Monday, October 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹መንግሥት ካፒታል ገበያን በመጠቀም በጀቱን ለመደገፍ ቢጠቀም በጣም ንፁህ መንገድ ነው›› መለሰ ምናለ፣ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ከፍተኛ አማካሪ

ጠንካራ ኢኮኖሚ ያላቸው ያደጉ አገሮችም ሆነ በማደግ ላይ የሚገኙ አገሮች ለኢኮኖሚ ዕድገታቸው ቁልፍ የፋይናንስ ምንጭ የሆነው የካፒታል ገበያ (Stock Market) ወይም የገንዘብ ነክ ሰነዶች ገበያ እንደሆነ ይነገራል። ይህ የገበያ ሥርዓት በኢትዮጵያ እንዲቋቋም በርካታ የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ለረዥም ዓመታት ሲወተውቱ መቆየታቸው የሚታወስ ነው። በስተመጨረሻም ይህ ምክረ ሐሳብ ሰሚ አግኝቶ የዛሬ አንድ ዓመት ገደማ የገንዘብ ነክ ሰነዶች ገበያ በኢትዮጵያ እንዲቋቋም የሚያስችል የካፒታል ገበያ ማቋቋሚያ አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቋል።  አዋጁ ከፀደቀ በኋላም የአገሪቱን የካፒታል ገበያ ለማቋቋም የባለሙያዎች ቡድን ተመሥርቶ የዝግጅት ሥራዎችን በማድረግ ላይ ይገኛል። በቅርቡም የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያን በመሥራችነት ለማቋቋም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግና የእንግሊዝ መንግሥት ኩባንያ የሆነው FSD የመግባቢያ ስምምነት ፈርመዋል።  የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያን ለማቋቋም እየደረገ ያለውን የዝግጅት ሒደትና የቀጣይ ምዕራፍ ተግባራት እንዲሁም የገበያው መመሥረት የሚኖረውን ፋይዳ አስመልክቶ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያን ለማቋቋም የተደራጀው የባለሙያዎች ቡድን ሰብሳቢና የብሔራዊ ባንክ ገዥ የማክሮ ኢኮኖሚ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪ ከሆኑት አቶ መለስ ምናለ ጋር አሸናፊ እንዳለ ያደረገውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበንዋል።

ሪፖርተር፡- እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን የካፒታል ገበያ ለማቋቋም በዝግጅት ላይ ነው። የካፒታል ገበያውን የማቋቋሙ ሒደቱ በአሁኑ ወቅት በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

መለሰ ምናለ፡– በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያን ለማቋቋም ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወንን እንገኛለን። የካፒታል ገበያውን የሚቆጣጠረውን ባለሥልጣን ለመመሥረት የሚያስፈልገውን ተቋማዊ አደረጃጀትና ኃላፊነት የሚወስን የሕግ ማዕቀፍና የቁጥጥር ማዕቀፉን የተመለከተ የሕግ ማዕቀፍ ለማበጀት ሕጎችን እያረቀቅን ነው። በተጨማሪም የካፒታል ገበያውን ለመምራትና ገበያውን በብቃት ለማንቀሳቀስና ለመቆጣጠር የሚያስፈልገውን የሰው ኃይል ከወዲሁ ዝግጁ ለማድረግ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን እያከናወንን እንገኛለን። 

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያን ለማቋቋም የሚያስችል አንድ ስምምነት ከሰሞኑ ተፈርሟል። ስምምነትቱን የተፈራረሙት በቅርቡ የተመሠረተው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግና የብሪታኒያ መንግሥት ተቋም የሆነው FSD ናቸው። ይህንን ስምምነት በተመለከተ የሚነሳ አንድ ጥያቄ አለ ይኸውም የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያን የማቋቋም ኃላፊነት የተሰጠው ለማነው የሚለው ነው? በዚህ ላይ ምን ይላሉ? አያይዘውም የስምምነቱን ምንነትና ፋይዳ ቢገልጹልን?

መለሰ ምናለ፡- ጥሩ ጥያቄ ነው። ባለፈው ዓመት የካፒታል ገበያ ማቋቋሚያ አዋጅ ከፀደቀ በኋላ ብሔራዊ ባንክ የካፒታል ማርኬት ፕሮጀክት ትግበራ ቡድን አቋቁሟል። ይህ የፕሮጀክት ትግበራ ቡድኑ በዓለም አቀፍ ሕግ፣ በኢትዮጵያ ሕጎች እንዲሁም በማክሮ ኢኮኖሚና ከካፒታል ማርኬት ጋር የተገናኘ ዓለም አቀፍ ልምዶችን ያካበቱ ባለሙያዎች ይዞ በብሔራዊ ባንክ ውስጥ ራሱን የቻለ ቢሮ ተደራጅቶለት የኢትዮጵያ ካፒታል ማርኬትን ለማቋቋም ጠቃሚ የሆኑ ቅድመ ዝግጅቶችን ሲያከናውን ቆይቷል። ይህ የፕሮጀክት ትግበራ ቡድን ላለፉት ጊዜያት ሲያከናውናቸው ከነበሩ አበይት ጉዳዮች መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ካፒታል ማርኬትን የሚቆጣጠረውን ባለሥልጣን ለማቋቋም የሚያስፈልገውን የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት ነው። በዚህም የሚቋቋመውን ባለሥልጣን ተቋማዊ አደረጃጀት፣ ባለሥልጣኑን ለማቋቋም የሚያስፈልገውን ሀብት የተመለከቱ ረቂቆችን አዘጋጅተናል። የሚቋቋመው ባለሥልጣንን የሠራተኞች አስተዳደር የተመለከተ ረቂቅም አዘጋጅተናል። ከዚህም በተጨማሪ ሌሎች ባለሥልጣኑን ለማቋቋም ቁልፍ የሆኑ ጉዳዮችን የተመለከቱ የሕግ ማዕቀፎችን ረቂቅ አዘጋጅተናል። ይህንን ባለሥልጣን ለማቋቋም ቅድሚያ የተሰጠበት ምክንያት የኢትዮጵያ ካፒታል ማርኬትን የመመሥረት ኃላፊነት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተረክቦ ምሥረታውን የሚያከናውነው ይህ ተቋም በመሆኑ ነው። የፕሮጀክት ትግበራ ቡድኑ እያከናወነ የሚገኘው ሁለተኛው ጉዳይ በሚቋቋመው ካፒታል ማርኬት ላይ ባለሥልጣኑ የሚያደርገውን ቁጥጥር የተመለከተ የቁጥጥር ማዕቀፍ ማዘጋጀት ነው። ምክንያቱም አዋጅ ብቻውን የቁጥጥር ሥራን ለማከናወን በቂ አይደለም። አዋጁን የተሟላ የሚያደርጉ መመርያዎችና ደንቦች ያስፈልጋሉ። በመሆኑም እስካሁን ድረስ አሥር የሚሆኑ ደንቦችን እንዲሁም አሥራ አምስት የሚሆኑ መመርያዎችን አርቀቀናል። በእነዚህ ረቂቅ የሕግ ማዕቀፎች ላይ ግብአት ለመሰብሰብም የባለድርሻ አካላት ውይይት ማድረግ ጀምረናል። ከዚህ በተጨማሪም የተለያዩ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን እየሠራን ቆይተናል። የፕሮጀክት ትግበራ ቡድኑ ለቀጠራቸው ባለሙያዎች ከካፒታል ማርኬት ጋር የተገናኙ የተለያዩ ሥልጠናዎችን ስንሰጥ ቆይተናል። በፕሮጀክት ትግበራ ቡድኑ ለቀጠራቸው ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በካፒታል ማርኬት ዓውድ ውስጥ ተሳትፎ ለሚያደርጉ አካላት ሥልጠናዎችን እንዲሁም የውጭ የትምህርት ዕድሎችን በመስጠት እንዲሠለጥኑ አድርገናል አሁንም እያደረግን እንገኛለን። በተጨማሪም ከተለያዩ የልማት አጋሮችን በማነጋገር የካፒታል ማርኬት ሥልጠናዎችን፣ ከካፒታል ማርኬት ጋር የተገናኘ የጋዜጠኝነት ኮርስ የሚሰጥበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ጭምር ጥረት እያደረግን እንገኛለን። በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የካፒታል ማርኬት ባለፈው ዓመት በጸደቀው አዋጅ በሕግ ደረጃ ተቋቁሟል። ይህ ተቋም የገንዘብ ነክ ሰነዶች ግብይት አገልግሎትን የሚሰጥ ነው። በአዋጁ እንደተደነገገው ይህ ካፒታል ማርኬት በመንግሥትና የግል አጋርነት (Public Private Partnership) አግባብ የሚቋቋም ሲሆን፣ መንግሥት በዚህ ውስጥ ዝቅተኛ ድርሻ እስከ 25 በመቶ የሚሆን ድርሻ በመያዝ የሚቋቋም ይሆናል። የተቀረው 75 በመቶ ድርሻ ለግሉ ዘርፍ የሚተው ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ተቋም እንደመሆኑ መጠን መንግሥት በካፒታል ማርኬት ውስጥ የሚኖረውን ድርሻ ወክሎ አክሲዮን ሊይዝ አይችልም። ከዚህ አኳያ መንግሥት ወክሎ ባለድርሻ መሆን የሚችለው ትክክለኛ ተቋም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆሊዲንግ ነው። ይህንን ተቋም ያቋቋመው አዋጅም የመንግሥትን ሀብት የማስተዳደርና መንግሥትን ወክሎ በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ላይ መሳተፍ እንደሚችል ይደነግጋል። ቀደም ሲል እንደገለጽከውም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የኢትዮጵያ ካፒታል ማርኬትን ለመመሥረት የሚደረገውን ጥረት አንድ ዕርምጃ ወደፊት የሚወስድ እንቅስቃሴ ውስጥ ገብቷል። በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እና FSD Africa ወይም Financial Sector Deepening Africa የተባለው መቀመጫውን ኬንያ ካደረገው የእንግሊዝ ኩባንያ ጋር ስምምነት ተፈራርሟል። በሁለቱ መካከል በተደረገው ስምምነት FSD የኢትዮጵያ ካፒታል ማርኬትን ለመመሥረት የሚያስፈልገውን ዝግጅት የማከናወን ኃላፊነት የተሰጠው የፕሮጀክት ትግበራ ቡድን ወጪዎች ለመሸፈን ተስማምቷል። ይህ ማለት ግን የካፒታል ገበያውን ለመመሥረት እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል። በመሆኑም የፕሮጀክት ትግበራ ቡድኑ የኢትዮጵያ ካፒታል ማርኬትን ለማቋቋም የሚያስፈለገውን ሁሉንም ነገር የሚከውን ይሆናል ማለት ነው። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ካፒታል ማርኬት አክሲዮን ኩባንያ ሆኖ በንግድ ሚኒስቴር እንዲመዘገብ ማድረግ፣ ቢዝነስ ፕላኑን መቅረፅ፣ አክሲዮኖችን መሸጥ፣ ከሚቋቋመው የካፒታል ማርኬት ባለሥልጣን ፈቃድ ማውጣት፣ ለገበያው ጠቃሚ የሆኑ የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማቶችን ግዥ መፈጸምና መሰል ጉዳዮችን ማሟላት ናቸው። 

ሪፖርተር ፡- ትክክለኛውን የስቶክ ገበያ ሥነ ምኅዳር ለመፍጠር እንደ ኢንቨስትመንት አማካሪዎች ክሬዲት ኤጀንሲዎች (ደረጃ ሰጪ ኤጀንሲዎች) አገናኞችና ሌሎች መሰል ተቋማትን መፍጠር ያስፈልጋል። እነዚህ ደግሞ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሉም። አሁን ስኮላርሺፕ እያገኙ ያሉት ባለሙያዎች እንደዚህ ያሉ ኩባንያዎችን እንዲፈጥሩ ታስቦ ነው? 

መለሰ ምናለ፡- በትክክል። የካፒታል ገበያ በጣም የተወሳሰበ ሥነ ምኅዳር ነው። ከገበያው ጋር በቁርኝት የሚሠሩ የተለያዩ ቁልፍ ተቋማት ለምሳሌ አገናኞች (Intermediaries) የኢንቨስትመንት ባንኮች፣ የክሬዲት (ብድር) ደረጃ ሰጪ ኤጀንሲዎች፣ አዘዋዋሪዎች፣ ደላሎች፣ የገበያ ልውውጥ አቅራቢዎችና የመሳሰሉት ያስፈልጋሉ። እነዚህ ደግሞ የየራሳቸውን ክህሎትና ዕውቀትን ይጠይቃሉ። በአሁኑ ወቅት ይህንን ሊሠሩ የሚችሉ ባለሙያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ የሉም ምክንያቱም የካፒታል ገበያ ስለሌለን። በተጨማሪም የካፒታል ገበያን ስንመሠርት ራሱን የቻለ የሰው ኃይል ያስፈልጋል። ችሎታን በተመለከተ ደግሞ ወደፊት ራሳችንን መቻል አለብን።

እስካሁን ከ600 በላይ ባለሙያዎችን አሠልጥነናል። ያስቀመጥነውን መሠረታዊ የክህሎት ደረጃ ያሟሉ በመረጡት የአገልግሎት ዘርፍ የተሻለ ሥልጠና እንዲያገኙ እያደረግን ነው። የሚቋቋመው የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ደግሞ ለካፒታል ገበያው አገልግሎት ሰጪዎች የራሱ የሆኑ አነስተኛ የብቃት መመዘኛ ደረጃን የሚያወጣ ይሆናል። ለምሳሌ ፈንድ አስተዳዳሪዎች የተራቀቀ ክህሎት ያስፈልጋቸዋል፣ በገበያው የሚሳተፉ ደላሎች (Brokers) ግን መሠረታዊ መመዘኛዎችን ብቻ አሟልተው ሊሳተፉ ይችላሉ። አስፈላጊው ብቃት ያለው የሰው ኃይል በአገር ውስጥ እስኪፈጠር ድረስ እንደ ኬንያ ያሉ የውጭ አገር ባለሙያዎች መጥተው እነዚያን አገልግሎቶች ሊሰጡ ይችላሉ። በእነዚህ አገልግሎቶች ሥልጠና የወሰዱና የተመሰከረላቸው የአገር ውስጥ ባለሙያዎች ደግሞ ከውጭ ባለሙያዎች ጋር በመሥራት በመጨረሻም የውጭ ዜጎችን በመተካት የራሳቸውን የአገር ውስጥ ድርጅቶች በማቋቋም ዕውቀቱን ወደ አገር ውስጥ እንዲያስተላልፉ ነው የታቀደው።

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት የተረቀቁት አሥር ደንቦችና አሥራ አምስት መመርያዎች የውጭ አገር ባለሙያዎችና ኩባንያዎች ፈቃድ አውጥተው በስቶክ ገበያ አገልግሎት አቅራቢነት በኢትዮጵያ እንዲሰማሩ የሚያስችሉ ናቸው?

መለሰ ምናለ፡- በትክክል። የካፒታል ገበያ አዋጁ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶችን፣ ባለሙያዎችን፣ የኢንቨስትመንት ባንኮችን፣ ደረጃ ሰጪ ኤጀንሲዎችን፣ አከፋፋዮችን፣ ደላላዎችን፣ አሳዳጊዎችንና ሌሎችንም አይለይም። አሁን እያረቀቅነው ያለው የፈቃድ አሰጣጥ መመርያ የትኛውንም መሥፈርት የሚያሟሉ ተወዳዳሪዎች ፈቃድ አግኝተው የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪ ሆነው እንዲሠሩ ያስችላቸዋል።

ሪፖርተር፡- የሚቋቋመው የአክሲዮን (ካፒታል) ገበያ መጠን ወይም የገበያው ካፒታል ምን ያህል ይሆናል?

መለሰ ምናለ፡- ብሔራዊ ባንክ የባንኮች የተከፈለ የካፒታል ምን ያህል ሊሆን እንደሚገባ የሚወስነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንደሆነው ሁሉ፣ ለሚቋቋመው አክሲዮን ገበያ የካፒታል መጠን የሚወሰነው በሚቋቋመው የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ነው። ባለሥልጣኑ ከተመሠረተ በኋላ ከሚያወጣቸው መሥፈርቶች አንዱ ይህ ነው።

 

ሪፖርተር፡- የአክሲዮን ገበያው የካፒታል መጠንን የሚወስኑት ጉዳዮች ምን ምን ናቸው?

መለሰ ምናለ፡- መሠረታዊ መለኪያው የአደጋ ተጋላጭነት ነው። ከአደጋ ተጋላጭነት አንፃር ተመዝኖ ይህንን አደጋ ለመመቋቋም እንደ ቋት ሆኖ የሚያገልግለው ካፒታል ነው። ይህንንም ለመወሰን የሚገበያዩት የኩባንያዎች ድርሻ፣ የባለሀብቶች ብዛት፣ ከግምት ይገባሉ። የአክሲዮን ገበያ አገልግሎትን ለመስጠትና ገበያውን ለመቆጣጠር ጥቅም ላይ የሚውለው ቴክኖሎጂም የካፒታሉ አካል ይሆናል። ኤፍኤስዲ (FSD) ለሚቋቋመው የኢትዮጵያ የአክሲዮን ገበያ በጣም አዋጭ የሆነ ቢዝነስ ሞዴል በመንደፍና የውጭ ባለሀብቶችን ጨምሮ ከፍተኛ ባለሀብቶችን መሳብ ከቻለ፣ የአክሲዮን ገበያው በትልቅ ካፒታል የሚቋቋም ይሆናል። እስካሁን ባለው ሒደት ከውጭ ባለሀብቶች ወይም ኩባንያዎች ከፍተኛ ፍላጎት መኖሩን አይተናል። በተለይም ኤፍኤስዲ በሌሎች አገሮች የአክሲዮን ገበያዎችን ያቋቋሙ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን በአጋርነት ካመጣ፣ በጣም ትልቅ ካፒታልና ከፍተኛ የገበያ ልውውጥ የሚካሄድበት ይሆናል።

ሪፖርተር፡- መንግሥትን ወክሎ እስከ 25 በመቶ ድርሻ የሚይዘው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ድርሻውን በብር ነው የሚከፍለው?

መለሰ ምናለ፡- መንግሥት የሚይዘው የ25 በመቶ ድርሻ የካፒታሉ አካል ነው የሚሆነው። ግን መንግሥት ይህንን ድርሻ እንዴት ለመክፈል እንዳሰበ አላውቅም። በጥሬ ገንዘብ ማስገባት ወይም ንብረት ሊያቀርብ ይችላል። ዞሮ ዞሮ ግን መንግሥት ድርሻውን ለመክፈል የሚያቀርበው ማንኛውም ነገር እንደ ካፒታል ነው የሚቆጠረው።

ሪፖርተር፡- የኤፍኤስዲ አፍሪካ ባለሥልጣናት ካፒታል ገበያውን ለማቋቋም ለተዋቀረው የፕሮጀክት ቡድን ወጪ መሸፈኛ የሚያቀርቡት ገንዘብ በሒደት ኤፍሲዲ በአክሲዮን ገበያው ውስጥ የሚኖረው ድርሻ ሆኖ እንደሚቀየር ነግረውኛል። የአክሲዮን ገበያውን ለማቋቋም የሚወጣው ወጪ ምን ያህል ነው?

መለሰ ምናለ፡- የመጀመሪያው የፕሮጀክት ወጪ ትልቅ አይደለም። እውነት ነው ይህ ወጪ የሚሸፈነው በኤፍኤስዲ አፍሪካ ነው። ሕጋዊ ሒደቶችን ለመፈጸም፣ የካፒታል ገበያውን በንግድ ሚኒስቴር ለማስመዝገብ፣ ለአክሲዮን ልውውጥ ፈቃድ ለማግኘት፣ ለባለሙያዎች ቅጥር፣ ለባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወጪዎች፣ አክሲዮኖችን ለዓለም አቀፍ ባለሀብቶች ለመሸጥ፣ ዓለም አቀፍ ጉዞዎችን ጨምሮ የመንገድ ትዕይንት ወጪዎችንና ሌሎች ወጪዎችን የሚሸፍነው በኤፍኤስዲ አፍሪካ ነው። እነዚህ ወጪዎች ሊመለሱ የሚችሉ ናቸው ወይም በአክሲዮን ልውውጥ ወቅት ወደ አክሲዮንነት ሊቀየሩ ይችላሉ። ይህንን የሚወስነው ኤፍኤስዲ አፍሪካ ቦርድ ነው።

ሪፖርተር፡- የአክሲዮን ባለቤትነት ማረጋገጥ ተግባር በሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ተቋም ነው የሚከናወነው ወይስ በራሱ በካፒል ገበያው ነው የሚረጋገጠው?

መለሰ ምናለ፡- አይደለም። በይፋ ግብይት የሚካሄድባቸው ሁሉም አክሲዮኖች በወረቀት ቅርፅ ሊቀመጡ እንደማይችል የካፒታል ገበያ አዋጁ ይደነግጋል። ይህ ማለት ሁሉም አክሲዮኖች ወደ ዲጂታል ፎርማት መቀየር አለባቸው ማለት ነው። በተጨማሪም በማዕከል የተመዘገቡና ፈቃድ ባለው የአክሲዮን አስቀማጭና አስወጋጅ ኩባንያ መያዝ አለባቸው። ለምሳሌ የዘመን ባንክ ባለአክሲዮኖችን ማወቅ ከፈለግክ ወደ ዘመን ባንክ በመሄድ ሁሉም ባለአክሲዮኖች በእጅ የተመዘገቡበት ትልቅ ማኑዋል ደብተር ይሰጡሃል። ያ መቀየር አለበት ምክንያቱም ለባለቤቶቹ ደኅንነቱ የተጠበቀ አይደለም። ወደ ካፒታል ገበያው ስንመጣ ግን ይህ አሠራር አይኖርም። የእያንዳንዱን አክሲዮን ደኅንነት በተመለከተ ኃላፊነት የሚወስድ ፈቃድ ያለው የአክሲኖች ጠባቂ ኩባንያ ይኖራል። እያንዳንዱ አክሲዮን የራሱ የሆነ መለያ ቁጥር ይኖረዋልና ባለቤቶች በልዩ ሁኔታ ተለይተው የሚታወቁበት ሥርዓት ይኖራል። የአክሲዮኖች ልውውጥ ወይም ግብይት በተፈጸመ ቁጥር ወዲያውኑ የአክሲዮን ባለቤትነቱ በኤሌክትሮኒክ መንገድ ከሻጩ ወደ ገዢው ይተላለፋል። ይህ የሚከናወንበት ቴክኖሎጂ መልካም ጎኖች ዋነኛው ለባለሀብቶች አስተማማኝና በጣም የተጠበቀ መሆኑ ነው።

ሪፖርተር፡- የካፒታል ገበያ አዋጁ የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ ካፒታል ላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ይፈቅዳል። እነዚህ የውጭ ኩባንያዎች በቢትኮይን (Bitcoin) ወይም በሌሎች ዲጂታል ምንዛሬዎች ኢንቨስት ለማድረግ ቢጠይቁስ?

መለሰ ምናለ፡- እንደ ቢትኮይን ያሉ ዲጂታል ምንዛሬዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ለግብይት አይቀርቡም። አሁን ባለው ሁኔታ የውጭ ባለሀብቶች የፋይናንስ ተቋማትን አክሲዮን እንዲገዙ አይፈቀድላቸውም። የባንክ አክሲዮኖችን መያዝ ለውጭ አገር ዜጎች የተከለከለ በመሆኑ። ስለዚህ በኢትዮጵያ አክሲዮን ገበያ ውስጥ የውጭ ባለሀብቶች በመሳተፍ እንዲገዙ የተፈቀደላቸው አክሲዮኖች ለውጭ ዜጎች በተፈቀዱ መስኮች ማለትም ከንግድ ሥራዎች ወይም ዘርፎች የሚመነጩ አክሲዮኖችን ብቻ ነው። የውጭ ባለሀብቶች በአክሲዮን ገበያው መሳተፍ የሚችሉት አሁን ባለው የኢንቨስትመንት ሕግ ለእነሱ በተፈቀደው ዘርፍ ላይ ብቻ ይሆናል።

ሪፖርተር፡- በካፒታል ገበያው የሚሳተፉ የውጭ ባለሀብቶች ካፒታላቸውን በተደጋጋሚ ወደ አገራቸው ለመመለስ ቢጠይቁስ? የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያለማቋረጥ የውጭ ምንዛሪ ማቅረብ ይችላል?

መለሰ ምናለ፡- በአሁኑ ጊዜ ከፊል ክፍት የሆነ የካፒታል ፍሰት ሥርዓት አለን። የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት አድርጎ መሸጥና በፈለገው ጊዜ መሄድ ይችላል። የማይቻል ነገር የፖርትፎሊዮ ፍሰቶች ማለትም (የአክሲዮን ገበያ ኢንቨስትመንትን የማስወጣት ተግባር) ነው። አሁን ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት እንደ አንድ የቱሪስት ባለሀብት ነው። ትኩስ ገንዘብ ተብሎም ይጠራል። እዚህ መጥተህ ኢንቨስት ታደርጋለህና በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ስትሆን ትሄዳለህ። የፖርትፎሊዮ ኢንቨስትመንትን የማስወጣት ጉዳይ በፖሊሲ ይወሰናል። በብሔራዊ ባንክና በሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚወሰን ይሆናል። ሁለቱንም የሚያጣምር ውሳኔ መስጠትም ይችላል። ለምሳሌ መንግሥት የውጭ ባለሀብቶች ከስድስት ወራት በፊት ዋስትና እንዳይሸጡ የሚያዝ ፖሊሲ ሊያወጣ ይችላል። በጣም ተለዋዋጭ ገበያን ለማስወገድ እንደዚህ ያሉ ፖሊሲዎችን መተግበር ይቻላል።

ሪፖርተር፡- የአክሲዮን ገበያው የካፒታል አካውንት ሊበራላይዜሽን (ነፃ ማድረግን) ይፈቅዳል?

መለሰ ምናለ፡- የካፒታል አካውንት ሊበራላይዜሽን በከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ብቻ ሊወሰን የሚችል የፖሊሲ ጉዳይ ነው። የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ያስፈልገዋል። በአሁኑ ጊዜ ከፊል የተከፈተ የካፒታል አካውንት አስተዳደር ሥርዓት ነው ያለን። የውጭ ዜጎች ካፒታላቸውን ወደ አገራቸው መመለስ እንደሚችሉ ሲፈቀድላቸው የገዙትን አክሲዮን በመሸጥ መመለስ ይችላሉ። የካፒታል አካውንት ሊበራላይዜሽን ግን የፖሊሲ ጉዳይ በመሆኑ ወደፊት ታይቶ የሚወሰን ነው የሚሆነው። 

ሪፖርተር፡- በአክሲዮን ገበያው የሚሳተፉ ኩባንያዎች እንዴት ነው የሚለዩት? አንዳንዶች ገበያው ሥራ የሚጀምረው 50 ኩባንያዎችን በመለየት ነው ይላሉ?

መለሰ ምናለ፡- ገበያዎች በመንግሥት የሚታዘዙ አይደሉም፡፡ ነገር ግን በመንግሥት ማበረታቻዎች ያድጋሉ። በአክሲዮን ገበያው የሚሳተፉትን ወይም የሚዘረዘሩትን ኩባንያዎች ብዛት መንግሥት የሚወስንበት መንገድ የለም። በማበረታቻዎች ላይ በመመሥረት ግን ገበያውን መገንባት ይቻላል። ለዚህ መንግሥት ማበረታቻ መስጠት አለበት። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ብዙ ኩባንያዎች ይፋዊ ወደ ሆነው የአክሲዮን ግብይት እንዲመጡ ካሮትና ልምጭ ሊያስፈልግ ይችላል።  ቀድሞውኑ የሕዝብ ኩባንያዎች የሆኑት በአክሲዮን ገበያው ለመሳተፍ ሰፊ ዕድል ያላቸው። በተለይ አክሲዮን ለሕዝብ የሚሸጡ የአክሲዮን ኩባንያዎች ተሳታፊ ይሆናሉ። ምክንያቱም ቀድሞውኑም ለሕዝብ የተሸጡ አክሲዮኖች አሏቸው። በዚህ ሒደት የሚፈጠረው መገበያየት ብቻ ነው። ምን አልባት ድርሻቸውን ለመገበያየት አነስተኛ መስፈርቶችን እንዲያሟሉ ይጠየቁ ይሆናል እንጂ የተለየ ነገር አይኖርም። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የአክሲዮን ገበያ የለም። የዋጋ ግኝት፣ ግልጽነት፣ ወዘተ የለም። ዋጋ በአቅርቦትና በፍላጎት መወሰን አለበት። ስለዚህ ባለአክሲዮኖች ኩባንያዎቻቸውን ዝቅተኛውን መስፈርቶች አሟልተው በይፋ ወደ አክሲዮን ገበያው እንዲገቡ ግፊት ማድረጋቸው አይቀርም። ስለዚህ ሁሉም ኩባንያዎች፣ ባንኮች፣ ኢንሹራንስ፣ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች፣ የቢራ ፋብሪካዎችና ሌሎችም በአክሲዮን ኩባንያ የተደራጁ ኩባንያዎች በአክሲዮን ገበያው የሚሳተፋ ይሆናል። ነገር ግን በዚህ ገበያ ለመሳተፍ ዝቀተኛውን መስፈርት ማሟላት አለባቸው። ለዚህም ከኩባንያዎች ጋር በአቅም ግንባታ ላይ እየሠራን ነው።

ሪፖርተር፡- የመንግሥት ልማት ድርጅቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ሥር ናቸው። ሆልዲንግ ኩባንያው ደግሞ በአክሲዮን ገበያው ላይ የ25 በመቶ ድርሻ እንደሚኖረው ተገልጿል። የመንግሥት ልማት ድርጅቶች በአክሲዮን ገበያው ውስጥ የሚሳተፉ ከሆነ የውስጥ ለውስጥ ግብይት ሊከሰት አይችልም። ይህንን እንዴት ማስቀረት ይቻላል? 

መለሰ ምናለ፡- የውስጥ ለውስጥ ንግድ ጉዳይ የሚፈጠር አይመስለኝም። አዎ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ኩባንያው የበርካታ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ባለቤት ነው። የመንግሥት ልማት ድርጅቶች በአክሲዮን ገበያው ከሚኖራቸው የንግድ ልውውጥ አንፃር ሁለት ውሳኔ የሚሹ ጥያቄዎች አሉ። የመጀመሪያው የፖሊሲ ውሳኔ የሚሻ ጥያቄ ነው። አንደኛው የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን ሊበራላይዝ ማድረግ ወይም አለማድረግ የሚለው የፖሊሲ ጥያቄ ነው። ይህ በመንግሥት ደረጃ የሚወሰን ጉዳይ ነው። ለምሳሌ መንግሥት አሥር በመቶውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለመሸጥ ከወሰነ እያንዳንዱ ዜጋ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ድርሻ እንዲያገኝ ማድረግ የሚቻለው በአክሲዮን ገበያው ነው። ይህ አካሄድ የፕራይቬታይዜሽን ሒደቱን ዴሞክራሲያዊ ያደርገዋል። ከዚህ ቀድም ግን የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ወደ ግል ሲያዛውረው ገዥው የአገር ውስጥ ወይም የውጭ አገር ትልቅ ሀብታም ባለሀብት ይሆናል። ትልልቅ ኢንተርፕራይዞችን በሀብታሞች መዳፍ ውስጥ ማስገባት ደግሞ የፖለቲካ ችግር ይፈጥራል። አሁን እየተፈጠረ ባለው ዕድል ግን ሀብታምም ሆንክ ደሃ አንድ ድርሻ መግዛት ትችላለህ። ሁሉም ሰው በመንግሥት ልማት ድርጅቶች ውስጥ ወይም በግል ኩባንያዎች ላይ ድርሻ እንዲኖረው ማድረግ ይቻላል። ይህም ግልጽነትን፣ እኩልነትን ያረጋግጣል። በአክሲዮን ገበያው የሚዘረዘሩ የመንግሥት ልማት ድርጅቶችንም ግልጽና ለሕዝብ ተጠያቂ ያደርጋቸዋል። እነዚህ ድርጅቶች በመንግሥት የተያዙናና በሙስና የተተበተቡ ብቻ ናቸው። ስለዚህ የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን ለተወሰኑ ባለሀብቶች ከመሸጥ ይልቅ ወደ ግል ማዞር በጣም የተሻለ ነው።

የውስጥ ለውስጥ ግብይት የሚፈጠረው አንድ ሰው ስለ አክሲዮን ገበያ ውስጥ ስለተዘረዘረ አንድ ኩባንያ የውስጥ አዋቂ መረጃ ሲኖረው ነው። የውስጥ አዋቂው መረጃን ከሕዝብ ቀድሞ ያገኛልና መረጃውን ተጠቅሞ አክሲዮኑን ለመገበያየት ይጠቀምበታል። በዚህ ሁኔታ የውስጥ ለውስጥ ንግድ ሊፈጠር አይችልም። የኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ኩባንያው በአክሲዮን ገበያው ላይ ድርሻ ይኑረው እንጂ የአክሲዮን ገበያው ራሱን የቻለ ኩባንያ ነው። በእርግጥ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ኩባንያው በሥሩ ስላሉት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች መረጃ ሊኖረው ይችላል። ነገር ግን ይህ መሆኑ የውስጥ ለውስጥ ንግድ እንዲፈጠር ያደርጋል የሚለው አይታየኝም።

ሪፖርተር፡- አንዳንዶች የአክሲዮን ገበያው የመንግሥት የበጀት ጉድለቶችን ለመሙላት የፋይናንስ ምንጭ ሆኖ እንዳያገለግል ይሠጋሉ። ሌሎች ደግሞ መንግሥት የውጭ ባለሀብቶችን በመሳብ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመፍታት ነው የአሲዮን ገበያውን እያቋቋመ ያለው ይላሉ። በዚህ ላይ ምን ይላሉ?

መለሰ ምናለ፡- እውነት ነው። ከዓላማዎቹ አንዱ የበጀት ጉድለትን ለመሸፈን ነው። መንግሥት ካፒታል ገበያን በመጠቀም በጀቱን ለመደገፍ ቢጠቀም በጣም ንጹህ መንገድ ነው። ዛሬ መንግሥት ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ድልድይ ወይም መንገድ መገንባት ከፈለገ ወይ ከውጭ መበደር አለበት አልያም ከብሔራዊ ባንክ መበደር አለበት። ይህ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ቀውስና የብድር ዘላቂነት ችግር፣ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባትን እየፈጠረ ነው። ከብሔራዊ ባንክ መበደርም የዋጋ ንረት ፈተናን ያስከትላል። ነገር ግን መንግሥት ወደ ካፒታል ገበያ ሄዶ የአሥር ወይም የሃያ ወይም የሰላሳ ዓመት ቦንድ በመሸጥ የሚፈልገውን ካፒታል ማግኘት ይችላል። ይህ ካፒታል ቀድሞውኑም በኢኮኖሚው ውስጥ የነበረ በመሆኑ ምንም ማክሮ ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ አይኖረውም። አዲስ ገንዘብ አይደለም ፈሰስ የተደረገው ወይም የገንዘብ ማተም የተገኘ አዲስ ገንዘብ አይደለም። ስለዚህ አንዱ ማሳካት የተፈለገው ዓላማ ይህ ነው።

ሪፖርተር፡- በዚህ መንገድ ብዙ ገንዘብ ከባንክ ወደ አክሲዮን ገበያው ይሸጋገራል ማለት ነው። ይህ በባንኮች የገንዘብ ልውውጥና በብሔራዊ ባንክ የገንዘብ አቅርቦት ላይ ተፅዕኖ አያሳድርም?

መለሰ ምናለ፡- በባንኮችና በአክሲዮን ገበያ ውስጥ የሚኖረው የገንዘብ ሁኔታ የተለያየ ነው። ባንኮች የአጭር ጊዜ ጥቅም የሚሰጥ ገንዘብ ይይዛሉ። በባንኮች የሚቆጥቡ ሰዎች ከተወሰነ ጊዜ በኋላ፣ አብዛኛውን ጊዜ ከወራት በኋላ የቆጠቡትን ገንዘብ ያወጣሉ። በካፒታል ገበያ ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውለው ገንዘብ የረዥም ጊዜ ተቀማጭ ነው። በአሁኑ ወቅት ሰዎች ከባንክ ይልቅ በሪል እስቴት ላይ ገንዘባቸውን እያወጡ ነው ይህ የሆነበት ምክንያት ከባንክ የሚያገኙት ትርፍ አነስተኛ በመሆኑ ነው። ስለዚህ የአክሲዮን ገበያው በባንኮች ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል። ባንኮች የ20 ዓመታት ዕድሜ ያለው ፕሮጀክት ፋይናንስ ማበደር ቢፈልጉ ዛሬ ማድረግ አይችሉም። ምክንያቱም ባንክ ያለው ሀብት የደንበኞቹ ተቀማጭ ገንዘብ ነው። ይህ ገንዘብ የአጭር ጊዜ ተቀማጭ ነው። ባንኮች የአጭር ጊዜ ተቀማጭ ገንዘብ ሰብስበው ለረዥም ጊዜ ፋይናንስ ማበደር አይችሉም። በባንኮች ላይ ችግር ይፈጥራል።

ሪፖርተር፡- የአክሲዮን ገበያው መቼ ወደ ሥራ ይገባል ባለሥልጣኑስ መቼ ይቋቋማል?

መለሰ ምናለ፡- ቴክኒካዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ እየሠራን ነው፡፡ ነገር ግን ባለሥልጣኑን ለማቋቋም አንዳንድ ፎርማሊቲዎች ይቀራሉ። ለባለሥልጣኑ ዳይሬክተሮችና የቦርድ አባላትን መልምለን በዕጩነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ልከናል፣ ውሳኔያቸውን እየጠበቅን ነው። የአክሲዮን ገበያው መቼ ወደ ሥራ ይገባል የሚለውን በተመለከተ ማለት የሚቻለው፣ የአክሲዮን ገበያን የመመሥረት የሚጠይቀው ዝግጅት ብዙ ጊዜ የሚወስድ ነው። የአክሲዮን ገበያን ለማቋቋም የሚወስደው ጊዜ አንድን ባንክ ለማቋቋም ከሚጠይቀው የዝገግጅት ጊዜ በላይ ይሆናል እንጂ አያንስም። እንደዚያ ማሰቡ ይሻላል። አንደ ባንክ በሩን እስኪከፍት ድረስ ከሁለት እስከ ሦስት ዓመታት ይወስዳል። የአክስሲዮን ገበያው ከአሥራ ስምንት ወር እስከ ሁለት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ እንደሚገባ ተስፋ እናደርጋለን። ይህ የእኛ ዕቅድ ነው ነገር ግን በተግባር እንዴት እንደሚሆንና ምን ያህል ጊዜ እንደሚወስድ አናውቅም።

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች