Monday, May 20, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የምግብ ችግር ከመጠን በላይ እየከፋ ነው!

በአሁኑ ጊዜ በርካታ ሚሊዮኖችን የሚያሳስባቸው የምግብ ዕጦት ነው፡፡ እንኳንስ በቀን ሦስት ጊዜ ማዕድ ለመቅረብ አንድ ጊዜ ለመመገብ የሚያዳግታቸው በርካቶች ናቸው፡፡ በገጠርም ሆነ በከተማ ምግብ ለብዙዎች ብርቅ እየሆነ ነው፡፡ ከምግብ ችግር በተጨማሪ መጠለያ፣ ልብስ፣ ጤና፣ ትምህርትና የመሳሰሉት መሠረታዊ ፍላጎቶች ሲታከሉበት የችግሩ ፅኑነት ለማንም ግልጽ ይሆናል፡፡ በከተማ ወላጆች ለልጆቻቸው ወተት ማቅረብ እየተሳናቸው ነው፡፡ ከሰብል እህሎች በተጨማሪ አልፎ አልፎ ማዕድ ላይ ዕንቁላል፣ ሥጋ፣ ቅቤ፣ ዓይብ፣ ዓሳና ሌሎች የምግብ ውጤቶችን ማግኘት እጅግ በጣም ከባድ ሆኗል፡፡ ባልተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት ምክንያት መቀንጨርን ጨምሮ ለበርካታ የበሽታ ዓይነቶች ተጋላጭ የሆኑ ወገኖች ጉዳይ፣ ከመንግሥት ጀምሮ የሕዝብ ጉዳይ ይመለከተናል የሚሉ ወገኖችን ትኩረት ይሻል፡፡ የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት የማይችል ማኅበረሰብ በመማርም ሆነ በማምረት ሒደት ውስጥ ንቁ ተሳታፊ መሆን አይችልም፡፡ “በምግብ ራስን መቻል” የሚባለው ጽንሰ ሐሳብ ከመፈክር ማለፍ ባልቻለባት ኢትዮጵያ ውስጥ፣ “መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ መሠለፍ” የሚባለው ቀቢፀ ተስፋ መቀለጃ እየሆነ ነው፡፡ ዋነኛው የድህነት ማሳያ ደግሞ የምግብ ዕጦት ነው፡፡

ኢትዮጵያ አሁንም ከዓለም ደሃ አገሮች መሀል አንዷ እንደሆነች የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት በርካታ ሚሊዮኖች የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ይፈልጋሉ፡፡ ከእነዚህ ወገኖች መካከል አብዛኞቹ በተለያዩ ሥፍራዎች በተከሰቱ ግጭቶችና ጦርነቶች የተፈናቀሉ ናቸው፡፡ በድህነት ምክንያት በሴፍቲኔት በምግብ ለሥራ ፕሮግራም መታቀፍ ያለባቸው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወገኖች አሉ፡፡ በገጠርና በከተማ በዓለም አቀፍና በአገር በቀል ረድዔት ድርጅቶች ምገባ የሚፈልጉ በርካቶች ናቸው፡፡ በአጠቃላይ በርካታ ሚሊዮኖች ፍፁም ከድህነት ወለል በታች ናቸው፡፡ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገው ፍልሰት በጣም ጨምሯል፡፡ ይህ ሁሉ ችግር በተከመረባት ኢትዮጵያ ውስጥ የኑሮ ውድነቱ ከፍቷል፡፡ ብዙዎች ምግብ ማግኘት እያዳገታቸው ነው፡፡ ከምግብ የሚቀድም ሌላ ነገር የለምና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ መላ ይፈለግ፡፡ መንግሥት የመጪውን ዓመት በጀት ሲያቅድ ከካፒታል ፕሮጀክቶችና ከሌሎች ዘርፎች ቀናንሶ የምግብ አቅርቦት ላይ ማተኮር ይኖርበታል፡፡ ችግሩ ከመጠን በላይ እየከፋ ነው፡፡

ከሩሲያና ከዩክሬን ጦርነት በባሰ በአገር ውስጥ የሚስተዋሉ ግጭቶች ማምረትንም ሆነ አቅርቦትን እያስተጓጎሉ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ገበያ የነዳጅና የምግብ ምርቶች ዋጋ በየቀኑ ማሻቀብ ሌላው ራስ ምታት ነው፡፡ ይህንን እውነታ በሚገባ በመገንዘብ በአገር ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የማምረት እንቅስቃሴ መፍጠር ይገባል፡፡ ከእርሻና ከእንስሳት ውጤቶች የሚገኙ የተለያዩ የምግብ አቅርቦቶች በሰፊው እንዲገኙ ለማስቻል፣ በተፈጥሮ የተቸሩ ፀጋዎችንና የሰው ኃይልን በማቀናጀት በባለሙያዎች ዕገዛ ውጤታማ ሥራ መጀመር ይኖርበታል፡፡ የፕላን ሚኒስቴርም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት ለምግብ ምርቶች ማደግና ለአቅርቦታቸው መቀላጠፍ የሚረዱ ዕቅዶች ላይ ያተኩሩ፡፡ ኢትዮጵያ ክረምት ከበጋ በዓመት ሦስት ጊዜ ያህል ምግብ የሚመረትባት አገር መሆን ሲገባት፣ ለሌሎች ለማይጨበጡ ጉዳዮች ጊዜንና ሀብትን ማባከን ይቁም፡፡ በአስመራሪው የኑሮ ውድነት እየተፈተነ ላለ ከ115 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ምግብ ማቅረብ ካልተቻለ ለአገር አደጋ ነው፡፡ መንግሥት ይህንን መራር እውነታ በመገንዘብ ውጤታማ ዕቅድ ላይ ያተኩር፡፡ ለዚህም ዕቅድ በተግባር የተፈተነ ልምድ ያላቸውን ኢትዮጵያውያን ዕገዛ ይጠይቅ፡፡

ኢኮኖሚያዊ አቅምን መገንባት የሚቻለው እጅ ላይ ያለ ሀብትን በሚገባ በመጠቀም ነው፡፡ ከ80 በመቶ ያላነሰ ሕዝብ በእርሻና በከብት አርቢነት በሚተዳደርባት ኢትዮጵያ ውስጥ፣ ከፍተኛ ትኩረት መሰጠት ያለበት ለግብርናው ዘርፍ መሆን አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ሰፊ ለም መሬት፣ ከፍተኛ የውኃ ሀብት፣ አመቺ የአየር ፀባዮች፣ ከሁሉም በላይ መጠኑ ከፍተኛ የሆነ የወጣት ኃይል ይዛ ስንዴ ከውጭ ትገዛለች፣ ባስ ሲልም ትመፀወታለች፡፡ በቅርቡ የተጀመረው የመስኖ ስንዴ ልማት አበረታች ቢሆንም ብዙ ይቀራል፡፡ በአገር ውስጥ መመረት የሚገባቸው መሠረታዊ ሸቀጦች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጥቶባቸው ከውጭ ይገዛሉ፡፡  በከተማ ግብርናም ሆነ ሰፊ የሰው ኃይል ባለበት በገጠር ግብርና፣ እንዲሁም በግዙፉ የእንስሳት ሀብት አማካይነት ቢያንስ ፍላጎትን ማርካት ይቻላል፡፡ ለመሆኑ ክልሎች በመስኖም ሆነ በዝናብ ሊታረሱ ከሚችሉ መሬቶች ምን ያህሉን እየሠሩባቸው ነው? የእንስሳት ሀብትን በሚገባ ለመጠቀም ምን ዓይነት ስትራቴጂ ተነድፏል? በከተማ ወጣቶች በተለያዩ መስኮች እንዲሰማሩና አምራች እንዲሆኑ ማድረግ ለምን ያዳግታል? ለሥራ የማያመቹ ልማዶችን አስወግዶ በኅብረት መነሳት የግድ መሆን አለበት፡፡

ከከተማ እስከ ገጠር በዕቅድ፣ በጠንካራ ክትትልና አፈጻጻም ሥራ የሚከናወንበት ሥርዓት ያስፈጋል፡፡ በጠንካራ ተቋማት፣ በዕውቀታቸውም ሆነ በልምዳቸው በተመሰከረላቸው ባለሙያዎችና አመራሮች የሚታገዝ ሥርዓት ሲኖር፣ ከአገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ለአፍሪካ ጭምር የሚተርፉ የተለያዩ የምግብ ምርቶችን ማምረት ይቻላል፡፡ ከሌብነት፣ ከሸፍጥና ከክፋት በፀዳ ክህሎትና ሰብዕና መመራት ሲቻል ሀብት ይትረፈረፋል፡፡ ከአገር ውስጥ አልፎም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያ እየሆነ ያለው ግን በዓባይ ውኃ የበቀሉ ብርቱካንና ሽንኩርት በውጭ ምንዛሪ ከግብፅና ከሱዳን ማስገባት ነው፡፡ የአትክልት መሸጫዎችንና የሸቀጣ ሸቀጥ ግሮሰሪዎችን ያጣበቡት የውጭ ምርቶች እንደሆኑ ለማረጋገጥ ትንሽ ዞር ዞር ማለት በቂ ነው፡፡ የስንዴ፣ የዘይት፣ የስኳር፣ የወተትና የመሳሰሉት መሠረታዊ ምርቶች የውጭ ግዥ አልበቃ ብሎ፣ የዓባይ ውኃ ውጤት የሆኑትን የጎረቤት አገር ምርቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ማየት ያማል፡፡ በአፍሪካ ሁለተኛ ግዙፍ የሕዝብ ቁጥር ያላት ኢትዮጵያ የባህል አብዮት አካሂዳ ወጣቱን ሥራ ላይ ማሰማራት እንዴት ያቅታታል ሊባል ይገባል፡፡ ጠንካራ ተቋማት እንዲኖሩ ከመሥራት ጎን ለጎን እያፈጠጠ ከመጣው መከራ ለመትረፍ፣ በተቻለ መጠን በእጅ ላይ ያለውን ሀብት ሥራ ላይ ለማዋል መጣደፍ የወቅቱ ዋነኛ ጉዳይ መሆን አለበት፡፡

የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከገባበት አጣብቂኝ ማውጣት ይቻላል፡፡ ለዚህም ብሩህ ተስፋ እንዳለ በርካታ አመላካቾች አሉ፡፡ ነገር ግን የአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ቁልፍ ሚና እንዳለው ልብ ሊባል ይገባል፡፡ የትኛውም የአገሪቱ አካባቢ ከግጭት ነፃ መሆን አለበት፡፡ ሰዎች ከቦታ ወደ ቦታ ተዘዋውረው የመኖርና የመሥራት መብታቸው መከበር ይኖርበታል፡፡ ለንግድና ለኢንቨስትመንት ፀር የሆኑ ሕገወጥ ድርጊቶች መቆም አለባቸው፡፡ የቱሪዝም ፍሰቱ አስተማማኝ መሆን አለበት፡፡ ምርቶችና አገልግሎቶች ሳይስተጓጎሉ መቅረብ አለባቸው፡፡ ለሰላምና ለመረጋጋት እንቅፋት የሆኑ ችግሮችን የማስወገድ ትልቁ ኃላፊነት የመንግሥት ሲሆን፣ እያንዳንዱ ዜጋም አስተዋጽኦውን ማበርከት ይጠበቅበታል፡፡ ሰላም በሌለበት ዕድገት አይታሰብም፡፡ ለዚህም ሲባል ፖለቲከኞች አርዓያ መሆን አለባቸው፡፡ በዚህ ደረጃ ኃላፊነትን መወጣት ከተቻለ ኢኮኖሚው ከገባበት አጣብቂኝ ውስጥ ወጥቶ ከፍተኛ ውጤት ማግኘት ይቻላል፡፡ ሕዝቡን ከኑሮ ውድነት ለመታደግና አስተማማኝ የኢኮኖሚ መሠረት ለመጣል ሰላም ወሳኝ ነው፡፡ የምግብ ጉዳይ ትልቅ ትኩረት ይሻል፡፡ የምግብ ችግር ከመጠን በላይ እየከፋ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...

በስድስተኛው ዙር ጠቅላላና ድጋሚ ምርጫ የሚሳተፉ ፓርቲዎች በገዥው ፓርቲ ላይ ተቃውሞ እያቀረቡ ነው

በ2013 ዓ.ም. ስድስተኛው ምርጫ ባልተካሄደባቸው ክልሎች በጠቅላላና በድጋሚ ምርጫ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...

የመግባቢያ አማራጮችን ተባብሮ መፈለግ ከጥፋት ይታደጋል!

በአሁኑ ጊዜ ሕዝብና አገርን ጤና የሚነሱ በርካታ ችግሮች በየቦታው እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ችግሮቹ ከመጠን በላይ እየተለጠጡ ቅራኔዎች ሲበረክቱ ሰከን ብሎ ከመነጋገር ይልቅ፣ የጉልበት አማራጭ...

አገርን ከቀውስ ውስጥ ማውጣት ብሔራዊ አጀንዳ ይሁን!

የአገራቸው መፃኢ ዕድል የሚያሳስባቸው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ወገኖች፣ በየቀኑ የሚሰሟቸው ማቆሚያ ያጡ ልብ ሰባሪ የግጭትና የጦርነት ዜናዎች እንቅልፍ ይነሷቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ማንኛውም...