Thursday, June 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትበዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የሚካፈሉ አትሌቶች አመራረጥ ቅሬታ አስነሳ

በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የሚካፈሉ አትሌቶች አመራረጥ ቅሬታ አስነሳ

ቀን:

የማራቶን አትሌቶች ቅሬታቸውን ለፌዴሬሽን አቅርበዋል

በአሜሪካ ኦሪገን ሂውጂን ከተማ ለሚከናወነው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና  በማራቶን የሚወዳደሩ 10 አትሌቶችን ስም ዝርዝር ይፋ ያደረገው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ቅሬታ ቀርቦበታል፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ እንዳስታወቀው፣ ከሁለቱ ጾታዎች አምስት፣ አምስት አትሌቶችን የመረጠው፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ ዓለም አቀፍ የጎዳና ውድድሮች ላይ ተካፍለው የተሻለ ሰዓት ያስመዘገቡትን በመመልከት ነው፡፡

 ምርጫውን ተከትሎም አትሌቶችና አሠልጣኞች ቅሬታቸውን ለብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ማስገባታቸው ተናግረዋል፡፡

ፌዴሬሽኑ ከቀናት በፊት ከወንዶች ታምራት ቶላ፣ ሙስነት ገረመው፣ ልዑል ገብረሥላሴ፣ ሲሳይ ለማና ጫሉ ዴሶን መምረጡን ይፋ ሲያደርግ፣ በሴቶች እሸቴ በከሬ፣ አባበል የሻነህ፣ ጎይቶም ገብረሥላሴ፣ ደጊቱ አዝመራውና ሕይወት ገብረኪዳንን መርጦ ይፋ አድርጓል፡፡

ስማቸው የተዘርዘሩ አትሌቶች ደግሞ ከሰኞ ጀምሮ መደበኛ ልምምዳቸውን እንዲጀምሩ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጥሪ አድርጓል፡፡

አትሌቶችን የመምረጥ ኃላፊነት የተሰጠው የፌዴሬሽኑ ቴክኒክ ኮሚቴ አትሌቶች የተመረጡት በሁለት ዓመታት ውስጥ የተሳተፉበት ውድድር የማገገሚያ ጊዜና ወቅታዊ አቋም ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ የተከናወነ እንደሆነ ቢጠቅስም፣ በአሠልጣኞችና አትሌቶች ግን ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡

በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአምስትና አሥር ኪሎ ሜትር፣ እንዲሁም በግማሽ ማራቶን እና በማራቶን ውድድሮች የኢትዮጵያን ክብረ ወሰን የጨበጠችው የዓለም ዘርፍ የኋላ በምርጫ ውስጥ አለመካተቷ ከፍተኛ ክርክር አስነስቷል፡፡ አትሌቷ እ.ኤ.አ. 2019 ኢትዮጵያን ወክላ በሞሮኮ ራበት አፍሪካ ጨዋታ ላይ በመሳተፍ በግማሽ ማራቶን የውድድሩን ክብረ ወሰን ለመጀመርያ ጊዜ ከሰበረች በኋላ አዳዲስ ክብረ ወሰኖችን በእጇ መጨበጥ ችላለች፡፡

የዓለም ዘርፍ የአፍሪካ ጨዋታ ጀምሮ ኢትዮጵያን ወክላ እንዲሁም በግሏ ከ16 በላይ ውድድሮችን ማድረግ የቻለች ሲሆን፣ አምስት የግማሽ ማራቶን ውድድሮችን በበላይነት አጠናቃለች፡፡ በቅርቡ በስፔን በተደረገ የአሥር ኪሎ ሜትር ውድድር 29፡14 በመግባት የዓለም ክብረ ወሰንን በእጇ ማስገባት ችላለች፡፡

በጀርመን ሐምቡርግ በተደረገ የማራቶን ውድድር ላይ ተካፍላ 2፡17፡23 በማጠናቀቅ፣ የብሔራዊ እንዲሁም የቦታውን ክብረ ወሰን በእጇ ማስገባት መቻሏ ይታወሳል፡፡ በዚህም አትሌቷ በማራቶን አገሯን ለመወከል ዕድል ሊሰጣት ይገባል በማለት የሚከራከሩ በርካቶች ናቸው፡፡

የቴክኒክ ኮሚቴ ያስቀመጣቸው መመዘኛዎች ቢኖሩም፣ ቅድመ መመዘኛው ብሔራዊ ቡድኑን በሚፈይድ መልኩ እንዳልሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ሪፖርተር ምርጫውን ተከትሎ ባናገራቸው አሠልጣኞች አስተያየት ከሆነ፣ የዓለም ሻምፒዮና በተከናወነ የአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የለንደን ማራቶን መኖሩን ተከትሎ፣ አትሌቶች የማገገሚያ ጊዜ ስለማይኖራቸው፣ በዓለም ሻምፒዮናው ማራቶን ውድድር ላይ የሚኖራቸው ንቁ ተሳትፎ ከግምት ውስጥ የገባ አይደለም ሲሉ ሥጋታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡

እንደ አሠልጣኞቹ ሥሌት ከሆነ፣ የዓለም ሻምፒዮና ከሐምሌ 8 እስከ 17 ቀን 2014 ዓ.ም. የሚከናወን ሲሆን፣ በአንፃሩ ለንደን ማራቶን መስከረም 22 ቀን 2015 ዓ.ም. ይከናወናል፡፡ በዚህም አትሌቶቹ በቂ የማገገሚያ ጊዜ ስለማይኖራቸውና በርካታ አትሌቶች በለንደኑ ማራቶን ተሳታፊ ስለሚሆኑ፣ በሻምፒዮናው ላይ የሚኖራቸው ትኩረት የመቀነስ ዕድሉ ሰፊ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

ለዚህም በተለያዩ የዓለም አቀፍ ሻምፒዮናዎች ላይ ገና ውድድሩ ሳይጋመስ አቋርጠው የሚወጡ አትሌቶችን እንደ መነሻነት ያነሳሉ፡፡ በዚህም መሠረት ፌዴሬሽኑ ምርጫውን ሲያከናውን የአትሌቶችን የማገገሚያ ጊዜን ከግምት ውስጥ ያላስገባ እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡

ምርጫውን ተከትሎ ቅሬታቸውን ለፌዴሬሽኑ ያስገቡ አትሌቶች መኖራቸውን የሪፖርተር ምንጮች ሲያስረዱ በቅርቡ ምላሽ እንደተሰጣቸውና በምርጫው ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ አለመደረጉን እንዲሁም ሰኞ ግንቦት 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ሆቴል ገብተው ዝግጅታቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ መደረጉ ተናግረዋል፡፡

በዘንድሮ የዓለም ሻምፒዮና ኢትዮጵያን የሚወክሉ የ5 ሺሕና 10 ሺሕ ሜትር አትሌቶች ለመምረጥ ግንቦት 28 እና 29 ቀን 2014 ዓ.ም. በሄንግሎ የማጣሪያ ውድድር እንደሚደረግ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡

በሌሎች ርቀቶች ላይ የሚሳተፉ አትሌቶችም በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ እየተካፈሉ የሚገኙ መሆኑን ተከትሎ፣ በፌዴሬሽኑ የተለያዩ ድጋፎች እየተደረገላቸው ሲሆን፣ የዶፒንግ ምርመራና የቪዛ ሒደት እየተከናወነ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...

የባንክ ማቋቋሚያ መሥፈርት እንደሚጠነክር ሚኒስትሩ ተናገሩ

 ባንኮች ስለውህደት እንዲያስቡም መክረዋል በኢትዮጵያ ውስጥ ባንክ ለማቋቋም የሚያስፈልገው መሥፈርት...

ማን ይቻለን?

በጠዋት የተሳፈርንበት ታክሲ ውስጥ በተከፈተው ሬዲዮ፣ ‹‹ይኼኛው ተራራ ያን...