Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

ሰሞኑን በአዲስ አበባ “ቀለሜዋ፣ ቀለሜዋ ነይ ነይ ቀለሜዋ” የሚለው ዘፈን እየተዘፈነ ነው። የአዲስ አበባ መስተዳድር በዘጠኝ ወራት ግምገማው ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጣትን አቅጣጫ በመከተል የከተማው ሕንፃዎች ቀለም ግራጫ እንዲሆን ወስኗል ሲል ሪፖርተር በሰሞኑ ዕትሙ አስነብቧል። ይህንን መነሻ አድርገው ብዙ ሐሳቦች እየተፋጩና ክርክሮች እየተደረጉ ነው። “ኧረ እንዴት ነው ነገሩ?” አለች ነፃነት መለሰ። ነገሩማ መሆን ያለበት እንዲህ ነው ስንል እኛም የራሳችንን ሐሳብ እንወርውር።

ቀለም ኢነርጂ ነው። ቀለም ሁሉ የየራሱ ኢነርጂ አለው። በአንድ ዓይነት የቀለም ተፅዕኖ ስር ለረጅም ጊዜ መቆየትና የቀለሙ መብዛት፣ ከፍ ያለ የዚያን ቀለም ኢነርጂ ጫና እንድንቀበል የሚያደርግ ነው። ታድያ በአንድ ዓይነት ኢነርጂ ተፅዕኖ ሥር ብቻ እንድንቆይ ለምን እንገደዳለን?

ኢነርጂ ቀላል ጉዳይ አይደለም። ኢነርጂ ከሁሉ ነገር ጋር የተሳሰረ ነው። ባለፈው ከወደ እንግሊዝ “5G” ነው ኮቪድ ያመጣብን የሚሉ ሰዎች ሁሉ ተሰምተዋል። ሳይንሳዊነቱን አላጣራሁምና በዚህ ጉዳይ ብዙ አልልም። ኢነርጂ ሰፊ ተፅዕኖ ያለው መሆኑ ግን አያከራክርም።

እያንዳንዱ ቀለም የራሱ እርግብግቢት (Frequency) መጠን አለው። “Frequency” ደግሞ ነገሮችን እስከማፍረስና ማደፍረስ የሚያስችል ዓቅም አለው። በዚህ ረገድ የ“Natural Frequency” ጉዳይን ማንበብ ይረዳል።

የድምፅ ጩኸትና ዝምታ እንዳለ ሁሉ፣ የቀለም ጩኸትና ዝምታም አለ። ሁለቱም በሁባሬ (Harmony) ሲኖሩ እንጂ የአንዱ የበዛ ተፅዕኖ ለሆነ የተለየና የተመረጠ ዓላማ ካልሆነ በቀር ጠቃሚም ተፈጥሯዊም አይደለም። ተፈጥሮ ግራጫ ብቻ አይደለችም። ተፈጥሮ አንድ ቀለም (Mono-chromatic) አይደለችም። ተፈጥሮ ባለብዙ ቀለም ነች።

ተፈጥሮ ያላት ቀለም ከወቅት ጋር የሚቀያየርም ነው። የተፈጥሮ ቀለም ከጠዋት እስከ ማታ እንኳ አንድ አይደለም። ቀለም ሌላው ይቅርና በሙቀት እንኳ የሚሰጠው ስሜት ይለያያል። ለዚህም በፎቶግራፍና ፊልም ቴክኖሎጂ (Color Temperature) የሚባል ጽንሰ ሐሳብ (Concept) አለ። የዘርፉ ባለሙያዎች ሲያስተምሩ ውብ ቀለማት የሚገኙት ጠዋት 4:00 ሰዓትና ምሽት 10:00 ሰዓት አካባቢ ነው ይላሉ። ይህ በእኛ አገር መሆኑ ነው። እዚህ ላይ ዋናው ጉዳይ ሰዓቱ ሳይሆን የ“Color Temperature” መሆኑ ልብ ይባልልኝ።

ቀለማት ለውበት ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው። ያ ማለት ግን የቀለማት ተፅዕኖ ውበት (Aesthetics) ብቻ ነው ማለት አይደለም። ለሆስፒታሎች ነጭና ውኃ ሰማያዊ ቀለም መመረጡ ያለ ምክንያት አይደለም። ከትኩሳት ጋር የሚያያዝ ጉዳይ ስላላቸው ነው። ይህ በብዙ አገሮች የሚተገበር መሆኑ የተቀባይነቱን ልክ ያሳያል። በቀዶ ጥገና ክፍል አረንጓዴ ቀለም መለበሱ ከደም ቀለም ቀይነት ጋር የተያያዘ ምክንያት አለው። ዝርዝር ምክንያቱን የሳይንስ መረጃ እያቀረቡ እዚህ ለመሟገት አይመችም፣ ቦታውም አይደለም።

የቀለማት ኅብረት ወይም ሁባሬ (Harmony) የቱ ቀለም ከየትኛው ጋር እንደሚስማማ የሚታይበት ነው። ይህም በብዙ ጉዳዮች ላይ የሚወሰን ነው። ከእነዚህም መካከል ቅርርብና ተቃርኖ በምክንያትነት የሚጠቀሱ ሲሆኑ ሌሎችም ጉዳዮች አሉ።

መሠረታዊ ቀለማት ብዛታቸው ጥቂት ቢሆኑም፣ ከእነዚህ የሚፈጠሩት ቀለማት ግን በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ናቸው። የቀለም ሳይንስም ይሁን ተፅዕኖው ሰፊና በቀላል የማይታይ ነው። በዚህም ምክንያት የከተማ የቀለም ውሳኔ ለተወሰኑ ግለሰቦችና ቡድኖች ለተወሰኑ ቀለማት ብቻም ሊሰጥ የማይገባው ነው።

ቀለም በማርኬቲንግ “ሳይንስ” የራሱ ከፍ ያለ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው። በብራንድና ሎጎ ቀለማት ምርጫ ላይ እያንዳንዱ ቀለም በሰው ሥነ ልቦና ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ብዙ ተጠንቷል። ያንን የፈለገ በርብሮ ያንብብ። ቀይና ኦሬንጅ ቀለማት ለምግብና ለመጠጥ ቤቶች መመረጣቸው የራሱ ምክንያት አለው።

ቀለማት በግዥ ውሳኔና በሱቅ ውስጥ የቆይታ ጊዜን በመወሰን በኩል የራሳቸው የሳይኮሎጂ ተፅዕኖ አላቸው። በዚህና መሰል ጉዳዮች ላይ ያሉ ጥናቶችን እዚህ አቅርቦ መከራከር ቦታውም ተገቢም አይደለም። የፈለገ ፍንጩን ተከትሎ ያሻውን ያህል መበርበርና ማጥናት ይችላል።

ቀለማት የቦታ ስፋትና ጥበት፣ የአካባቢ ሙቀትና ቅዝቃዜ ላይ የራሳቸው ተፅዕኖ አላቸው። እንዲህ ከፍ ያለ ተፅዕኖ ያለውን ጉዳይ፣ በአንድ ሰፊ ከተማ ውስጥ አንድ ዓይነት እንዲሆን ለማድረግ መነሳት ስህተት ነው፣ ተፈጥሯዊም አይደለም። የሚገርመው ደግሞ ይህን ባለ ሰፊ ተፅዕኖ ጉዳይ በአጭር ጊዜና በተወሰኑ ሰዎች ስብሰባ ብይን መስጠት ሲሆን፣ ይህም ትልቅ ስህተት ነው።

ከተማ የሕዝብ ነው። የከተማ ቀለም ውሳኔ የሚያስፈልገው አይመስለኝም። እንዲያ እንዲሆን ግዴታ ካስፈለገ እንኳ ለሕዝብ ትችት መቅረብ አለበት። አንድ ወቅት የከተማው ባቡር ቀለም ምርጫ እንኳ ለሕዝብ ቀርቦ ነበር እኮ፡፡እንደ እኔ ግን የከተማን ቀለም በአንድ ቀለም መወሰን ተገቢ አይመስለኝም።

ቀለማትን በመብራትና ማግኔት ተፅዕኖ መቀያየር ላይ በተደረሰበት ዘመን ከተማው ሁሉ አንድ ቀለም ብቻ ይሁን ማለት ተገቢ አይመስለኝም። ምናልባትም ይህን ቀለም ያስመጣ ባለሥልጣን አለ ይሆን ያሰኛል። ትንሽ ቆይቶ እንደ ደርግ ዘመን አንድ ዓይነት ልብስ (Uniform) ልበሱ የሚል ውሳኔ እንደማይከተልም እርግጠኛ አይደለንም።

አንድ ድሮ የሰማሁትን የቀለም ተፅዕኖ በመጥቀስ ሐሳቤን ላሳርግ። በማኦ ዘመን ሶሻሊስት ቻይና ውስጥ ሰውን በቀለም ያሰቃዩና ያሳብዱ ነበር ይባላል። ይህንን ሲያደርጉም ታሳሪዎችን በቢጫ ቀለም ቤት ውስጥ በማቆየት፣ ቢጫ ልብስ በማልበስ፣ ምግብን ቢጫ ቀለም እንዲኖረው በማድረግና በቢጫ የመመገቢያ ዕቃዎች በማቅረብ ነበር ይባላል። ቢጫ ቀለም የበዛበት ታሳሪም ትንሽ ቆይቶ ይጨልላል (ያብዳል) አሉ። ይህንን የሰሙ አሳሪዎች ደግሞ እንዳይሞክሩት አደራ፡፡

ለማንኛውም ቀለምን ከተፈጥሮ ተምሮ ሁባሬውን ጠብቆ እንዲሄድ ማድረግ እንጂ በአንድ መበየን አይገባም እላለሁ። አካባቢው እንደ ዶቢ ጨው በረሃ ነጭ ይሁን ካላልን በቀር፣ የአዲስ አበባ የተፈጥሮ ቀለም (Multicolour) ነግቶ እስኪመሽም፣ ከመስከረም እስከ ሐምሌም የሚቀያየር ነው። እንዲያው ግን የከተማው ቀዳሚ ችግር የቀለም ነውን? የቀለሙ ጉዳይ የዋጋ ትኩሳትን ያበርዳልን? እንዲያው ብቻ ትኩረታችን ሁሉ ግን ግርም ይለኛል፡፡

(ፔስ ነጋ፣ በፌስቡክ ገጹ ያጋራው)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...