Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየእንረዳዳ ተራድዖ በአረጋውያኑ መንደር

የእንረዳዳ ተራድዖ በአረጋውያኑ መንደር

ቀን:

ሰውን ማክበርና በሰው መከበር ራሱን የቻለ ግብ፣ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መከናወን ያለበትና መለኪያውም ሰብዓዊ ፍጡርነት ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ለአገር ብዙ ያበረከቱ፣ ያቀኑ፣ ለአሁኑ ትውልድ አቅጣጫ ያስያዙና ልዩ ልዩ ውጣ ውረድ በማለፍ በርካታ ዕውቀቶችንና ልምድ አካብተው በአሁኑ ጊዜ ቀሪ ዘመናቸውን በዕረፍት በማሳለፍ ላይ የሚገኙ አረጋውያን አባቶች ክብር ሊቸራቸው ይገባል፡፡

በዕድሜ ዘመናቸው ያካበቷቸውን ዕውቀቶች መቅሰም፣ ልምዳቸውንና ተሞክሮአቸውን መጋራት፣ ታሪካቸውንና ጠብቀው ያኖሩትን መልካም ዕሴቶች ለትውልድ እንዲተላለፍ ማድረግ ብልህነት ነው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ደግሞ በዕድሜ ማምሻ ጧሪና ተንከባካቢ አጥተው ድጋፍ በሚሹበት ወቅት አለኝታነትን በተግባር ማሳየት፣ መደገፍና መንከባከብ ግድ ይላል፡፡

በአይዟችሁ ባይነትና በአብሮነት ስሜት እየተካሄደ ባለው በዚሁ የመንከባከብና የመደገፍ እንቅስቃሴ ላይ መንግሥታዊ የሆኑም ሆነ ያልሆኑ ግብረ ሠናይ ድርጅቶች፣ የሲቪክና የሙያ ማኅበራት እንዲሁም የእምነት ተቋማት ወዘተ አቅም በፈቀደ መጠን የየበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ ይስተዋላል፡፡ ከእነዚህ ድርጅቶች አንዱ የእንረዳዳ የአረጋውያን መረጃ ማዕከል ነው፡፡ ማዕከሉ በሚሰጠው ድጋፍ ተጠቃሚ የሆኑ አረጋውያን አባቶችን አነጋግረናል፡፡

የኢትዮጵያ አባቶች ቀን ለ14ኛ ጊዜ በዚሁ ማዕከል ታስቦ በዋለበት ሥነ ሥርዓት ላይ ካነጋገርናቸው አረጋውያን አባቶች መካከል የ97 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ የሆኑት አቶ መኩሪያው ካሳ ይገኙበታል፡፡ እንደ አባት መኩሪያ አነጋገር ዕድሜያቸውን ሙሉ በድምፃዊነት (አዝማሪ) ከዚያም በዘበኝነት ሲተዳደሩ ቆይተዋል፡፡ ሦስት ልጆችና አምስት የልጅ ልጆች አፍርተዋል፡፡ ባለቤታቸውና ልጆቻቸው በሞት ሲለዩአቸው የልጅ ልጆቻቸው ደግሞ በተለያዩ ቦታዎች ተሰማርተው የየራሳቸውን ኑሮ ይመራሉ፡፡

አረጋዊው አባት ሌላ ሁለተኛ ሚስት አግብተው ቢኖሩም ጉልበታቸው እየተዳከመ፣ ዓይናቸው እየፈዘዘ በመምጣቱ እርጅና ተጫጫናቸው፡፡ በመኪና አደጋ ምክንያትም በወገባቸው ላይ ጉዳት ስለደረሰባቸው በክራንች መንቀሳቀስ ግድ እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡ በዚህም ሳቢያና በዕድሜያቸው መግፋት ምክንያት ሥራቸውን እንዳቆሙ፣ ይህም በመሆኑ በቤታቸው የሚላስ የሚቀመስ ጠፍቶ ‹‹የጧሪ ያለህ›› እያሉ በሚጮሁበት ወቅት ማዕከሉ እንደደረሰላቸው ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ከማዕከሉ በየወሩ በሚደረግላቸው የምግብ ራሽን እየተደገፉ ሕይወታቸውን ማቆየት እንደቻሉ፣ ይህንን ሁኔታቸውን በቴሌቪዥን የተመለከቱ፣ በአሜሪካ ነዋሪ የሆኑና ስማቸው እንዲገለጽባቸው ያልፈለጉት ትውልደ ኢትዮጵያዊት በየወሩ ሦስት ሺሕ ብር እንደሚለግሷቸው፣ ምግብ ራሽኑ ለሌላ አረጋዊ እንደተላለፈ፣ ይህም ከሆነ ከሁለት ዓመት በላይ እንደሆነው ነው ያመለከቱት፡፡

በአንድ የእምነት ተቋም ጥግ ተጠልለው ኑሯቸውን በመግፋት ላይ ያሉት አቶ ምሕረት ሙላት የዚሁ ማዕከል ድጋፍ ተጠቃሚ ናቸው፡፡ እንደተጠቃሚው አነጋገር ተወልደው ካደጉበት ከባህር ዳር ከተማ ከ45 ዓመት በፊት የቀረበላቸውን የእናት አገር ጥሪ ተቀብለው ወደ ምሥራቅ ጦር ግንባር በመዝመት የሶማሊያን ወረራ ተከላክለዋል፡፡ በዚህም የቀኝ ዓይናቸውና ጭንቅላታቸው ከጠላት በተተኮሰ ጥይት ለጉዳት እንደተዳረገ ተናግረዋል፡፡

ከሰባ ዓመቱ የዕድሜ ባለፀጋው ማብራሪያ ለመረዳት እንደተቻለ ከዘመቻውም መልስ የተለያዩ የግል ሥራዎችን ሲያከናውኑ ቆይተዋል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ዕርጅናም እየጫጫናቸውና ጉዳቱም እየበረታባቸው መጣ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ጡረታ ባይኖራቸውም ከማዕከሉ በየወሩ የምግብ ራሸንና የ100 ብር ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡

ያነጋገርናቸው ሌላው አረጋዊ አባት ደግሞ ዕድሜያቸው ከ80 ዓመት በላይ የሆኑት አቶ ወሰኑ ወምቤቶ ናቸው፡፡ እንደ እሳቸው አነጋገር ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት ሲሆኑ ቤተሰቦቻቸውንም የሚያስተዳድሩት እሳቸውና ባለቤታቸው የቀን ሥራ እየሠሩ በሚያገኙት ገቢ ነው፡፡ ልጆቻቸውም ለትምህርት እንጂ ለሥራ ያልደረሱ እንደሆነ ነው ያመለከቱት፡፡

ዕድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ እንደልብ መንቀሳቀስ ስላቃታቸው የቀን ሥራውን እርግፍ አድርገው እንደተዉት ገልጸው ይህም በመሆኑ ማዕከሉን መጠጋታቸውንና በዚህም በየወሩ የምግብ ራሽንና የ250 ብር ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አስረድተዋል፡፡

ግንቦት 15 ቀን በተከናወነው መሰናዶ ላይ የአባቶችን እግር አጠባና የጋቢ ማልበስ የተከወናነ ሲሆን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ አየለች እሸቴ ንግግር አድርገዋል፡፡

በንግግራቸውም ላይ ‹‹ለአገራችን በጎ የዋሉ፣ መልካም ዕሴቶችን ያሻገሩ እነዚህ አረጋውያን የማኅበራዊ ችግር ተጎጂ ከሆኑባቸው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖዎች አንዱ ቤተሰብ ተገቢውን ሚና ያለመጫወቱ ሲሆን ይህን ችግር ለማስተካከል በመረጃ የተደገፈ ሥራ በመሥራት ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

አረጋውያን ታሪክና ባህል እንዲቀጥል፣ አገራዊ ዕውቀት ለትውልድ እንዲተላለፍ በጎውን መንገድ በማሳየትና ትውልድን በመቅረጽ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረከቱ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡ ከዚህ አኳያ በዘርፉ ያሉ የሕግ ማዕቀፎችን ተግባራዊ በማድረግና አረጋውያን የእኩል ዕድል ተጠቃሚና ሙሉ ተሳታፊ ለማድረግ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በቅንጅት ሊሠራና በባለቤትነት ሊንቀሳቀስ እንደሚገባ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

‹‹ለአረጋውያን መሥራትን ከቤታችን ልንጀምረው ይገባል›› ያሉት ሚኒስትር ደኤታዋ፣ ይህን በጎ ምግባር ቤት፣ ጎረቤት፣ አካባቢ፣ አገር እየተባለ የሚያድግ ተግባር መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በቤት ውስጥ አባቶችን ማክበርና ተገቢውን እንክብካቤ ማድረግ ከተቻለ በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን አገራዊ ሥዕል በመልካም ለማስተካከል ዋናው መሠረት እንደሚሆን ነው የጠቆሙትን፡፡

‹‹ይህ ዕለት የኢትዮጵያ አባቶች ቀን ሆኖ የተመረጠበት ዋነኛ ምክንያት ለኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን ለጥቁር ሕዝቦች ነፃነት የተዋደቁ ጀግኖች አባቶቻችንን ለማሰብና እነዚህ አባቶቻችን ጣልያንን ድል በመድረግ ከወራት ዘመቻ በኋላ ተመልሰው ወደ አዲስ አበባ የገቡበት ዕለት ለመዘከር ነው፤›› ብለዋል፡፡

የእንረዳዳ የአረጋውያን መረጃ ማዕከል ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሠናይት ድንቁ ማዕከሉ 170 አረጋውያንን በመንከባከብ ላይ እንደሚገኝ ከእነዚህም መካከል 90 ከመቶ ያህሉ እናቶች መሆናቸውን ነው የተናገሩት፡፡

ለአረጋውያኑ እንክብካቤ የሚያስፈልገውን የፋይናንስ ወጪ በመሸፈን በዋናነት እየተባበረ ያለው ኸልፕ ኤጅ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ የተባለ ግብረ ሠናይ ድርጅት ሲሆን ማዕከሉ ከተቋቋመበት ከ1990 ዓ.ም. ጀምሮ ለሥራ እየተገለገለበት ያለውን ቤት በጊዜያዊት የረዱት ደግሞ ወ/ሮ ንጋቷ አስፋው የተባሉ በጎ አድራጊ መሆናቸውን ነው  የገለጹት፡፡

በጎ አድራጊዋ ማዕከሉ ለተወሰነ ጊዜ በነፃ እንዲገለገልበት የሰጡት ቤት የጊዜ ገደቡ በመጠናቀቁ እንዲመለስላቸው ጠይቀዋል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ኢቢኤስ ቴሌቪዥን ለማዕከሉ የገቢ ምንጭ ማስገኛ የሚውልና በቀን 2,000 ብሎኬቶችን የማምረት አቅም ያለው ማሽን በዕርዳታ መስጠቱን፣ ይህም ሆኖ ግን በቦታ ዕጦት የተነሳ ያለምንም አገልግሎት እንደተቀመጠ ተናግረዋል፡፡

ማሽኑን ለማንቀሳቀስ የሚያስችል ቦታ እንዲሰጠው ማዕከሉ ጉዳዩ ለሚመለከተው መንግሥታዊ አካል በተደጋጋሚ ጊዜ በጽሑፍ ጠይቆ እስካሁን ምንም ምላሽ እንዳላገኘ ከሥራ አስኪያጇ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...