Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የሸማቹን መብት ለማስጠበቅ የተቋቋሙት ተቋማት የት አሉ?

ተደጋግሞ እንደሚነገረውና በተጨባጭ እንደምናየውም የአገራችን የግብይት ሥርዓት መረን የለቀቀ ነው፡፡ አልዘመነም፡፡ በሥነ ምግባር የሚመራም አይደለም፡፡ ኢኮኖሚውን ያገናዘበ የትርፍ ሥሌት የለም፡፡ በዘፈቀደ የሚፈጸም ግብይት ይበዛዋል፡፡  የግብይት ሰንሰለቱ የበዛና የተንዛዛ ነው፡፡ የደላሎች ጡንቻ ፈርጥሞ የሚታይበትም ነው፡፡ ለሸማቹ የሚቀርቡ በርካታ ምርቶች በትክክለኛ ዋጋቸው እንዲሸጡ የሚያስችል አሠራር የለም፡፡ የገበያ ዋጋ በደላሎች የሚዘወር በመሆኑ ለአጠቃላይ የግብይት ሥርዓቱ መበላሸት እንደ ዋና ምክንያት እየተጠቀሰ ነው፡፡ በሸማቾችና በንግድ ኅብረተሰቡ መካከል የአገልጋይና ተገልጋይ መንፈስ አልሰፈነም፡፡ ‹‹ደንበኛ ንጉሥ ነው›› የሚባለው በጥቅስ ብቻ ሆኖ ቀርቷል፡፡

በአብዛኛው ተጠያቂነት የሌለበትም በመሆኑ የአገራችን የግብይት ሥርዓት ቅርፅ አልባ የሚሆንበት አጋጣሚ የበዛ ነው፡፡ ይህ ሥር የሰደደ ችግር ትክክለኛውን የንግድ ትርጓሜ አዛብቶታል፡፡ በስመ ነፃ ገበያ የሚፈጸሙ ሸፍጦችን ስናክልበት ደግሞ በአግባቡ ነግዶ ሸማቹን እንደ ደንበኛ አክብሮ የሚያስተናግድ ነጋዴ ለማግኘት ከባድ እየሆነ መጥቷል ማለት ይቻላል፡፡  

የትርፍ ህዳጉን መጥኖ ሸማቾችን አስቦ የሚሠራ ጨዋ ነጋዴ ባይጠፋም ብዙው ግን ባገኘው አጋጣሚ ስንጥቅ ትርፍ አትርፎ በአጭሩ ለመክበር የሚታትር ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ የሚታዩ ህፀፆች የበዙ ስለመሆናቸው ሌላም ማሳያ አለ፡፡ ደረጃቸውን ያልጠበቁ ምርቶች ለገበያ ማቅረብ፣ ጊዜው ያለፈባቸውን ምርቶች ያለኃፍረት ሼልፍ ላይ ደርድሮ መሸጥ፣ የተለያዩ ምርቶችን ከባዕድ ነገሮች ጋር ቀላቅሎ መሸጥና የመሳሰሉትን መጥቀስ እንችላለን፡፡

የልኬት መሣሪያዎችን በማዛባት የሚፈጸሙ ሸፍጦች፣ ተቧድኖ ምርትን በመሸሸግ ገበያ ላይ እጥረት መፍጠርና መሰል ክፋት የተጣባቸው ተግባራቶች በየዕለቱ በግብይት ሥርዓታችን ውስጥ የሚታዩ ናቸው፡፡

በእነዚሁና በሌሎች ፀያፍ ተግባራት ሸማቾች የሚገጥማቸው ችግሮች ብዙ ናቸው፡፡ ከወቅታዊ ሁኔታ አንፃር ካየነውም ለአገራችን የዋጋ ግሽበት መንስዔ ከሆኑ በርካታ ምክንያቶች መካከል በመጀመርያዎቹ ረድፍ ማስቀመጥ የምንችለው ይህንኑ ብልሹ የግብይት ሥርዓት ነው፡፡

ችግሩ በየትኛውም የንግድና የአገልግሎት ዘርፎች ላይ የሚታይ ነው፡፡ ነገር ግን የችግሩን ግዝፈት ለማስተካከልና በሥነ ምግባር የሚመራ የግብይት ሥርዓት ለመፍጠር ይኼ ነው የሚባል ሥራ እየተሠራ አይደለም፡፡ በግብይት ሥርዓቱ ብልሽት በሸማቹ ላይ እየደረሱ ያሉ የከፉ ጥቃቶችን የሚከላከል ስለሌላ ችግሩ እየሠፋ መጥቷል፡፡ የሸማቹን መብት ለማስጠበቅ የተቋቋሙ ተቋማትም ቢሆኑ ያሉ ግን የሌሉ ሆነዋል፡፡  

አገሪቱ ይብዛም ይነስም የሸማቾችን መብት ያስጠብቃሉ የተባሉ ሕጎች ያሉ ቢሆንም ይህንን የሚያስፈጽም አካል የለም፡፡ ሕጎቹን ያስፈጽማሉ የተባሉ ተቋማት ዛሬ ላይ ስለመኖራቸው እርግጠኛ የማንሆንበት ምክንያት የሸማቹን ሮሮ ሰምተው መፍትሔ ባለማበጀታቸው ነው፡፡ ቢንያስ በደሉን ሊያስተጋቡለት ሲገባ ድምፃቸውን በማጥፋታቸው ጭምር ነው የምንወቅሳቸው፡፡  

ቢኖሩማ ዛሬ የግብይት ሥርዓቱ ብልሽት የወለዳቸው ያልተገቡ የዋጋ ጭማሪዎች በአደባባይ ሲታዩ የሸማቾችን መብት ለማስጠበቅ ይወጡ ነበር፡፡ ስለዚህ ሸማቹ ድረሱልኝ እያለ ድምፃቸው የማይሰማ የሸማች ተቆርቋሪዎች እንዴት አሉ ሊባል ይችላል? ለሸማች ጥበቃ መብት እንዲሟገቱ በመንግሥት ደረጃ የተቋቋማትስ ተቋማት የታሉ? ድምፃቸውን ሳንሰማ ምን ያህል ሸማቹን እንደታደጉ የሚነግሩን መቼ ነው? የሚገርመው ግን እነዚህ ተቋማት ግብራቸውን ሳናውቅ ዛሬም በየዓመቱ በጀት ይያዝላቸዋል፡፡ ሠራተኞቻችሁ ምንዳ ይቆረጥላችኋል፡፡ ለከርሞም የሚፈልጉትን በጀት ይጠይቃሉ፡፡

በአጠቃላይ ለሸማቾች ራስ ምታት ለአገራዊ ኢኮኖሚ አደገኛ የሆነውን የግብይት ሥርዓት ብልሽት ግን አንዳንድ ወገን ብቻ ተወቃሽ የምናደርግበት አይደለም፡፡ መንግሥት፣ የንግድ ኅብረተሰቡ፣ ሸማቹና የተለያዩ ተቋማት ጭምር በየደረጃው ለችግሩ መባባስ የየራሳቸው ድርሻ ይወስዳሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ብዙ ተቋማትን ልንጠቅስ እንችላን፡፡ ሁሌም የሚገርሙኝ ግን በየደረጃው የተቋቋሙና የንግድ ኅብረተሰቡን ይዋክላሉ የተባሉት ንግድ ምክር ቤቶች የአገሪቱን የግብይት ሥርዓት ለማከም አንድም ጊዜ ድምፃቸው አለመሰማቱ ነው፡፡ የንግድ ኅብረተሰቡ በሥርዓትና በምግባር እንዲሠራ ለአፋቸው እንኳን ተናግረው አያውቁም፡፡ በተለይ በዚህ ወቅት ገበያን ለማረጋጋት የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ ቢሆንም እንደ አንድ የንግድ ኅብረተሰብ ወኪልነታቸው እኛስ ምን እናድርግ? አላሉም፡፡ ሕጋዊ የግብይት ሥርዓት እንዲኖር በተቋም ደረጃ ብዙ መሥራት አለባቸው ከሚባሉ ተቋማት መካከል እነዚህ ንግድ ምክር ቤቶች ቢሆኑም እነሱ ሌላ ሥራ ላይ ናቸው፡፡ ስለዚህ የግብይት ሥርዓቱ ብልሽት ደረጃው ይለያይ እንጂ ብዙዎችን የሚመለከት ነው፡፡ የሸማቹም እጅ አለበት፡፡

ሸማቹንም ይመለከታል ስንል ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የሌለው የዋጋ ጭማሪ ሲያጋጥመው አልገዛም ሲል አይታይም፡፡ መብቱን ለማስጠበቅ ልምምድ የለውም፡፡ ጭራሽ ተወደደ የተባለ ዕቃ ሊጠፋ ነው ብሎ ዕቃውን በማግበስበስ ገበያው የበለጠ እንዲጦዝ ሲያደርግ በተደጋጋሚ ተመልክተናል፡፡ እንደ ሸማችም የግብይት ባህላችን የተበላሸ በመሆኑ ችግሩ የሁሉም ነው እንድንል ያስደፍረናል፡፡ አጠቃላይ የግብይት ሥርዓቱ ፈር እንዲይዝ ግን ብልጫ ያለው ኃላፊነት በመንግሥት እጅ ነውና ዘመናዊ የግብይት ሥርዓትና በሥነ ምግባር የሚመራ የንግድ ኅብረተሰብ እንዲኖረን ጠበቅ ያለ ሕግ ማውጣትና ይህንንም መተግበር ነበረበት መቆጣጠር ነበረበት፡፡ ነገር ግን ይህንን ለማድረግ የሚያስችል አቅም ያለው ቢሆንም እየሠራበት አይደለም፡፡ አንዳንዴ በዘመቻ መልክ የሚያካሂደውም አንዳንድ የቁጥጥር ሥራዎች ለሌብነት በር ከፍቶ አቅሙ ሲብረከረክ ይታያል፡፡ ስለዚህ እየገፋ የመጣውን ችግር ለመቅረፍ ሥር ነቀል ለውጥ የሚያሻ ይሆናል፡፡ ካልሆነ ግን ግብይቱ የበለጠ ይበላሻል፡፡ በአጠቃላይ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ያሉ ተዋንያኖች የሚገዙበትን ሕግ ካልተገበርንና ሁሉም ያገባኛል በሚል መንፈስ ለግብይት ሥርዓቱ ጤናማነት ተግቶ ካልሠራ ከዚህ በኋላ የሚጠብቀን አሁን እየገጠመን ካለው ችግር በላይ የከፋ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ጤናማ የግብይት ሥርዓት ለመፍጠር ሁሉም የበኩሉን ያድርግ፣ በተለይ መንግሥት ገዥ ሕግ ይኑረው፡፡  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት