጅግ ያሳዝናል። በመላው ዓለም ላይ ሰላም ሲሰፋ አዕምሮም ስትበራ እኛ በጨለማ እንኖራለን። እርስ በርሳችን መጠራጠርንም አልተውንም። ሕዝቦቹም ሁሉ እርስ በርሳቸው በፍቅር ተቃቅፈው ስለልማታቸው ባንድነት ሁነው ሲደክሙ እኛ አንድ ዘርና ወንድማማች መሆናችንን ገና አልተገለጸልንም፤›› ነበር ያሉት፡፡

ይህ ምክርና ማሳሰቢያ ሰሚ ባለማግኘቱ ግን ኢትዮጵያ በፈረቃ በተቀያየሩ መንግሥታትም ሆነ ሥርዓቶች ሰላም ማግኘት አልቻለችም፡፡ በእኩልነትና በፍትሐዊነት የአገረ መንግሥት ግንባታ ላይ ማተኮር ሲገባ፣ በተለያዩ ምክንያቶች እርስ በርስ ለመጋጨት የሚያገለግሉ ችግሮችን መፈልፈል ልማድ ሆኗል፡፡ ከረዥሙ የኢትዮጵያ ታሪክ መገንዘብ እንደሚቻለው በየዘመኑ የተነሱ ልሂቃን የሚያደርጉት ፉክክር፣ የሕዝቡን መስተጋብርና የጋራ ማኅበራዊ እሴቶች ስለማያከብር ለንፁኃን ዕልቂትና መከራ ሰበብ መሆኑ የተለመደ አሳዛኝ ትዕይንት ነው፡፡ ሌላውን ትተን ያለፉትን 50 ዓመታት የኢትዮጵያን ውጣ ውረድ በወፍ በረር ብናስተውል፣ ብዙዎቹ ችግሮች መነሻቸው የዘመናት የተጠራቀሙ ብሶቶችን በአገር በቀል ዘዴ ለመፍታት አለመፈለግ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ከውጭ እንደ ኮንትሮባንድ ሸቀጥ የገቡ ርዕዮተ ዓለሞችና ዕሳቤዎች ላይ በመንጠልጠል፣ አገር ከመገንባት ይልቅ ለማፍረስ የሚያግዙ ትርምሶች ተፈጥረው ብዙዎች አለቁ፡፡ አሁንም በከንቱ ተስፋና በማይጨበጡ ሕልሞች መልካም ነገሮችን መመኘት ላይ በመተኮሩ፣ እውነተኛውን ችግር አውቆ መፍትሔ ለማግኘት አልተቻለም፡፡ አገራዊ ሕመሙ ፅኑና ፍቱን መድኃኒት የሚፈልግ በመሆኑ፣ ጨከን ብሎ ትክክለኛውን ፈውስ ማግኘት ካልተቻለ መከራው ይቀጥላል፡፡ 

ነጋድራስ ገብረ ሕይወት የወደፊቱን ጭምር ያዩ በሚመስል አኳኋን፣ “እርስ በርሳችን መፋጀትም እስከ ዛሬ ድረስ ጀግንነት ይመስለናል። ስለዚህም እግዚአብሔር ለብርታት የሚሆነውን ስጦታ ሁሉ ሰጥቶን ሳለ ባለቤቶቹ ሰነፍነ። ሌሎቹም ነገሥታት እንደ ሰነፎች ይቆጥሩናል፣ ይንቁናልም። የሚበላውንና የሚለበሰውንም ያጣ ድሃ የተወለደበትን አገር የሚወድበትን ምክንያት ያጣልና ያገሩ መንግሥት ቢበረታ ወይም ቢጠፋ ግድ የለውም፡፡ ስለዚህም መንግሥት የሚጠቀምበት ያገሩ ሀብት በመላው ሕዝቡ ሲከፋፈለው ነው እንጂ። ያገሩን የሠራተኛው ድሃ አኗኗር ዓይነቱ እንበለ መጠን የሚራራቅበት አገር መንግሥቱ ከጥፋት አፋፍ እንደ ደረሰ ያስረዳል። የኢትዮጵያንም ሕዝብ ሁኔታ ብንመለከት እንደዚሁ ያለ ጥፋት እንዳይደርስ ያስፈራል። አዕምሮ የሌለው ሕዝብ ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ሳያውቅ የእግዚአብሔር ጠበቃ ሊሆን ይወዳል። አዕምሮ የሌለው ሕዝብ ሥርዓት የለውም። ሥርዓት የሌለው ሕዝብም የደለደለ ኃይል የለውም። የኃይል ምንጭ ሥርዓት ነው እንጂ የሠራዊት ብዛት አይደለም። ሥርዓት ከሌለው ሰፊ መንግሥት ይልቅ በሕግ የምትኖር ትንሽ ከተማ ሞያ ትሠራለች፤” ብለው ነበር፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡

በሥርዓት ለመኖርና አገር ለመገንባት ከሚያስፈልጉ ግብዓቶች መካከል አንዱ ሕግ ነው፡፡ በሕግ የበላይነት ወይም በሕግና በሥርዓት መመራት ያስፈልጋል ሲባል፣ አንዱ በሌላው ላይ ጉልበተኛ የሚሆንበት አንዳችም ክፍተት እንዳይኖር ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን በገዛ አገራቸው በብሔራቸው፣ በእምነታቸው፣ በባህላቸውና በመሳሰሉት ሁሉ በእኩልነት መስተናገድ የሚችሉት ሕግ ሲከበር ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግሥት የሚባለው አካል በሕጉ መሠረት የተሰጠውን ኃላፊነት መወጣት አለበት፡፡ ተቀዳሚ ኃላፊነቱ ሕግ ማስከበር ነው፡፡ ቤተ መንግሥትና ቤተ እምነት በሕጉ መሠረት ለአገር ጉዳይ ይደጋገፋሉ እንጂ፣ አንዱ በሌላው ሥራ ውስጥ ጥልቅ ማለት የለባቸውም፡፡ አገር የሚመሩም ሆነ በየደረጃው የሚገኙ ሹማምንት መንግሥትና እምነት አይቀላቅሉ፡፡ አንዱ በሌላው ጉዳይ ውስጥ ገብቶ አይፈትፍት፡፡ አማኞችም እንደሚከተሉት እምነት ቀናውን ጎዳና በመያዝ ከነውጠኝነት ራሳቸውን ያርቁ፡፡ ዳር ሆነው በማኅበራዊ የትስስር ገጾች እሳት የሚቆሰቁሱ አደብ ይግዙ፡፡ እሳቱ እነሱን የማያገኝ ቢመስላቸው እንኳ ከቤተሰቦቻቸው ወይም ከወዳጆቻቸው መሀል እንደሚነጥቃቸው ልብ ይበሉ፡፡ ለአገር ህልውና ሲባል ሕግ ይከበር!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ከውጭ ይገቡ የነበሩ 38 ዓይነት ምርቶች እንዳይገቡ ዕግድ ተጣለ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 38 ከውጪ የሚገቡ ምርቶች ላይ ዕገዳ...

የአየር መንገድ ተጓዦች በሻንጣ የሚያስገቡትን የልብስና የጫማ ብዛት የሚገድብ ረቂቅ መመርያ ተዘጋጀ

ከቀረጥ ነፃ ይገቡ የነበሩ ዕቃዎች 87 በመቶ እንዲቀንሱ ተደርጓል መንገደኞች...

አሜሪካ ሕወሓትን በማሳመንና በመጫን በሰላም ሒደቱ ትልቅ ሚና መጫወቷን የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ አስታወቁ

የተመድና የአውሮፓ ኅብረት አበርክቶ አሉታዊ እንደነበር ጠቁመዋል በመንግሥትና በሕወሓት መካከል...

ብሔራዊ ባንክ ለጥቃቅንና አነስተኛ ብድሮች ዋስትና መስጠት ሊጀምር ነው

ኢንተርፕራይዞችን ብቻ የሚያገለግል የፋይናንስ ማዕከል ሥራ ጀመረ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ምሥረታ ዝግጅቶችና ከገበያው የሚጠበቁ ዕድሎች

ኢትዮጵያ ከ50 ዓመት በኋላ ዳግም የምታስጀምረውን የካፒታል ገበያ ዘመኑን...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...

መንግሥት የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ድንበር ጥሰው የሚያደርሱትን ጥቃት እንዲያስቆም ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ...

አዲስ ሲኖዶስ አቋቁመዋል በተባሉና በኦሮሚያ መንግሥት ላይ ክስ ለመመሥረት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ ከገባችበት አረንቋ ውስጥ በፍጥነት ትውጣ!

የአገር ህልውና ከሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡ አገር ሰላም ውላ ማደር የምትችለው ደግሞ የሕዝብ ደኅንነት አስተማማኝ ሲሆን ነው፡፡ ሕዝብና መንግሥት በአገር ህልውና...

የፈተናው ውጤት የፖለቲካው ዝቅጠት ማሳያ ነው!

በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከአጠቃላይ ተፈታኞች ውስጥ 3.3 በመቶ ያህሉ ብቻ ማለፋቸው፣ የአገሪቱን የትምህርት ጥራት ደረጃ በሚገባ ያመላከተ መስተዋት እንደሆነ አድርጎ መቀበል ተገቢ ነው፡፡...

የምግብ ችግር አገራዊ ሥጋት ስለደቀነ ፈጣን ዕርምጃ ይወሰድ!

ኢትዮጵያ ውስጥ የሰው ልጆችን አቅም በብርቱ እየፈተኑ ያሉ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ከችግሮቹ ብዛት የተነሳ አንዱን ከሌላው ለማስቀደም የማይቻልበት ደረጃ ላይ የተደረሰ ቢሆንም፣ የምግብና የሰላም...