Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ትርፍ እንዲያስመዘግቡ የሚጠየቁበት ጊዜ እንዲራዘም ጠየቁ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ሥራ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ትርፍ እንዲያስመዘግቡ የሚጠየቁበት ጊዜ እንዲራዘም ጠየቁ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የግሉ ዘርፍ በቴክኖሎጂ ላይ ያለውን ሚና ማሳደግን የተመለከተ ከቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ጋር ውይይት ያደረገ ሲሆን፣ በውይይት መድረኩ የተገኙ ተሳታፊዎችም የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች እንደ ሌላው የንግድ ዘርፍ መታየት እንደሌለባቸው ገልጸዋል።

የኦርቢት ሔልዝ መሥራች አቶ ፓዚዎን ቸርነት በቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች እንዲያሟሉ የሚጠይቋቸው መሥፈርቶች በርካታ መሆናቸውን፣ ይህም ከዘርፉ ባህሪ አንፃር አስቸጋሪ መሆኑን ይገልጻሉ። የቴክኖሎጂ ኩባንያ እንደ ሌላው ዘርፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ ትርፍ ማግኘት የሚያስችል ባለመሆኑ፣ መንግሥት የሚጠይቀውን የትርፍ ማስመዝገቢያ ጊዜ ሊያራዝም ይገባል ብለዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም የታክስ ማሻሻያ እንደሚያስፈልግና ድርጅቶቹ ራሳቸውን የሚያጎለብቱበት ጊዜ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ገልጸው፣ በእንዲህ ዓይነት ምክንያቶች በርካታ በቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች እየከሰሙ መሆኑን አክለዋል።

በተጨማሪም ሐሳብ ብቻ ይዘው ወደ ሥራ መግባት ለሚፈልጉ፣ የሐሳቡ አዋጭነት ተመዝኖ መንግሥት ዋስትና በመግባት ብድር የሚመቻችበት አሠራር ወደ ሥራ መግባት አለበት ብለዋል። ይህም በዘርፉ ፈታኝ የሆነውን የገንዘብ አቅርቦት ችግር ለመፍታት ያስችላል ብለዋል።

በቴክኖሊጂ ዘርፍ የኢንተርኔት አገልግሎት እየተሻሻለ ቢመጣም፣ የገንዘብ እጥረት አሁንም ከፍተኛ ችግር መሆኑን የየኔ ፔይ መሥራች አቶ ኑር ሐሰን መንሱር ተናግረዋል።

በተለይም መንግሥት ከሚያቀርበው በተጨማሪ ኩባንያዎቹ በራሳቸው ለሚያፈላልጓቸው የኢንቨስትመንት አጋርነቶች፣ አሁን ያለው አሠራር ምቹ አለመሆኑን ይገልጻሉ።

ምቹ የገበያ ሥርዓት አለመኖሩ፣ የኤሌክትሮኒክስ ቲኬት አለመጀመርና መሰል ችግሮችን ገንዘብ ያላቸው ባለሀብቶች ወደ ዘርፉ እንዳይገቡ የሚከለክል መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር አብዮት ባዩ (ዶ/ር)፣ ‹‹የግሉ ዘርፍ በቴክኖሎጂው ላይ ያለው ተሳትፎ ሊያድግና የመንግሥት ተሳትፎ ሊቀንስ ይገባል፤›› ብለዋል።

ለዚህም ለዘርፉ ትልቅ ፈተና የሆነውን የፋይናንስ አቅርቦት ለመፍታት ማበረታቻዎች በመዘጋጀት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። ከውጭ ለሚገቡ ዕቃዎች የሚሰጥ የቀረጥ ቅነሳ፣ የታክስ ዕፎይታና የሥራ ቦታን ማመቻቸት መንግሥት ለማቅረብ ከተዘጋጀባቸው ማበረታቻዎች መካከል ይገኛሉ ሲሉ አስረድተዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች