አንጋፋው የቴሌኮም አቅራቢ ኢትዮ ቴሌኮም ይፋ ካደረገው ዓመት በሞላው የቴሌ ብር አገልግሎት 57 ተቋማት አገልግሎታቸውን አስተሳስረዋል አለ፡፡
ለዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት መስፋፋት የራሱን አሻራ እያስቀመጠ ይገኛል በተባለው የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት፣ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከ19.4 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ተገልጋይ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
ኩባንያው ከግዙፉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አንስቶ እስከ ጀማሪ የቢዝነስ ፈጣሪዎች ጋር የስምምነት ውል አስሮ እየሠራ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪም የኤሌክትሪክ ክፍያ አገልግሎት፣ የትራፊክ ደንብ መተላለፍ ቅጣት፣ የውኃና ፍሳሽ ክፍያ፣ እንዲሁም ሌሎች ወርኃዊ አገልግሎቶች በቴሌ ብር መስጠት ከጀመሩ ወራት ተቆጥረዋል ተብሏል፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ የቴሌ ብር አገልግሎት ተግባራዊ ከተደረገ ጀምሮ ከ18.7 ቢሊዮን ብር በላይ የኤሌክትሮኒክ ገንዘብ መፈጸሙን ገልጸው፣ ቴክኖሎጂው ከሕግጋት ወይም ከብዙ መመርያዎች መሻሻል በፊት በመምጣቱ ብዙ አስቻይ ያልሆኑ መመርያዎች እስኪሻሻል መጠበቅ ነበረበት ብለዋል፡፡ በእስካሁኑ እንቅስቃሴ የተፈጸመው የገንዘብ ዝውውር ኩባንያው የመመርያዎችን መሻሻል እግር በእግር እየተከተለ ያሳካው ውጤት መሆኑን ገልጸው፣ አገልግሎቱን የሚገድቡት እክሎች ባይኖሩ ከተገኘው ውጤት የበለጠ ይመዘገብ ነበር ብለዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ከ12 ባንኮች ጋር ከባንክ ወደ ቴሌ ብር፣ እንዲሁም ከአሥር ባንኮች ጋር ከቴሌ ብር ወደ ባንክ ገንዘብ ለማስተላለፍ ትስስር መፍጠሩ ተመላክቷል፡፡
ቴሌ ብር የመንግሥት ተቋማት በቀላሉ ዜጎች ካሉበት፣ ከመሥሪያ ቤታቸውና ከአካባቢያቸው ሆነው አገልግሎት ማግኘት ማስቻሉን ወ/ሪት ፍሬሕይወት ገልጸዋል፡፡
ቀደም ሲል ክፍያን በዲጂታል መንገድ ለማከናወን የሚያስችል ሲስተም እንዳልነበረ ያስረዱት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ ቴሌ ብር መምጣቱ ተቋማት የክፍያ ሥርዓታቸውን እንዲያዘምኑ ዕድል መፍጠሩን አስረድተዋል፡፡
የሞባይል ገንዘብ አገልግሎቱ የመንግሥትና የግል ተቋማት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ገንዘቦችን እጅ ላይ ባለ የስልክ ቀፎ እንዲገለገሉ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን፣ የተቋማቱን ወጪዎች ከመቀነስ ባሻገር ዜጎች ምቹ አገልግሎት እንዲያገኙ አስተዋጽኦ እንዳለው ተብራርቷል፡፡
በተያያዘም ኩባንያው በሽያጭ ማዕከላት አማካይነት ያለውን ተደራሽነት ለማስፋት፣ ከ40 ሺሕ በላይ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ካሉት የራይድ ትራንስፖርት ጋር የአጋርነት ስምምነት አድርጓል፡፡
የራይድ የትራንስፖርት አገልግሎት ክፍያዎችን በቴሌ ብር ከማከናወን ባለፈ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ አሽከርካሪዎች የተለያዩ አገልግሎቶችን በውክልና ወይም ኤጀንት በመሆን ያገለግላሉ።
የአጋርነት ስምምነት ፊርማ በተከናወነበት ሁነት ላይ የተገኙት ወ/ሪት ፍሬሕይወት፣ ስምምነቱ የኩባንያውን አገልግሎቶች ከራይድ የትራንስፖርት አገልግሎት አሠራር ጋር በማስተሳሰር የኩባንያውን ምርትና አገልግሎቶች ለማድረስ ያሰበ ነው ብለዋል፡፡
የራይድ ትራንስፖርት አሽከርካሪዎች አዲስ ደንበኞችን መመዝገብ፣ የደንበኞችን የቴሌ ብር ደንበኝነት ማሳደግ፣ የአየር ሰዓትና የጥቅል አገልግሎቶችን መሸጥ፣ ገንዘብ ማስቀመጥና ማውጣት፣ አዲስ ሲም ካርድ መሸጥ፣ ምትክ ሲም ካርዶችን ማዳረስና ለደንበኞች በርካታ የዴሌቨሪ አገልግሎቶች ይሰጡበታል ተብሏል፡፡
የሃይብሪድ ዲዛይንስ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ሳምራዊት ፍቅሩ በበኩላቸው፣ ኩባንያው ከጀማሪ የሥራ ፈጣሪ ተነስቶ በዚህ ወቅት የደረሰበትን ደረጃ አስታውሰው፣ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የፈጠሩት አጋርነት በዘርፉ አዲስ የሆነ አገልግሎት ለማቅረብ አስችሎታል ብለዋል፡፡
በተለይም በሳምንቱ የዕረፍት ቀናት የፋይናንስ አገልግሎት አቅራቢዎች በብዛት ስለማይሠሩ የሚያጋጥሙ የገንዘብ ዝውውር ፍላጎቶችን፣ የራይድ አሽከርካሪዎች በቴሌ ብር አማካይነት ለመቀነስ የሚያስችላቸው መሆኑን ወ/ሪት ሳምራዊት ገልጸዋል፡፡