Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉበአገራዊ ውይይት ሒደት በታሳቢነት መታየት ያለባቸው መሠረታዊ ነጥቦች

በአገራዊ ውይይት ሒደት በታሳቢነት መታየት ያለባቸው መሠረታዊ ነጥቦች

ቀን:

በመኮንን ዛገ

አገራዊ ውይይት ከሌሎች የዜጎችና የልሂቃን መነጋገሪያ መድረኮች፣ የሐሳብ ማስታረቂያ ሒደቶችና የፖለቲካ ተቃርኖ መፍቻ ሥልቶች በተለየ በተነፃፃሪ እጅግ ሰፊ ጊዜን፣ የባለሙያዎችን ፈርጀ ብዙ ዕውቀታዊ አበርክቶን፣ የበርካታ “ያገባኛል ይገባኛል ባይ” አካላትን ተሳትፎ፣ የምልዓተ ዜጎችና የፖለቲካ አመራርን ቁርጠኝነት፣ እጅግ ግዙፍ ዓይነታዊና ገንዘብ ነክ መዋዕለ ነዋይ፣ አገር በቀል ዕውቀትና የውጫዊ ኃይሎችን ቴክኒካዊ፣ የፋይናንስ፣ የሎጂስቲክስና ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ የሚፈልግ ዓይነተኛ የግጭት መፍቻና የፖለቲካ ሽግግር ማሳለጫ መሣሪያ ነው፡፡ ስለሆነም እነዚህን መሰል ውይይቶችን ለማከናወን ሲታሰብ እጅግ ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ የሚጠይቅ፣ ቁርጠኝነትን የሚሻ፣ ለተጠባቂ ውጤቱና ትግበራው ሁሉን አቀፍ ቅን መሻትን የሚፈልግ በመሆኑ ለአገር አቀፍ የፖለቲካ ውይይት በፅንሰት፣ በንድፍና በዝግጅት፣ በክንውንና በውጤት ትግበራ ሒደት ረገድ ታሳቢ ሊደረጉ የሚገቡ አሥር መሠረታዊ ነጥቦች አሉ፡፡ እነዚህም እንደሚከተለው በዝርዝር ቀርበዋል፡፡-

ውይይቱና የአወያይ አካሉ ሥነ ሥልጣንና ተልዕኮው ከየት ነው የመነጨው?

በተለያዩ አገሮች የተካሄዱ አገራዊ ውይይቶችን መሠረት አድርገው የተከናወኑ በርካታ የጥናት ሰነዶች እንደሚያመለክቱት፣ አገራዊ ውይይቶች በዋናነት በአራት መሠረታዊ ገፊ ምክንያቶች (ወይም አነሳሽነት) ሊካሄዱ ይችላሉ፡፡ እነዚህም አንደኛ በአገር ውስጥ ተከታታይና ሰፊ ሕዝባዊ አመፅና ተቃውሞ ሲከሰት (Popular Uprising, Violence and Conflict)፣ የፖለቲካ ኃይላት አንዱ በአንዱ ላይ ፍላጎቶቻቸውን በኃይል ለመጫን፣ ጥቅማቸውን  ለማስጠበቅና  ፖለቲካዊ  ሥልጣን  ለመቆጣጠር  በመካከላቸው ጦር ሰብቀው በሚዋጉበት ጊዜ (Armed Conflcit and War)፣ ቀደም ሲል የተጠቀሱትን ሁለት መነሻዎች ተከትሎ በአገር የፖለቲካ ልሂቃን መካከል በሁለንተናዊ የፖለቲካ ሁናቴና የሰላማዊ ሽግግር ሒደት ላይ የቀደመ የልሂቃኑ ድርድር ሲኖር (Prior Elite Negotiations) እንዲሁም በአራተኛ ደረጃ ቀደም ሲል ለነበሩ ፖለቲካዊ አለመግባባቶችና ግጭቶች መፍትሔነት በሦስተኛ ወገን አማካይነት የተደረገ አጠቃላይ የሰላም ስምምነትና የተኩስ አቁም አዋጅ (Comprehensive Peace and Cease-fire Agreement) ሲኖር ነው፡፡

በእዚህ ረገድ ስናየው አብዛኛውን ጊዜ የአገራዊ ፖለቲካዊ ውይይት ዝግጅት ወሰነ ሥልጣንና ተልዕኮ በግልጽ፣ የሚወሰነው ቁልፍ በሆኑ የፖለቲካዊ፣ የማኅበራዊና የወታደራዊ ተዋናዮች መካከል በሚደረግ የቅድመ ድርድር ሒደት ነው። ስለሆነም እነዚህ ልሂቃን አንዴ በይዘቱና በሒደቱ ላይ ከተደራደሩና በአጠቃላይ ቅርፁ (General Framework) ላይ ከስምምነት ከደረሱ በኋላ ወሰነ ሥልጣኑና ተልዕኮው ተዘርዝሮ በአዋጅ፣ በደንብ፣ በድንጋጌ ወይም የአገር የሕግ ሥርዓት በሚፈቅደው ሌላ ማንኛውም መንገድ ጉዳዩ በሚመለከታቸው ሕገ መንግሥታዊ ተቋማት (በእኛ አገር ሁኔታ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት) አማካይነት እንዲፀድቅ ይደረጋል።

በተለይ ደግሞ አገራዊ የፖለቲካ ውይይቶች ቁልፍ የፖለቲካ ልሂቃኑ በቅድመ ውይይት የድርድር ሒደት በዝርዝር በተስማሙባቸው ነጥቦች፣ እንዲሁም በተቻለ መጠን በሰፊው የውይይቱ ተዋንያንና በየተዋረዱ ባሉ ሕገ መንግሥታዊ ተቋማት በፀደቁ ደንቦች በተበየኑ ግልጽ ሥልጣኖች ከተቋቋሙ፣ ለውይይቱ የዝግጅትና ትግበራ ስኬት በእጅጉ ጠቃሚ ናቸው። እንዲህ ዓይነት ሁሉን አቀፍ ድርድሮች በዋነኛ የፖለቲካው ተዋናዮች መካከል ሲደረጉና ከምልዓተ ሕዝቡ የመተማመኛ ድጋፎች ሲሰጧቸው ሁሉም ተሳታፊ አካላት ለውይይቱ መሳካት ቁርጠኝነት እንዲኖራቸው፣ እንዲሁም በውይይቱ ተጠባቂ ግቦችና የምክረ ሐሳቦች ትግበራ ላይ እንዲስማሙ የማረጋገጫ ማኅተም ይሰጣሉ። ይህም የምክክር፣ የውይይቱንና የመግባባቱን የትግበራ ሒደት ያሳልጣል፣ ሕጋዊ ቅቡልነቱን ያጠናክራል፡፡ እንዲሁም፣ ውይይቱ አንዴ ከተጀመረ በኋላ የሚነሱና በተልዕኮ፣ በግቦችና በወሰነ ሥልጣን ረገድ ሊፈጠሩ የሚችሉ አለመግባባቶችን በእጅጉ ይቀንሳል፡፡

በተቃራኒው ከውይይቱ በፊት በሁሉም ትልልቅ ተሳታፊ ቡድኖች መካከል የቅድመ ውይይት የድርድር መድረክ ካልተዘጋጀና በተቻለ መጠን ደግሞ የዋነኛ ተዋንያን እምነት ካልተጣለበት፣ እንዲሁም የዴሞክራሲያዊ ተቋማት ድጋፍ ካልተደረገለት በአንዳንድ ወሳኝ ቡድኖችና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለ ሰብዕናዎች ዘንድ በውይይቱ ላይ በቁርጠኝነት ለመሳተፍ ፈቃደኛ አለመሆን፣ የውይይቱን ሒደት በገቢር ወይም በቸልታ ማሰናከል፣ ሐሳቡን ማቃለል፣ እንዲሁም ትግበራው ላይ ሳንካ በመፍጠር እንዳይሆን ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ ስለሆነም የአወያይ አካሉ ወሰነ ሥልጣን በዋና ዋና የፖለቲካ ልሂቃን ትምምን እንዲፈጠርበት፣ የምልዓተ ሕዝብ ሱታፌ፣ እምነትና ቅቡልነት እንዲኖረው፣ እንዲሁም በአገሪቱ ባሉ ሕገ መንግሥታዊ ተቋማት ውይይትና ማፅደቅ ሊኖርበት ይገባል፡፡

ወሰነ ሥልጣኑ ቁልፍ ጉዳዮች ምን ምንድናቸው?

አገራዊ የፖለቲካ ውይይቶች ከመጀመራቸው በፊት በአገር በሚደረጉ ግልጽ ቅድመ ድርድሮች ላይ ተመሥርተው ከሚካሄዱ ፖለቲካዊ የሽግግር ሒደቶች ጋር በሚገባ የተገለጸና የተረጋገጠ ትስስር ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በአንፃሩም ከእዚሁ የሚመነጭ ግልጽ፣ ወጥና በአግባቡ ሊመራ የሚችል ወስነ ሥልጣንና ተልዕኮ መኖሩ ደግሞ ውይይቱን በማፋጠን ረገድ በእጅጉ ጠቃሚ ነው፡፡ ስለሆነም አገራዊ የፖለቲካ ውይይቶችን የማዘጋጀት ኃላፊነት የተጣለባቸው አካላት ውይይቱ ከመጀመሩ አስቀድሞ በሚከተሉት መሠረታዊ ጥያቄዎች ላይ መደራደር ይኖርባቸዋል። እነዚህም፣

ውይይት መድረኩ በምን በምን ጉዳዮች ላይ ይወያያል?

ይህም ውይይቱ ትኩረት የሚያደርግባቸው ዋና ዋና ነጥቦችን መዘርዘር ነው፡፡ በአገራዊ ውይይት ሒደት መነሳት  ያለባቸው  ነጥቦች  መሠረታዊ፣ እጅግ  አንገብጋቢዎችና ወሰነ ሰፊ  መሆን  ያለባቸው  ሲሆን፣ ለአብነትም በተጨባጭ ያሉ አሁናዊ ለግጭት መንስዔ በሆኑ ጉዳዮች፣ የአገረ መንግሥቱንና የአጠቃላይ የአገሪቱን ህልውና አደጋ ላይ የጣሉና ወይም የሚጥሉ ሥጋቶች፣ የሕዝቦችን ሰላምና ወንድማማችነትን የሚያናጉ ቅራኔዎች፣ የአገር ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነትን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በተጓዳኝ ደግሞ በምክክሩ ሒደት ላይ ለመወያያነት መነሳት ያለባቸው ጉዳዮች ዝርዝራቸው በአግባቡ ሳይንዛዛ ሊመራ የሚችል እንጂ፣ ከአቅም በላይ አለመሆኑን አስቀድሞ መወሰንም እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። በዚህም የመወያያ አጀንዳዎች ከሚገባው በላይ የተለጠጡና በርካታ ዝርዝር ጉዳዮችን ያካተቱ ከሆኑ ዋና ዋናዎቹ ወይም አንገብጋቢ ጉዳዮች በቸልታ እንዲዘለሉ ወይም ጥቂቶቹ ላይ ደግሞ በትክክል እንዳይወያዩ አልያም ደግሞ በጥልቀት እንዳይዳሰሱ ሊያደርጋቸው ይችላል። በእዚህ የተነሳ የትኩረት መበታተንም ሊያጋጥም ስለሚችል በመሠረታዊ ነገር ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ በአጭር አገላለጽ በተመጠኑ፣ በመሠረታዊ፣ በአንገብጋቢና በወቅታዊ አጀንዳዎች ላይ ማተኮር ይገባል፡፡

ዩ ተቋም ምን ዓይነት ሥልጣንና አቅም ይኖረዋል?

በአንድ ወገን አገራዊ የፖለቲካ ውይይት አዘጋጁ ተቋም ሌሎች በአገሪቱ የሚገኙ ሕገ መንግሥታዊ ተቋማት (ለምሳሌ ፓርላማ ወይም ሌሎች የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት) እንደ ሁኔታው ተቀብለው ሊተገብሩት ወይም ሊጥሉት የሚችሉትን ምክረ ሐሳብ የማቅረብ ሥልጣን ብቻ ሊኖረው ይችላል። በሌላ አማራጭ ደግሞ የውይይት አዘጋጁ ሌሎች ተቋማት ያለ ምንም ገደብና አማራጭ ተቀብለው እንዲተገብሯቸው የሚጠበቅባቸውን አስገዳጅ ውሳኔዎች ሊያስተላልፍ ይችላል። ሌላው ደግሞ ባለሁለት ፈርጅ ወይም የተዳቀለ ሞዴል የሚባለው ደግሞ ለፖለቲካዊ ውይይት አዘጋጅ አካላት ጠንካራ የውሳኔ ምክረ ሐሳብ አቅራቢነትና ውሳኔ ሰጪነት ሥልጣን (አቅም) ይሰጣል፡፡ ይህም ሆኖ ደግሞ ለሌሎች ሕገ መንግሥታዊ ተቋማት ከውይይቱ የመነጩ ውሳኔዎችንና ምክረ ሐሳቦችን ከማፅደቃቸው በፊት የመወያየት ሥልጣንና የማሻሻያና ማጎልበቻ ሐሳቦችን የማከል አቅም ይሰጣቸዋል።

ውይይቱ ከነባር ሕገ መንግሥታዊ ተቋማት ጋር እንዴት ይገናኛል?

አብዛኛውን ጊዜ አገራዊ የፖለቲካ ውይይት መድረኮች በውይይቱ ክንውን ሒደት ወቅት ስለተነጋገሩበት አጀንዳ፣ ስለደረሱበት ስምምነት፣ የተመዘገቡ ውጤቶችና ስለተሰነዘሩ ምክረ ሐሳቦች በመደበኛ መዋቅር ሥር ላሉ የመንግሥት ተቋማት ዕለታዊ ሪፖርቶችን እንዲያዘጋጁ አይጠበቅባቸውም፡፡ እንዲያቀርቡም አይገደዱም። ሆኖም በአንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ የመንግሥት ባለሥልጣናት ወይም የፓርላማ ተወካዮች በውይይቱ ውስጥ ተቋሞቻቸውን ወክለው ወይም በግላቸው ይሳተፋሉ። ምናልባትም በውይይቶቹ ጅማሮ የመክፈቻ ንግግርና የሥራ መመርያ ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ ከዚህ አንፃር የእነዚህ ወኪሎችና ባለሥልጣናት በውይይቱ ላይ መታደም የወከሏቸው ተቋማት ስለአጠቃላይ የውይይቱ አዝማሚያና በውይይቱ ሒደት ውስጥ ያሉትን ዕድገቶች በጥልቀት እንዲከታተሉ ያስችላቸዋል፡፡ በዚህም የውይይቱን ምክረ ሐሳቦችና ውሳኔዎችን የሐሳብ መዛነፍ ሳይኖር በቀላሉ ተግባራዊ ለማድረግ ሊያበረታታቸው ይችላል፡፡ ስለሆነም በመካከል ያለውን አሉታዊ ጫና ለመቀነስ እንዲቻል በተቻለ መጠን በአገራዊ ውይይት አዘጋጁ አካልና በመደበኛ ሕገ መንግሥታዊ ተቋማት መካከል ግልጽና አቻዊ ግንኙነት መፍጠር ይገባል፡፡

ውይይቱ ለምን ያህል ጊዜ ይቆያል?

በአንድ በኩል አገራዊ የፖለቲካ ውይይቶች ለዘመናት ምላሽ ያላገኙ ሕዝባዊ ጥያቄዎችን በውይይት የሚያስተናግዱ፣ እንዲሁም ለእነዚህ ጥያቄዎችና መሻቶች በሁለንተናዊ ሱታፌ ዘለቄታዊ መፍትሔ የሚሆኑና ሁሉን አግባቢ የጋራ ድምዳሜዎች ላይ ለመድረስ የሚያስችሉ አወዛጋቢ፣ አጨቃጫቂና ውስብስብ ጉዳዮችን በጥንቃቄ ለመፍታት የሚሞክሩ ናቸው፡፡ ከእዚህ አንፃር በተያዙ አጀንዳዎቻቸው ላይ የሁሉንም ወገን ሐሳብ ለማስተናገድ፣ በየፈርጀ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት፣ አስፈላጊ ፖለቲካዊ ማሻሻያዎችን ለመደራደርና ሁሉን አሸናፊ ስምምነት ላይ ለመድረስ በቂ ጊዜ ያስፈልጋቸዋል። በሌላ በኩል የአገራዊ ውይይት ክንውን ሒደቶች በተነፃፃሪ ረጅም ጊዜ የሚቆዩ ከሆነ ደግሞ ተገቢውን የችግር ፈችነት አቅም፣ ግለተ ኃይል (Momentum) እና የመቋጫ አቅጣጫ ሊያጡ ይችላሉ፡፡

በዚህም የተነሳ ምልዓተ ሕዝቡ በውይይቱ ላይ ያሳደረውን ተስፋና ያለውን ፍላጎት ቀስ በቀስ ሊያጣ ይችላል፡፡ እንዲሁም የአገሪቱ የፖለቲካ መሪዎችና ልሒቃኑ በእዚህ የተራዘመ የውይይት ሒደት ያላቸውን ተሳትፎ ልክ ጠብቀው ለረዥም ጊዜ መዝለቅ አይችሉም፡፡ ስለሆነም የፖለቲካ ውይይቶችን የሚነድፉና የሚያዘጋጁ አካላት በተቻለ መጠን በልሂቃን፣ በሐሳብ መሪዎችና በምልዓተ ሕዝቡ የተነሳሽነት ማነስ፣ የአቅጣጫ ዕጦት፣ የግለት መቀዛቀዝና ትኩረት እያደር መቀነስ ሳይገጥማቸው እዚያው እንዳለ በበቂ አሳታፊ ውይይት ለማድረግ በሚያስችል ሚዛናዊ የጊዜ ምጣኔ ላይ አስቀድመው መስማማት አለባቸው።

 ራዊ የፖለቲካ ውይይት ተሳታፊ በምን ያህል ስፋት ልክ መሆን አለበት?

በተደጋጋሚ ጊዜ እንደሚገለጸው አገር አቀፍ የፖለቲካ ውይይት ሒደቶች አንድ አገር ሊወስዳቸው በሚገቡ ቁልፍ አገራዊ የፖለቲካ ትርክት ማስተካከያ፣ የመንግሥታዊ ሥርዓት ማሻሻያ ዕርምጃዎች ላይ ኅብረተሰብ አቀፍ መግባባትን መፍጠርን ያለሙ ናቸው። ስለሆነም እንደዚህ ዓይነት ሁሉን አቀፍ መግባባት ላይ ለመድረስ ደግሞ በተቻለ መጠን በርካታ የምርጫ ክልሎችን ተወካዮችና ተሳታፊዎችን በውይይቱ መወከል ያስፈልጋል፡፡ በዚህም ምክንያት አገራዊ ውይይቶችን የሚያዘጋጁ ወገኖች ውይይቶቹ በምን ያህል የተሳትፎ ስፋት ልክ መሆን አለባቸው የሚለውን ለመወሰን ከፍተኛ አጣብቂኝ ውስጥ ይገባሉ።

ሁለት ወይም ከእዚያ በላይ አልያም ጥቂት መቶ አካላት ተሳታፊዎች

በጣም ጥቂት ተወካዮች ተሳታፊ የሆኑባቸው አነስተኛ አገራዊ የፖለቲካ ውይይቶች የሚከተሉት ባህርያት አሏቸው።

 1. 1. በአግባቡ ውይይቱን ለማስተዳደር ቀላል ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
 2. 2. ሁሉም ተዋንያን በምልዓተ ጉባዔ ደረጃ በመሳተፍ በተደጋጋሚ መገናኘት ይችላሉ፡፡
 3. 3. ተወካዮችን በምልዓተ ጉባዔ ደረጃ በማሳተፍና ተጨባጭ ውይይቶችን በስፋትና በተመጣጣኝ ውጤታማነት ማከናወን ይችላሉ።
 4. 4. በአንፃራዊነት ሲታይ በጥቂት የጉዳይ ክበባትና አነስተኛ በሆኑ የሥራ ቡድኖች ብቻ መከፋፈል ያስፈልጋቸዋል፡፡
 5. 5. ሆኖም አነስተኛ ውይይቶች ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች በምልዓት በማካተት ላይሳካላቸው ስለሚችሉ እጅግ ጠቃሚ የምርጫ ክልሎችና ሀቀኛ የሕዝብ ተወካዮችን በማግለል ረገድ በፅኑ ይተቻሉ።

ድ ሺሕ የሚጠጉ ወይም ከዚያ በላይ ተሳታፊዎች

በቁጥር ከአምስት መቶ በላይ ወደ አንድ ሺሕ የሚጠጉ ወይም ከዚያ በላይ ተሳታፊ ያሏቸው ትልልቅ አገራዊ የፖለቲካ ውይይቶች የሚከተሉት ባህሪያት አሏቸው፡-

 1. 1. በርካታ ቁጥር ያላቸውን የምርጫ ክልሎችና ተወካዮቻቸውን በስፋት ማካተት ይችላሉ፡፡
 2. 2. ሆኖም በቆይታቸው ጊዜ ሁሉ ጥንቃቄ የተሞላበት አመራርና ቁጥጥር ሥርዓት ይፈልጋሉ፡፡
 3. 3. በምልዓተ ጉባዔ ደረጃ በተደጋጋሚ መገናኘት አይችሉም፡፡
 4. 4. በምልዓተ ጉባዔው ወቅት በተጨባጭ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ በስፋትና በጥልቀት መወያየት አይችሉም።
 5. 5. እንደ ውይይቱ አጀንዳ ይዘት በበርካታ የሥራ ቡድኖች መከፋፈል ያስፈልጋቸዋል፣ እንዲሁም አንዳንዶቹ ቡድኖች በራሳቸው ትልቅ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
 6. 6. የአብዛኞቹ ተወካዮችን ውጤታማ ተሳትፎ ለማበረታታት ዝርዝርና በጥንቃቄ የተነደፉ የአሠራር ደንቦችንና መመርያዎችን ማዘጋጀት ሊጠይቁ ይችላሉ።

በአጠቃላይ አገራዊ ውይይት የማዘጋጀት ኃላፊነት የሚመለከታቸው አካላት የፖለቲካ ምክክሮች መጠን ሲነድፉ፣ የመረጡትን ፖለቲካዊና የአመራር ሥነ ዘዴ አንድምታ አስቀድመው ከግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርባቸዋል።

በአር አቀፍ የፖለቲካ ውይይት ውስጥ የትኞቹ የምርጫ ክልሎችና አካላት ይወከላሉ?

የአገራዊ ውይይቶች ዓበይት ግቦችና ተልዕኮ ኅብረተሰብ አቀፍ፣ ዘላቂና ሰላማዊ የጋራ መግባባት መፈጠር ባለባቸው ዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮችና ፖለቲካዊ ማሻሻያዎች ላይ እንደ መሆኑ፣ በተቻለ መጠን በርካታ ምሁራን፣ የፖለቲካ፣ ወታደራዊና ማኅበራዊ የልሂቃን ቡድኖች በውይይቱ ውስጥ መካተታቸው በእጅጉ አስፈላጊ ነው። በተለምዶ አብዛኞቹ የፖለቲካ ውይይቶች ዋና ዋና የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የታጠቁ ቡድኖችን፣ ኢመንግሥታዊ ታጣቂዎችን፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን፣ የአገር ሽማግሌዎችን፣  ወጣቶችን፣  ሴቶችን፣  የጎሳ  መሪዎችንና  የሲቪል  ማኅበረሰብ  ድርጅቶችን  ያካትታሉ። በአንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ የሙያ ማኅበራትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማትም ሊሳተፉ የሚገባ ሲሆን አብዛኞቹ ምክክሮች የሴቶችን፣ የወጣቶችንና የተገለሉ ቡድኖችንና የኅዳጣን ማኅበረሰቦችን ውክልናም ያረጋግጣሉ።

የአገራዊ የፖለቲካ ውይይት ተሳታፊዎችን ስብጥር ለመወሰን ታሳቢ የሚሆኑ ተጠቃሽ ጉዳዮች የሚከተሉት ናቸው። መጠነ ሰፊ የምርጫ ክልል (ወካይና ደጋፊ ሕዝብ) ያላቸውና የእነዚህ የምርጫ ክልሎች ሀቀኛና ሕጋዊ ተወካዮች ነን የሚሉ ቡድኖች የትኞቹ ናቸው? ሕዝባዊ ድጋፍስ ያላቸው የትኞቹ ናቸው? የፖለቲካ ውይይቱ ሊወስዳቸው በሚችለው ማናቸውም ዕርምጃዎች፣ ውሳኔዎችና ምክረ ሐሳቦች አፈጻጸም ላይ ጉልህ ተፅዕኖ የመፍጠር ኃይል ያላቸው የትኞቹ ቡድኖች ናቸው? የአገሪቱን ችግሮች ለመፍታት ያለ ምንም አድልኦና ወገንተኝነት በቅንነት ገለልተኛ ሆኖ በመሥራት ረገድ ልምድና መልካም የኋላ ታሪክ ያላቸው የትኞቹ ቡድኖችና ግለሰቦች ናቸው? የአገሪቱን ችግሮች በዘላቂነት እንዴት መፍታት እንደሚቻል በምሁራዊ መንገድ አዳዲስ የፈጠራ ሐሳቦች የሚያመነጩና ሁነኛ አማራጮች ያሏቸው ቡድኖች የትኞቹ ናቸው? በውይይቱ በተነሱት ጉዳዮች ላይ ጥናትና ምርምር ያደረጉ፣ ሙያዊ ተሞክሮና ዕውቀት ያላቸው የትኞቹ ቡድኖች ናቸው?

ከላይ ከተገለጹት ሐሳቦች ላይ በመንደርደር በፖለቲካ፣ በወታደራዊ፣ በመንግሥትና በሲቪል ማኅበረሰብ ተዋናዮች ጥምረት ሰፊ አገራዊ መግባባት ሊፈጠር ይችላል። ይህንን የሕዝቦች ዙሪያ መለስ የውክልና ስብጥር ለማግኘት ይረዳ ዘንድ አገራዊ ውይይቶች ብዙውን ጊዜ ለገለልተኛ አካላት (ቡድኖችና ግለሰቦች)፣ ለሲቪል ማኅበረሰብ ተዋናዮች፣ ለባለሙያዎች፣ ለሴቶችና ለወጣቶች በቂ የሆኑ መቀመጫዎችን ለይተው በቋሚነት ያስቀምጣሉ። እንዲሁም የተሳትፎ ወሰን በምርጫና በቀጥታ ሕዝብ ውክልና መሆኑን ማረጋገጥና ለዚህም ተገቢውን ምጣኔ ማውጣት ያስፈልጋል፡፡

ር አቀፍ የፖለቲካ ውይይት የአሠራር ሥነ ዘዴ ምን መምሰል አለበት?

አብዛኞቹ የውይይቶች አስተባባሪ ተቋማት የማወያየት ሥራቸውን በተገቢው ውጤትና  ቅልጥፍና ለማከናወን ይረዳቸው ዘንድ፣ ምክክሮችን በምልዓተ ጉባዔ (ጠቅላላ ስብሰባዎች) በርዕሰ ጉዳይ ወይም በሥራ ቡድኖች ውይይት መካከል በመከፋፈል ያከናውናሉ። በምልዓተ ጉባዔ ደረጃ የሚደረጉ ውይይቶች በአብዛኛው በጠቅላላ አገራዊ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ፣ ፈርጀ ብዙ መልክና ተዋንያን ያሉባቸው፣ ወጥ የአጀንዳ ማዕቀፍ ያልተበጀላቸው፣ ከበርካታ የጉዳይ ስብስቦች መካከል ጥቅል ሐሳብ ለማደራጀት ጥቅም ላይ የሚውሉ ሲሆን፣ በሌላ በኩል በሥራ ቡድኖች (Working Groups) የሚደረጉ ምክክሮች ደግሞ የተመረጠ ውስን ርዕሰ ጉዳይ ላይ ተመሥርተው፣ በየፈርጃቸው የጥናትና ምርምር ጽሑፎች እየቀረበባቸው፣ ተገቢው የንቃተ ህሊና ማዳበሪያ ሥልጠና እየተሰጠ፣ የባለሙያ ምክርና አስተያየት በአስረጅነት እየቀረበ የሚከናወኑ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ለሥራ ቡድኖች ተለይተው የሚሰጡ የውይይት ርዕሰ ጉዳዮች በማዕቀፍ እየተቀመጡ ለፖለቲካው ልሂቃን የድርድር፣ የምክክር፣ የስምምነትና የመግባባት አጀንዳዎች የሚቀመርባቸው ናቸው፡፡ በአንፃሩ ምልዓተ ጉባዔዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎችን የሚያካትቱና በርካታ የተሰባጠሩ የውይይት አጀንዳዎች የሚነሳባቸው ሊሆኑ ስለሚችሉ፣ ሐሳቦችን ለማሰባሰብና የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ አዳጋች ያደርጋቸዋል፡፡ ስለሆነም ከምልዓተ ጉባዔ ተሳታፊዎች ከተሰበሰቡ አስተያየቶችና አጀንዳዎች ላይ በመነሳት የውይይት ምክረ ሐሳቦችን ማዘጋጀት፣ የአሠራር ሥርዓትና ደንቦችን መቅረፅና የውሳኔ ሐሳቦችን ማርቀቅ በሥራ ቡድኖች ውስጥ ይከናወናል፡፡ በዚህ ረገድ ካየነው የአብዛኛዎቹ የአገር አቀፍ የፖለቲካ ውይይቶች ተጨባጭ ሥራዎች የሚከናወኑት በሥራ ቡድኖች ውስጥ ነው። ስለሆነም ከታች በተጠቀሱት ጉዳዮች ላይ በመመሥረት የሥራ ቡድኖች ስብጥር፣ አደረጃጀትና ተልዕኮዎች፣ ወዘተ በጥንቃቄ መነደፍ አለባቸው። የሥራ ቡድኖች በውይይቱ ሒደት ወይም መባቻ የሚያቀርቡት ምክረ ሐሳብና የትግበራ ዕቅድ፣ በውይይቱ በሚሳተፉ ሁሉም የምርጫ ክልሎችና ተወካዮቻቸው ምሉዕ ይሁንታና ተቀባይነት ወይም የአብላጫ ስምምነት እንዲያገኝ ሚዛናዊ ውክልና ሊኖራቸው ይገባል፡፡ እያንዳንዳቸው ጭብጥ ተኮር (Theme Oriented) የሥራ ቡድኖች የተሰፈሩላቸውን ተግባራት በቅልጥፍናና በልህቀት፣ እንዲሁም በውጤታማነት እንዲያከናውኑ ለማድረግ ግልጽ የአሠራር ሥርዓት፣ የውሳኔ አሰጣጥ መርህ፣ በተጨማሪም የትግበራ መመርያና ደንቦች ሊኖራቸው ይገባል። የምልዓተ ጉባዔውንና የሥራ ቡድኖችን ግንኙነትና ተመጋጋቢነት በሚገባ የሚዘረዝሩ ግልጽ ሕጎችና ደንቦች መኖራቸው ለውጤቱ እጅግ ጠቃሚ ይሆናል።

በተለያዩ የሥራ ቡድኖች መካከል መደበኛ ትስስር የሚፈጥር ቅርፀ ብዙ የግንኙነት መስመርን የሚያመቻች፣ እንዲሁም አብዛኛዎቹ የውይይቱ ተሳታፊዎች በሁሉም የሥራ ቡድኖች ውስጥ ያሉ ለውጦችንና ዕርምጃዎችን በቅርበት እንዲያውቁ የሚያስችል አካል (ኮሚሽነር) መኖር እጅግ ጠቃሚ ነው።

በተለያዩ የሥራ ቡድኖች ውስጥ ያሉ ለውጦችን እየተከታተለ የሚመዘግብና የሚቆጣጠር፣ እንዲሁም የውይይት ሒደቱን ትስስር የሚያረጋግጥ የግንኙነት ሥነ ዘዴ (Communication System) መኖር እጅግ ጠቃሚ ይሆናል። የሥራ ቡድን አባላቱ በመካከላቸው የሚፈጠሩ የሐሳብና የአካሄድ አለመግባባቶችን በሁሉ አሸናፊነት እንዲቋጩና ከስምምነት ላይ እንዲደርሱ የሚያግዙ የቅርቃር ወይም የግጭት አፈታት ዘዴዎች ሊኖራቸው ይገባል። ለጥቂት ጊዜ (ለምሳሌ ወራት) የሚቆዩ አገራዊ የፖለቲካ ውይይቶች በምልዓተ ጉባዔ ደረጃ በየተወሰኑ ወቅቶች ለጥቂት ጊዜያት የሚገናኙ ሲሆን፣ በአንፃሩ የሥራ ቡድኖቻቸው ደግሞ ለበርካታ ጊዜያት በየዕለቱ አልያም በየሳምንቱ ተገናኝተው በየአጀንዳው መሥራት ሲኖርባቸው፣ አለፍ ሲልም ከአጭር ዕረፍት በኋላ እየተሰበሰቡ መሥራት ይችላሉ። በአጠቃላይ ሲታይ የአገራዊ ምክክሮች አደራጅ ተቋማት ያለ ማሰለስ በተከታታይ እየተገናኙ በትጋት መሥራት ይጠበቅባቸዋል።

ራዊ የፖለቲካ ውይይቶች ምን ዓይነት የውሳኔ አሰጣጥ ደንቦችን ይቀበላሉ?

አገራዊ የፖለቲካ ውይይቶች ውሳኔ የሚሰጡባቸው፣ ምክረ ሐሳብ የሚያቀርቡባቸውና ዕርምጃ የሚወስዱባቸው ደንቦችና የአሠራር አካሄዶችን በተመለከተ ውይይቱ ከመጀመሩ አስቀድሞ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በአቻነት በዝርዝር መደራደርና ስምምነት ላይ መድረስ ይኖርባቸዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎችና አዘጋጅ አካላት የውሳኔ አሰጣጥ ሕጎችን በሚነድፉበት ጊዜ፣ ለሚከተሉት ጥያቄዎች ተገቢውን መልስ ማስገኘት አለባቸው::

 በአገራዊ የፖለቲካ ውይይቱ ለተነሱ ጉዳዮች ውሳኔዎች የሚተላለፉት በተሳታፊዎች ስምምነት ወይስ በተደነገገ የአብላጫ ድምፅ አሰጣጥ ሥርዓት?

  የድምፅ መስጠት የውሳኔ ሥርዓት ጥቅም ላይ ከዋለ ውሳኔው የሚያልፈው በከፍተኛ ድምፅ ብልጫ ወይስ በቀላል ልዩነት የድምፅ ብልጫ ላይ ተመሥርቶ ይሆናል? በውይይቱ ላይ ለተነሱት ርዕሰ ጉዳዮች ሁሉ ተመሳሳይ የውሳኔ አሰጣጥ ሒደቶች ተፈጻሚ ይሆናሉ? ወይስ የውይይቱ ተሳታፊዎች በሥራ ቡድን ከተከፋፈሉ እነዚህ የሥራ ቡድኖች ከውይይቱ ምልዓተ ጉባዔ ጋር አንድ ዓይነት የውሳኔ አሰጣጥ አካሄድ ሥርዓት ይኖራቸዋል? ወይስ ሌላ አማራጭ ይከተላሉ? ምልዓተ ጉባዔው የሥራ ቡድኖቹ አርቅቀው ያቀረቧቸውን ምክረ ሐሳቦች በቀላሉ የመቀበል ወይም ውድቅ የማድረግ ኃላፊነት ይኖረዋል? ወይስ ምልዓተ ጉባዔው በተራው እነዚህን ዕቅደ ሐሳቦች ያስተካክላል? ያርማል ወይስ ቅልቅል ዘዴን ይከተላል? እንደሚታወቀው የአገራዊ የፖለቲካ ውይይቶች ዋነኛ ዓላማ በመሠረታዊና አንገብጋቢ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ኅብረተሰብ አቀፍ ውይይት ማከናወንና በእዚሁ ላይ ተመሥርቶ መጠነ ሰፊ አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ያለመ እስከሆነ ድረስ፣ የውሳኔ አሰጣጥ ሕጎችና አሠራሮች አብዛኛውን ጊዜ በመግባባት ላይ ያተኮሩ ወይም በስምምነት መሆን አለባቸው።

በሌላ በኩል ደግሞ እንደ እኛ አገር ባሉ ሥር የሰደዱ የሥርዓተ መንግሥት ቁርሾዎች፣ ያልተቋጩ የዘመናት የታሪክ አጀንዳዎችና የልሂቃን የተለጠጡ የፖለቲካ ፍላጎቶች ባሉበት ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ መግባባት ላይ ለመድረስ እጅግ አስቸጋሪ ከመሆኑ አንፃር፣ አወያይ አካላት አብዛኛውን ጊዜ የውይይቱ አካሄድ የሥነ ሥርዓት ሕጎች ለተሳታፊዎቹ በድርድር ላይ ተመሥርተው ስምምነቶች ላይ እንዲደርሱ (ለመስማማት እንዲደራደሩ) የሚያግዝ የቅርቃር መፍቻ ሥነ ዘዴ (Deadlock Breaking Mechanism – DBM) አስቀድመው ያዘጋጃሉ፡፡ በመሆኑም እንዲህ ዓይነቱ የአሠራር ሥነ ዘዴ በሥራ ቡድኖች፣ በተሳታፊዎችና ከሕዝቡ በተወከሉ የምርጫ ክልሎች መሪዎች መካከል ስምምነት ላይ መድረሱን ለማረጋገጥ እንዲረዳ በየውይይቱ መካከል ድርድር የሚደረግበትን አግባብ ያመቻቻል፡፡

ለአገር አቀፍ የፖለቲካ ውይይቶች ዝግጅት ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያደርገው ማነው?

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መጠነ ስፋት፣ ከሚነሱ አጀንዳዎች ብዛትና ስሱነት፣ ከልሂቃን ጠንካራ የፖለቲካ ሥልጣን መሻትና የጥቅም ግጭቶች ከውጭ ኃይሎች ግዙፍ ተፅዕኖ፣ ወዘተ. የተነሳ የአገር አቀፍ የፖለቲካ ውይይቶች ዝግጅት በከፍተኛ ደረጃ ፖለቲካዊና እጅግ አከራካሪ ሒደት ነው። በዚህም ‹‹ለውይይቱ ዝግጅት ማን ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል?›› የሚለው ጥያቄ እጅግ አከራካሪ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ በውይይቱ ሕጋዊነትና የሕዝብ ቅቡልነት ላይ አዎንታዊና አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል፡፡ ብዙውን ጊዜ የዝግጅት ሒደት ተሳታፊዎችን በተመለከተ ሦስት ከግምት የሚገቡ ሐሳቦች አሉ፡፡

 1. 1. በአገር አቀፍ የፖለቲካ ውይይት የዝግጅት ሒደት ላይ የሁሉም ቁልፍ የምርጫ ክልል አመራሮችና ሀቀኛ ወኪሎችና ተሳታፊዎች የነቃ ተሳትፎና ድጋፍ መኖር እጅግ ጠቃሚ ነው። በዝግጅቱ ሒደት ከሁሉም ከፍተኛ መንግሥታዊ አካላት፣ ሀቀኛ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ልሂቃን በከፍተኛ ደረጃ ድጋፍ ማግኘት በዝግጅት ሒደቱ የሚተላለፉ ውሳኔዎችም ሆነ በቀጣይ ርከኖች የሚሰጡ ምክረ ሐሳቦች በሚገባ መሬት ወርደው ተግባራዊ እንደሚሆኑ ዓይነተኛ ማረጋገጫ ይሆናል፡፡
 2. 2. በመርህ ደረጃ ሁሉም አጀንዳው የሚመለከታቸው የምርጫ ክልሎችና ሀቀኛ ወኪሎቻቸው በአገር አቀፍ የፖለቲካ ውይይት ዝግጅት ሒደት ላይ መሳተፍ አለባቸው። ይህም አብዛኞቹ የምርጫ ክልሎችና ተሳታፊዎች የተወሰዱ ዕርምጃዎችና የተላለፉ ውሳኔዎች ሕጋዊና ቅቡልነት ያላቸው እንደሆኑ እንዲገነዘቡ ያደርጋል።
 3. ከአዘጋጆቹ በተጨማሪ ሌሎች በዘርፉ ልምድና ተሞክሮ ያላቸውን ባለሙያዎች ማካተት ያስፈልጋል፡፡ በየዝግጅት ሒደቶች ምዕራፍ ከአዘጋጅ አካላቱ ዘንድ በብቃት የማይገኙ የቴክኒካልና የባለሙያዎች ድጋፍ ማደራጀት ተጠቃሚ ይሆናል፡፡

ስተራዊና የሎጂስቲክስ ዕቅድ

አገር አቀፍ የፖለቲካ ውይይቶች ከአጀንዳዎች ስብጥር፣ ከተሳታፊዎች ብዝኃነት፣ ከሚወስዱት ሰፊ የጊዜ ምጣኔ፣ ከሚሹት ክህሎትና ሌሎች ታሳቢዎች የተነሳ በውስብስብ ሁነቶች የታጀቡና ፈርጀ ብዙ ክስተቶች የሚያስተናግዱ ሒደቶች ናቸው፡፡ ስለሆነም በዝርዝር የተቀመጡ አስተዳደራዊ ዝግጅቶችንና የሎጂስቲክ ዕቅድን በጥንቃቄ ማቀናጀትን ይጠይቃሉ፡፡ ይህም ውይይቱ በሚገባው የአመራር ብቃትና ትግበራ የማስተናገድ ብቃትን ይፈጥራል፡፡ እነዚህም የዕቅድ ዝግጅቶችና የመርሐ ግብር መንደፍ ሥራዎች በራሳቸው እጅግ አከራካሪና ፖለቲካዊ ውዝግብ የሚያስነሱ ሊሆኑ ይችላሉ።

ቀለል ካለ ምሳሌ ብንነሳ እንኳ አገር አቀፍ የፖለቲካ ውይይቱ የሚካሄድበት ቦታና አዳራሽ መምረጥ በራሱ ተለምዷዊ የሎጂስቲክስ ሥራ ብቻ ሳይሆን ከሚኖረው የፋይናንስ፣ የደኅንነትና ተምሳሌታዊ (Symbolic) ጉዳዮች የተነሳ ፖለቲካዊ ይዘት ሊኖረው ይችላል። ሌላው በውይይቱ ላይ የሚሳተፉ የምርጫ ክልሎችና ተወካዮቻቸው በውይይቱ አዘጋጅ አካል መዋቅሮች ላይ የበኩላቸውን ተፅዕኖ ማሳደር ስለሚፈልጉ፣ ለአገራዊ የፖለቲካ ውይይት አዘጋጅ አካል አስተዳደራዊና የባለሙያዎች ድጋፍ ሰጪ መዋቅሮችን ማቋቋም በራሱ ፖለቲካዊ ጥያቄ የሚያስነሳ አወዛጋቢ ተግባር ሊሆን ይችላል፡፡ ስለሆነም የአስተዳደር ዕቅድና የሎጂስቲክስ አወቃቀሩ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ሊከናወን የሚገባው ሲሆን፣ ከተቻለም የውይይት መድረኩን ፖለቲካዊ ፈርጅ በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መድረክ ቢዘጋጅ ይመረጣል።

ራዊ የፖለቲካ ውይይቶች ጽሕፈት ቤት ድጋፍ ምን መምሰል አለበት?

አገር አቀፍ የፖለቲካ ውይይት ሒደቶች እጅግ መጠነ ሰፊ የአስተዳደር፣ የሎጂስቲክስና የባለሙያዎች ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። ይህ ድጋፍ የሚከተሉትን ቦታዎች ይሸፍናል፡፡

ሎጂስቲክስ ጉዳዮች፡- የተሳታፊዎች መጓጓዣና ማረፊያ፣ የውይይት ቦታዎች መረጣ፣ የአዳራሽ አገልግሎትና የደኅንነት ሁኔታ፣ ወዘተ. ናቸው፡፡

የጽሕፈት ጉዳዮች፡- ቃለ ጉባዔ አያያዝ፣ የዜና መግለጫዎች ጽሑፍ፣ ማስታወሻዎችን መውሰድ፣ በውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የመረጃ ልውውጥ፣ የሰነድ አያያዝና አስተዳደር፣ የማኅደር አቀማመጥ፣ ወዘተ. ላይ ያተኮሩ ናቸው።

ባለሙያ ድጋፍ፡- በቴክኒካዊና ወሳኝ ተጨባጭ ጉዳዮች ላይ በባለሙያዎች የሚቀርቡ ምክሮችና ገለጻ፣ በጥናትና ምርምር ሰነዶች የማቅረብ ሥራ ወይም በሴሚናሮች መልክ በማቅረብ፣ እንዲሁም ከየቴክኒክ ቡድኑ ደጋፊ ባለሙያ ምክርና ርዕስ ተኮር ሥልጠና በመስጠት ናቸው፡፡

የሚዲያ ግንኙነትና የሕዝብ ተደራሽነት፡- የውይይቱ ቀረፃዎችን ለመገናኛ ብዙኃን ማቅረብ፣ ድረ ገጽን ማስተዳደር፣ ለሕዝብ የሚደርሱ የመረጃ ዘመቻዎችን ማደራጀት፣ በመላ አገሪቱ የመረጃ ማሠራጫ ነጥቦችን ማዘጋጀት፣ በቴሌቪዥን ላይ ውይይቶችና ክርክሮችን ማዘጋጀት፣ ወዘተ. ናቸው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የውይይቱ አዘጋጅ ጽሕፈት ቤት የሚደራጀውና በሙሉ አቅም የሚቋቋመው የፖለቲካ ውይይቱ ከመጀመሩ በፊት ነው።

ሕዝብ ግንዛቤና ተሳትፎ ማበረታታት

አገራዊ የፖለቲካ ውይይቶች በሚዘጋጁበት ወቅት ስለሚደረጉ ምክክሮች መላው ኅብረተሰብ በሚገባ ሲያውቅ፣ ውይይቱ እምነት የሚጣልበትና የበለጠ ተቀባይነት ያለው ይሆናል። በዚህ መሰል ሁነቶች ወቅት ግልጽነትና በቂ የመረጃ ልውውጥ መኖር የውይይት ሒደቱን ትክክለኛነትና ቅቡልነት ያጠናክራል፡፡ በመሆኑም የሕዝብ መረጃ ማሠራጫና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስትራቴጂ ሲነደፍ፣ መረጃው በተቻለ መጠን ሰፊው የኅብረተሰብ ክፍል ዘንድ በቀጥታና በቀላል ተደራሽ አቀራረብ መድረሱን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ ያህል በአንድ አገር ውስጥ ያለው ያልተማረ የኅብረተሰብ ክፍል በቁጥር ከፍተኛ ከሆነ፣ መረጃዎችን በተቻለ መጠን ለእዚህ ማንበብና መጻፍ ለማይችለው ሰፊው ሕዝብ በሚያደርስ የሚዲያ ዘዴ ማሠራጨት ያስፈልጋል። በተመሳሳይ ሁኔታ በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች የተወሰኑ የመረጃ ማሠራጫ ሚዲያዎች የማይገኙ ከሆነ ተገቢውን ሚዲያ በመለየት መጠቀም ያስፈልጋል። በአንዳንድ አካባቢዎችም የማኅበረሰቡን ወግና ልማድ በማጥናት (ለምሳሌ እንደ አፋር ዳጉ ዘዴ) በባህሉ መሠረት መረጃ ማሠራጨትና የሕዝቡን ንቃተ ህሊና ማዳበር ይገባል፡፡

በተጨማሪም ሕዝቡ በአገራዊ የፖለቲካ ውይይቱ አንዳንድ ምክክሮች ላይ በቀጥታ ሊሳተፍ ይችላል። ይህም በትልልቅ የከተማ አዳራሽ ውስጥ በሚደረጉ ጉባዔዎች ወይም ከተወሰኑ የምርጫ ክልሎች ከተወከሉ ተሳታፊዎች ጋር በሚደረጉ በትንንሽ ስብሰባዎች ሊከናወን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ በሲቪል ማኅበረሰብና በሌሎች ወካይ ቡድኖች አማካይነት አጀንዳዎችን በማቅረብና ምክረ ሐሳቦችን ወደ ውይይቱ ማቅረብን ሊያካትት ይችላል። በጥቅሉ አገራዊ የፖለቲካ ውይይቶች የተለያዩ የሕዝብ መረጃዎችንና የተሳትፎ ተግባራትን በሚያከናውንና ውይይቱን በሚደግፍ ጽሕፈት ቤት ውስጥ ከሚገኝ ጠንካራ አካል ጋር ተባብረው ቢሠሩ እጅግ ይጠቀማሉ። አመሠግናለሁ!!!!!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል [email protected] አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...