Monday, March 4, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የቅንነት የአብሮነትና የመደጋገፍ መገለጫ – የበጎ ፈቃድ አገልግሎት

በዓለማየሁ ማሞ

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በማኅበራዊ ኑሮ ውስጥ የመረዳዳት ባህል አንዱ የኢትዮጵያውያን መገለጫ እንደሆነ የሚመሠክሩ በርካታ ጥናቶች አሉ፡፡

ቀደም ባሉት ዓመታት የአገርን ዳር ድንበር ለማስጠበቅና ነፃነትን ለማስከበር ንቅናቄዎችን በመምራት ረገድ ወጣቶች ሰፊ ድርሻ እንደነበራቸው አይዘነጋም፡፡

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት ብሔራዊ የወጣቶች ፖሊሲ ክፍል አምስት ላይ፣ ወጣቶች በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ጠንካራ የአካባቢ ጥበቃና ማኅበራዊ አገልግሎት እንቅስቃሴዎች ውስጥ በንቃት ተሳትፈው ራሳቸውንና ማኅበረሰባቸውን ሊጠቅሙ የሚችሉባቸውን ሁኔታዎች ማመቻቸት እንደሚገባ ይገልፃል፡፡

ይህንንም ፖሊሲ መነሻ በማደረግ የተቀረፀው የኢትዮጵያ ወጣቶች የዕድገት ፓኬጅ እንደደሚገልጸው፡ ‹‹የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች በመንግሥት የወጡ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ኘሮግራሞችን መሠረት በማድረግ አስፈላጊ የሆኑ የማስፈፀሚያ ስልቶች ተነድፈውላቸው ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባና እንዲሁም መንግሥት በቀየሰው የድህነት ቅነሳ ስትራቴጂ አተገባበር ዙሪያ የራሳቸውን ተሳትፎ በማድረግ ተጠቃሚነታቸውን ሊያረጋግጡ ይገባል፡፡››

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የማኅበረሰቡ የዕድገት ደረጃ ማሳያ፣ በቅንነት ላይ የተመሠረተ የአብሮነት፣ የእርስ በእርስ መደጋገፍና የመረዳዳት ውጤት ሲሆን በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ ዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊና የአንድ አገር የሥልጣኔ መገለጫ የድርጊት መርሐ ግብር ነው ማለት ይቻላል፡፡

ከተመድ የተገኘው ፅንሰ ሐሳብ ሲተነተን በተለያዩ መስኮች እያንዳንዱ ሰው ያለትርፍ ፍለጋ፣ ያለክፍያ፣ ሙያዊ አፅንኦት ባልተጫነው ሁኔታ ግለሰቦች ለጐረቤታቸው፣ ለማኅበረሰባቸውና ለሕዝብ የሚያበረክቱትን አስተዋፅኦ ያመላክታል፡፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወጣቶች በራሳቸው ተነሳሽነትና መልካም ፈቃድ በለኅብረተሰቡ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በማሳተፍ ነፃ አገልግሎት የሚያበረክቱበት ተግባር ነው፡፡

በመሠረቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እድሜና ፆታ፣ ማኅበራዊ ደረጃ፣ መልክዓ ምድራዊ ወሰን ሳይገድበው የሰብዓዊነት መርህ ብቻ መሠረት በማድረግ የሚሰጥ ወይም የሚከናወን ተግባር ሲሆን፣ ለዚህ ስታንዳርድ ጠቀሜታ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተለይቶ ትኩረት እንዲሰጠው ተደርጓል፡፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወጣቱ የማኅበረሰቡን መልካም እሴቶች እንዲቀስም ለማስቻል፣ የወጣቱን ተሳትፎ ለማበረታታትና ለማሳደግ፣ የወጣቱ እምቅ አቅም ለመጠቀም፣ ለሕፃናትና ለታዳጊ ወጣቶች አርአያ የሚሆን ወጣት ትውልድ ለማፍራትና ያልተሸፈኑ የኅብረተሰቡና የመንግሥት ፍላጐቶችን ለማሟላት ያገለግላል፡፡

በተጨማሪም ለኅብረተሰቡ ተቆርቋሪና የኃላፊነት ሥሜት የሚሰማው ወጣት ትውልድ ለማፍራት፣ወጣቶች ከአልባሌ ቦታዎች ርቀው ለኅብረተሰቡ ጠቃሚ በሆኑ መስኮች የሚሠማሩበትን እድል ለመፍጠር ያገለግላል፡፡

በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ውስጥ መሳተፍ ወጣቶች የዜግነትን ኃላፊነታቸውን እንዲገነዘቡ፣ አገራዊና ብሔራዊ ግዴታዎችን እንዲያውቁና የአገርና የወገን ፍቅርን የሚያዳብሩበት ሁኔታ ከመፍጠር አንጻር አስፈላጊነቱ የላቀ ነው፡፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መንግሥታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች ለሙያና ፆታ ማኅበራት፣ ለንግድና አገልግሎት ኅብረቶች መፈጠር መሠረት በመሆኑ ወጣቶች፣ የዕድሜ ባለፀጐች፣ የአካል ጉዳተኞች፣ ቤተሰቦች እና ሌሎች ማኅበራዊ ቡድኖች በሀገራዊ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ፣ የፖለቲካ፣ የባህልና የአካባቢ ጥበቃ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በንቃት እንዲሳተፉ የሚያስችል ወሳኝ መሣሪያ ነው፡፡

አጠቃላይ ውጤቱም እንደየአገሩ ታሪክ፣ ፖለቲካ ሥርዓት፣ አገርን ማኅበረሰብንና ራስን የሚጠቅም የዕድገትና የብልፅግና ምንጭ ከመሆኑም ባሻገር በሃይማኖትና በባህል ሲቃኝ ደግሞ የተለያየ ትርጉምና ቅርፅ ሊይዝ ይችላል፡፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደማንኛውም የአገልግሎት ዘርፍ በሁሉም አገር ሕዝቦች የሚታወቁና የተለመዱ መርሆዎች ያሉት ሲሆን፣ ከእነዚህ ጐን ለጐን ደግሞ የበጎ ፈቃድ ሰጪው ከሚሰማራባቸው የአገልግሎት መስኮች የሚመነጩ ለምሳሌ ከሕክምና ወይም ከቀይ መስቀል መርሆዎች ጋር ሊመሳሰል ይችላል፡፡

በዚህ መሠረት ቁርጠኝነት፣ ፈቃደኝነት፣ ነፃ አገልግሎት፣ ሰብዓዊነት፣ ዓለም ዓቀፋዊነት፣ የማኅበረሰቡ እሴቶችን ማክበርና ከሌሎች ለመማር ዝግጁ መሆን የተሰኙትን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተፈጥሯአዊ (ተወራሽ) መርሆዎች ማመሳሰል በቂ ነው፡፡

የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዋና ዓላማ የአገራችን ወጣቶች በራሳቸው ተነሳሽነት፣ መልካም ፈቃድና ፍላጐት ተንቀሳቅሰው በኅብረተሰቡ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥረቶች ውስጥ የበኩላቸውን ድርሻ የሚያበረክቱበትንና ለኅብረተሰቡም ጠቃሚ የሆኑ የሕይወት ክህሎቶችን የሚቀስሙበትን ተቋማዊ ሥርዓት ለመፍጠርና በበጎ ፈቃደኝነት አስተሳሰብና መርህ የሚታነፁበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው፡፡

በዚህ መሠረት የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በመጪው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሐ ግብር በሚቀርቡት የአገልግሎት ዘርፎች እንደየምርጫችን ተሳታፊ በመሆን የላቀ ውጤት ለማስመዝገብና የተሻለ አስተዋጽዖ በማበርከት፣ ኅብረተሰቡንም ተጠቃሚ ለማድረግ በተለይም ለተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ችግሮች የተጋለጡ ወገኖቻችንን በዘላቂነት ለማቋቋም፣ እነዚህን የማኅበረሰብ ክፍሎች በባለቤትነት ለመደገፍ የሚደረገው ርብርብ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ንቅናቄ ላይ ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ ከወዲሁ የቅድመ ዝግጅት እንዲደረግ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]  ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles