Monday, March 4, 2024

የፓርላማ አባላት በትራንስፖርት ዘርፍ የሚስተዋለው የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ቅሬታቸውን አሰሙ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በመላው አገሪቱ በትራንስፖርት ዘርፍ የሚስተወለው አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ቅሬታቸውን አሰሙ፡፡

የፓርላማ አባላቱ የትራንስፖርት ዘርፉ ችግሩ እንዲፈታ የጠየቁት፣ ግንቦት 18 ቀን 2014 ዓ.ም. የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴርን የ2014 ዓ.ም. የመጀመሪያ አሥር ወራት ዕቅድ አፈጻጸም በገመገሙበት ወቅት ነው፡፡

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ወ/ሮ ዳግማዊ ሞገስ የተቋማቸውን ሪፖርት ካቀረቡ በኋላ፣ ቁጥራቸው በርከት ያሉ የምክር ቤት አባላት በትራንስፖርት ዘርፉ የሚታዩ ብልሹ አሠራሮች እንዲስተካከሉ አምርረው ጠይቀዋል፡፡

ለአብነትም በመናኸሪዎች አካባቢ በተገልጋዮች ላይ የሚደርሰው እንግልትና ከታሪፍ በላይ ክፍያ የሚጠየቀው፣ ተገልጋዮችም ለምን ብለው መጠየቅ የማይቻሉበት ደረጃ መደረሱን በተመለከተ ወ/ሮ እየሩሳሌም ሌዊ የተባሉ የምክር ቤት አባል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

የትራንስፖርት ተገልጋይ መብቱን ሲጠይቅ ከፈለግክ ተሳፈር ካልፈለግክ ወርደህ ሂድ እየተባለ ከፍተኛ ችግር ውስጥ መግባቱን በመግለጽ፣ ሚኒስቴሩ ለችግሩ መፍትሔ እንዲፈልግ ጠይቀዋል፡፡

በሌላ በኩል ከሌሊቱ አሥር ሰዓት ጉዞ የሚጀምሩ ልዩ አገር አቋራጭ አውቶብሶች በበላይነት የሚቆጣጠራቸው አካል ማን እንደሆነ ለማወቅ እንደተቸገሩ የገለጹት ወ/ሮ እየሩሳሌም፣  ባለንብረቶቹ ትኬት በቢሯቸው ከመቁረጥ ይልቅ ትኬቱን ለደላላ አሳልፈው በመስጠት ተሳፋሪዎች በተጨማሪ ክፍያ እንዲገዙ መገደዳቸውን አስረድተዋል፡፡

በዓላት ሲቃረቡና ለየት ያሉ አጋጣሚዎች ሲኖሩ፣ በተለይም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መሄጃና መመለሻ በሚደርስበት ወቅት ትኬት ከባለንብረቶቹ ቢሮ ማግኘት እንደማይቻል ወ/ሮ እየሩሳሌም ተናግረዋል፡፡ ለአብነትም ወደ ሚዛን ለመጓዝ በሕጋዊ መንገድ 600 ብር ይከፈልበት የነበረውን በሕገወጥ መንገድ 1,000 ብር ከደላላ እንደሚገዙ በተጨባጭ መረጃ አለኝ ብለዋል፡፡

አቶ አስቻለ አላምሬ የተባሉ ሌላ የምክር ቤት አባል በበኩላቸው፣ በሐዋሳ ከተማ ሰሌዳ የሌላቸው ተሽከርካሪዎች መኖራቸውን፣ እንዲሁም መናኸሪያዎች ከልካይ እንዳጡ በመግለጽ፣ ‹‹ወልዳ ያሳደገች እናት የምትሰደበው መናኸሪያ ውስጥ ነው፤›› በማለት ሚኒስቴሩ በዚህ ጉዳይ ላይ ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ረገድ ከታሪፍ በላይ በግልጽ እየተከፈለ መሆኑን፣ ለዚህም ዋነኛው ምክንያት በመንገድ ትራንስፖርት ባለሙያዎችና በትራፊክ ፖሊሶች ዘንድ በገሃድ የሚታይ ችግር እንደሆነ የገለጹት ወ/ሮ አበባ ሳዲቅ የተባሉት የምክር ቤት አባል ናቸው፡፡ አብዛኞቹ የመንገድ ትራንስፖርት ባለሙያዎችና የትራፊክ ፖሊሶች፣ አሽከርካሪዎች ከታሪፍ በላይም ሆነ ከተፈቀደላቸው ሰው በላይ ጭነው ሲያገኟቸው፣ ተሽከርካሪዎችን መንገድ ዳር አስቁመው በረዳቶቻቸው አማካይነት ተደራድረው እንደሚለቋቸው ተናግረዋል፡፡

‹‹የሕዝብ ምሬት ከምንናገረው በላይ ነው፡፡ በተሽከርካሪዎች ሥምሪት ችግርና በአሽከርካሪዎች ብልሹ አሠራር ምክንያት ሰዎች እንቅልፍ አጥተው መንገድ ላይ ቁጭ ብለው ሲጠብቁ ያድራሉ፡፡ ተሽከርካሪ ሲገኝም አንድ ተሽከርካሪ ሊይዘው ከሚቻለው በላይ ሦስትና አራት ዕጥፍ ሰዎችን ጭነው ይጓዛሉ፡፡ በዚህም የተነሳ ለአደጋ እየተጋለጡ ናቸው፤›› በማለት የተናገሩት አቶ ጀንበር አያልነህ የተባሉ የምክር ቤት አባል ናቸው፡፡

የተከዜ ተፋሰስ የሚባሉት የዋግ፣ የእብናትና የበላሳ አካባቢ በርካታ ሚሊዮን ሕዝብ የሚኖርበት ሆኖ አንድም አስፋልት መንገድና በቂ ተሽከርካሪዎች የሌሉበት እንደሆነ፣ በቅርቡ በዚህ መንገድ ከመጠን በላይ ጭነው ከሄዱ ተሽከርካሪዎች መካከል አንዱ ገደል ገብቶ አስከሬናቸው ያልተነሳ ሰዎች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ አክለውም ዋግን ያየ ኢፍትሐዊነቱ መሆኑን፣ በዚህ አገር ምን ዓይነት አስተዳደር እየተፈጠረ ነው ያስብለዋል ብለዋል፡፡

የመንጃ ፈቃድ ብቃት ማረጋገጫ ማሠልጠኛዎች ብቃት ያላቸው አሽከርካሪዎች እያፈሩ አለመሆኑን፣ በአንዳንድ የግል ኮሌጆች በገንዘብ እንደሚሸጠው ዲግሪና ዲፕሎማ  ሁሉ ገንዝብ ከፍለው የመንጃ ፈቃድ የሚያገኙ በርካታ መሆናቸውንና በይፋ እየተቸረቸረ መሆኑን የተናገሩት ወ/ሮ የሺመቤት ደምሴ የሚባሉ የምክር ቤት አባል  ናቸው፡፡

የመንገድ ቁጥጥር ሥራው ደካማ መሆኑን፣ በቴክኖሎጂ የተደራጁና ብቁ የሆኑ የአሽከርካሪ ማሠልጠኛዎች አለመገንባታቸው፣ በከፍተኛ መጠን ሐሰተኛ የመንጃ ፈቃድ ሥርጭት መኖሩንና ለትራፊክ አደጋ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሆነ የገለጹት አልማዝ አሰሌ (ኢንጂነር) የተባሉ የምክር ቤት አባል ናቸው፡፡

ምንም እንኳ የምክር ቤቱ አባላት በርከት ያሉ ጥያቄዎችን ቢሰነዝሩም፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሯ ወ/ሮ ዳግማዊት በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹በመናኸሪያዎች መሠረተ ልማቶችንና አፈጻጸሞችን በማዘመን ሞዴል መናኸሪያዎች በመፍጠር እያሰፋንና እያበዛን እንሄዳለን፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -