Saturday, April 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከተሞች ሀብታቸውን አስይዘው እንዲበደሩ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለድሬዳዋና ለባህር ዳር ከተሞች የሀብት ግመታ ተጠናቋል

ከተሞች ያላቸውን እርግጠኛ ንብረት (Real Property) እንደ ማስያዣ ተጠቅመው ብድር እንዲወስዱ የሚያስችል፣ የከተሞች ፋይናንስ ስትራቴጂ ረቂቅ ሰነድ ተዘጋጀ፡፡

በከተማና በመሠረት ልማት ሚኒስቴር የከተሞች ገቢ ማሻሻያ ጽሕፈት ቤት፣ ሰነዱን አዘጋጅቶ ለገንዘብ ሚኒስቴር ተልኮ ለማፅደቅ እየተጠበቀ ነው፡፡

‹‹ወደፊት ከተሞች ሀብታቸውን አስይዘው እንዲበደሩ ለማድረግ ሥርዓት መዘርጋት አለበት፡፡ አቅማቸውን መገንባትና ሀብታቸውን አውቀው ምን ያህል ገቢ ከዚያ ማመንጨት እንደሚችሉ ሥልጠና እየሰጠናቸው ነው፡፡ በዚህ ረገድ ብዙ የሄዱ አገሮች አሉ፣ ከእነሱ ልምድ ወስደናል፤›› ሲሉ የጽሕፈት ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ዚነት ኢብራሂም ገልጸዋል፡፡

መሬቶች፣ ሕንፃዎች፣ ፋብሪካዎች፣ ከ500 ካሬ ሜትር በላይ የሆኑ ቤቶች፣ የቅርስ ሀብቶችና ልዩ አገልግሎት የሚሰጡ እንደ ዩኒቨርሲቲ፣ ሆስፒታል፣ ሆቴልና ሌሎች በርካታ የሀብት ዓይነቶች ለከተሞች በሀብትነት ይመዘገባሉ ብለዋል፡፡

ጽሕፈት ቤቱ እስካሁን የድሬዳዋና የባህር ዳር ከተሞችን ጠቅላላ የሀብት ግመታ ማጠናቀቁን፣ ለከተሞቹ ማዘጋጃ ቤቶች አስተዳደር ማስረከቡን፣ የሀብት ግመታው በመቀሌም ተጀምሮ የነበረ ሲሆን፣ በጦርነቱ ምክንያት አዳማ ከተማ ተተክታለች፡፡

‹‹ሁለቱ ከተሞች ሀብታቸውን አስይዘው ለመበደር በቅድመ ውይይት ደረጃ ላይ ናቸው፡፡ አጠቃላይ ሀብታቸውን ለክተን ሰጥተናቸዋል፡፡ የሀብት ግመታው በየዓመቱ መካሄድ ስላለበት (Depreciation) ሥልጠና እየሰጠን ነው፡፡ በከተሞች ውስጥ ከግል ንብረቶች ውጪ በርካታ ንብረቶች አሉ፤›› ሲሉ ወ/ሮ ዘኒት አስረድተዋል፡፡

የሀብት ግመታው ከሕንፃ ሽያጭ መንግሥት የሚያጣውን ገቢም ከፍ ለማድረግ የታለመ ነው፡፡ ‹‹እስከ ዛሬ መንግሥት የግል ንብረቶች ዋጋ ዝርዝር ስለሌለው፣ አንድ ሆቴል ሲሸጥ በውሸት ውል ዋጋው እየተቀነሰ የመንግሥት ገቢ ሲቀንስ ነበር፤›› ብለዋል፡፡

በአዲሱ ሥርዓት ሀብቶች ተተምነው መለያ ኮድ ተሰጥቷቸው በጂአይኤስ (GIS) ካርታ ይመዘገባሉ፡፡ የዋጋ ትመናው ለኢንሹራንስም ይጠቅማል ተብሏል፡፡

አዲሱ ስትራቴጂ ከተሞች ከራሳቸው ገቢ እስከ 70 በመቶ ወጪያቸውን ለመሸፈን ለማስቻል ሲሆን፣ ለዚህም የንብረት ታክስ (Property Tax)፣ የሊዝ፣ የንግድ አገልግሎት ገቢ (Business Fee)፣ የመንገዶች ጥገና ፈንድና በአጠቃላይ ስድስት ዓይነት የገቢ ማስገኛ ሥልቶች መቀየሳቸውን ታውቋል፡፡

‹‹የንብረት ታክስ በአንዳንድ አገሮች ብቻውን 60 በመቶ የከተሞች ገቢን የሚሸፍን ቢሆንም፣ በኢትየጵያ ውስጥ አስተዋጽኦው ከአንድ በመቶ በታች ነው፡፡ የጣሪያና የግድግዳ ግብር ተብሎ በአንዳንድ ከተሞች ብቻ አነስተኛ ገንዘብ ይሰበስባሉ፡፡ በትክክል ለመተግበር አዲስ ሥርዓት እያበጀን ነው፤›› ሲሉ ወ/ሮ ዘኒት ተናግረዋል፡፡

የንብረት ታክስ አዋጅ እንደ አዲስ ተዘጋጅቶ ለገንዘብ ሚኒስቴር መላኩ ታውቋል፡፡ እስካሁን አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ከተሞች ወጪያቸውን የሚሸፍኑት ከፌዴራል መንግሥት ከሚሰጣቸው በጀትና ከውጭ በሚመጣ የፕሮጀክት ፈንድ ነው፡፡ ለምሳሌ የኮብልስቶን ሥራዎች በአብዛኛው በዓለም ባንክ ፈንድ የሚከናወኑ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ በውጭ ጫና ምክንያት እነዚህ ፈንዶች ቀጣይነታቸው አስማማኝ እንዳልሆነ ተገልጿል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች