Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናፍርድ ቤት በጋዜጠኛ ተመሥገን ደሳለኝ ላይ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ሰጠ

ፍርድ ቤት በጋዜጠኛ ተመሥገን ደሳለኝ ላይ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ሰጠ

ቀን:

ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ ተጨማሪ የምርመራ  ጊዜ ተጠየቀበት

ግንቦት 18 ቀን 2014 ዓ.ም ከቢሮው በፀጥታ ሰዎች ተወስዶ የታሰረው የፍትሕ መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ተመሥገን ደሳለኝ ግንቦት 19 ቀን 2014 ዓ.ም. በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ቀጠሮ ችሎት የቀረበ ሲሆን፣ መርማሪ ፖሊስ በጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ላይና ተጠርጣሪው፣ ‹‹መጠርጠርም ካለብኝ፣ መጠየቅ ያለብኝ በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ነው፤›› በሚለው ላይ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለነገ ግንቦት 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ጋዜጠኛው በቁጥጥር ሥር የዋለው መከላከያ ሠራዊትን በሕዝብ ዘንድ አመኔታ ለማሳጣትና ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት ወንጀል መሆኑን ፖሊስ ለፍርድ ቤት አስታውቋል።

መርማሪ ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው፣ ጋዜጠኛ ተመሥገን የተጠረጠረበትን ሁከትና አመፅ ማስነሳት ወንጀል በምስክር ለማስመስከር፣ የምስክር ቃል ለመቀበል፣ ተጨማሪ ማስረጃ ለመሰብሰብና የምርመራ ሥራውን አጠናክሮ ለመቅረብ 14 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት እንዲፈቀድለት ፖሊስ ጠይቋል።

ለጋዜጠኛ ተመሥገን ጠበቃ ሔኖክ አክሊሉ የቆሙለት ሲሆን፣ መከላከያን መተቸት እምነት ማሳጣት አለመሆኑን ጠቅሰው ተከራክረዋል። ምስክር ማስመረጥ ለተባለውም ቢሆን ተመሥገንን አገር የሚያውቀው በመሆኑ፣ ማስመረጥ ጥያቄው ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

ጠበቃው አክለውም፣ ጋዜጠኛ ተመሥገን የሚሠራበት ሚዲያ ፈቃድ ያለው ሕጋዊ ተቋም እንደመሆኑ፣ ወንጀል ሠራ ቢባል እንኳ በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ እንጂ በጊዜ ቀጠሮ ሊጠየቅ እንደማይገባ በማስረዳት ተከራክረዋል።

ፖሊስ በዩቲዩብ ቃለ መጠይቅ እያደረገ ከሌሎች አካላት ጋር ሁከትና አመፅ የማነሳሳት ሥራ እየሠሩ ነው ሲል ባቀረበው የመነሻ ምርመራ ሪፖርትን በተመለከተ፣ ጋዜጠኛ ተመሥገን ከአራት ዓመት ወዲህ ምንም ዓይነት፣ ከማንም ጋር ቃለ መጠየቅ እንዳላደረገ ጠበቃ ሔኖክ አብራርቷል።

በሚሠሩበት ሚዲያ የአገር መከላከያ ተቋምም ቢሆን ‹‹ተተችቻሁ፣ በሕዝብ ዘንድ እምነት አጣሁ›› ብሎ አለመቅረቡን ጠበቃው ጠቅሰው ቢከራከሩም፣ በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ መሠረት በሚሠራበት ሚዲያ ማስተካከያ በማድረግ እንደማይታለፍ በመናገር ፖሊስ ተከራክሯል፡፡

ጋዜጠኛ ተመሥገን በሙያው በመሞገት የሚታወቅና የሚደነቅ ሰው መሆኑን ለችሎቱ የገለጹት ጠበቃ ሔኖክ፣ በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ እንጂ በጊዜ ቀጠሮ የሚታይበት የሕግ አግባብ እንደሌለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹ጉዳያቸው በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ነው መታየት ያለበት›› ለተባለውን ጥያቄ በሚመለከት በጉዳዩ ላይ ምን አስተያየት እንዳለው በፍርድ ቤቱ የተጠየቀው መርማሪ ፖሊስ፣ ፍርድ ቤቱ አምኖበት በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ይታይ ካለ እንደማይቃወም መልስ ሰጥቷል።

ጠበቃ ሔኖክ በትናንትናው ዕለት በጋዜጠኛ ተመሥገን ደሳለኝ መኖሪያ ቤት፣ እንዲሁም በዛሬው ዕለት ደግሞ በመሥሪያ ቤቱ ፍተሻ ተደርጎ ፖሊስ የሚፈልገውን የሰነድ ማስረጃ የወሰደ መሆኑንና ጋዜጠኛ ተመሥገን አገሩን ትቶ የሚሄድ ባለመሆኑ፣ የዋስትና መብቱ ተጠብቆ በዋስ እንዲወጣ ሲሉ ጠበቃ ሔኖክ ችሎቱን ጠይቀዋል።

ጉዳዩን የተከታተለው የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት የፖሊስ የምርመራ መዝገብ እንዲቀርብ በማዘዝ፣ መርምሮ ትዕዛዝ ለመስጠት ለሰኞ ግንቦት 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል።

በሌላ በኩል በተመሳሳይ ቀን ግንቦት 18 ቀን 2014 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ውሎ የነበረው ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስም፣ በማግሥቱ ግንቦት 19 ቀን 2014 ዓ.ም. በፌዴራል የመጀመርያ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርቦ የምርመራ ጊዜ ተሰጥቶበታል፡፡

ፍርድ ቤት ያቀረበው መርማሪ ፖሊስ እንደገለጸው፣ ተጠርጣሪው የሚዲያ ጦርነት ከፍተው ከሚሠሩ ሰዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ ጋዜጠኛ ያየሰው ኢትዮ ፎረም በተሰኘ የዩቲዩብ ማኅበራዊ ሚዲያ እንደሚሠራ በመጠቆም፣ በተለይም በአገሪቱ በስውር የኢኮኖሚ ጦርነት የሚዲያ ጦርነት የከፈቱና የተደራጁ አካላት እንዳሉ ገልጾ፣ ብሔርን ከብሔር፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት ለማጋጨት፣ እንዲሁም የፌዴራል መንግሥትና ሕዝብ ሆድና ጀርባ እንዲሆኑ ሁከትና ብጥብጥ እንዲነሳ ሚዲያን በመጠቀም ከሚሠሩ ሰዎች መካከል አንዱ መሆኑን አብራርቷል፡፡ የምስክሮች ቃል መቀበሉን፣ ከተጠርጣሪው የተያዘ ኤሌክትሮኒክስ መሣሪያን ለማስመርመር ለብሔራዊ መረጃና ደኅንነት መስጠቱንና ተጠርጣሪውን በምስክር ለማስመረጥ፣ እንዲሁም ተጨማሪ ማስረጃ ለማሰባሰብ ተጨማሪ 14 ቀናት እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

ተጠርጣሪው በበኩሉ በአሁኑ ወቅት ሥራ እንደሌለውና በአዲስ አበባ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ነዋሪ መሆኑን በመግለጽ ፖሊስ ይዤዋለሁ ካለ፣ በየትኛው ሚዲያ? መቼ? ምን? የሚለውን በግልጽ አማርኛ ሊያቀርብ ሲገባ መርማሪው አለመግለጹን አስረድቷል፡፡

ከዚህ በፊትም ሥራውን እንዳይሠራ ስላስፈራሩት ሥራ ማቆሙን ጠቁሞ፣ በሕዝብ ላይ አሳመፀ ከተባለም በሕዝብ ላይ የደረሰውን ጉዳት ሊያቀርብ ሲገባ አለማቅረቡን ተናግሯል፡፡ ከዚህ በፊትም ሐሰተኛ መረጃ አሠራጭተሃል ተብሎ ለ54 ቀናት አዋሽ አርባ ታስሮ የነበረ ቢሆንም፣ ጥፋተኛ እንዳልተባለና እንዳልተፈረደበት አብራርቷል።

ጠበቃው አቶ ታደለ ገብረ መድኅን በበኩላቸው፣ ደንበኛቸው የተጠረጠረበት ወንጀል በግልጽ አልቀረበም፡፡ አንድ የተጠረጠረ ሰው ስለተጠረጠረበት ነገር በግልጽ ቋንቋ መነገር እንዳለበት ተደንግጓል፣ መርማሪ መከተል ያለበትን ነጥብና ማሟላት ያለበትን ሁኔታዎች አሟልቶ፣ ግልጽ ምርመራ ማድረግ እንዳለበትና ኢትዮጵያ ተቀብላ የደነገገቻቸው ሕጎች እንዳሉ ጠቁመው፣ መርማሪ ፖሊስ ደንበኛቸው ብጥብጥና ሁከት አስነሳ ካለ፣ ‹‹ምን?›› በሚልና ‹‹በማን ዩቲዩብና መቼ›› የሚለውንና ስንት ምስክር ይመሰክራል የሚለው ግልጽ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

 መርማሪ ፖሊስ በድጋሚ እንዳስረዳው፣ እየተከፈላቸው የሚዲያ ጦርነት የሚያካሄዱ የተደራጁ ኃይሎች አሉ፡፡ ተጠርጣሪውም ከእነሱ መካከል ነው፡፡ ኢትዮ ፎረምን ጠቀስን እንጂ ሌሎችም አሉ፡፡ በተመሳሳይ ጉዳይ ጋዜጠኛ ያየሰው በተደጋጋሚ መታሰሩን ራሱም መግለጹን አስታውቆ፣ ቢፈታ ምስክሮችን አስፈራርቶ ሊሰወሩ እንደሚችሉ ጠቁሞ፣  የጀመረውን ሰፊ ምርመራ ለማከናወን የጠየቀው የ14 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ እንዲፈቀድለት ጠይቋል።

ጉዳዩን ያየው የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ፖሊስ ከጠየቀው 14 ቀናት ውስጥ 10 ቀናትን በመፍቀድ የምርመራ ውጤት ለመጠባበቅ ለግንቦት 29 ቀን 2014 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...